Sunday, May 26, 2024

የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ወደ ትግራይ የሚጓጓዝ ስድስት ሺ ቶን ማዳበሪያ ለፋኦ ማስረከቡን አስታወቀ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በትግራይ ክልል ላሉ አርሶ አደሮች የሚላክ ከስድስት ሺ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) ማስረከቡን አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ በብቸኝነት ማዳበሪያን ወደ አገር ውስጥ የሚያስገባው ኮርፖሬሽኑ፣ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ 6,200 ኩንታል ማዳበሪያ ለፋኦ፣ ያስረከበው ከአንድ ወር በፊት የግብርና ሚኒስቴር፣ ፋኦ ከኮርፖሬሽኑ ማዳበሪያ እንዲገዛ የሰጠውን ፈቃድ ተከትሎ ነው፡፡

ኮርፖሬሽኑ በየዓመቱ ‹‹ከአቅም በላይ የሆነ አጥረት እንዳይፈጠር›› በሚል ከሚይዘው መጠባበቂያ ላይ በመቀነስ ይኼንን የማዳበሪያ መጠን ለፋኦ ማስረከቡን የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማሪያም ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ ኮርፖሬሽኑ ይኼንን የማዳበሪያ መጠን ለፋኦ የሸጠው፣ ማዳበሪያው የተገዛበት፣ የታሸገበትና ወደ አገር ውስጥ የተጓጓዘበትን ወጪ በማሰብ ብቻ ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ ከዚህ ቀደም ባለው አሠራር ከአርሶ አደሮች ውጪ ላሉ አካላት የአፈር ማዳበሪያ የሚሸጠው ተጨማሪ ትርፍ በማከል ነበር፡፡

ኮርፖሬሽኑ ለፋኦ ካስረከበው የአፈር ማዳበሪያ ግማሽ ያህሉ ኤንፒኤስ (NPS) ማዳበሪያ ሲሆን ቀሪው ዩሪያ ነው፡፡ ፋኦ ኤንፒኤስ ማዳበሪያን ከኮርፖሬሽኑ ወስዶ መጨረሱንና ዩሪያ ማዳበሪያን እያጓጓዘ መሆኑን  ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡

ፋኦ ወደ ትግራይ የሚያጓጉዘውን ተጨማሪ ስድስት ሺ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ለመረከብ፣ ጥያቄ ማቅረቡን የተናገሩት አቶ ክፍሌ፣ ድርጅቱ ተጨማሪውን ለመግዛት አስፈላጊ ሒደቶችን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንደሚያስረዱት ኮርፖሬሽኑ አሁን ያስረከበውንም ሆነ በቀጣይ ለድርጅቱ የሚሸጠውን የማዳበሪያ ሽያጭ ክፍያ ተረክቦ የሸጠውን ያህል ማዳበሪያ ወደ መጠባበቂያው ይተካል፡፡ የመጀመሪያውን ስድስት ሺ ቶን ሽያጭ ክፍያ ለመቀበል በሒደት ላይ ሲሆን፣ ፋኦ ሁለተኛውን ስድስት ሺ የአፈር ማዳበሪያ እንደሚገዛ የመጨረሻ ማረጋገጫ ሲሰጥ ለመተኪያው የግዢ ሒደት እንደሚጀመር አስታውቀዋል፡፡

ለመተኪያ የሚሆነው ማዳበሪያ ግዢ የሚፈጸመው ከተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ መሆኑንና በአምስት ቀናት የመርከብ ጉዞ ጅቡቲ ወደብ መድረስ እንደሚችል አቶ ክፍሌ አክለዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ፣ የመጀመሪያ ዙር የሆነውን 262 ቶን የአፈር ማዳበሪያ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር ወደ ትግራይ ክልል ማስገባቱን አስታውቋል፡፡ ፋኦ በመግለጫው በመጀመሪያው ዙር ወደ ትግራይ ክልል ያስገባው ማዳበሪያ፣ በክልሉ ያለውን የምግብ ዋስትና ዕጦት አደጋ ለመግታት ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ማግኘት የቻለው 19,300 ቶን ማዳበሪያ አካል መሆኑን ገልጿል፡፡

በመጪዎቹ ሳምንታት ከአጋር አካላት ጋር በመሆን 60,000 ቶን ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ማቀዱን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል፡፡ በትግራይ ክልል ያለው የምርት ጊዜው እየተጠናቀቀ መሆኑን ያነሳው የፋኦ መግለጫ፣ ይሁንና የኢትዮጵያ መንግሥት ማዳበሪያውን በገዛበት ገንዘብ ለመሸጥ ያቀረበውን ዕድል በመጠቀም ዩሪያ ማዳበሪ ማቅረብ እንደሚችል አስታውቋል፡፡

በትግራይ ክልል ያለው የዝናብ መጠን ለእርሻ ምቹ ነው ተብሎ እንደሚታሰብና የክልሉ አርሶ አደሮች ከማዳበሪያም ባሻገር ምርጥ ዘሮችና የተለያዩ ግብዓቶችን ማግኘት እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡ ይሁንና አንዳንድ የዘር ዓይነቶች የመዝሪያ ጊዜያቸው እየተጠናቀቀ መሆኑን የፋኦ መግለጫ አስረድቷል፡፡

ድርጅቱ በክልሉ ያለውን የማዳበሪያ አቅርቦትና ፍላጎት ለማሟላት የ53 ሚሊዮን ዶላር ጉድለት እንዳለበት አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -