Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት 16 የግል ባንኮች ከታክስ በፊት ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ አተረፉ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • አዋሽ ባንክ ከታክስ በፊት ትርፉ 9.17 ቢሊዮን ብር ደረሰ

በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ 16 የግል ባንኮች በ2014 የሒሳብ ዓመት ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ሲያተርፉ፣ ከዚህ ዓመታዊ ትርፍ ውስጥ 20 ቢሊዮን ብር ያህሉ በሦስት የግል ባንኮች የተገኘ መሆኑ ታውቋል፡፡

የግል ባንኮቹ በ2014 የሒሳብ ዓመት ትርፍ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡ ሪፖርተር ያገኘው ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ ዘንድሮ ከግል ባንኮች አዋሽ ባንክ ከፍተኛ ትርፍ በማግኘት ቀዳሚ መሆን ችሏል፡፡ ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ያስመዘገበው ትርፍ 9.17 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

አዋሽ ባንክ በሒሳብ ዓመቱ ያስመዘገበው ትርፍ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 3.32 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባንኩ በ2013 የሒሳብ ዓመት ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ያገኘው ትርፍ 5.84 ቢሊዮን ብር እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ከአዋሽ ባንክ ቀጥሎ ከግል ባንኮች ሁለተኛውን ከፍተኛ ትርፍ ያስመዘገበው አቢሲኒያ ባንክ መሆኑን ዓመታዊ ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ አቢሲኒያ ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ያገኘው ትርፍ 5.4 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

አቢሲኒያ ባንክ የዘንድሮ የትርፍ ምጣኔው ከግል ባንኮች ሁለተኛውን ከፍተኛ የትርፍ መጠን ያስመዘገበበት ዓመት ከመሆኑም በላይ፣ የትርፍ ምጣኔውን በእጥፍ ለማሳደግ መቻሉንም አመላክቷል፡፡   

ባንኩ በ2014 የሒሳብ ዓመት ያገኘው ትርፍ ባለፈው ዓመት ካገኘው በ2.76 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው ሲሆን፣ በ2013 የሒሳብ ዓመት ባንኩ ያስመዘገበው ትርፍ 2.66 ቢሊዮን ብር በመሆኑ የዘንድሮ ትርፉ ከእጥፍ በላይ አድርጎ 5.4 ቢሊዮን ብር ሊደርስ ችሏል፡፡

ዳሸን ባንክም 4.48 ቢሊዮን ብር በማትረፍ የሒሳብ ዓመቱን ያጠናቀቀ ሲሆን፣ ዓመታዊ ትርፉንም በ1.4 ቢሊዮን ብር ማሳደግ ችሏል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ አገኛለሁ ብሎ ካቀደው በላይ ትርፍ ማግኘቱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከግርድፍ የሒሳብ ሪፖርቱ መረዳት እንደተቻለው፣ ከእነዚህ ባንኮች ሌላ ዓመታዊ ትርፋቸውን ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ማሳደግ ከቻሉት ውስጥ ኅብረት ባንክ፣ የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ፣ ዘመን ባንክ፣ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክና ንብ ባንክ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በግርድፍ የሒሳብ ሪፖርቱ መሠረት በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የትርፍ ምጣኔያቸውን ካሳደጉ ባንኮች መካከል ኅብረት ባንክ 2.7 ቢሊዮን ብር፣ ኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ 3.9 ቢሊዮን ብር፣ ዘመን ባንክ 2.27 ቢሊዮን ብር፣ ኦሮሚያ ባንክ 1.89 ቢሊዮን ብር፣ ቡና ባንክ 1.62 ቢሊዮን ብር፣ ወጋገን ባንክ 1.43 ቢሊዮን ብር፣ ንብ ባንክ 2.42 ቢሊዮን ብር ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ትርፍ አግኝተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች