አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ እየተባባሰ የመጣውን የምግብ እጥረት ለማቃለል 1.18 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግ የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሳማንታ ፓወር ገለጹ፡፡ ቻይናን ጨምሮ ሌሎች አገሮችም እጆቻቸውን እንዲዘረጉም ጠይቀዋል፡፡
የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት እንዳስታወቀው፣ በአፍሪካ ቀንድ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከ18 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለረሃብ የተጋለጡ በመሆናቸው አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡
በአፍሪካ ቀንድ በምግብ እጥረቱ የተነሳ ከአሥር ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በችግር ውስጥ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ ደግሞ ለረሃብ አደጋ፣ ቢያንስ 1,103 ሕፃናት ለሕልፈተ ሕይወት፣ ሌሎች ሰባት ሚሊዮን ሕፃናት ደግሞ ለተመጣጠነ የምግብ እጥረት መዳረጋቸውን ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡
ይህ ዓይነቱ ሁኔታ በተለይ ውዥንብርና አለመረጋጋት በሚታይባቸው እንዲሁም ግጭቶች በተባባሱባቸው ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያና ኬንያ ችግሩን በይበልጥ እንደሚያወሳስበው ከሳማንታ ፓወር ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ቃል በተገባውም ገንዘብ በአካባቢው በብዛት ለምግብነት የሚዘወተረውን ማሽላ፣ እንዲሁም በተመጣጠነ ምግብ እጦት ለተጎዱት ሕፃናት ደግሞ ተጨማሪ ምግብ ለውዝ መግዣና ጉዳት ለደረሰባቸው የቀንድ ከብቶች የሕክምና አገልግሎት መስጫ እንደሚውልም ተመልክቷል፡፡
‹‹ረሃብ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናትን ለከፋ ጉዳት ከመዳረጉ በፊት ሌሎች አገሮችም የዕርዳታ እጆቻቸውን ሊዘረጉ ይገባል፤›› ያሉት ሳማንታ ፓወር፣ በዓለም ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የስንዴ ላኪ በሆነችው ዩክሬን ውስጥ እየተካሄደ ባለው ጦርነትና በጦርነቱም ሳቢያ ለውጭ ገበያ የሚላክበት መተላለፊያው በመዘጋቱ የተነሳ በዓለም ውስጥ የምግብ ዋጋ የሰማይ ጥግ ያህል ውድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ቻይና ማዳበሪያ ወይም እህል ለዓለም ገበያ ወይም ለዓለም የምግብ ፕሮግራም ብታቀርብ፣ በምግብና በማዳበሪያ ላይ የታየው የዋጋ ውጥረት እየረገበ ሊሄድ እንደሚችል ነው የገለጹት፡፡
ኢንዶኔዥያም በፓልም ዘይት ላይ አሳድራ የነበረውን ቁጥጥር ማላላቷን ዋና ዳይሬክተሯ አድንቀው፣ ሌሎችም አገሮች ተመሳሳይ ዕርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ሳማንታ ፓወር ከሐምሌ 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት በምሥራቅ አፍሪካ ጉብኝት ያደርጋሉ፡፡ በእነዚህም ጊዜያት በድርቁ ሳቢያ እህልና ከብቶቻቸው ያለቁባቸውን ማኅበረሰቦች በመጎብኘት ድርቁ በመጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ በጤና፣ በከብቶችና በአጠቃላይ በሕይወት ላይ ያደረሰውን ተፅዕኖ በስፋት ለመገንዘብ ያስችላቸዋል፡፡
ከዚህም ሌላ የተለያዩ የጤና ተቋማት ከመጎብኘት ባሻገር የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት የአስቸኳይ የምግብ ማከፋፈያ ጣቢያዎችን እየተዘዋወሩ እንደሚመለከቱ፣ ከሰብዓዊ ዕርዳታ አጋሮች፣ ከሲቪክ ማኅበራትና ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣኖች ጋር በመገናኘት መንግሥታቸው ለድርቁ እያበረከተ ያለውን ምላሽና በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት በምግብ ዋስትና ላይ ያስከተለውን ተፅዕኖ በተመለከተ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት ድርቅን መቋቋም የሚችሉ ሰብሎችን የማስፋፋት፣ ከምርት በኋላ የሚኖረውን ብክነትን ለመቀነስ በተለያዩ መርሐ ግብሮች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናከሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል፡፡