Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በቤኒሻንጉል ክልል በበጀት ዓመቱ ከወርቅ ኩባንያ ሊገኝ የታቀደው 36 ኪሎ ግራም ብቻ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማዕድን ሚኒስቴር ከቀናት በፊት በጀመረው የ2015 ዓ.ም. በጀት ዓመት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለማግኘት ካቀደው 3036 ኪሎ ግራም ወርቅ ውስጥ፣ ሦስት ሺሕ ኪሎ ግራም ወይም 98.8 በመቶው የሚገኘው ከባህላዊ ወርቅ አውጪዎች ነው፡፡

በክልሉ በከፍተኛ የማዕድን ማምረት ሥራ ላይ ለማምረት ከማዕድን ሚኒስቴር ፈቃድ ከወሰዱት ከ20 በላይ ኩባንያዎች ውስጥ፣ አሁን እያመረተ ያለው በአሶሳ ዞን ፈቃድ የወሰደው ኤልኔት ቴክኖሎጂ ግሩፕ የተሰኘ አገር በቀል ኩባንያ ነው፡፡ ይኼ ኩባንያም ቢሆን በ2015 ዓ.ም. ያመርታል ተብሎ ዕቅድ የተያዘው 36 ኪሎ ግራም ወርቅ ብቻ መሆኑን ሪፖርተር ከማዕድን ሚኒስቴር መረጃ ተመልክቷል፡፡

ይህ ቁጥር በኦሮሚያ ክልል በቀጣዩ ዓመት ይመረታል ተብሎ ከታሰበው 4775 ኪሎ ግራም ወርቅ ውስጥ 45.9 በመቶውን ከሚያመርተው ሚድሮክ ኩባንያ ጋር ሲወዳደር እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ በአንጻሩ በጋምቤላ ክልል ሊመረት ከታቀደው 1727 ኪሎ ግራም ውስጥ 27 ኪሎ ግራሙን ከሚያመርተው ስቴላ የተሰኘ ኩባንያ ጋር ተቀራራቢነት አለው፡፡

በተጠናቀቀው የ2014 ዓ.ም. በጀት ዓመት ከአገር አቀፍ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ሁለተኛውን ቦታ የያዘው ማዕድን ዘረፍ በዓመቱ ከተገኘው 4.12 ቢሊዮን ብር ውስጥ 14 በመቶውን ሸፍኗል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ወርቅ ሲሆን፣ ወርቅ የ11 ወራት አፈጻጸም 513.9 ሚሊዮን ዶላር አስገኝቷል፡፡

ማዕድን ሚኒስቴር  በቀጣዩ ዓመት 10,378 ኪሎ ግራም ወርቅ የመሰብሰብ ዕቅድ ያለው ሲሆን፣ ከዚህም 879.3 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት አስቧል፡፡ በዚህ ዕቅድ ውስጥ ኦሮሚያ ክልል 46 በመቶውን ወርቅ በማስገኘት ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ተቀምጧል፡፡ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 29.2 በመቶውን በማምረት ሁለተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡

ክልሉ በተጠናቀቀው በጀተ ዓመት 2315 ኪሎ ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ አስገብቷል፡፡

የቤኒሻልጉል ጉሙዝ የማዕድን ሀብት ልማት ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ናስር መሐመድ፣ በክልሉ ለማምረት ከፌዴራል መንግሥት ፈቃድ የወሰዱት ሚድሮክ፣ ኩርሙክ ሌሎች ኩብንያዎች በሰላም መደፍረስና በውጭ ምንዛሪ ዕጦት ምክንያት ሥራ መጀመር አለመቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት መተከልና ካማሺ ዞን እንዲሁም ማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳ የፀጥታ ችግር እንዳለባቸው አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን ፈቃድ ከወሰዱ ከአሥር ዓመት በላይ የሆናቸው ኩባንያዎች በመኖራቸው የፀጥታ ችግር ብቻ መጠቀስ እንደማይችል አቶ ናስር ተናግረዋል፡፡

ይኼም ሆኖ በበጀት ዓመቱ በሥራ ላይ ካለው ኤልኔት ቴክኖሎጂ ግሩፕ የተሰኘው ኩባንያ ይገኛል ተብሎ የታሰበው 36 ኪሎ ግራም ብቻ መሆኑ እንደማያስማማቸው አስታውቀዋል፡፡ ዳይሬክተሩ ባለፈው ወር ሰኔ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ማዕድን ሚኒስቴር ይኼንን ዕቅዱን ባስረዳበት መድረክ ‹‹ድርጅቱ በዓመት 36 ኪሎ ግራም ብቻ ያመርታል ማለት በጣም አነስተኛ ነው ብዬ ተናግሬአለው›› ሲሉ ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው ለምርት የወሰደው ቦታ ያለው የወርቅ ክምችት አነስተኛ ከሆነ በባለሙያዎች መረጋገጥ እንዳለበት ያስረዱት ዳይሬክተሩ፣ ካልሆነ ግን የሚመሩት ቢሮ ኩባንያው ዕቅዱን ማስተካከል አለበት የሚል እምነት እንዳለው አስረድተዋል፡፡

የክልሉ መንግሥትም ኩባንያውን ለማነጋገርና ያጋጠመው ችግር ካለ ለመፍታት ለውይይት ጥሪ ማድረጉንም አቶ ናስር አስታውቀዋል፡፡

ኤልኔት ቴክኖሎጂ ግሩፕ በተያዘው ዓመት ፈቃድ ወስዶ ወደ ምርት ከገባ ሦስት ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ሰባት ኪሎ ግራም ወርቅ ማምረቱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ኩባንያው፣ በታኅሳስ 2014 ዓ.ም. የድንጋይ ከሰል በአገር ውስጥ ለማምረት ፈቃድ ለወሰዱ ስምንት ድርጅቶች ውስጥ አንዱ ሲሆን በክልሉ ካማሺ ዞን ድንጋይ ከሰል ለማምረት ፈቃድ ወስዷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች