Wednesday, February 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 336.7 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰበሰበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የተሰበሰበው ገቢ ከታቀደው ዕቅድ በ23 ቢሊዮን ብር ያነሰ ነው

በ2014 የበጀት ዓመት 83 ከመቶ የሚሆነውን የመንግሥት ገቢ ከታክስ እንዲሰብስብ ኃላፊነት ተሰጥቶት የነበረው የገቢዎች ሚኒስቴር በ2013 የበጀት ዓመት ከተሰበሰው አጠቃላይ ገቢ የ57.4 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው የ336.7 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር በጠቅላላው የሰበሰበው ገቢ በ2013 የበጀት ዓመት ከተሰበሰበው የ279 ቢሊዮን ብር ሆኖ የ57.4 ቢሊዮን ብር ብልጫ የታየበት ሲሆን፣ በአንፃሩ በበጀቱ ዓመቱ ይሰበሰባል ተብሎ ከታቀደው የ360 ቢሊዮን ብር ገቢ በ23 ቢሊዮን ብር ያነሰ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፣ በ2014 ዓ.ም የተሰበሰበው ገቢ፣ በአገሪቱ በተፈጠረው ጦርነት ሳቢያ ብዙ ተቋሞች ከሥራ ውጪ በሆኑበት፣ የንግድ እንቅስቃሴዎች በተቀዛቀዙበት ዓመት የተገኘ ሲሆን፣ በሌሎችም አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ሳቢያ ተቋማት በአግባቡ ሥራቸውን ለመሥራት መቸገራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የንግዱ ማኅበረሰብም ሥራውን ተረጋግቶ አለመሥራቱ ከግምት ሲገባ የተሰበሰበው ገቢ የተሻለ የሚባል መሆኑን ጠቅሷል፡፡

 ከአገር ውስጥ ታክስ የተሰበሰበው ገቢ 196.2 ቢሊዮን ብር የሚሸፍን ሲሆን፣ ከዚህ የገቢ ምንጭ 205 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ግብ ተጥሎ እንደነበር ተመላክቷል፡፡ በሌላ በኩል ከውጭ ንግድ ቀረጥና ታክስ 140.4 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡ ከውጭ ንግድ ቀረጥና ታክስ 154.7 ቢሊዮን ለመሰብሰብ መታቀዱ ይታወሳል፡፡

 የ2015 በጀት ዓመድ ዕቀድ ሪፖርት በቀረበበት ወቅት እንደተመላከተው፣ በ2011 በጀት ዓመት መጀመሪያ ግማሽ ዓመት ተስፋ ሰጪ የታክስ አሰባሰብ ታይቶ የነበረ ቢሆንም፣ ከኮቪድ ወረርሽኝ መከሰት ጋር ተያይዞ በተከሰተው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መዳከም ምክንያት የተጠበቀው ውጤት ሳይገኝ መቅረቱ፣ ከዚያም በኋላ ባሉት ሁለት ዓመታት ከተከሰተው ጦርነት ጋር ተያይዞ በገቢ ረገድ የተቀመጠውን የታክስ ጂዲፒ (GDP) ጥመርታ ማሻሻል ሳይቻል ቀርቷል፡፡ ነገር ግን በአንጻራዊነት የታክስ ገቢ አሰባሰቡ ዓመታዊ ዕድገት አላሳየም ማለት እንደማይቻል ተገልጾ ነበር፡፡

 ከ2011 እስከ 2013 ዓ.ም ጠቅላላ የመንግሥት ገቢ 18.6 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት ማስመዝገቡ ከዚህ ቀደም የተገለፀ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ የታክስ ገቢ ዓመታዊ ዕድገት 18.3 በመቶ ነበር፡፡ የታክስ ገቢ በተጠቀሱት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከአጠቃላይ የመንግሥት ገቢ ውስጥ በአማካይ 79.3 በመቶ ድርሻ ነበረው፡፡

ከዚህ ቀደም የገቢዎች ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፣ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ በመቀሌ ገቢዎችና ሚኒስቴር ጉምሩክ ኮሚሽን ቅርንጫፎች በ2014 የበጀት ዓመት የመጀመርያዎቹ አምስት ወራት ብቻ በድምሩ 1.8 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ምንም ገቢ ያልተሰበሰበ ሲሆን፣ በተመሳሳይ በኮምቦልቻ ገቢዎችና ጉምሩክ ኮሚሽን ቅርንጫፎች በአምስት ወራቱ ውስጥ ለመሰብሰብ ታቅዶ ከነበረው 2.3 ቢሊዮን ብር የተሰበሰበው 1.9 ቢሊዮን ብር ብቻ እንደነበረ ተገልጿል፡፡ በዚህም በተጠቀሱት ወራት ውስጥ ከመቀሌና ኮምቦልቻ አራት ቅርንጫፎች ይሰበሰባል ተብሎ ከታቀደው 3.3 ቢሊየን ብር ውስጥ፣ 1.9 ቢሊየን ብር ብቻ እንደተሰበሰበ መገለጹ የሚታወስ ሲሆን፣  በጠቅላላው 2.3 ቢሊየን ብር ሳይሰበሰብ መቅረቱ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች