Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

የኢትዮጵያ ውስጣዊ ሰላም የሚታወከው የታሪካዊ ጠላቶች መሣሪያ በመሆናችን እንደሆነ ብዙ የተባለበት ነው፡፡ ይህንን ችግራችንን ሳስብ ከዛሬ አርባ ዓመታት በፊት ያጋጠሙን ችግሮች ፊቴ ድቅን ይሉብኛል፡፡ በእኛ አገር አንድ አሳሳቢ ነገር ሲያጋጥም ሰዎች በአብዛኛው ከአገር ጋር የሚገናኙ ጉዳዮችን ማንሳታቸው አይቀሬ ነው፡፡ እኔም የአገሬን የዓመታት መከራ ሳስብ የሕዝባችን ሰቆቃ ትውስ ይለኛል፡፡ ለዘመናት በጦርነት ውስጥ ያሳለፈች አገር በዚህ በሠለጠነ ዘመን ጦርነት ውስጥ ስትገባ ያሳስበኛል፡፡ ጦርነት ለአፍ ቀላል ሲሆን፣ ሲገቡበት ግን እጅግ በጣም ከባድ መሆኑን ብዙዎች አይስቱትም፡፡ ብዙ ጊዜ የታሪካዊ ጠላቶቻችን ተላላኪ ሆነው ጦርነትን የሚቀሰቅሱ የሚማግዱት ንፁኃንን ስለሆነ፣ እነሱ ከውጤቱ እንጂ ከሒደቱ ጉዳይ የላቸውም፡፡ ከቀናቸው ሥልጣን ይዘው እንዳሻቸው ለመሆን፣ ካልቀናቸው ደግሞ በደህና ጊዜ ራሳቸውን ስለሚያዘጋጁ መሸሻ አላቸው፡፡ እስቲ ወደኋላ ወስጃችሁ ከዛሬው ጉዳዬ ጋር ላገናኛችሁ፡፡

በ1966 ዓ.ም. የፈነዳውን አብዮት ተከትሎ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደ ገጠር እንድንዘምት ተወሰነ፡፡ “ዕድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ” በሚባለው ታዋቂ ፕሮግራም ከዘመቱ የወቅቱ ወጣቶች መካከል አንዱ ነበርኩ፡፡ አርሶ አደሩን ከአዲሱ የመሬት ለአራሹ አዋጅ ጋር ለማስተዋወቅና ከአብዮቱ ጎን ለማሠለፍ ክተት በተባለበት ዘመቻ፣ የእኔ ምድብ ጣቢያ ጎንደር አዲስ ዘመን ነበር፡፡ ከጣራ ገዳም ተራራ ጀርባ የምትገኘው አዲስ ዘመን ደርሰን ከአርሶ አደሮች ጋር መገናኘት ስንጀምር፣ የኢሕአፓ መልማዮች ቀድመው ደርሰው ተመለመልን፡፡ የተወሰኑ ወራት እንደ ቆየን የአካባቢውና ራቅ ያሉ ወጣቶች ኢሕአፓ ሆነን ትግሉን ቀጠልን፡፡ እየዋልን እያደርን ግን ችግር ተፈጠረ፡፡

ከደርግና ከመኢሶን ጋር ሆድና ጀርባ የሆነው ኢሕአፓ ዘመቻው ተግባራዊ መሆን የሚችለው፣ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ሲመሠረት ነው በማለት ዘመቻ ጣቢያዎቹ መዘጋት ጀመሩ፡፡ ያመረሩት በረሃ ሲወርዱ ሌሎቻችን ወደ መጣንበት መመለስ ጀመርን፡፡ በአጭሩ በዚያ አካባቢ ያሉ በርካታ ዘመቻ ጣቢያዎች ተዘግተው ዘመቻው ቆመ፡፡ እኔና አንድ የክፍል ጓደኛዬ የነበረ ዘማች ወደ ጎንደር ሄድን፡፡ ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ብናስብም፣ ጓደኛዬ የት እንደ ደረሰ ሳላውቅ ተለያየን፡፡ በውጥረት ውስጥ የነበረችው ጎንደር አስፈሪ ስለነበረች፣ እዚያ በደረስኩ በሁለተኛው ቀን ሰማያዊና ቢጫ ቀለም የነበረው የዘመኑ ታዋቂ አውቶብስ ድርጅት (ሰሜናዊ ትራንስፖርት) ላይ ተሳፈርኩ፡፡

ባለሁለት መቀመጫ ወንበር ላይ አንድ ትልቅ ሰው መስኮቱን ተደግፈው ተቀምጠዋል፡፡ አውቶብሱ ውስጥ ገብቼ አነስተኛ የእጅ ሻንጣዬን ፍርግርጉ ብረት ውስጥ ለማስቀመጥ ባዶ ቦታ ስፈልግ፣ አዛውንቱ በጥቅሻ ጠርተውኝ አጠገባቸው እንድቀመጥ አደረጉኝ፡፡ ሻንጣዬንም ከላይ ያለው ማስቀመጫ ውስጥ አስቀመጥኩት፡፡ ጉዞ ተጀመረ፡፡ አዛውንቱ ሐጂ አህመድ ሐሰን፣ ‹‹አንተ አሽከር ወዴት እየሄድክ ነው?›› በማለት ጨዋታ ጀመሩ፡፡ በጎንደር አሽከርና ውሪ ለወጣትና ለሕፃን የተሰጡ ስያሜዎች ስለሆኑ የሚያስከፉ አይደሉም፡፡ ዘመቻውን አቋርጬ እየተመለስኩ መሆኑን ነገርኳቸው፡፡ ጎፈሬዬንና አጠቃላይ ሁኔታዬን በዓይናቸው ሲመዝኑ ቆይተው ዝም አሉ፣ ጉዞው ቀጠለ፡፡

ወረታ ከተማ ስንደርስ፣ ‹‹እኔ ሙስሊም ነኝ፡፡ በአሁኑ መንግሥት ከሌሎች ዜጎች እኩል የእምነት ሥርዓታችንን በነፃነት እንድናከናውንና በዓላቱን እንድናከብር በመደረጉ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ነገር ግን አብዮቱን ያመጣችሁት እናንተ ወጣቶችና ወታደሮች፣ አገር አፅንተው ያስተዳደሩትን ንጉሥ ከእነ ባለሟሎቻቸው ገድላችሁ እርስ በርስ መታኰስ ጀመራችሁ፡፡ አንድ ዓይነት ነገር እያወራችሁ መስማማት ያቃታችሁ፣ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት በተላላኪው አማካይነት ውስጣችሁ ስለገባ ነው፡፡ ይህንን እንኳን ለምን እንደማታመዛዝኑ አይገባኝም፡፡ አሁንማ ለይቶላችሁ መጋደል ጀመራችሁ፡፡ ምን ዓይነት መጽሐፍ እያነበባችሁ ምን እንደምታስቡ አይገባኝም፤›› ብለው ዝም አሉ፡፡ እኔ በወቅቱ በጥራዝ ነጠቅ የማውቀውን ማርክሲዝም እየቀላቀልኩ አገሪቱን ከኋላቀርነት ስለማላቀቅና ማኅበራዊ እኩልነት ስለማምጣት ስቀባጥር፣ ‹‹ተው እባክህ… ይኼ የአገርን ታሪክና የሕዝቡን አኗኗር የማያገናዝብ ወሬ ወዲያ በልልኝ…›› ብለው ገሰፁኝ፡፡ እንደ ተኳረፍን ሲመሽ ደብረ ማርቆስ ገባን፡፡

በነጋታው ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ጀምረን ፍቼ እስክንደርስ ድረስ አልተነጋገርንም፡፡ ደብረ ሊባኖስ ገዳም አካባቢ ስንቃረብ፣ ‹‹የእኔ ልጅ ይቅርታ አድርግልኝ፡፡ የያዛችሁት ጉዳይ ቀላል አይደለም፡፡ በእሳት ቀልድ የለም፡፡ በገዛ ወገኑ ላይ ጠመንጃ እየተኮሰ ‹የፍየል ወጠጤ…› የሚባልበት ዘመን ላይ ነን፡፡ ልጅ ከአባቱ፣ ወንድም ከእህቱ፣ ጓደኛ ከጓደኛው የማይተማመኑበት የአውሬ ጊዜ ውስጥ ነን፡፡ ይኼ ደግሞ የጠላት ሴራ ነው፡፡ ጠላት ደግሞ መልምሎ ውስጣችን ባስገባው ተላላኪ አማካይነት እያፋጀን ነው፡፡ መገዳደሉን አቁሙና አገሪቱን ከጥፋት ታደጓት…›› እያሉኝ አዲስ አበባ ገባን፡፡ የነገሩኝ ብዙ ቢሆንም በአጭሩ ሲጠቃለል በጠላት ሴራ አትፋጁ ነው ያሉት፡፡ ሌላው ቀርቶ በወቅቱ በሆሄያትና በቃላት ስንጠቃ የሚደረገው ትንቅንቅ በእሳቸው አገላለጽ አሳፋሪ ነበር፡፡

ከዚያማ ምን ይጠየቃል? የቀይ ሽብር ጭፍጨፋ ተካሂዶ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ወጣቶች አስከሬናቸው ሜዳ ላይ ተጥሎ፣ ብዙ ሺዎች የት እንደ ደረሱ ሳይታወቅ፣ የተቀሩት ደግሞ ከየተገኙበት ተለቅመው በየእስር ቤቱ ሲታጎሩ እኔና ጓደኛዬም ከፍተኛ 16 የሚባለው ሾላ ገበያ አካባቢ የሚገኝ እስር ቤት ገባን፡፡ ከወራት ቆይታ በኋላ ማዕከላዊ ተጓዝን፡፡ ከዚያም ከርቸሌ ተወረወርን፡፡ ማታ ማታ በርካቶች እየተወሰዱ ሲረሸኑና አገሪቱ ማቅ ስትለብስ እኛን አዛውንት አስታወስኳቸው፡፡ አሁን በሕይወት ካሉ ታዋቂ ሰዎች ጀምሮ የተገደሉ የኢሕአፓና የመኢሶን ሰዎች ከርቸሌ ታጉረንና በመከራ ውስጥ ሆነን እንገለማመጥ ነበር፡፡ እጅግ በጣም ጥቂት ከሚባሉ ሰዎች በስተቀር ሰላምታ እንኳን መለዋወጥ ተስኖን እንደ አባት ገዳይ እንተያይ ነበር፡፡ በዚህ ሁሉ መሀል ሐጂ አህመድ ትዝ ይሉኛል፡፡ ‹‹ታሪካዊ ጠላት መሀላችሁ ገብቶ እያባላችሁ ነው…›› ያሉት ግራ እየገባኝ ‹ማን ይሆን?› እላለሁ፡፡

ከአርባ ምናምን ዓመታት በኋላ ግን ሚስጥሩ ተፈታልኝ፡፡ በቀደም ዕለት አንድ የቆየ ወዳጃችን፣ ‹‹ዛሬም ድሮም መስማማት አቅቶን እንዴት እንደምንዘልቅ እንጃ? ይህች ግብፅ የምትባል አውሬ ወያኔንና ሻዕቢያን አደራጅታ፣ አስታጥቃና አሠልጥና ላያችን ላይ የለቀቀችው እኮ እርስ በርስ እየተባላን ዓባይን እንዳንጠቀምበት ነው፡፡ ያኔ ሻዕቢያና ወያኔ ደርግ፣ መኢሶንና ኢሕአፓ ውስጥ ሰርገው ገብተው አብዮቱን አስቀለበሱት፡፡ ለ27 ዓመታት የመንግሥት ሥልጣን ይዞ አገር መምራት አቅቶት ሕዝባችንን መከራ ሲያሳይ የነበረው ወያኔ፣ በሕዝባዊ እንቢተኝነት ከሥልጣኑ ከተባረረ በኋላ የሽፍትነት ተግባር ውስጥ ገብቶ አገር ለማፍረስ መነሳቱ የታሪካዊ ጠላታቶቻችን ተላላኪነቱን ማሳያ መሆኑን መዘንጋት የለብንም…›› ሲለኝ፣ የሐጂ አህመድ የዓመታት የታመቀ መልዕክት ትዝ አለኝ፡፡ አይ እኛ? አሁንስ ከታሪካዊ ስህተታችን የምንማረው መቼ ይሆን? 

(ዘለዓለም ታያቸው፣ ከጉርድ ሾላ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...