Monday, December 4, 2023

የኢትዮጵያና የሱዳን አመራሮች ስለጋላባት ድንበር መከፈት ለመነጋገር ቀጠሮ ያዙ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮጵያና የሱዳን አመራሮች ለአንድ ወር ገደማ ተዘግቶ የቆየውንና በመተማ በኩል ኢትዮጵያና ሱዳንን የሚያዋስነው የጋላባት ድንበር መከፈት በተመለከተ ለመነጋገር፣ ለነገ ሐሙስ ሐምሌ 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ቀጠሮ ያዙ፡፡

የሱዳን ወታደራዊ ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄኔራል ነቢል አብደላህ ዓሊ እሑድ ሐምሌ 10 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ ሱዳን ድንበሩን እንደከፈተች ቢገልጹም፣ እስካሁን ድረስ የሰውም ሆነ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ አለመጀመሩን የመተማ ዮሐንስ ከተማ አስተዳደር ሚዲያ ልማትና ብዝኃነት ቡድን መሪ አቶ ልዑልሰገድ አሰፋ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በሱዳን ወታደራዊ አመራር የተሰጠውን መግለጫ ተከትሎ በሱዳን በኩል ያለው ኬላ በመከፈቱ ረዕቡ ሐምሌ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ነዳጅ የጫኑ ሁለት ተሽከርካሪዎች ወደ መተማ ዮሐንስ ከተማ መጥተው እንደነበር የገለጹት አቶ ልዑልሰገድ፣ መኪኖቹ ከእነ ጭነታቸው እንዲመለሱ መደረጉን አስረድተዋል፡፡ እንደ ቡድን መሪው ገለጻ መኪኖቹ እንዲመለሱ የተደረገው፣ ስለድንበሩ መከፈት በሁለቱ ከተሞች በኩል የጋራ ንግግርና ስምምነት ባለመኖሩ ነው፡፡

አቶ ልዑልሰገድ አሁን ስለድንበሩ መከፈት ንግግር የሚደረገው በሱዳን መንግሥት በኩል በቀረበ ጥሪ መሆኑን ጠቁመው፣ በኢትዮጵያ በኩልም ለንግግር ፍላጎት ቢኖርም ንግግሩ በሚደረግበት ቦታ ላይ እስካሁን መግባባት እንዳልተደረሰ ገልጸዋል፡፡ በሱዳን በኩል ንግግሩ፣ በሱዳን ጋላባት ከተማ እንዲደረግ ሲፈልጉ፣ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ ከዚህ በፊትም ንግግር የሚደረገው በመተማ ዮሐንስ ከተማ እንደሆነ በመጥቀስ፣ ንግግሩ በከተማዋ ይደረግ የሚል ሐሳብ መኖሩን አስረድተዋል፡፡ የሱዳን ሠራዊት ጄኔራሎችና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጄኔራሎች የንግግር ቦታውን ለመወሰን በውይይት ላይ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡

የቡድን መሪው እንደሚያስረዱት፣ ድንበሩ ከአንድ ወር ገደማ በፊት ሰኔ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. የተዘጋው ሱዳን ‹‹ስምንት ወታደሮች ተገድለውብኛል›› በማለት ያነሳችውን ቅሬታ ተከትሎ ነው፡፡ ‹‹በፈለጉ ሰዓት የሚዘጉት፣ ደስ ሲላቸውም የሚከፍቱት እነሱ ናቸው፤›› ያሉት አቶ ልዑልሰገድ፣ የአሁኑን ጨምሮ በተደጋጋሚ ድንበሩን መዝጋትና የመክፈቱ ውሳኔ በአንድ ወገን የተወሰነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አሁን የድንበር ተከፍቷል ውሳኔው ከሱዳን በኩል ይምጣ እንጂ ለከተማው አመራር የተገለጸ ነገር አለመኖሩን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው ልምድ ጥምር ግብረ ኃይሉ የሚገናኘው ከሁለቱም ማኅበረሰቦች የተውጣጡ ሽማግሌዎችና ወጣቶች በሚያደርጉት ግፊት መሆኑን ተናግረው፣ ‹‹አሁን ከእነሱ መንግሥት መምጣቱ ትንሽ ግር ይላል፤›› ብለዋል፡፡

በከተማው የሚገኙትን የጉምሩክ፣ የኢምግሬሽን፣ የሰላምና ደኅንነት ቢሮዎችን፣ እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊትና ፖሊስን የያዘ የሁለቱ ከተሞች የድንበር ጥምር ግብረ ኃይል መኖሩን ገልጸው፣ ከዚህ በፊትም ድንበሩ የሚከፈተው ግብረ ኃይሉ ንግግር ካደረገ በኋላ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የአማራ ክልል ከፍተኛ ኃላፊ፣ ሐሙስ ዕለት ይደረጋል በተባለው ንግግር ቀጠሮ መያዙን አረጋግጠዋል፡፡

‹‹ጠንከር ያለ ግምገማና ንግግር መደረግ አለበት፤›› ያሉት ኃላፊው፣ በኢትዮጵያ በኩል ስለተደጋጋሚው የድንበር መዘጋት ጉዳይና ጥቃት ስለሚፈጽሙ በሱዳን ያሉ ታጣቂዎች ጉዳይ ቁርጥ ያለ አቋም እንዲያዝ ፍላጎት መኖሩን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ታጣቂዎቹ ትጥቅ ይፍቱ ወይም ለኢትዮጵያ ተላልፈው ይሰጡ›› የሚል አቋም ሊያዝ እንደሚችልም አክለዋል፡፡

ከዚህ በፊት የድንበሩ ጉዳይ ሲነሳ ሕዝባዊ ግንኙነቱን ማጠናከር ላይ ትኩረት ይደረግ እንደነበር አውስተው፣ አሁን ጉዳዩ ፖለቲካዊ አዝማሚያ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

የጋላባት ድንበር ከዚህ ቀደም ለስድስት ወራት ተዘግቶ ከቆየ በኋላ፣ በብርጋዴር ጄኔራል በሽር ሰዒድ የሚመራ የሱዳን ወታደራዊ መኮንኖች ልዑክ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አመራሮች፣ እንዲሁም ከአማራ ክልል አመራሮች ጋር ንግግር ካደረገ በኋላ ድንበሩ እንዲከፈት ስምምነት ላይ ተደርሶ የካቲት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. እንዲከፈት ተደርጎ ነበር፡፡

በየካቲት ወር በከተማዋ በተደረገው ንግግር ድንበር ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ መፍታት እንጂ፣ ድንበር መዘጋት እንደሌለበት ስምምነት ላይ ተደርሶ እንደነበር አቶ ልዑልሰገድ ገልጸዋል፡፡

ባቄላ፣ ዳቦ፣ ውኃና ሌሎች መሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎችን ወደ ጋላባት ከተማ የሚገቡት ከኢትዮጵያ መሆኑን አቶ ልዑልሰገድ ተናግረው፣ በዚህም ምክንያት ወታደራዊ አመራሩ ድንበሩን እንዲከፍት ከፍተኛ ጫና እንደሚያደረግ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሕዝባቸው ጫና ሲያሳድርባቸው ድንበሩን እንክፈት ይላሉ፡፡ የራሳቸውን ፖለቲካዊ ፍላጎት ለማስፈጸም ደግሞ መልሰው ይዘጋሉ፤›› በማለት ሁኔታውን አስረድተዋል፡፡

በሱዳን የሚገኙና በአገሪቱ መንግሥት የሚደገፉ ኃይሎች በተደጋጋሚ ድንበር አልፈው በመምጣት ጥቃትና ዘረፋ እንደሚፈጽሙ አቶ ልዑልሰገድ አስረድተዋል፡፡ በሱዳን ይገኛሉ የተባሉት እነዚህ ኃይሎች የሕወሓት፣ የቅማንትና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የጋምቤላና የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መሆናቸውን የገለጹት ቡድን መሪው፣ ከሳምንት በፊት በመተማ ወረዳ ‹‹ቱመት›› በሚባል ቀበሌ ነዋሪዎች ላይ ጥቃትና የከብት ዝርፊያና መፈጸማቸውን ተናግረዋል፡፡ ጥቃት የተፈጸመበት አካባቢ ከመተማ ዮሐንስ ከተማ በቅርበት የሚገኝ በመሆኑ ተመሳሳይ ጥቃትን ለመመከት የከተማው የፀጥታ መዋቅር በከተማው የሚገኙ የመንግሥትና የግል የጦር መሣሪያ ባለቤቶች፣ ከልዩ ኃይልና ከመከላከያ የተሰናበቱ አባላት፣ እንዲሁም የሚሊሻና የፋኖ አባላትን በኮማንድ ፖስት ሥር እያደራጀ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -