ዓምና በነሐሴ ወር መካተቻ የበኩር (ሌጀንድ) ድምፃዊ ዓለማየሁ እሸቴ ዜና ዕረፍትን ተከትሎ ዕውቋ የነገረ ሙዚቃ (ሚዩዚኮሎጂ) ባለሙያ ትምክሕት ተፈራ (ዶ/ር)፣ ዕውቁን ድምፃዊ እንደሚከተለው ገልጻ ነበር፡፡ ‹‹የዓለማየሁ እሸቴ ዘፈኖች በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችም ሆኑ አዛውንቶች ዓውደ ሕይወታቸውን እንዲቃኙ ያደረጉ፣ የማነቃቂያ ምንጭም የሆኑላቸው ናቸው፡፡››
ትምክሕት (ዶ/ር) የዓለማየሁ የሙዚቃ ትሩፋቶችን ስትተነትን ከልጅነትና ታዳጊነት አልፎ እስከ ልሂቅነት በሕይወት መንገድ ለውጥ እንዲመጣ ማድረጋቸውም አውስታለች፡፡ በዓለማየሁ ሙዚቃ ሥራዎች ላይ በርካታ ጥናቶችን አዘጋጅታ በጆርናሎች ማሳተሟም አይዘነጋም፡፡
ዘንድሮ ደግሞ የድምፃዊውን ሕይወት ታሪክና ሥራ የሚገልጸውን መጽሐፏን ማሳተሟንና በአማዞን እንደሚገኝም ሰሞኑን በማኅበራዊ ትስስር ገጽዋ አስታውቃለች፡፡ የመጽሐፉ ርዕስም Reminisscing the Ethiopian James Brown Alemayehu Eshete`s Artistic Legacy ይሰኛል፡፡
አዘጋጇ በመግለጫዋ መጽሐፉ በ1950ዎቹ የኪነጥበብ ሥራውን የጀመረውንና እስካረፈበት 2013 ዓ.ም. ድረስ ለስድስት አሠርታት የቀጠለውን የታዋቂ ድምጻዊ ዓለማየሁ እሸቴ የሙዚቃ ትሩፋቱን ይቃኛል፡፡ በዋናነት ከ1950ዎቹና 1960ዎቹ የተውጣጡ ከ400 በላይ ጊዜ የማይሽራቸው ዜማዎቹን አበርክቷል፡፡ ልዩ በሆነው የአዘፋፈን ስልቱና ዘውጎቹ የታዋቂውን ጀምስ ብራውንን ስልት በማንፀባረቁ ‹‹ኢትዮጵያዊው ጀምስ ብራውን›› መሰኘቱ ተወስቷል።
ዓለማየሁ ገና በጉልምስና ሕይወቱ በአለባበሱና በአዘናነጡ፣ ከፀጉር አቆራረጥ ሥልቱ በመነሳትም፡- ‹‹የአቢሲኒያው ኤልቪስ›› የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶት የነበረ መሆኑም ይወሳል፡፡
ትምክሕት በቀዳሚዎቹ በአካዴሚያ ከላይ በታተሙት ጥናቶቿ የጠቀሰቻቸው አዲስ አበባ ቤቴ፣ ጭሮ አዳሪ ነኝ፣ ሕይወቴ አባቴ ነው፣ ማን ይሆን ትልቅ ሰው? መማር መመራመር፣ ተማር ልጄ፣ ትምህርት ቤቴ እና እናት እንጀራ እናት የተሰሙትን ጥቂቶቹን ዘፈኖች በዘመን አይሽሬ ቅኝት አግዝፋዋለች፡፡
በተለይ ‹‹ወርቃማ ዘመን›› ተብሎ በሚታወቀው የ1950ዎቹ እና 60ዎቹ ዓረፍተ ዘመን ገንነው ከተነሱት ድምፃውያን ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሠለፈው ዓለማየሁ ዘፈኖቻቸውን በሸክላ ካሳተሙ የመጀመርያዎቹ ድምፃውያን አንዱ ነበር፡፡ በአምሃ እሸቴ ሪከርዲንግ የተቀረፁት ሁለቱ ሥራዎች ‹‹ትማረኪያለሽ›› እና በሱዳንኛ ያቀነቀነው ‹‹ያታራ›› ናቸው፡፡
ዓለማየሁ በአለባበሱና በአዘናነጡ፣ ከፀጉር አቆራረጥ ሥልቱ በመነሳትም፡-
‹‹ዓለማየሁ ቴክሱ
ነጭ ነው ፈረሱ
ፊት ለፊት ይታያል
ፒያሳ ሲደርሱ›› የሚባለው ግጥማዊ ብሂልን በዚህ አጋጣሚ ይታወሳል፡፡
በ1933 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የተወለደው ዓለማየሁ እሸቴ፣ በፖሊስ ሠራዊት ኦርኬስትራ በ1955 ዓ.ም. ተቀጥሮ ለስድስት ዓመታት አገልግሏል፡፡ በእነዚያ ዘመናት ያቀነቀናቸው ዘፈኖች ተቃውሞና ፖለቲካ አዘል እንደነበሩ የትምክሕት ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ከነዚያ ዘፈኖች መካከል ያበጠው ይፈንዳ፣ ስቀሽ አታስቂኝ፣ ሲያውቁልሽ አታውቂ፣ ወልደሽ ተኪ እናቴ ይጠቀሳሉ፡፡
የፖሊስ ባንድ ባልደረባ የነበሩት የኮሎኔል ግርማ ኃይሌ ድርሰትና ቅንብር የሆነው ‹‹ወልደሽ ተኪ እናቴ›› በዘመኑ የነበረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ ጭቆና፣ ጉቦ፣ ኢፍትሐዊ አስተዳደርን በሰምና ወርቅ መንገድ የተገለጸውን ነው ዓለማየሁ ያቀነቀነው፡፡
ሃይ ዘራፍ እያሉ እያረረ አንጀቴ
እኔስ አልረባሽም ወልደሽ ተኪ እናቴ
አጋምና ቀጋ ለኔ ተስማምቶኛል
ቅቤማ ከጠጣሁ እንጥል ይወርደኛል
በስቃይ ወልደሽኝ በስቃይ አድጌ
መቼም አልተሻሻልኩ ልኑር ከሰው ግርጌ
ዮሜሳን ለሆዴ መች ይገዛልኛል
እንቆቆ እየተጋትኩ ዶሮ ማታ ይሉኛል
ቅቤውም ይትረፍረፍ ጮማም ይቆረጥ
እማማ እኔና አንቺ ሽሮ እናሯሩጥ፡፡
ዓለማየሁ ከፖሊስ ሠራዊት የኦኬስትራ ከለቀቀ በኋላ ባንዶች በሮሃ፣ ሸበሌ፣ አይቤክስ፣ ሶሊኮስ ባንድና በሙላቱ አስታጥቄ ባንድ በርካታ የሙዚቃ ሥራዎችን ማበርከቱን ገጸ ታሪኩ ያሳያል፡፡
በትውልድ ቅብብሎሽ ገዝፈው ከተገኙት ሥራዎቹ የሆነው ስለ ትምህርት የተጫወተው ‹‹ተማር ልጄ›› ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 በጀርመን ሽልማት ያገኘበት የዚህ ዘፈን አንዱ አንጓ የመማርን ልዕልና ያንፀባርቃል፡፡
‹‹ተማር ልጄ ተማር ልጄ
ወገን ዘመድ የለኝ ሀብት የለኝ ከጄ
ስማኝ ልጄ ሌት ፀሓይ ነው
ላልተማረ ሰው ግን ቀኑ ጨለማ ነው››
በአፍሪካ አሜሪካውያንም ሆነ በደቡብ አፍሪካ የሚታየውን የነጮች የበላይነትና የጥቁሮች መረገጥን የሚኮንነው ‹‹ጥቁር ግስላ›› ዓለማየሁን ካስከበሩት ሥራዎቹ መካከል ይጠቀሳል፡፡ በፊሊፕስ ሪከርድስ በ1965 ዓ.ም. የተለቀቀውና ከሸበሌ ባንድ ጋር የተጫወተውን ሙዚቃ ዓለማየሁ የጻፈው ሲሆን፣ ሙዚቃውን ያቀናበረው ደግሞ ግርማ በየነ ነው፡፡
ሽጉጥ መትረየሱን አንግቶታል
ያ ጥቁር ግስላ ደም ሸቶታል
ነጭ እባብ መሬቱን እያገላበጠ
ሠርተው እንዳይበሉ ሁሌ እያሯሯጠ
ሆዱን አደምብቶ ለሌሎቹ ተርፎ
ግስሎቹን ሁሉ ጨረሳቸው ነድፎ
ጥቁር እንደ አራዊት የተቆጠረበት
ምን ይሆን ምክንያቱ እንወቅ ምናለበት?
ብሎ በማለቱ በግር ተሰቀለ፡፡
በኩሩ ድምፃዊ ዓለማየሁ እሸቴ፣ በ80 ዓመቱ ያረፈው ነሐሴ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. እንደነበር ይታወሳል፡፡