Wednesday, May 22, 2024

ፈታኝ የሆነው የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በዓለም አቀፍ ደረጃ የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶችን ጀርሞች ከመላመዳቸው ጋር ተያይዞ በየዓመቱ ከ700 ሺሕ በላይ ዜጎች ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡ ይህም የሚያሳየው በጉዳዩ ላይ ትኩረት ተደርጎ አለመሠራቱና ክፍተት መኖሩን የዘርፉ ተዋናይ የሆኑ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በኢትዮጵያ የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መላመድ ከፍተኛ ሥጋት መሆኑን በአንድ መድረክ ተገልጿል፡፡ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመሥራት ኮሚቴ አዋቅሮ ወደ ሥራ መግባቱን ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ውይይት ባደረገበት ወቅት አስታውቋል፡፡

በውይይቱም ላይ ንግግር ያደረጉት የጤና ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሙሉጌታ እንዳለ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶችን በአግባቡና በትክክለኛው መንገድ ላቦራቶሪ ምርመራ አድርጎ የታዘዙ መድኃኒቶችን ያለመጠቀም እንዲሁም ደግሞ ጀምሮ በማቋረጥ የተነሳ ችግሩ ይከሰታል፡፡

የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መላመድ በሰው ልጆች ላይ ብቻ ሳይሆን በእንስሳት እንዲሁም በዕፀዋት ላይ እንደሚከሰት የገለጹት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፣ ይህም ችግሩን እንደሚያገዝፈውና የጎንዮሽ ተመጋጋቢ ጉዳት እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡

በፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መላመድ ሆኖ እንዳይቀጥል ማኅበረሰቡ ላይ መሥራት እንደሚገባ ገልጸው፣ ይህንንም ለማሳካት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የመድኃኒትና የሕክምና መሣሪያ አቅርቦትና አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰይፈ ደምሴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መላመድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሥጋት ከሆኑ ነገሮች ተርታ ይመደባል፡፡

ቢሮው የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት በቅርቡ ኮሚቴ ማዋቀሩን የተናገሩት አቶ ሰይፈ፣ የተዋቀረውም ኮሚቴ አምስት መሠረታዊ ነገሮችን በማካተት የሚሠራ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡

ከሌሎች አገሮች አንፃር ይህ ሥራ እንዳልተሠራ፣ በተለይም የጉዳቱን አሳሳቢነት በመረዳት ቢሮው የምርምር ተቋሞች ላይ በመሄድ ወጥ የሆነ ሥራ ለመሥራት ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን አብራርተዋል፡፡

በተለይም የፀረ ተህዋስያን በሽታ የሚሆኑ መድኃኒቶች በጀርሞች መላመዳቸው አሳሳቢ ያደርገዋል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ እነዚህም መድኃኒቶችን 90 በመቶ ለሕሙማኑ የማዳን አቅማቸው የተዳከመ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የሕክምና ተቋማትና ፋርማሲዎች ላይ በመሄድ ምን ያህል መድኃኒቶቹ በሽታዎችን የመከላከል አቅም አላቸው? የሚለውን ማጤን እንደሚገባና ይህንን ተፈጻሚ ለማድረግ ኮሚቴው የሚሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዘርፉ ላይ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ እ.ኤ.አ. ከ2021 ጀምሮ እስከ 2025 ድረስ የሚቆይ አሠራር መዘርጋቱን አስታውሰው፣ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሥጋት ሆኖ የነበረውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አንፃር መታየት እንደሚኖርበት ጠቁመዋል፡፡

በየጤና ዘርፉ የሚገኙ ባለሙያዎችን ሆነ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ በመሄድ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የንፅህና አያያዝ ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ አክለዋል፡፡

ይህ ችግር በዚህ ከቀጠለ እ.ኤ.አ. በ2050 ከአሥር ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሕይወታቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ ገልጸው፣ ይህንንም ለመታደግ ቢሮው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሠራ አቶ ሰይፈ ተናግረዋል፡፡

የችግሩ አሳሳቢነትን በመረዳት ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ሦስት ተቋማት በጋራ ለመሥራት ስምምነት ማድረጋቸውን ጠቅሰው፣ በቅርቡም የችግሩን ሁኔታ በማሰብ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ላይ የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል፡፡

የፀረ ተህዋስያን ጀርሞች መላመድ ጋር ተያይዞ ከሚነሱ በሽታዎች መካከል ለአብነት ያህል ተቅማጥ እንደሆነ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ ለዚህም በሽታ የሚሆኑ መድኃኒቶች የማዳን አቅማቸው የተዳከመ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -