Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትበዝናብ ውስጥ ጥላን አያጥፉም! ገለባ ላይ ተኝቶ በእሳት አይጫወቱም!

በዝናብ ውስጥ ጥላን አያጥፉም! ገለባ ላይ ተኝቶ በእሳት አይጫወቱም!

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

  1. በኢትዮጵያችን ውስጥ ጥርጣሬ ሥር የሰደደ ችግር ነው፡፡ የጥርጣሬያችንን ውል መፍታትም እንደዚያው ከባድ ነው፡፡ ከውጭ የመጣ ፈረንጅን ‹‹የሚሻው ሚስጥር አለው›› ብሎ መጠርጠር እጅግ የቆየ ነው፡፡ ይህንኑ ያህል ምንም ማስረጃ (ምስክር ወረቀት) ማየት ሳያሻን በፈረንጅነቱ አዋቂ ነው ብሎ ማመንም አብሮን ከእኛ ጋር ኖሯል፡፡ በውጭ አገር ተምሮ ሐኪም ነው፣ ዶክተር ነው የተባለ ኢትዮጵያዊን ግን ልሙጥ ፈረንጅን የምናምነውን ያህል ለማመን እንቸገር ነበር፡፡ ከአየር መርዝ ጋዝ በመርጨትና ቦምብ በማዝነብ ብዙ ያጠቃን ፋሺስት ጣሊያን ተሸንፎ ከወጣ በኋላ በተጀመረ የአየር ኃይል ግንባታ ሒደት ውስጥ የፈረንጅ አውሮፕላን አብራሪዎችንና አሠልጣኞችን ያየ ዓይናችን ‹‹ኢትዮጵያውያንም እያበረሩ ነው››› ማለትን ማመን ተቸግሮ ነበር፡፡ ከዚህ ይልቅ ‹‹ውሸት ነው፣ ኢትዮጵያውያን እያበረሩ ነው የሚባለው ፈረንጆቹ እያበረሩ ነው›› የሚል ጥርጣሬና ግምት ማመን ቀሎ ነበር፡፡ ይህንን ጥርጣሬ ሰብሮ በኢትዮጵያውያን ችሎታ እምነት እንዲጣል ሲባል አፄ ኃይለ ሥላሴ ኢትዮጵያውያን በሚያበሩት አውሮፕላን ላይ መሳፈራቸው ግድ ሆኖም ነበር (ከማይጨው እስከ ኦጋዴን በተሰኘ መጽሐፍ እንደተተረከው)፡፡ ይህንን ዓይነቱን ተጠራጣሪነት ከሥልጣኔ ማነስ ጋር ልናያይዘው እንችል ይሆናል፡፡ ዛሬ ጠላቶቻችን ከፋፍለውና አባልተው አገር ሊያሳጡን ሐሰተኛ የወሬ መርዝ እየረጩብን ሳለ የመንግሥትንና የኢትዮጵያ መገናኛዎችን አንደበት ተጠራጥሮ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚበተን ተባራሪ ወሬን ማመን ግራ ያጋባል፡፡ መንግሥታዊ መረጃን መሠረት በማድረግ ‹‹ጭፍን ጥቃት የሚፈጽሙ ቡድኖችን መንግሥት እየቀጣቸው ነው›› ተብሎ ሲወራ፣ ‹‹ምን ማስረጃ አለህ? መንግሥት ስላለ ነው?›› ያለ አዕምሮ፣ ይህንኑ ጥርጣሬና ጥያቄ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሳያሳርፍ ሲቀር፣ እንዲያውም አርቲ ቡርቲያቸውን ማመን ሲጥመው ማየት ይደንቃል፡፡ ኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ ተዛማች በሽታ ተብሎ ተጠንቀቁ እየተባለና ብዙ ሰው በዓለም እያጠቃ መሆኑ እየተነገረ ‹‹ሐበሻን አይነካም›› የሚል መዳፈር፣ የጤና ሊቃውንት የለፉበትና ዓለም እየወሰደው ያለው ክትባት መጥቶ ተከተቡ ሲባል፣ ከይፋ የጤና ሙያተኞች መረጃ ይልቅ ስለክትባቶቹ የተረጩ የሹክሹክታ ወሬን አምኖ ከመከተብ ማፈግፈግ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ የአፈና ጊዜ ኑሮና የለውጥ ዕድል አያያዛችንን በተመለከተ ልምድ ውስጥም ግራ አጋቢ ልክ ማጣት አለ፡፡ በደርግ የአምባገነን ሥርዓት ውስጥ ጥፊና ቡጢ እየቀመስን፣ ቤተ እምነት ወደ መዝናኛ ቤት እየተቀየረ፣ ምዕመናንና የእምነት መሪዎች እየተሳደዱ፣ የእምነት ክብረ በዓል ይከናወንባቸው የነበሩ ሥፍራዎች ወደ አብዮት አደባባዮች እየተቀየሩ ሰጥ ለጥ ብለን የኖርንበት ጊዜ ነበር፡፡ በሕወሓት/ኢሕአዴግ ጊዜም የፀጥታ ኃይሎች የመስጊድና የቤተ ክርስቲያን ግቢ ድረስ ገብተው ሲደበድቡና ሲተኩሱ፣ በሃይማኖት መሪነት ቦታ ላይ አሻንጉሊቶች ሲጎለቱ ታይቷል፡፡ ይህም ሆኖ አንገት በመድፋት ተኑሯል፡፡ በዚህ ዓይነት የኑሮ ልምድ ውስጥ አልፈን የለውጥ/የነፃነት ጭላንጭል ብቅ ስትል ደግሞ፣ አያያዝ ባለማወቅ (ያዙኝ ልቀቁኝ በማለት፣ የዛሬን እንዴት አድሬ የሚል መሻነን ውስጥ በመግባት፣ ብልኃትና ስክነት አጥቶ በመናቆር) ጭላንጭል ማምከን ደጋግሞናል፡፡ የለውጥ ጭላንጭል ካጠፋን በኋላ፣ በእንቶኔ ጊዜ የለውጥ ዕድል ነበረን ግን አጨናገፍነው እያልን ማውራትም እናውቅበታለን፡፡ ግን በአግባቡ ጥፋታችንን መርምረንና መታረም ያለበትን ለይተን አቅምን ከፍ ማድረግ ዳገታችን ነው፡፡ ጫፍ ይዞና እንጥፍጣፊ ዕውቀት ልሶ የሚያወራና አውቃለሁ የሚል ሞልቶናል፡፡ ለመጠራጠር፣ ለማማትና ለመተቸት ፈጣን የሆንን፣ ራስን ለመተቸትና ጥፋትን ለመቀበል ግን ዳተኛ የሆንን፣ እንዲያውም እንዲህ ያለ ጥፋት ሠርቻለሁ ብሎ ራስን መውቀስና የሌላውን መልካም ሥራ ማድነቅ፣ ራስን ማሳነስ ሆኖ የሚተናነቀን ብዙዎች ነን፡፡ ዛሬ ባለን የአስተሳሰብና የፖለቲካ መስተጋብር ውስጥም የእነዚህ ችግሮች ፈለጎች ያሉ ይመስለኛል፡፡
  2. በቅድሚያ አንድ ነገር ጥርት እናድርግ፡፡ ስለውስጥ ጠላቶች ስናወራ ‹‹ጠላት›› የሚለውን ቃል የምንጠቀመው ለፖለቲካ ሙቀት አይደለም፡፡ ወይም እነዚህ ቡድኖች በትልቅ አገርነት የመቀጠል የህልውና ጉዳያችንን ስለተፃረሩ ብቻ አይደለም፡፡ እነዚህ ቡድኖች በመታወቂያነት ከለጠፏቸው ስሞቻቸው ጋር አንዳችም ግንኙነት የላቸውም፡፡ ሸኔ፣ የጉሙዝ ምንትስ፣ የጋምቤላ ምንትስ፣ የቅማንት ምንትስ የሚባሉት ቡድኖች በተቀዳሚነት ‹‹ሕወሓት›› የሚባል ቡድን ሎሌዎች ናቸው፡፡ ሎሌዎቹና ጌታቸው በአንድ ላይ መጠሪያ ካደረጓቸው ሕዝቦች ጋር የሚያገናኘቸው ብሔርተኛነት የለባቸውም፡፡ ሸኔ ለኦሮሞ የቆመ ሠራዊት አይደለም፡፡ ሕወሓት ለትግራይ ሕዝብ የቆመ አይደለም፡፡ ሁሉም ብሔርተኝነትን (ለተወሰነ ሕዝብ ‹‹መቆምን››) ቀቅለው ከበሉት ውለው አድረዋል፡፡ ለስማቸውም በየስማቸው ለሚጠቅሱት ሕዝብም ጠላት ናቸው፡፡ በደም ሥራቸው ውስጥ የሚዘዋወረው ግፍ፣ ጥላቻ፣ ጭካኔ፣ መጨፍጨፍ፣ ማጨፋጨፍና ብተና ነው፡፡ ብተናና ማጨፋጨፍ ሥልታቸውም መድረሻቸውም ሆኖ ተቀላቅሏል፡፡ በሥልታቸውም በመድረሻቸውም ውስጥ የየትኛውም ሕዝብ ደም መፍሰስና መጎሳቆል ከሒሳባቸው ውጪ ነው፡፡ መንግሥት ሆኖ ፍትሕንና መብትን የማስተዳደር ነፍስ የላቸውም፡፡ ለሰው የመራራትም ሆነ የቅንነት ምንቄያቸው ተበጥሷል፡፡ ደም እየላሱ ከመርካት በቀር፣ ከብተናና ከመጨፋጨፍ በኋላ ሰው ምን ይተርፈዋል ብሎ የሚያስብ አዕምሮ የላቸውም፡፡ ይህን ያህል ‹‹ሁለመና›› ጥፋት ሆነው መዝቀጣቸውም የኢትዮጵያውያንን መፋጀትና መበታተን ለሚሹ የውጭ ጠላቶች፣ አስተማማኝ ቅጥረኞች (ወደ ልቦናቸው የመመለስ ወሰናቸውን የተላለፉ) ያደርጋቸዋል፡፡ በሌላ አነጋገር የውጭ ጠላቶቻችን ገንዘብ ቢሰጧቸውም ባይሰጧቸውም፣ ቢያመሠግኗቸውም ምላሳቸውን ቢያወጡባቸውም የጠላት አጀንዳን የማስፈጸም አዘቅት ውስጥ ወርደዋል፡፡ ይህ የቅጥረኝነትና የደም ላሽነት ባህርይ ፈረንጅ አገር ያሉትን የጥፋት ፕሮፓጋንዳ አናፋሾችን ሁሉ የሚጨምር ነው፡፡ በቅጥረኝነቱ ሚና ውስጥም የውጭ ጠላቶቻችን አባባይ ሳይሆኑ ደጅ ተጠኚ ናቸው፡፡ ይህም የእኛን ጉዶች በበለጠ አደገኛ ያደርጋቸዋል፡፡ ለዚህም ነው በአግባቡ የፖለቲካ ሥራ ሳንሠራ ቀርተን፣ እነዚህ ቡድኖች ‹‹አድራሻችን›› በሚሉት የሕዝብ ሠፈር ውስጥ ሸሻጊ ዛሬም ያላቸው መሆኑ የሚያስገርመው፡፡
  3. የውስጥ ጠላቶቻችን የሚያካሂዱብን ጦርነት ባለሁለት ምድብ ነው፡፡ የሸኔ ዓይነቶቹ የሕወሓት ሎሌዎች የሚና ምድባቸው እዚያም እዚህም ውርውር እያሉ በመግደል፣ በመጨፍጨፍና በማወዳደም ተግባራቸው፣ አገራዊ የህልውና ርብርቡ ላይ ቀልቡን ያሳረፈው የሕዝቦች ኃይል ደኅንነት እንዳይሰማውና እንዲመረር አድርጎ ቀልቡን ማሳት፣ የስሜት ግለቱን መስለብ (ብሎም ርብርቡን መበታተን) ነው፡፡ ይህንን ዓይነቱን ሁኔታ ተጠቅሞ ዋናውን ሰይጣናዊ ሥራ የማቀናበር ምድብ የያዘው ደግሞ የአንድ ክልል ሕዝብ አግቶ አሳር እያበላ የሚገኘው ሕወሓት ነው፡፡ ይህ ቡድን በየትም በየት በትግራይ ውስጥ የውጭ ወታደራዊ ኃይል መትከል ተቀዳሚ ፍላጎቱ ነው፡፡ እዚህ ላይ ለመድረስ የሚነግድባቸው ሁለቱ መንገዶች አሁን ተዘግተውበታል፡፡ አንደኛው ማወናበጃው ‹‹የትግራይን ሕዝብ ማስራብ የጦርነት ሥልት ሆነ›› የሚል ነበር፡፡ አሁን ያለው የዕርዳታ አገባብ መልሶ ራሱን ጥያቄ ላይ የሚያስቀምጥ ሆኗል፡፡ ለሰላምና ለድርድር ‹‹የቆመ›› ማስመሰሉም ከሆነልህ ና! ለሕዝብ አሳቢ ከሆንክ መንገዱ ክፍት ነው ተብሏል፡፡ አንድ የቀረው መንገድ የለመደው የጦረኝነት መንገድ ነው፡፡ ይህንን መንገድም መጠቀም ቀላል አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከውጊያ መራቅ ፅኑ ፍላጎቱ መሆኑን በይፋ ለዓለም ማሳወቁና በተግባርም ማሳየቱ ማሳበቢያ ቀዳዳ እንዲጠበው አድርጎቷል፡፡ አንድ የቀረው ቀዳዳ ቢኖር ራሱ ውጊያ ለኩሶ ተዘመተብኝ እያለ መለፍለፍ ነው፡፡ እንዲህ ባለ ሰበብ የማይናቅ (እንዲያውም ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባ) ጥቃት እየደገሰ መሆኑን ማወቅ ይገባል፡፡ የትኛው ላይ ባተኩር ‹‹ያዋጣኛል›› ወይም የትኛውን ከየትኛው ባቀናጀው ‹‹አሸናፊ›› ያደርገኛል የሚለው ሥሌቱ አይታወቅም እንጂ፣ ፊት ይጓጓቸው የነበሩ ሦስት የጥቃት አቅጣጫዎች ላይ ማማተሩ የሚታወቅ ነው፡፡ የኤርትራ ሕዝብ ራሱን ከአምባገነን አገዛዝ ነፃ ወደ ማውጣት ተሸጋገረ በሚል ተውኔት ውስጥ ተደብቆና ይህንኑ ተውኔት ከኤርትራ ጥቃት ደረሰብኝ ከሚል ሰበብ ጋር አላልሶ፣ ኤርትራን ማመሳቀልና ኤርትራን የውጭ ጠላት ማዕከል ማድረግ አንዱ ትልሙ ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ ትልም የኤርትራ መመሳቀል የኢትዮጵያም መመሳቀል ነው፡፡ ሌላው አቅጣጫ በምዕራብ በኩል የኢትዮጵያን መከላከያ ኃይል ከሁለት በኩል በሚመጣ እሳት ውስጥ ማስገባት ነው፡፡ ይህን ለማሳካት የቋፍ ሁኔታ ውስጥ ያለውን የጎረቤት መንግሥት ወደ ጦርነት ለመሳብ የሚለፋ መሆኑም የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ የሚሳካለት መስሎትም ዱርዬው ጌታቸው ረዳ ከትግራይ ሕዝብ ደምና ሰላም ይልቅ ለሱዳን ሕዝብ መሬት አሳቢ ነኝ ባይ ሆኗል፡፡ የትግራይን ሕዝብ ታሪካዊ ዘመድ አማራን ክዶ፣ እነ ጎንደር የትግራይን ያህል ለትግራይ ሕዝብ የትውልድ ማኅበራዊ ሥፍራዎች ሆነው ሳለ፣ ለትግራይ ሕዝብ ባለውለታነት የሱዳን ሕዝብን አብልጧል፡፡ ሦስተኛው ማድቢያው፣ ብዙም አላዋጣው ያለውን ምሽግና ረድፍ የያዘ የጦርነት ግጥሚያ መጥኖ፣ አዲስ አበባ ድረስ በረዘመ የሽብር ሥልት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማሽመድመድ መሞከር ነው (ጠላት ያሰበውንም ያላሰበውንም ማተት ስለሚሆን ከዚህ ያለፈ ዝርዝር ውስጥ አልገባም)፡፡ ሰፊ ሥፍራና ጊዜ የሚሸፍን እንቅስቃሴ ያላቸውን ባለሁለት ምድብ የውስጥ ጠላቶቻችንን አንድ ላይ ለመመከት መሞከር ዘዴ የለሽ ከመሆን ቁጥር ነው፡፡ ከዘዴኛነት አኳያ እስከ ዛሬ ውርውር ባይ ቡድኖችን ለመሰባበር ከተደረገው ጥረት በላይ፣ ሕዝብ ደኅንነት በሚሰማው ደረጃ የእነ ሸኔ ዓይነቶቹን እንቅስቃሴዎችና የሥርዓት አልባነት ዝንባሌዎችን ጠራርጎ ቁጥጥር ውስጥ ለማስገባት፣ በተለይ ከግንቦት 2014 ዓ.ም. ጀምሮ እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ ከመዘግየቱ በቀር ትክክል ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ለእንደገና ግርሻ የተዘናጋ ቀዳዳ መሰጠት እንደሌለበት፣ መደበኛ የፀጥታ ኃይልን ከሕዝባዊ የሰላም ዘብነት ጋር አዋድዶና ፖለቲካዊ ግንዛቤን ታች ድረስ አዝልቆ የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት እንዲጠናከር ማድረግ መካሪ የማያሻው (አስቀድሞ ልብ የተባለ) ተግባር ነው፡፡ ይህንን የማሳካትና የማዝለቅ ትግል፣ ከጎረቤት አገሮች ጋር የድንበር ፀጥታን ከማሻሻል ሥራ ጋር መሳላት መቻሉ (ሰኔ 28 ቀን 2014 ዓ.ም. የሰማነው ዓይነት የሱዳንና የኢትዮጵያ መንግሥታት ችግሮችን በሰላም ለመፍታት መስማማት) የሕወሓት ጦረኞችን በብረት ፍርግርግ ውስጥ የተጠመዱ ተወራጮች ያደርጋቸዋል፡፡ ኢትዮጵያንም ጥንቃቄንና የተለሳለሰ የጎረቤት ግንኙነቶችን ያዛመደች ያደርጋታል፡፡ ከቤት ወጥቶ በሰላም መግባት ወደ አስተማማኝነት እያደገ መምጣት፣ አገር ይኖረኛል ወይ የሚል ሥጋትንና ሁሉን ‹‹ፖለቲከኛ›› ያደረገ ወሬ ፈትፋችነትን በእጅጉ ያቃልላል፡፡ አማራ ሕዝብ አካባቢ ጎልቶ የምናገኘው ንጭንጭና የተጠቂነት ብሶት፣ የሙጥኝ በተያዘ ስህተተኛ ግንዛቤ ተጠምዶ ዋና ተጠቂ ከመሆን ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህንን ተረድቶ፣ ጉዳትና ብሶቱን የእኔም-የሁላችንም፣ የኢትዮጵያ ብሎ በሚጋራ ልባዊ ተራክቦ (ኮምፓሽን) ማስተናገድ አዎንታዊ ውጤቱ ትልቅ ነው፡፡ ጥቃቱን የሁላችን አድርጎ መንገብገብ የብልጠት ጉዳይ አይደለም፡፡ የአማራ ጥቃት የሁላችንም መጠቃት ነው፡፡ የአማራ ዋና የጭፍጨፋና የመርዘኛ ፕሮፓጋንዳ ዒላማ መሆን ሁላችንንም ወደ የሚያወራርድ አዘቅት ለማድረስ ጥሩ አቋራጭ ተብሎ የተያዘ መንገድ ነው፡፡ የውስጥ ፀጥታና ደኅንነታችን ወደ አስተማማኝነት ማደግ፣ አማራን ህሊና አሳጥቶ በማወራጨት ዘዴ የታቀደልንን ደባ ያመክነዋል፡፡ ብዙ ንጭንጭን እያደረቀ ያራግፋል፡፡ የአማራና የኦሮሞ ሕዝብን የእርስ በርስ ግንኙነት ከጥርጣሬ ነፃ ያወጣል፡፡ በመንግሥትና በብልፅግና ፓርቲ ላይ ተፈጥሮ የቆየውን አሉባልታ መሠረት ያሳጣል፣ ሰሚ የለሽ ያደርጋል፡፡ ይህ ሆነ ማለት ‹የመጣው ይምጣ› ፖለቲካ ድጋፉ ተፈረካከሰ፣ አገራዊ ርብርቡ የመጎልበት ምቹ አየር አገኘ ማለት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የትግራይን ሕዝብ ከሕወሓት ዕገታ የሚያወጣ ትግል ለማሞቅ መቻል ደግሞ፣ የሕወሓትን ሴራና ጦርነት ደጋሽነት የማዝረክረክ ሒደት ውስጥ መግባት ነው፡፡
  4. ለነገሩ ባለድልነት ሒደቱ በፖለቲካም፣ በወታደራዊ መስክም ከተጀመረ ውሎ አድሯል፣ የማሳዳጉ ዕርምጃ በተለያዩ ምክንያቶች እየተወለካከፈ ዘገየ እንጂ:: አሁንም የሰላምና የደኅንነት ሁኔታ እያስተማመነ መሄድ ይዞት የሚመጣው ውጤት የውዥንብር ድፍርስርስ እያጠራ ብዙ አገር ወዳዶችን ወደ ቀልባቸው ከመመለስም ያልፋል፡፡ የብሔራቸው ሕዝብ የተሻለ ዘመን ውስጥ እንዲገባ የሚያስቡና ይህም የሚሳካው በኢትዮጵያ እንደ አገር መቀጠል ውስጥ መሆኑን ያስተዋሉ ብሔርተኞች፣ በአገራዊ ርብርብ ውስጥ ያላቸው ክምችት ከበፊቱ ጨመረም አልጨመረም ሠልፋቸው ከድንግዝግዝ ይጠራል፡፡ ፅንፈኛ ብሔርተኞች የፅንፈኛ ዓላማቸውን ፋይዳ ሕዝቤ ከሚሉት ማኅበረሰብ ጥቅም አኳያ መመዘን ተስኗቸው (የጭካኔና የጥላቻ ሲሳይ ሆነው) ‹‹ማኅበረሰቤ›› ከሚሉት ሕዝብ ጋር መሰነባበታቸው በራሱ ለአገራዊው ርብርብ የፖለቲካ ድል ነው፡፡ ‹‹የአምባገነንነት መጠቀሚያ አንሆንም›› በሚል ዘይቤ ራሳቸውን እያታለሉ ከአገራዊ ርብርብ ዳር ቆመው የጭፍጨፋና የብተና ኃይሎችን ወላፈን የሚሞቁ ብሔርተኞችም ወይ ወደ ጭፍጨፋ/ብተና ሠፈር፣ አለዚያም አገር ወደ ማዳኑ ሠፈር የሚዘረዘሩበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ለዚያ እንዲያግዛቸው እግረ መንገዳችንን አንድ እውነት እናጋራቸው፡፡ ‹‹አምባገነንና ዋና ጥፋተኛ›› የሚሉት መንግሥት እንደሚሉት ሆነም አልሆነ፣ ከዳር ቆሞ የብተናና የጭፍጨፋ ኃይሎችን ከመቀላወጥ ይልቅ ከአምባገነን ጋር አገር ማዳን ውጤቱ የተሻለ ነው፡፡ ብሔርተኛ ትግል ከርክሶ ሕዝቤ ከሚለው ብሔር ሊፋታና የውጭ ጠላት ዓላማ መሣሪያ ሊሆን እንደሚችል ሁሉ፣ ለኢትዮጵያ ቆሜያለሁ የሚል ቡድንም መንግሥትን በመበቀል ታውሮም ሆነ በገንዘብ ተገዝቶ የኢትዮጵያ ቀበኛ ሊሆን መቻሉም ድፍርስርስ ሲጠራ ቁልጭ ብሎ ይታያል፡፡ ኢትዮጵያዬ እያሉ የአሜሪካ ምክር ቤቶች በኢትዮጵያ ላይ ያዘጋጁትን የማዕቀብ ማነቆ እንዲያፀድቁብን ከመለማመንና የእነ ሕወሓትን አጀንዳ ከመሻረክ ጋር የሚቆዩት ቡድኖች የዚህ ዓይነቱ የጠራ ክህደት ማሳያዎች ናቸው፡፡ የንጭንጭ ‹‹ፖለቲካ›› ጠወላልጎ ሠልፉ እንዲህ ኩልል ብሎ እየጠራ ሲኮሰምን፣ የአገራዊ ህልውና ርብርቡ ሠፈር ደግሞ ይደረጃል፣ ይጎለምሳል፡፡ ጉልምስናውም ድንበር የሚሻገር መልካም ጠረን ይረጫል፡፡ በኢትዮጵያ ድክመት እጠቀማለሁ ከማለት ይልቅ ከኢትዮጵያ ጋር መተጋገዝ ይበልጥ ይበጃል የሚል ጠረን፡፡
  5. አሁን ያለው የኑሮ ውድነትና የዋጋዎች አተኳኮስ አስደንጋጭ ነው፡፡ እንደዚህም ሆኖ በእኛ አገር አስተያየት አሰጣጥ ውስጥ አመሥጋኝነት ውድ ነገር ሆኖ እንጂ፣ በዚህ የጦርነት ሁኔታ ውስጥ ያለውን የኑሮ ውድነት በተለያየ መልክ ለመደጎም እየተካሄደ ያለው ጥረትና በዘላቂ ልማት ላይና የምግብ ዋስትናን የቅርብ ጊዜ እውነታ በማድረግ ላይ የሚታየው መፍጨርጨር እስካሁን በእኔ ዕድሜ ያየኋቸው ቀዳሚ መንግሥታት በመደበኛ ጊዜ ካደረጉት ጥረት የላቀ ነው፡፡ ከሌሎች የእኛ ቢጤ አገሮች ጋር ሲተያይም ‹‹ጎሽ ተስፋ አለን!›› የሚያሰኝ እንጂ የሚሽሟጠጥ አይደለም፡፡ አምስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ይቅርና በተትረፈረፈ የሥልጣን ዘመኑ ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ዋና መጣጭ የሆኑ ገቢ ሸቀጦች የትኞቹ እንደሆኑ ለይቶ፣ በአገር ውስጥ ሊተኩ የሚችሉትን ያህል ለመተካት ቆርጦ ሲሠራ የትኛው የኢትዮጵያ መንግሥት ታየ? በጦርነት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የቱሪዝም ገቢ የሚያሳድጉ ልማቶችን የሠራ፣ በግብርና ልማታችን ላይ እመርታዊ ለውጥ የሚያመጣ፣ የበጋ ስንዴ ልማትን ወደ መሬት ያወረደና ማዛመት የተያያዘ፣ ጥላ የማይሻና ገና በአጭር ቁመት ፍሬ ለጉድ የሚይዝ ቡና በአማራ ክልል ሊለማ እንደሚችል ያሳየ፣ ከመሬት ብቅ ሳይሉ በፍሬ የሚጨናነቁ የአቮካዶና የፓፓዬ ተክሎችን ያለማ የትኛው መንግሥት ነው? ምሥራቃዊ ደቡብና ደቡብ ኢትዮጵያ የድርቅ ጥቃት ይወደዋል፡፡ የአሁኑ ደግሞ እንደተነገረን የከፋ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ድርቅ ሲደርስ የውጭ ዕርዳታ ላይ በመመርኮዝና በማንጋጠጥ ሳይወሰን ከአካባቢ አካባቢ ያሉ የውስጥ አቅሞችን በማስተጋገዝ የተቻለውን ያህል እንስሳትን ለማትረፍ፣ ያ ቢጓደል እንኳ ሰዎችን ለማትረፍ የተሟሟተ መንግሥት የትኛው ነው? ‹‹ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ የአፈርን ለምነት በሒደት ውስጥ ይመርዛል፣ ያራቁታል…፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ግን በጊዜያት ውስጥ ለምነቱ ያለቀ መሬትን ያድሳል፣ ያበለፅጋል›› የሚል ምርምራዊ ግንዛቤ ከተፈጠረ ብዙ ጊዜው ነው፡፡ በተፈጥሮ ማዳበሪያ የተመረተ ሰብል፣ ፍራፍሬና አትክልት የጌታ አገሮች ሀብታሞች በውድ የሚገዙት ነገር መሆኑ የቆየ ጉዳይ ነው፡፡ ከጦርነት ወጪና ከማዕቀብ ጋር ተያይዞ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የሩሲያ-ዩክሬይን ጦርነት አመጣሽ የሆነ የማዳበሪያ ዋጋ ንረት በገጠመን ጊዜ፣ በተሻሻለና በፈጠነ የአዘገጃጀት ጥበብ የተፈጥሮ ማዳበሪያን ሰንቆ በማሳ ደረጃ ሰው ሠራሽ ማዳበሪያን በከፊል የማጣጣትና ሙሉ ለሙሉ የመተካት ቁርጠኝነት በየትኛው የእኛ መንግሥት፣ በየትኛው ሌላ አገርስ ዓይተናል? ይህ ጥበብ ወደፊት እየተባ ሲሄድ የኬሚካል ማዳበሪያን ከሥራ ውጪ አያደርግስ ይሆን? ‹‹እናያለን ገና!›› የሚል ዘፈን ከተዘፈነ ውሎ አድሯል፡፡ በኢትዮጵያ ሕይወትን የሚለወጥ ለውጥ እየመጣ መሆኑን በማመልከት ረገድ ግን ዘፈኑ ትርጉም መስጠት የቻለው ዛሬ ነው፡፡

በሌላ በኩል የተወሰኑ ለብዙኃን ፍጆታ እጅግ አስፈላጊ ምርቶች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ማድረግ፣ ከዚህም አልፎ ወደ ውጭ ከሚሾልክ ኮንትሮባንድ ጋር ፍቅር ያለውን የ‹ፍራንኮ ቫሉታ› ንግድን ፈቅዶ ከኮንትሮባንድ፣ ከአሻጥር ንግድና ከውጭ ምንዛሪን ከማሸሽ ጋር መተናነቅ፣ የሸቀጥ እጥረትንና የዋጋ ግሽበትን የመታገል ገጾች ናቸው፡፡ የሽፋን ስፋቱ ከአዲስ አበባ ውጪ ምን ያህል እንደሆነ አላቅም እንጂ፣ በዓመት የተወሰነ ገንዘብ በመክፈል ብዙዎች ተጠቃሚ የሆኑበት የጤና ማኅበራዊ ዋስትና፣ ለመንግሥት ተማሪዎች በዓመት የሚሰጠው የደንብ ልብስና የደብተር ድጎማ፣ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚሰጥ ምገባ፣ የሸገር ዳቦ ቅናሽ ዋጋ፣ ዓውደ ዓመቶችን እያስተካከ/ከጊዜ ጊዜ የሚመጣ ማዕድ ማጋራት፣ ደጅ ከማደር የማይሻሉ የደሃ ደሃ ቤቶችን ክረምት ከመግባቱ በፊት ሕይወት የመስጠት መርሐ ግብር ሁሉ የኑሮ ውድነትን (የኑሮ ወጪ ጫናዎችን) የመጋራት ልዩ ልዩ መልኮች ናቸው፡፡ በዚህ ላይ በሸማቾችና በእሑድ ገበያዎች በኩል ሻል ባሉ ዋጋዎች ሸቀጣ ሸቀጦችን የማቅረብ ጥረትም የዕገዛ ፈርጅ ነው፡፡ ሥራ አጥ ወጣቶችን እያደራጁ ሥራ ፈጠራ ውስጥ እንዲገቡ ፈርጀ ብዙ ዕገዛ ከመስጠት ባሻገር፣ ድሆች ኑሯቸውን በሚደጉም ልዩ ልዩ ሥራ ውስጥ እንዲሰማሩ የሚደረገው ጥረትም ይስፋ የሚያሰኝ ነው፡፡ በመሥሪያ ቤቶችና በየቤቱ (አቅምና ግቢ ባላቸው ሰዎች ዘንድ) የከተማ ግብርና በተለይ የአትክልት ልማት ሥራዬ ተብሎ ቢያዝና መሥሪያ ቤቶች የሠራተኞቻቸውን ባለግቢዎችም የቤተሰቦቻቸውን ፍላጎት ቢሸፍን እንኳ፣ በገበያው ውስጥ ያለውን እጥረት/ሽሚያ በመቀነስ ዋጋን በተወሰነ ደረጃ የማቅለል ሚና መጫወት ይችላሉ፡፡ ወጣም ወረደ የከተማ ግብርና እንዲስፋፋ እንኳን ተወተወተ፡፡ ለወደፊትም የከተማ የግብርና ልማቱ፣ ያለ ሥራ የተቀመጡ መሬቶችን በማልማትና በምድር ቤቶች ግድም ሳይወሰን ፎቅ ቤቶች ድረስ እንዲወጣና ቀጣይነት እንዲያገኝ በሚያስችል መልክ ዘዴዎችንና የሥራ ክፍፍሎችን እያቀናበረ፣ የመጨረሻው ሰው ከአቅራቢያዎች የሚፈልገውን ግብዓትና ዕውቀት ሳይንከወከው (አታካች ልፋት ውስጥ ሳይገባ) የሚያገኝበት ደረጃ ላይ እንደሚደርስ ተስፋ አለኝ፡፡ የዚህ ዓይነቱ ግብርና መስፋፋት ከቻለ፣ በግንባታ ምክንያት ተምሶ የሚወጣ የላይ አፈርን ወደ ወንዝ የመድፋት አባካኝነት ቀርቶ አፈር የሚሳሰሉት ውድ ሀብት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በነገራችን ላይ የኑሮ ክብደትን በማቅለል ልዩ ልዩ መርሐ ግብር ውስጥ ከመንግሥትና ከበጎ አድራጊ ድርጅቶች ጋር ባለሀብቶች የሚያደርጉት አብሪ አስተዋጽኦ ‹‹ተመሥገን! ይበል! ይበል!›› የሚያሰኝ ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ለኅብረተሰባቸው ደኅንነት ደንታ አጥተውና በፈጣን ትርፍ ታውረው የተኩስ መሣሪያና ጥይት ሕገወጥ ንግድ ውስጥ የሚሳተፉ፣ በሸቀጥ ድብቃና ወደ ውጭ በማሻገር የአገር ውስጥ ገበያን እያራቆቱ የገዛ ወገናቸውን የሚቀጡ፣ ከሁሉም ከሁሉም ደግሞ ብዙ ወገኖቻችን ለነፍስ አድን ዕርዳታ በተጋለጡበት በአሁኑ ሰዓት ለዕርዳታ የሚውል ሀብት የሚበዘብዙ ጨቡዴዎችን ታሪካችን በነውረኛነት ይጽፋቸዋል፡፡ በሥራና በተገልጋይ ላይ የሚደርስ በደልንም ሆነ ሥውር የዝርፊያ መረቦችን በጥልቅ ዓይን መከታተል የጀመረውም እንቅስቃሴ ብዙ ጉድ እንደሚጠርግ ተስፋ አለን፡፡ በሌላ ጎን የኑሮ ውድነቱና በአስተማማኝ አልደፈን ያለ የፀጥታ ነገር እያነጫነጨ አስተያየትን ሊያዛባ ቢችልም፣ ተራው ሰው ‹‹ሰላም ሰላም! ሰላም ከሌለ ሠርቶ መብላትም አይቻልም›› ሲል ሰላም እስኪገኝ ሠርቼ ለመብላት አልጥርም ማለቱ አይደለም፡፡ ተማርኩ ባሉ ሰዎች ደረጃ፣ ሌላ ሌላውን ሥራ አላስፈላጊ (የከንቱ ውዳሴ ዓይነት) አስመስለው እየሸረደዱ፣ ‹‹መንግሥት ሌላ ሌላውን ትቶ በፀጥታ ማስከበር ላይ ያተኩር…፣ ፕሮጀክቱ፣ የበጋ ስንዴ ምናምኑ ሁሉ ትርጉም የሚኖረው ሰው ሲኖር ነው›› ብሎ መተቸት ግን የጤና ሳይሆን፣ የገዛ ህሊናን ከአሉታዊነት ጋር የሚያቆራኝ ነው፡፡ እንዲያም ሲል ሚዛናዊ ሆኖ ማሰብን ከማኩረፍ የራቀ አይደለም፡፡ መንግሥት ፀጥታና ደኅንነትን ለማስከበር ወገቡን ታጥቆ መሥራት ቁልፍ ሥራው መሆኑ አንድና ሁለት የለውም፡፡ ‹‹ሌላ ሌላውን ትቶ›› ብሎ ነገር ግን ምን ማለት ነው? ሌሎች ባለልዩ ልዩ ዘርፍ የሥራ አውታሮች ተጠቃለው ወደ ፀጥታ ማስከበር ይዙሩ ወይም ፀጥታ እስኪከበር ሥራ ይፍቱ መባሉ ይሆን? ብለን አንል ነገር፣ እንዲያ ተብሎ ይታሰባል ብሎ ማመን ያስቸግራል፡፡ ፀጥታና ሰላምን የማረጋገጥ ነገር ሸኔን ማሳደድ ብቻ አይደለም፡፡ የትኛውንም ዓይነት የውስጥና የውጭ ጥቃት ነቅቶ መከታተልን፣ ወታደራዊ በሆነና ባልሆነ ትጥቅና ስንቅ ሁሉ ሁሌ ዝግጁ መሆንን ይሻል፡፡ ይህ ሁሉ ዝግጅትና እንቅስቃሴ ከጉርስ ጀምሮ የሚጠይቀው አያሌ ወጪ የሚገኘው ደግሞ ከኢኮኖሚ-ገብ ሥራዎች ነው፡፡ ፀጥታና ሰላም ከማስከበር ቀጥተኛ ተግባር ውጪ ያሉ የሲቪል ዜጎች በልቶ ማደሪያ ሥራዎች መስፋፋትና መቀጨጭም ሰላምን ከማረጋገጥ ጋር ግንኙነት አላቸው፡፡ በሌላ አነጋገር የፀጥታ ጉዳይ (የሰዎችና የሥራዎች ደኅንነት) ኢኮኖሚና ጉርስ ላይ ተፅዕኖ እንዳለው ሁሉ፣ በኢኮኖሚ ነክ የሥራ መስኮች ዘንድ የሚመጣ ስኬታማነትና ውድቀት በፀጥታና በሰዎች ህልውና ላይ ተፅዕኖ አለው፡፡ ምናልባት ወንጪ፣ ኮይሻ፣ ጎርጎራ የሚባሉ መዝናኛ ነክ ፕሮጀክቶችንና ዛፍ ግጥገጣን በአግቦ ጎነጥ ለማድረግ ተፈልጎ ይሆን? እንደዚያ ታስቦ ከሆነም ይቁረጥላችሁ፣ መዝናኛ/መናፈሻም ሆነ ዛፍ፣ ቅርጥፍ ተደርጎ ይበላል፣ ሥራና ዳቦ ይሆናል፡፡ ብርና የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል፡፡ በነቃ የሕዝብ ተሳትፎ በየዓመቱ በቢሊዮኖች የሚተከሉት (ከዚህ በፊት በየትኛውም መንግሥት በዚህ ስፋት ያልተከናወኑት) ዛፎች በስንት ዓይነት መልክ ወደ ምግብነት እንደሚቀየሩ ስንቱ ይወራል? ፍራፍሬ ከሚሰጡት ሌላ ለማገዶና ለጣውላ ኢንዱስትሪ የሚውሉት ሁሉ ይበላሉ፡፡ ከደን ልማት የሚገኘው ፈርጀ ብዙ የአካባቢ እንክብካቤ በውኃ ሀብት፣ በአፈር ሀብት፣ በአየር ንብረት መሻሻል፣ በግድቦች እንክብካቤ፣ ወዘተ ሁሉ በደፈናው ኑሮን የሚያነሳ (የሚበላ) ነው፡፡ እንኳን በደን የሚመጣ ለውጥ ትምህርት ላይ፣ የቢሮክራሲ እንግልትና ሙስና ላይ የሚመጣ አዎንታዊ ለውጥ ሁሉ መብል ይሆናል፡፡ ይህ ሁሉ ተጠቃሎ፣ የፀጥታ ማስከበሪያ/አገር የማስቀጠያ ቴክኖሎጂና ክህሎት ማሳደጊያ ስንቅና ትጥቅ ማደራጃም ይሆናል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ በሁሉም ዘርፍ ለውጥ ለማምጣት ከምሁራንና ከባለሙያዎች ጋር እየተፍጨረጨረ ያለው መንግሥት ምሥጋና ይድረሰው (መንግሥትን ሳመሠግን ከብልፅግና ሰዎች ጋር ‹ለአገሬ ለውጥ ይትረፋት› ብለው የሚተጉትን ከሌሎች ፓርቲ የመጡና ከፓርቲዎች ውጪ የሆኑ ሰዎችን ጨምሬ ነው)፡፡ ዛሬ ሰውየው ለምሥጋና ነው ቆርጦ የተነሳው የሚለኝ ይኖራል፡፡ አዎ ነው፡፡ ግን የእኔ ምሥጋና ዋና ፍሬ ጉዳይ ለማመሥገን ብሎ ማመሥገን አይደለም፡፡ በጎ ሥራዎችን ጎሽ አለማለት አገራዊ ርብርባችን ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ፣ ከጎሽታም በላይ የሆኑ ሥራዎችን ማስተዋልና ማመሥገንም አገራዊ ርብርባችንን እንደሚያጠነክር ማስገንዘብ ነው፡፡

  1. ምንነታችንንና ልካችንን በቅጡ ማወቅ አለማወቃችንም ሚናችንን በትክክል ለይቶ የመወጣት ብቃታችንን ይወስናል፡፡ በአሁኑ ደረጃ በቀላል አገላለጽ ‹‹በቡሃ ላይ ቆረቆር›› ሊባል በሚችል እውነታ ውስጥ ነን፡፡ በተቀዳሚ ከቅድመ ዴሞክራሲ (ከሰው ገዥነት ሥርዓት) ሕግ ገዥ ‹‹ወደ ሆነበት›› ሥርዓት ለመግባት ወግ ወጉን የጀመርን ነን፡፡ ‹‹ወደ ሆነበት›› የሚለውን ቃል በጥቅስ ምልክት ውስጥ ያስገባሁት ሁለት መቶና መቶ ዓመታት ሞላን/አለፈን በሚሉት አገሮች አካባቢ እንኳ የሕግ ገዥነት ከሰው ገዥነት ጋር ትግያ ዛሬም ያለበት ስለሆነ ነው፡፡ በአሜሪካ በትራምፕ የሥልጣን ጊዜ በጠቅላይ (ሱፕሪም) ፍርድ ቤት ውስጥ የነበረውን የአንድ ዳኛ መጉደል በመሙላት ረገድ፣ የወግ አጥባቂ ወግ አጥባቂ [መደገሙ ስህተት አይደለም!] በሆኑትና ከዚያ መለስ ባሉት መሀል ምን ያህል መጓተትና አስሊነት እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ዛሬ በአሜሪካም ውስጥ በዓለምም ውስጥ እየሆነ የምናየው ሁለቱም ፓርቲዎች ወግ አጥባቂነት ሠፈር ውስጥ መሆናቸውን የሚናገር ነው፡፡ ‹‹ግራ›› ተደርጎ ዛሬ ዛሬ የሚቆጠረውም ነገር ይበልጡን ከልሽቀት (ዲካደንስ) ጋር የተያያዘ አዝማሚያ ነው፡፡ የሰብዕናና የባህል ልሽቀት ሰብዓዊ መብት በሆነበትና እየሆነ ባለበት የዛሬ ዓለማችን ጊዜ፣ የሴቶች የህልውና ጉዳይ የሆነው ፅንስ የማስወረድ መብት አሜሪካ ውስጥ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውስጥ በመጣ የአክራሪ ወግ አጥባቂነት የቁጥር ብልጫ ሲሸመቀቅ ለማየት በቃን፡፡ በአሜሪካ ውስጥ የጤና ማኅበራዊ ዋስትና ሁሉን አቀፍ እንዳይሆን አንቆ የያዘው፣ ጦር መሣሪያ የመያዝ መብትንም በጠንካራ ሕግ እንዳይገደብ ያወከው ከበስተጀርባ ያለው የዲታዎች የገቢ ጥቅም መሆኑን አንዘንጋ፡፡ ዓለምን ጠቅላላ ያንገላታው የሩሲያ-ዩክሬይን ጦርነትም የዓለምን ለሰው ልጅ መብትና ደኅንነት የመራራት ልክን አጋልጦ መሳቂያ ያደረገ ልምድ ነው፡፡ ለጦርነቱ መዘዝ የሆነው ዩክሬይንን የኔቶ አባል የማድረግ ተንኳሽ ፍላጎት መሆኑ ዕውቅ ነው፡፡ ጦርነቱ ከተጀመረም በኋላ፣ ጦርነቱ በሰው ልጆች ደኅንነት ላይ የሚያስከትለውን ግዙፍ ጉዳት (በዕልቂት፣ በስደትና በውድመት) ከአያያዙ ገምግሞ የዩክሬናውያንን የኔቶ አባል የመሆን ‹‹መብት›› በማገድ ጦርነቱን ማስቆም ይቻል ነበር፡፡ የዩክሬይን የኔቶ አባል የመሆን ‹‹መብት›› ከዩክሬናውያን በሺዎች መሞትና መቁስል፣ በሚሊዮኖች ከመፈናቀልና ከመሰደድ፣ ከዩክሬይን ከተሞችና መሠረተ ልማቶች ዶግ አመድ መሆን ‹‹የሚበልጥ›› ሆነና፣ የምዕራብ ኃያላን አገሮች ሁሉ የጦርነት አጃቢና ማገዶ መጋቢ ሆኑ፡፡ ይህንን ወፈፌ ውሳኔ በተግባር አፅድቆ የሰው ልጅ ጉስቁልናን የሚያመርተው፣ ዓለም አቀፍ የሰው ልጆች መብትና ደኅንነት ሕግ ሳይሆን፣ የኃያላን የመጣጣል (የበላይነት) ግብግብ ነው፡፡ ይህ ልምድ በዓለም ውስጥ የዴሞክራሲ ተግባራዊነትን እንመራለን በሚለው የምዕራብ ዴሞክራሲ ውስጥ ሰብዓዊ መብትና የሕግ ገዥነት ከሰው ገዥነት ጋር ያለውን ርቀት ለመፍረድ አያንስም፡፡ ስፖርትንና ተመድን ጭምር በአዙሪቱ የጠለፈው ይህ የቅሌት ልምድ፣ የእኛ የሕግ የበላይነትና የዴሞክራሲ ወሬ፣ ልኩ ምን ያህል ግርጌ ላይ እንዳለ ለመረዳት የሚያግዝ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አገራችን ዛሬ ያለችበት ሁኔታ እንዳሻ የሚቀባዠርበት አይደለም፡፡ ያለንበትን እውነታ ጥርት አድርገን አውቀን በብልኃትና በአርቆ አስተዋይነት መንቀሳቀስን የሚጠይቅ ነው፣ እየጠየቀንም ነው፡፡ ያለንበት እውነታ በአንድ ጊዜ አገራዊ ህልውናችንን ከአደጋ የመጠበቅና ከቅድመ ዴሞክራሲ ወደ ዴሞክራሲ የመሸጋገር አደራዎች አንድ ላይ ተቆራኝተው ትከሻችንን ያጎበጡበት ነው፡፡ እውነቱን ፍርጥ እናድርገው፡፡ የዴሞክራሲ ሕይወት ውስጥ አይደለንም፡፡ ዴሞክራሲያዊ የምርጫና የውድድር ቅርስ ገና አላበጀንም፡፡ የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ ዘርፍ፣ ፓርላማችን፣ ፓርቲዎች ራሳቸው፣ ጋዜጠኝነትና ሚዲያዎች፣ እንዲሁም የመንግሥት አውታራት ሁሉ የዴሞክራሲ ሕይወት አላቸው የሚባሉ አይደሉም፡፡ ዴሞክራሲ በራፍ ላይ ሆነን ወግ ወጉን ጀማምረናል፡፡ ሊገልጸን የሚችለው አባባል ይህ ነው፡፡ በመንግሥት ሥራ አስፈጻሚና በፓርላማ ደረጃ የፓርቲ ይዘቶችና መሪነት ከመንግሥት መሪነትና ይዘቶች ጋር ዛሬም እየተሳከሩ ነው፡፡ በሙያ አውታራት አመራርና የተግባር አፈጻጸም ውስጥም ዛሬ ድረስ ፖለቲካና ሙያተኝነት እየተደበላለቁ ነው፡፡ አገር የማዳን ፈተናችን ወደ ሥርዓተ አልበኛነት ሊያንከባልሉ ከሚችሉ ከፀጥታ ችግሮች፣ ከጭፍጨፋና ከማፈናቀል ጥቃቶች ጋር ትንቅንቅ የገጠመ ሆኖ ሳለ፣ ከዚሁ ተግባር ጋር በተቆራኘው ወደ ዴሞክራሲ የመግባት ጅምራችን (የንግግር ነፃነት ፍንጣቂ) ውስጥ፣ ብሔርና ሃይማኖት ነክ ሰላማችንንና የፖለቲካ ሰላማችንን ረብሸው፣ እንቢኝ ወዳልነው የመባላትና የመበታተን አዙሪት ውስጥ ለከቱን የሚችሉ የነገር እሳቶች ይወረወራሉ፡፡ በየወረዳውና በየመሥሪያ ቤት አካባቢ ያለው የስብሰባና የማኅበራዊ ተግባር ጥሪ ውስጥ ‹‹እንዳትቀሩ! ከአስተዳደር/ከፖሊስ የሚመጡ ሰዎች አሉ… የቀረን ሰው ስም እናስተላልፋለን! በኋላ ለሚደርሰው ነገር ተጠያቂ አይደለንም››፣ ወዘተ የሚል በፍራትና በማስፈራራት የሚሠራ ሥልት ዛሬም አለ፡፡ ዛሬም አለ ስንል በሌላ አነጋገር የደርግንና የኢሕአዴግን ዘመን ሥልት ገና አልገፋነውም ማለታችን ነው፡፡ የዴሞክራሲ በራፍ ላይ ሆነን ‹‹የንግግር ነፃነታችን ተነካ! የሠልፍ መብት ተደፈረ! የሕግ የበላይነት ተጣሰ! ጥፋተኝነት ሳይጣራ ለምን ሰው ይያዛል?! አስሮ መረጃ መሰብሰብ ዛሬም አልቀረ! ዴሞክራሲ አለ ለማለት የሚያስደፍረን ዋናው ሒደቱ ነው! በአውሮፓ ዴሞክራሲ ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ፍርድ ቤት አቁሞ እስከ መጠየቅ በተቻለ ነበር! ወደ አምባገነንነት እየሄድን ነው…›› እያሉ ማለት ያለንበትን እውነታ ዘንግቶ ከመዘላበድ የተለየ አይደለም፡፡ ስለአስተሳሰባችን ዴሞክራሲዊነትና ለዴሞክራሲ ስላለን ተብከንካኝነት ከማውራታችን በፊት፣ ምን ያህል ራሳችንን መፈተሽ እንዳለብን ለማስገንዘብ አንድ ምሳሌ ላክል፡፡ በ1960ዎች ‹‹የተራማጅ›› ፖለቲካ ውስጥ የነበርን ሰዎች በጊዜው ያገኘነው ልምድ መራርነቱ ከማንም በላይ ራስን ወደ መውቀስና የሰላማዊ ትግል ፅኑ ተከራካሪ ወደ መሆን የሚገፋ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ ጥብሳታም ልምድ ሰዎችን ሁሉ እኩል ይገራቸዋል ተብሎ ግን አይጠበቅም፡፡ የሕወሓት ሙጣጮች ዕብደት የከፋው የገንታራነት ገጽታ ነው፡፡ በቅርቡ በባላገሩ ቴሌቪዥን በተከታታይ ባየነው ቃለ መጠይቅ ላይ ‹‹ያ ትውልድ››ን የጻፈው ክፍሉ ታደሰ፣ ኢሕአፓ የግድያ የከተማ ትግል የጀመረው አዋጅ ታውጆ ጥቃት ስለተከፈተበት ነው በሚል መከራከሪያ የቅንደባ ሥልትን ተገቢ ነበር ለማለት የለፋው ልፋት ሌላው ገጽ ነበር፡፡ እንደ ልምዱ መራርነት መሆን የነበረበትና ለዛሬው የቡድኑ ፖለቲካ ሥርየት ይጠቅመው የነበረው፣ ያ የትግል ሥልት ፈፅሞ መጀመርም መቀጠልም ያልነበረበት የተሳሳተ—ታጋይ አስጨራሽ—ሥልት ነበር የሚል ንስሃን እንደ ችቦ ማንሳት ነበር፡፡

ወደ ዛሬ የአገራችን እውነታ እንመለስ፡፡

- Advertisement -

የውስጥና የውጭ ሰበዞች ያሉት የህልውና ፈተናችን ተያያዥ ተግባራትን ለማቃናት፣ የውስጥ ፀጥታና ሰላምን በአግባቡ (ቢያንስ ጨፍጫፊዎችን በየትም መፈናፈኛ በማሳጣት ደረጃ) መቆጣጠር ግድ ይለዋል፡፡ የትኛውንም ውጤት የሚያመጣ መንገድ ሁሉ ተጠቅሞ ሰላምና ፀጥታን የማስተማመን ነገር በዛሬ የኢትዮጵያውያን አበሰኛ ሕይወት ረገድ፣ መጀመርያ መቀመጫዬን የሚባልለት ተግባር ነው፡፡ ሌሎች ተያያዥ መብቶች [የሥራ ልማቶችና የመልሶ ግንባታዎች አላልኩም!] በሰላም ገብቶ የመውጣት ተከታዮች ናቸው፡፡ በዚህ አተያይ ተሬው ሕዝባችን አንድም ‹‹የሒደቱ ሕጋዊነት… የንግግር ነፃነት/የሠልፍ ምንትስ›› የሚል መቀዣበር እንደሌለው ዓይኔን ጨፍኜ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡ እየተለፋበት ያለው አውታራትን በሙያ የማላቅ ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በተለያየ ጥበብ ግልጽና ሥውር አውታራት ከቅድመ ወንጀልና ከእስራት በፊት ማስረጃ የማሰባሰብ አቅማቸው አገሪቱ ከገጠማት ፈተና ጋር ምን ያህል ይቻቻላል? አስሮ መረጃን ለመፈልፈልስ ቢሆን ምን ያህል ፈጣንና የተጠርጣሪዎችን የመደፋፈን ጮካነት አልፎ የሚሄድ ብቃት አለ? ከደኅንነትና መረጃ አውታር አንስቶ ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግና ፍርድ ቤት ድረስ ምን ያህል የሚያስተማምን ለሙያ የመገዛት፣ የልምድ ትባት፣ የቴክኒክና የጥበብ አቅም አለ? የሚሉ ጥያቄዎች ሁሉ ማንሳት ይቻላል፡፡ በዚህ ሁሉ ፈርጅ ውስጥ ያለ ወጣ ገባነት ወደኋላና ወደፊት ሊያወዛውዘን የሚችል ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ መንግሥታዊ ሕገወጥነትን/የሕግ ጥሰትን ሰበቤ በሚል እንዳሻ እንዳንሆንበት አገራዊ ህልውናችንን የማትረፍና የማስቀጠል ነገር፣ ከዴሞክራሲ ግንባታ ጋር የተቆራኘ መሆኑ ‹‹ዋ!›› እያለ ያስጠነቅቀናል፡፡ ይህንን ውስብስብና ከከባድም ከባድ የሆነ ድርብ ተግባር ለመወጣት እንድንችል ግን አገራዊ ርብርብ ራሱ ወርቃማ ገጸ በረከት ሰጥቶናል፡፡ ገጸ በረከቱ ለመንግሥትም፣ ለገዥው ፓርቲም፣ ለየትኞቹም አገሬንና ዴሞክራሲን እሻለሁ ለሚሉ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማኅበራት፣ ምሁራንና ዜጎች ሁሉ የቀረበ፣ ድርቡን ተግባር በትግዝግዝ እንዲያሳኩ የተሰጠ ክፍት ዕድል ነው፡፡ ይህ ዕድል ክፍት የሆነውም የእስከ ዛሬውን ልምድ ተመርኩዞ ጣት ጥቆማን፣ መወነጃጀልን፣ የዳር ተመልካችነትን ሁሉ የእንጭጭ/የጅልና የሰነፍ መላ ያደረገ በመሆኑ (ቢከሽፍ ከተጠያቂነት ንፁህ ነኝ የሚል ባለመኖሩ) ነው፡፡ 2013 ሰኔና 2014 የተካሄደው ምርጫ ከእነ እንከኖቹ ከቀዳሚዎቹ ምርጫዎች ይበልጥ የተሻለና የሕዝቦችን የለውጥ ተስፋ አዝሎ የዴሞክራሲ ቤት ደጃፍ ላይ አድርሶናል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ በመከላከያ፣ በደኅንትና በፌዴራል ፖሊስ ውስጥ ከለውጡ ወደዚህ የተካሄደው እየተካሄደም ያለው በብሔር፣ በሃይማኖትም ሆነ በቡድን ፖለቲካ ለመቃኘት ያልተመቸ (ኢትዮጵያን በመሰለ ጥንቅር አገራዊና ሙያዊ ተልዕኮን የመሠረት ድንጋዩ ያደረገ) ግንባታ ድርብ ተልዕኳችንን ለማሳካት ወሳኝ አቅም ነው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? እኛ ተግባራችንን አውቀን ብልህና ንቁ ሚናችንን ለመጫወት እስከቻልን ድረስ፣ የፈለገ ፀረ አንድነት ትንቅንቅ ቢገጥመን ለፌዴራላዊ የፀጥታ ኃይላችን ወደኋላ ከማሽቆልቆል ይልቅ በተያያዘው ለውጥ ውስጥ መቀጠል ይቀለዋል (ወደ ቀድሞው ዓይነት የቡድን ንብረትነት መዝቀጥ ይከብደዋል) ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለ ትኩስ ተቋማዊ ጥንካሬ በእጃችን እያለና አገራችንን የማስቀጠል ተግባር በኅብረት የመቆምን ዕንቁ ሰጥቶን እያለ፣ በእኛ ስንፍናና መመናቀር ነገሮች ቢበለሻሹ በማንም ልናሳብብ አንችልም፡፡ ሕዝብ በፀጥታና በደኅንነት ማጣት፣ በኑሮ መዳቀቅ ተንገሽግሾና በለውጥ ተስፋ አጥቶ ከሥርዓተ አልባነት አሥር እጅ አምባገነንነት ይሻለኛል ወደ ማለት ቢዞር፣ ገዥ ፓርቲም በደም አፍሳሽ ውድቀት ተስፈራርቶ ወደ እዚያው ቢያቀና አንድም ፖለቲከኛ ‹‹የፈራነው ደረሰ›› የማለት አፍ አይኖረውም፡፡ ተሰጥቶት የነበረው ወርቃማ ዕድል ራሱ፣ አምባገነንትን የሚያስናፍቅ ሁኔታ ሲፈጠር አንተ የት ነበርክ? አምባገነንነት እንዳይፈጠር ምን አስተዋጽኦ አደረግህ? ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ የደረሰው ኪሳራ ወደ አምባገነንነት መመለስም ሆነ መበታተን፣ ጥፋቱ ከራሳችን ውጪ አይሆንም፡፡ የአገራዊ ርብርቡ ተግባር፣ የግርግር/የመነቋቆርና የንጭንጭ አዙሪትን ለማመናመን፣ ጨፍጫፊዎችን አንድ ላይ ለማራወጥ፣ መንግሥትንና ፖለቲከኞችን ከመፈራራት ለማራቅ፣ በአጠቃላይ መንግሥትም የፖለቲካ ቡድኖችም ሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች በሕግ ጥሰት፣ በመብት ረገጣና በፀረ ዴሞክራሲያዊ ጥፋቶች ሳይጨመላለቁ የዴሞክራሲ ተቋማትን ግንባታ ከአገራዊ ህልውና ጋር ለማዋደድ ዕድሉ ነበራችሁ ብሎ ይፋረደናል፡፡ ወርቃማው ዕድል የሚጠይቀን አበለሻሽተነው ላይመለስ ከሄደ በኋላ ብቻ አይደለም፣ አሁንም አምባገንነት እንዳይመጣም ሆነ ውልቅልቃችን እንዳይወጣ ምን እየፈየዳችሁ ነው ብሎ እየጠየቀን ነው፡፡

  1. በቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ልምዳችን ውስጥ ‹‹አብን››ን እና ‹‹ኢዜማ››ን በተመለከተ በገዥው ፓርቲ መንግሥት ውስጥ በመሳተፋቸው ማጉተምተም (በድርጅታቸው ውስጥና ከድርጅቶቹ ውጪ) ደርሶ ነበር፡፡ ለምን? ይህንን ጥያቄ ያመጣሁት ስለድርጅቶቹ ለማውራት አይደለም፡፡ አገራዊ ርብርብ፣ ድርብ ተልዕኳችንን የምንወጣበት የወቅቱ ውድና ወርቃማ ሀብታችን መሆኑ ገብቶን ከሆነና ከልብ ተቀብለነው ከሆነ፣ የቅርብ ነገረ ሥራችንን ከዚሁ ውድ ሀብታችን አኳያ ለመመዘንና ለመታዘብ እንችላለን፡፡ የሰነዘርኩት ጥያቄም ይህንኑ የሚፈትሽ ነው፡፡ የአገራዊ ርብርብን የትግልና የድል አድራጊነት ወርቃማ መሣሪያነት በአግባቡ አለመገንዘብና ይህንኑ አጥብቆ ያለ መያዝ ክፍተት መወራጨትንና ንጭንጭን አስከትሏል፡፡ አብንና ኢዜማ ላይ የታየው ማብጠልጠልም የዚሁ ክፍተት ውጤት ነው፡፡ ወደ አብጠልጣይነት መዞርም ሆነ ‹‹ተፎካካሪ የሚል የዳቦ ስም አንሻም፣ ተቃዋሚ ነን›› ወደሚል ‹‹ንቃት›› መምጣትም ዘዴ መሆኑ ነው (ተባብሮ፣ ተጋግዞ መሥራትን ካነወረው ውርጭት ጋር ተሸናግሎ የድጋፍ መቀነስን የማጣጣት ዘዴ)፡፡ ሁነኛ ተግባርን በመሳት የደረሰ የድጋፍ ጉድለትን በርካሽ መሸናገል ቢያሟሉት ውሎ አድሮ ሊተን እንደሚችል፣ ለአገራዊ ተግባር ሲታመኑ የደረሰ ነቀፋ ጊዜዊ ሆኖ እንደሚያልፍና ለትክክለኛ ሚና ፀንቶ መቆም ብዥታ ሲጠራ የበለጠ ድጋፍንና መከበርን ይዞ እንደሚመጣ የተረዳ ግንዛቤ ቢኖር ኖሮ፣ የኢዜማ አመራርን መቀየር የፈለገ እንቅስቃሴ ከውስጥ ብቅ ባላለ ነበር፡፡ የአመራር ለውጥ ውድድር መጣ ሲባል እንደ እኔ ያሉ ሰዎች፣ ከውጭ ሆነን ሥጋት የገባንም የሰዎች አምልኮ በልጦብን ወይም ለምን የዴሞክራሲ ልምምድ አየን በማለት ሳይሆን፣ አገራዊ ርብርቡን የሚጎዳ ጀብደኛ ስሜታዊነት ወደ አመራር ይመጣ ይሆን የሚል ፍርኃት ነበር፡፡ ይህንን የመሳሰሉት ልምዶቻችን የሚያስተምሩን ትምህርት እንደሚከተለው መቀመጥ ይችላል፡፡ ዋና ተግባራችንን ላለመሳትና ለሕዝብ/ለአገር ጥቅም ፅኑና ታማኝ መሆንን ትርታችን ለማድረግ በመሥራት ፈንታ፣ መንግሥትን በማዋደቅና ከንጭንጭ ፖለቲካ ጋር በማሽቃበጥ የሚገኝ አልፎ ሂያጅ ድጋፍን በማሯሯጥ ውስጥ እስከ ቀለጥን ድረስ ፖለቲከኞች የገዛ ፓርቲያችንን፣ አገረ መንግሥታችንንና አገራችንን ከማንገላታት (የጠላት መጫወቻ ከመሆን) አናመልጥም፡፡

ይህንን ማጠቃለያ አጥብቆ ለመያዝ የሚረዱ ጥቂት ነጥቦችን አስፍሬ ልደምድም፡፡ መዳፈር ባይሆንብኝ ወደ ፖለቲካ ሊቅነትና ወደ ምሁርነት የሚጓዙ ሰዎች የአዕምሯቸውን ፍሬያማነት የመጠበቂያና የማበልፀጊያ ሀብታቸው የሚኖረው ባበረከቷቸው ዕውቅ ሥራዎች ውስጥ አይደለም፣ በራሳቸው ውስጥ እንጂ፡፡ ማለትም ጆሮዎቻቸው፣ ዓይኖቻቸውና አዕምሮዎቻቸው ሁሌ ክፍት፣ ሁሌ አስተዋይና ጥያቄዎች እያነሱ የመበርበር ሥራ የሚሠሩ በመሆናቸው ውስጥ ነው፡፡ ዕሳቤው ያዘላቸውን ነጥቦች ሰተርተር ብናደርጋቸው፣ ግምትና አስተያየትን ስለጣመን ብቻ ልንጠመጠምበት አለመሞከር፣ ይህ ሆነ/ተደረገ ተብሎ ሲነገረን ወሬውን ከየት አገኘህ? በምን አረጋገጥህ? ብሎ መጠየቅ፣ ለርካሽ ተቀባይነት ሲባል አለማዳነቅ፣ ግንዛቤዎችን በእቅጭ መረጃዎች መፈተሽ፣ የራስ ማጠቃለያዎችን ትችትንና ድጋፍን በጠንካራ መረጃዎች ላይ ማቋቋም፣ ነባር ዕሳቤያችንን የሚፈታተኑ/የሚቃረኑ መረጃዎች ሲገጥሙን ነባር ዕሳቤያችንን ላለመጣል ሲባል መረጃዎችን አለማጉበጥ፣ የመረጃ አመራረጥና አደረጃጀታችንን አድሏዊ አለማድረግ፣ በኑሯችን ውስጥ ዕለት በዕለት የሚያጋጥሙንን የአስተሳሰብ/የዘልማድና የኑሮ ልምዶች ሁሉ አንዳቸውን ከአንዳቸው፣ የዛሬዎቹን ከትናንትና ጋር እያገናኙ ትኩስና ጠለቅ ያለ ግንዛቤ ከመፍጠር ሥራ አዕምሮን አለማቦዘን የሚል ዝርዝር ሊወጣቸው ይችላል፡፡ የአዕምሮ የመመራመር ስለት ሳይደንዝ የሚቆየውም በዚህ ዓይነት ሃይጅን ሲሞረድ ነው፡፡ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ላይ ብዙ ዶክተሮች ሲናገሩ ተከታትያለሁ፡፡ ስለኑሮ ነክ ጉዳታችን በይሆናል ከመናገር በመቆጠብ፣ ልምዳቸውን ወይም ሄደው ያዩትንና ያጣሩትን በመመርኮዝ ወይ ማስረጃ ጠይቀው ማጣታቸውን አንተርሰው በመናገር ጥንቃቄያቸው ትውስታዬ ውስጥ ተሰክተው በሃይጅናዊ አስተሳሰብ ትዝ ትዝ ከሚሉኝ ሰዎች ውስጥ አንዷና የቅርቧ ፕሮፌሰር ሐረገወይን አሰፋ ናቸው፡፡ ከእሳቸው ጠንቃቃነት እኔ እንደተማርኩ ሁሉ ፖለቲከኞቻችንና አዲስ መጥ ምሁራኖቻችንም መማር የሚችሉ ይመስለኛል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...