የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ረጅም ሒደቶችን አልፎ ተዘጋጅቷል ያለውን የኤክስፖርት ስትራቴጂ፣ በተያዘው የበጀት ዓመት አፅድቆ ወደ ሥራ ለማስገባት እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን አስታወቀ፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እንዳለው መኮንን ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በ2015 የበጀት ዓመት ፀድቀው ወደ ሥራ ከሚገቡት ጉዳዮች መካከል የኤክስፖርት ልማትና ፕሮሞሽን ስትራቴጂ አንዱ ነው፡፡
የኤክስፖርት ስትራቴጂው በዋናነት የገበያ መዳረሻ አድማስን ማስፋት (Market Diversification)፣ እንዲሁም የሚላኩ ምርቶችን ማብዛት (Product Diversification) ላይ ትኩረት የሚሰጥ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ የተቋማት አደረጃጀት ጉዳዮችን የሚዳስስ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡
በተለይም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከዚህ በፊት አገሪቱ ለውጭ ገበያ በብዛት የማታቀርባቸውን የማዕድን ምርቶች ወደ ውጭ ልካ የተሻለ ገቢ መገኘቱ፣ በቀጣይ ስትራቴጂው ወደ ሥራ ሲገባ የተሻለ ውጤት እንደሚገኝ አመላካች መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በኤክስፖርት ዝርዝር ውስጥ የሚገኙትን ምርቶችን በብዛት ማምረት የሚለውና የምርት ስብጥርን ማብዛት (Product Diversification) በሚለው በረቂቅ ስትራቴጂው ክፍል የተዳሰሰ አንዱ ክፍል ነው ተብሏል፡፡
የመዳረሻ አገሮችን መጨመር ወይም ማብዛት (Target Market Diversification) ሁለተኛው የትኩረት ማዕከል መሆኑ ሌላው ከዚህ ቀደም የተገለጸ ሲሆን፣ ሦስተኛው ደግሞ የተቋማት አደረጃጀት (Institutional Arrangement) የሚመለከት ነው፡፡ ይህም ከተቋማት ጋር ተያይዞ ምን መድረግ አለበት? በተለይም ከውጤታማነት ጋር ተያይዞ የሚለውን የሚመለከት መሆኑን መገለጹ ይታወሳል፡፡
አቶ እንዳለው እንዳስታወቁት፣ የተቋማትን አደረጃጀት ማጠናከር ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ የትኞቹን ተቋማት በማበረታታት፣ አቅም በማሳደግና የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ በማድረግ ሊሠራባቸው ይገባል የሚሉትን ጉዳዩች ስትራቴጂው ያቀፈ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በአጠቃላይ የኤክስፖርት ስትራቴጂው የተቋማት አደረጃጀት፣ የምርት ስብጥር ማብዛት፣ እንዲሁም የመዳረሻ አገሮችን መጨመር የሚሉትን ጉዳዮች ባገናዘበ መንገድ የተዘጋጀ መሆኑን፣ ስትራቴጂው ፀድቆ ወደ ሥራ ሲገባ በርካታ ለውጦች ይኖራሉ ብለዋል፡፡
ከቁጥጥር ጋር ተያይዞ በግብረ ኃይል አማካይት የሚደረጉ ዕርምጃዎች ጊዜያዊ መፍትሔዎች መሆናቸውን ያስረዱት አቶ እንዳለው፣ በተለይም ከሕገወጥ እንቅስቃሴዎች ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን መከላከል የሚቻለው ወጥ የሆነ አሠራር ሲዘረጋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሚወጡ ሕጎች ተግባራዊ መደረግ እንዳለባቸው የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በ2015 የበጀት ዓመት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተሰጠውን ተልዕኮ በተሻለ መንገድ ለማከናወን እንዲችል ከክልሎች ጋር ቅንጅት ሊፈጠርባቸው በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ከሰሞኑ ምክክሮች መደረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የኤክስፖርት ፕሮሞሽን ስትራቴጂ ኤጀንሲ ተቋቁሞ በሥራ ላይ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ዋነኛ የተቋሙ ተልዕኮ የነበረው የአገሪቱን ኤክስፖርት ምርቶች ለዓለም ማስተዋወቅ ነበር፡፡ ከዚህ በሻገር ወደ ውጭ ምርቶቻቸውን የሚልኩ ባለሀብቶችን መደገፍ፣ ከውጭ ባላሀብቶች ጋር ማገናኘትና ሙያዊ ድጋፎችን ማድረግ ሌላው ለአጀንሲው የተሰጡ ተልዕኮዎች መሆናቸው የሚታወስ ነው፡፡
በ2014 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 4.63 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 4.12 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ ይታወሳል፡፡ በ2013 ዓ.ም. ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ 3.62 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከተገኘው የወጪ ንግድ ገቢ የግብርናው ዘርፍ 72 በመቶ ገቢ በማስገኘት ከፍተኛውን ድርሻ የያዘ ሲሆን፣ ማዕድን 14 በመቶ፣ ኢንዱስትሪ 12 በመቶ፣ እንዲሁም ኤሌክትሪክ ሁለት በመቶ ገቢ ማስገኘታቸውን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡