Sunday, May 26, 2024

የኢትዮ ሶማሊያ ግንኙነትና የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በቅፅል ስማቸው ‹ታርዛን› እያሉ ይጠሯቸዋል፡፡ በናይሮቢ የኬንያ አምባሳደር የሆኑት መሐመድ አህመድ ሰኔ 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ለፕሬዚዳንታዊ ግብዣ በሚመጥን ሁኔታ ተዘጋጅተው ነበር ከኡሁሩ ኬንያታ ቤተ መንግሥት የተገኙት፡፡ ወደ ቤተ መንግሥቱ እንደዘለቁ በአዳራሹ ያዩት ነገር ግን በንዴት የሚያጦፋቸው ሆነ፡፡ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በናይሮቢ መቀመጫቸውን ላደረጉ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ያዘጋጁትን ታላቅ የክብር ድግስ አምባሳደር መሐመድ (ታርዛን) ወዲያው ጥለው ወጡ፡፡

ታርዛንን በንዴት ያጦፋቸው በኡሁሩ ኬንያታ ግብዣ ላይ የሶማሌላንድ አምባሳደር መታደም ብቻ ሳይሆን፣ ከታይዋን በስተቀር ማንም የዓለም አገር እውቅና ያልሰጣት የሶማሌላንድ ሰንደቅ ዓላማ እንደ አንድ ሉዓላዊ አገር በአዳራሹ ሲውለበለብ ማየታቸውም እንደሆነ የተለያዩ የዜና አውታሮች ዘግበዋል፡፡

ሶማሊያ የራሷ ሉዓላዊ አካል አድርጋ የምትቆጥራትን የሶማሌላንድን አምባሳደር ኬንያዎቹ መጋበዛቸውና ባንዲራቸውን በግብዣው አዳራሽ ማውለብለባቸው፣ የሶማሊያን ክብር መንካት ተደርጎ ነበር በአምባሳደር ታርዛን የተወሰደው፡፡

የኬንያ ባለሥልጣናት የአምባሳደሩ መቆጣት አስደነገጣቸው፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው በኩል ሳይታቀድና በስህተት ችግሩ መፈጠሩን በመጥቀስ ለሶማሊያ የይቅርታ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ የሶማሊያ ሰዎች ግን በኬንያ ላይ ያላቸው ቅያሜ ከዚህ ያለፈ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2020 ኬንያ የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቡሂን ተቀብላ ማስተናገዷ ሶማሊያን አስቆጥቶ ነበር፡፡ ሁለቱ አገሮች በድንበር ውዝግብ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ከገቡ በኋላ፣ ኬንያ የሶማሊላንድን ፖለቲካ ለመጠቀም መሞከሯ ሶማሊያዎችን በእጅጉ ነበር ያስቆጣው፡፡

ይህ ሁኔታ ሳይረሳ ኬንያውያኑ የሶማሌላንድ አምባሳደርና ባንዲራ ባለበት የሶማሊያን ዲፕሎማት መጋበዛቸው፣ ሁለቱን አገሮች ዳግም የሚያጋጭ ጥፋት ሆኖ ታየ፡፡ ሆኖም ጉዳዩ እንደተገመተው ሳይሆን ወዲያው ሲበርድ ነው የታየው፡፡ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ተሰናብተው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ በሞቃዲሾ ቤተ መንግሥት ከተሰየሙ ወዲህ፣ የሁለቱ አገሮች ወዳጅነት እንደሚሻሻል የሚጠበቅ ነበር፡፡

ባለፈው ሳምንት (ሐምሌ 8 እና 9) አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ፣ ናይሮቢን ሦስተኛዋ የውጭ አገሮች ጉብኝታቸው መዳረሻ ያደረጓትም ያለ ምክንያት አለመሆኑን ነው ብዙዎች የሚናገሩት፡፡

ስሜ አይጠቀስ ያሉ አንድ የምሥራቅ አፍሪካ የደኅንነት ባለሙያ፣ የሶማሊያ መሪ ኬንያን በቀዳሚነት ከሚጎበኟቸው አገሮች አንዷ ማድረጋቸው በቂ ምክንያት ያለው ነው ይላሉ፡፡ ‹‹በፎርማጆ ዘመን የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ፕሬዚዳንቱ ማርገብ ፈልገዋል ማለት ነው፤›› ሲሉ የሚናገሩት የደኅንነት ባለሙያው፣ ከዚያ ይልቅ ኢትዮጵያን ቀድመው አለመጎብኘታቸው እንዳስገረማቸው ነው የተናገሩት፡፡

በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት አቶ ዑስማን መሐመድ፣ አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንትን ‹‹ስለኢትዮጵያ የተሻለ ዕሳቤ ያላቸውና ከሁሉም ጋር ሊያግባባ የሚችል ዲፕሎማሲያዊ ባህሪ ያላቸው ሰው ናቸው፤›› በማለት ይገልጿቸዋል፡፡ በምርጫ ፉክክሩ ወቅት፣ ‹‹በውስጥም ሆነ በውጭ የተስማማች ሶማሊያን መፍጠር›› የሚል መፈክርን ይዘው መነሳታቸውን ያስታወሱት አቶ ዑስማን፣ ሰውየው ከኬንያ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሁሉም የጎረቤት አገሮች ጋር መልካም ግንኙነት ለመመሥረት እንደማይቸገሩ ግምታቸውን ገልጸው ነበር፡፡

ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ኬንያ ከመጓዛቸው አስቀድሞ በቱርክና በኤርትራ ነበር ጉብኝታቸውን ያደረጉት፡፡ ኬንያን አስከትለው ደግሞ ወደ ጂቡቲ በማቅናት አራተኛውን የውጭ ጉብኝታቸውን አካሂደዋል፡፡ ይሁን እንጂ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ የሶማሊያ ጥብቅ ወዳጅ፣ በኢኮኖሚና በፀጥታ ጠንካራ አጋር የምትባለዋን ኢትዮጵያን እስካሁን አለመርገጣቸው ብዙ ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ሆኗል፡፡

ይህ የሀሰን ሼክ ዕርምጃ እንዳስገረማቸው የገለጹት ስሜ አይጠቀስ ያሉት የምሥራቅ አፍሪካ የደኅንነት ተንታኙ፣ ‹‹ሰውየው አዲስ አበባ ይመጣሉ ተብሎ ፕሮግራም ተይዞ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን በቀናት ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ የሚል መረጃ አለኝ፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡

ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ቀጣይ የጉብኝት መዳረሻቸው ኢትዮጵያ እንደሆነ የሚተነብዩ በርካቶች ቢሆኑም፣ ይህን ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ለማጣራት የተደረገው ጥረት ግን አልተሳካም፡፡

አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ከኢትዮጵያ አስቀድመው እነ ማንን ጎበኙ የሚለው ብቻ ሳይሆን፣ በእነዚህ አራት ተከታታይ ጉብኝቶቻቸው አሳክተዋቸው የተመለሱ ጉዳዮችም ቢሆኑ ብዙ ጥያቄ እያስነሱ ናቸው፡፡ ከሁሉ በፊት ቱርክን ለምን ቀድመው እንደረገጡ ማብራሪያ የሰጡት የደኅንነት ባለሙያው፣ ‹‹ቱርክን ከሁሉ ቀድሞ መጎብኘቱም ሆነ ቀጥሎ አስመራ መጓዙ ለውስጥ የፖለቲካ አሠላለፍ ያግዘዋል፤›› ብለዋል፡፡

በፎርማጆ ዘመን በርካታ ወታደሮችን በማሠልጠንም ሆነ የገንዘብና ሎጂስቲክስ ድጋፍ በማድረግ ቱርክ ቀዳሚዋ አገር እንደነበረች የደኅንነት ምንጩ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ፈጥነው ወደ አንካራ ቢሄዱ ለኃይል አሠላለፍ ስለሚረዳቸው ጥያቄ አያስነሳም፤›› ይላሉ፡፡

በፎርማጆ ዘመን ‹‹ልጆቻችንን መልሱልን›› የሚል ተቃውሞ በሞቃዲሾ እንደታየ ያስታወሱት የደኅንነት ምንጩ፣ በስተመጨረሻ የሥልጣን ዘመናቸው ሊያበቃ ሲል፣ ‹‹ልጆቹ ኤርትራ ተልከው በውትድርና እየሠለጠኑ መሆኑን ይፋ አድርገው ነበር፤›› በማለት ሀሰን ሼክ ወደ አስመራ ያቀኑት እነዚህን ወታደሮች ለማስመለስ መሆኑን አውስተዋል፡፡

የሀሰን ሼክ የኤርትራ ጉብኝት በልዩ ወታደራዊ ፕሮቶኮልና በደማቅ የሰርከስ ትርዒት የታጀበ እንደነበር የኤርትራ ቴሌቪዥን ደጋግሞ አሳይቷል፡፡ የሶማሊያ ወታደሮች በዚያ ለሦስት ዓመታት ሲሠለጥኑ ቆይተዋል መባሉና ሀሰን ሼክ ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር እነዚህን ወታደሮች መጎብኘታቸው፣ ሰፊ ሽፋን የተሰጠው የወሬ ርዕስም ነበር፡፡ በአንዳንድ የዜና ምንጮች እንደተዘገቡት ከሆነ ደግሞ፣ የሀሰን ሼክ የኤርትራ ጉብኝት ወደ 5,000 ሠልጣኝ ወታደሮች ወደ አገራቸው ለመመለስ ያለመ ነው ተብሏል፡፡

ሀሰን ሼክ በቀጣይ የቀጣናው አገሮች ጉብኝታቸው ምናልባት መዳረሻቸው ኢትዮጵያ ልትሆን ትችላለች ቢባልም፣ እሳቸው ግን ወደ ናይሮቢ መብረርን ነው ያስቀደሙት፡፡

‹‹ወደ ኢትዮጵያ ቀድመው መምጣት ነበረባቸው፣ ምክንያቱም ለሶማሊያ ከማንም በላይ መስዕዋት ስንከፍል የኖርነው እኛ ነን፤›› ሲሉ የተናገሩት የደኅንነት ምንጩ ግን፣ የፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ተከታታይ የጉብኝት መርሐ ግብር ቅደም ተከተል ግራ እንዳጋባቸው ነው ያስረዱት፡፡

ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ባልተጠበቀ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ቀድመው ወደ ኬንያ አቀኑ ቢባልም፣ ብዙዎች እንደገመቱት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ለማስተካከል ጥረት አድርገዋል ተብሏል፡፡ ሀሰን ሼክ ከፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር ተገናኝተው ከተነጋገሩ በኋላ ይፋ በተደረገው መግለጫ የኬንያ አየር መንገድ ወደ ሞቃዲሾ ዳግም በረራ እንዲጀምር መስማማታቸው ተገልጿል፡፡ ተቋርጦ የነበረው የኬንያ ጫት ኤክስፖርትም በአስቸኳይ እንዲቀጥል መሪዎቹ መግባባት ላይ መድረሳቸው በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ከኬንያ፣ ከጂቡቲ፣ ከኢትዮጵያ መሪዎችና ከቀድሞው የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ጋር
አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ከኬንያ፣ ከጂቡቲ፣ ከኢትዮጵያ መሪዎችና ከቀድሞው የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ጋር

በሰኔ ወር የሶማሊያ አምባሳደር መሐመድ አህመድ (ታርዛን) በቤተ መንግሥት ድግስ ላይ የሶማሌላንድ ባንዲራና አምባሳደርን አየሁ ብለው በመበሳጨታቸው፣ ኬንያዎቹ ግንኙነታችን ተበላሸ ብለው መደንገጣቸው የሚጨበጥ ሥጋት እንደሆነ የሀሰን ሼክ የናይሮቢ ጉብኝት ያረጋገጠ ይመስላል፡፡

ኬንያዊያኑ ከሶማሊያ ጋር ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ጎንበስ ቀና ሲሉ፣ ኤርትራ በወታደራዊ ማርቺንግ ባንድና በሰርከስ ትርዒት ሀሰን ሼክን ስትቀበል፣ ጂቡቲ በቀይ ምንጣፍ ስታስተናግዳቸው፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ምን እየሠሩ ነው የሚለው ጥያቄ ተከትሎ መምጣቱ አይቀርም፡፡

ሀሰን ሼክ አስቀድመው ወዴት አመሩ ወይም ከየትኛው አገር ጋር ምን ተስማሙ የሚለው ጥያቄ ብቻም ሳይሆን፣ በሀሰን ሼክ ከምትመራዋ ሶማሊያ ጋር እንዴት ግንኙነትን ማጠናከር ይቻላል የሚለው ጉዳይ የምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ጂኦፖለቲካን የሚበይን ጉዳይ እየሆነ ነው፡፡

ሶማሊያ እንደ ከዚህ ቀደሙ መንግሥት አልባ አገር (የከሸፈ መንግሥት) ተብላ የምትፈረጅ የጂኦፖለቲካ ጉዳይ አለመሆኗን ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ጂቡቲና ቱርክ ለአዲሱ ፕሬዚዳንት ካደረጉት አቀባበል ለመረዳት ብዙም እንደማይከብድ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

‹‹የቀድሞው የሶማሊያ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ ፎርማጆ ለደኅንነትና ለፀጥታ ጉዳይ ልዩ ትኩረት የሚሰጡ ነበሩ፡፡ የአሁኑ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ ደግሞ ለዲፕሎማሲና ለኢኮኖሚያዊ ትስስር ልዩ ትኩረት የሚሰጡ ሰው መሆናቸውን ከፖለቲካ ልምዳቸው ተነስቶ መናገር ይቻላል፤›› ሲሉ ይናገራሉ የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ምሁር አቶ ዑስማን መሐመድ ስለሁለቱ መሪዎች ልዩነት ሲያስረዱ፡፡

ብዙ ተንታኞች እንደሚናገሩት ከሆነ ደግሞ የቀጣናው አገሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ ሁሉም ከሶማሊያ ጋር ባላቸው ግንኙነት የደኅንነት፣ የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ትስስር መፍጠር ይሻሉ፡፡ ኬንያ ብቻ ሳትሆን እ.ኤ.አ. በ2020 ዓ.ም. 294 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሸቀጥ ወደ ሶማሊያ የላከችው ኢትዮጵያ፣ ሞቃዲሾ የጫት ምርት ገበያዋ ሆና እንድትቀጥል ትፈልጋለች፡፡

ለሽብር፣ ለጦርነት፣ ለረሃብና ለድርቅ ሁሌም ተጋላጭ በሆነው የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ያሉ አገሮች በሁሉም ረገድ ሚዛኑን የጠበቀ ግንኙነት መፍጠር ካልቻሉ ቀጣናው የበለጠ ተጋላጭ እንደሚሆን ብዙዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡

አንዳንድ ወገኖች ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ ከቀድሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ልዩ መቀራረብ እንደነበራቸው በማስታወስ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር እንደሚቸገሩ ይናገራሉ፡፡ እሳቸው ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ግንኙነት ማጥበቋን አልወደዱትም ይባላል፡፡ ኢትዮጵያ በሶማሌላንድ የወደብ ድርሻ ለማግኘት ያደረገችው ጥረት የሀሰን ሼክ ሶማሊያን እንደሚያስከፋ በመጥቀስ፣ አዲስ አበባን ያልረገጡበትን ምክንያት ከዚህ ጋር ያቆራኙታል፡፡

ይህን የማይስማሙበት የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲው አቶ ዑስማን ግን ሐሰን ሼክ ከአንድ አገር ጋር ብቻ ሳይሆን ከሁሉም ጋር መቀራረብ እንደሚችሉበት ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ፎርማጆ ሶማሊያን ከኢትዮጵያና ከኤርትራ ጋር በእጅጉ ቢያስተሳስሯትም፣ ነገር ግን ከሌሎች የቀጣናው አገሮች ጋር አቆራርጠዋት ቆይተዋል፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡ የአሁኑ መሪ ሀሰን ሼክ ግን ከኬንያ፣ ከጂቡቲም ሆነ ከኤርትራ ጋር ሶማሊያ እንድትተሳሰር እየጣሩ ነው የሚሉት አቶ ዑስማን፣ ይህ ማለት ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ይበጥሳሉ ማለት አለመሆኑን ያስረዳሉ፡፡

እሳቸው እንደገመቱት አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ከቀጣናው አገሮች ጋር ሚዛኑን የጠበቀ ትስስር ለመፍጠር አስበው ይሆን? ወይስ ኢትዮጵያን ከጉብኝታቸው ዝርዝር የዘለሉት የሚለው ጥያቄ በቀጣይ በሚፈጠሩ ለውጦች የሚታይ ይሆናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -