Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አነስተኛ ካፒታል ያላቸው ባንኮች በመዋሃድ አቅም እንዲፈጥሩ ጉምቱው የፋይናንስ ባለሙያ መከሩ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ እንዳይገቡ የሚከለክለውን ሕግ የማሻሻል ሥራ እንደተጀመረና ማሻሻያው ተጠናቆ በሕግ አውጪው አካል ሲጸድቅ የውጭ ባንኮች የኢትዮጵያን የባንክ ኢንዱስትሪ እንደሚቀላለቁ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ተናገሩ።

ባለፈው ቅዳሜ የአኃዱ ባንክን መርቀው የከፈቱት የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር)፣ የሕግ ማሻሻያ ሥራው መጀመሩን ጠቁመው፣ ቀኑ አይቆረጥ እንጂ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ በመንግሥት ደረጃ ተወስኗል ብለዋል።

ይህንኑ የሚያረጋግጡ መረጃዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጀምሮ በተደጋጋሚ ሲናገር የተደመጠ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር)ም ባለፈው ቅዳሜ የአኃዱ ባንክ የአገልግሎት ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ የሚገቡ በመሆኑ የኢትዮጵያ ባንኮች ተወዳዳሪ ለመሆን በቴክኖሎጂ ረገድ ዝግጁ እንዲሆኑ መክረዋል።

ለውጭ ባንኮች የኢትዮጵያ ገበያ ክፍት እንደሚሆን እንዲህ ባለው መንገድ ተደጋግሞ ይገለጽ እንጂ እነዚህ የውጭ ባንኮች የሚገቡት በምን መንገድ ነው? የሚለው ጥያቄ በእንጥልጥል ላይ ያለ ነው፡፡ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎችን የማሰናዳቱ ሥራ በመንግሥት በኩል እየተካሄደ እንደሆነ ግን ይታወቃል፡፡ 

ሆኖም የአገባባቸው ሁኔታ እንዴት ይሆን የሚለው ወሳኝ ጉዳይ በምን መልኩ እንደሚመለስ ግልጽ አለመሆኑ ማነጋገሩ አልቀረም፡፡  

ጉምቱው የፋይናንስ ባለሙያ አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፣ የውጭ ባንኮችን ወደ ኢትዮጵያ ገበያ የማስገባት ጉዳይ ዘገየ ካልተባለ በስተቀር ፋይዳው አጠያያቂ እንዳልሆነ ገልጸዋል። ነገር ግን የውጭ ባንኮቹ ወደ ኢትዮጵያ ገበያ የሚገቡበት ሒደት እንዴት ይሆናል የሚለው ጉዳይ በግልጽ መታወቅ እንዳለበት የተናገሩት አቶ ኢየሱስወርቅ፣ በዚያውም ልክ አገር በቀል ባንኮች በሁሉም ረገድ ዝግጁ እንዲሆኑ ከወዲሁ ብዙ መሠራት እንደሚገባቸው ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።

ከውጭ ባንኮች ጋር በተያያዘ የሚሰሙ መረጃዎች ሁሉ ‹‹ይገባሉ›› ከሚል በቀር እንዴት ይገባሉ የሚለውን ጥያቄ አለመመለሱን፣ ነገር ግን ይህ ጉዳይ ቁልፍ እንደሆነ የሚያመለክቱት አቶ ኢየሱስወርቅ መንግሥት የውጭ ባንኮች ሲገቡ ሁሉንም ነገር ወለል አድርጎ መክፈት እንደሌለበት ይሞግታሉ፡፡ 

እንደ እሳቸው ምልከታ የውጭ ባንኮች መግባት ያለባቸው ደረጃ በደረጃ ነው፡፡ መጀመርያ አሁን ካሉት የአገር ውስጥ ባንኮች ላይ አክሲዮን በመግዛት ሊሆን ይገባልም ይላሉ፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ የውጭ ባንኮች ሙሉ በሙሉ እንዲገቡ የሚፈቀድ ከሆነ ግን ኢኮኖሚያዊ ጦስ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የውጭ ፋይናንስ ተቋማትን ወደ አገራቸው እንዲገቡ ፈቅደው የነበሩ እንደ አርጀንቲና እና ፊሊፒንስ የመሰሉ አገሮች ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ የገጠማቸው በራቸውን ለውጭ ባንኮችን ሙሉ በሙሉ ወለል አንድርገው በአንድ ጊዜ እንዲገቡ በመፈቀዳቸው መሆኑን በማሳያነት ይጠቅሳሉ። 

የኢትዮጵያ መንግሥትም እንዲህ ካለው ታሪክ በመማር የውጭ ባንኮች የሚገቡበትን ሁኔታ በጥንቃቄ ማየት እንደሚኖርበትና በሩን ሙሉ በሙሉ ለውጭ ባንኮች ከመክፈት ይልቅ ደረጃ በደረጃ የሚገቡበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚሻል ይመክራሉ። የውጭ ባንኮች ይግቡ እንዲገቡ ማድረጉ ተገቢ ቢሆንም፣ ሁሉም በር ተከፍቶ በአንድ ጊዜ እንዲገቡ መፈቀድ የለበትም የሚለውን አቋማቸውንና ምክንያታቸውን የያዘ ምክረ ሐሳባቸውን ለብሔራዊ ባንክ በጽሑፍም በቃልም ማሳወቃቸውን ገልጸዋል፡፡ 

ከዚህ ባሻገር የውጭ ባንኮች ከመግባታቸው በፊት በአገር ውስጥ መከናወን ይገባዋል ያሉትንም ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡ የአገር ውስጥ ባንኮች ችግር የፋይናንስ አቅም ብቻ ሳይሆን የውድድር ልምድም እንደሌላቸው ይገልጻሉ።

‹‹ስለጤናማ የንግድ ውድድር (ፌር ኮምፒቲሽን) ብዙ ልምድ የለም አንዳንዴ የቢዝነስ ኮምፒቲሽን እንደ ጦርነት አድርገን ነው የምንቆጥረው፤›› ያሉት አቶ ኢየሱስወርቅ፣ የአገር ወስጥ የባንክ አገልግሎት ዘርፉ በቅድሚያ በነፃ የንግድ መርሕ ተገዝቶ እንዲሰራ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንና ይህንን ማድረግም የአገር ውስጥ ባንኮች ተቋማዊ ጉደለቶቻቸውን አርመው አቅማቸውን ለማሳደግ እንደሚጠቅማቸው ገልጸዋል። በተለይ የሰው ኃይል እጥረትን ለመቅረፍ ራሱን የቻለ የፋይናንስ ኢንስቲትዩት የግድ እንደሆነ ያሰምሩበታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ አንድም የባንክና የኢንሹራንስ ማሠልጠኛ ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ ባለመኖሩ የውጭ ባንኮችን አስገብቶ ተወዳደሩ ማለት ችግር ውስጥ መክተት እንደሚሆን ጠቅሰዋል፡፡ ይህንን ትልቅ ክፍተት ለመድፈን መፍትሔ ይሆናሉ ያልናቸውን ምክረ ሐሳብ ለብሔራዊ ባንክ ማቅረባቸውንም ገልጸዋል፡፡ 

‹‹መነሻ የሚሆን ሐሳብ ብትሰጡን ብለው በባንክ ዳይሬክተሮች የምክክር ማኅበር በኩል ተጠይቀን በኢንዱስትሪው ውስጥ የምንገኝ ወደ ሰባት የምንሆን ባለሙያዎች ሐሳብ አውጣጥተን መነሻ ሐሳብ አቅርበናል። በዋናነት ያነሳነውም የሥልጠና ኢንስቲትዩት ይቋቋም የሚል ነው፤›› ብለዋል። 

‹‹ኢንስቲትዩት ኦፍ ፋይናንሽያል ስተዲስ›› የሚባል ልህቀት ማዕከል ለምሥራቅ አፍሪካ ሁሉ ሊያገለግል በሚችል አደረጃጀት እንዲቋቋም ምከረ ሐሳብ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

ያቀረቡት ምክረ ሐሳብም በመጀመርያ ለመካከለኛ የባንክ አመራሮች ሥልጠና በመስጠት ለዘርፉ ማፍራት እንዲችል በዚህ ላይ እንዲያተኩር ወደፊት ግን በደንብ በፋይናንስ ዘርፍ በዲግሪ ደረጃ ትምህርት እንዲሰጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  

የሥልጠና ኢንስቲትዩቱ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው የሚመራና በመንግሥትና በግል ዘርፉ አጋርነት እንዲመሠረት በምክረ ሐሳባቸው መጠቆማቸውን የገለጹት አቶ እየሱስወርቅ፣ ሐሳቡ ተቀባይነት እንዳገኘና ወደ መሬት የማውረድ ሥራ ግን እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ 

ሌላው ከውጭ ባንኮች መግባት ጋር በተያያዘ ዝግጅት ሊደረግባቸው ከሚገቡ ጉዳዮች አንዱ ጉዳይ ጤናማ የንግድ ውድድር በአገሪቱ እንዲጀመር የሚያስችል ሥርዓት ማበጀትና ማለማመድ እንደሆነ ገልጸዋል።

በተለይ በዘር በሃይማኖትና በመሳሰሉት መንገዶች የተበጀን የንግድ ሥርዓት በመተው በአገልግሎት ላይ የተመሠረተ የንግድ ሥራን ማጠናከር እንደሚያስፈልግና ይህም የዝግጅቱ አንድ አካል መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ 

አሁን ባለው ሁኔታ ብዙ የአፍሪካ ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ ለመግባት ፍላጎት እንዳላቸው፣ ለዚህም ሲሉ አብዛኞቹ በሯቸውን በአዲስ አበባ እየከፈቱ አንደሆነ የገለጹት አቶ ኢየሱስወርቅ፣ የአገር ውስጥ ባንኮችም በጋራም ሆነ በተናጠል ለውድድሩ ዝግጁ የሚያደርጋቸውን ሥራ መሥራት እንደሚነባቸው መክረዋል፡፡ 

በተለይ አነስተኛ ካፒታል ያላቸው ባንኮች በመዋሃድ አቅም መፍጠር የሚገባቸው አሁን እንደሆነ፣ በዚህ ረገድም አንዳንድ ንግግሮች መጀመራቸውንም ጠቆም አድርገዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች