Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉበአገራዊ ውይይት ውስጥ የውጭ ኃይሎች የተሳትፎ ሚናና የሌሎች አገሮች ተሞክሮ (ክፍል...

በአገራዊ ውይይት ውስጥ የውጭ ኃይሎች የተሳትፎ ሚናና የሌሎች አገሮች ተሞክሮ (ክፍል አራት)

ቀን:

በመኮንን ዛጋ

 በውጫዊ ኃይሎች ተሳትፎ ረገድ ሊዳሰሱ የሚገቡ ቁልፍ ጉዳዮች

ከዚህ በላይ ከሞላ ጎደል የገለጽኳቸው ነጥቦች እንደሚያሳዩት ከሆነ፣ የውጭ ተዋናዮች በብሔራዊ ውይይቶች ውስጥ በግልጽነትና በመርህ ደረጃ መሳተፍ በአዎንታዊነት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የውስጠ አገራዊ ባለቤትነት መሠረታዊ መርህ በሆነባቸው ሁኔታዎችና ሒደቶች ውስጥ ግን፣ የውጭ ኃይሎች ተሳትፎ ምንም ዓይነት አደጋ የለውም ሊባል አይችልም፡፡ በመሆኑም በውጭ ተዋናዮች ተሳትፎ ረገድ የተለየ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ የማይታለፉ ሦስት ‘ቀይ መስመሮች’ አሉ። እነዚህም፣

የውጭ ኃይሎች ተሳትፎና የብሔራዊ ባለቤትነት

በእርግጥም የውጭ ተዋናዮች በብሔራዊ ውይይቶች ሒደት ውስጥ የውይይት ሥነ ምኅዳሩን በማስፋት፣ ከመንግሥት ውጭ ላሉ ተሳታፊዎች ከሥጋትና ከጭቆና የፀዳ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ወይም በሒደቱ እያንዳንዱ ምዕራፍ ውስጥ ያሉ እንቅፋቶችን ተከታትሎ በማስወገድ እጅግ ጠቃሚ አዎንታዊ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ ሆኖም እነዚህ የውጭ ተዋናዮች በውይይቱ እያንዳንዱ ሒደት ሙሉ ኃይልና ጉልበታቸውን ሲጠቀሙ፣ በተወያይ ወገኖች መካከል አድሏዊነት የተላበሰ ድጋፍ ሲሰጡና ሲነሱ፣ አላስፈላጊ ጫናም መፍጠር ሲጀምሩና የበለጠ ጠለቅ ብለው ገብተው የነቃ የማመቻቸት ሚና ሲጫወቱ ችግር ይፈጠራል፡፡ የእዚህ ንቁ ተሳትፎ አንዱ ተግዳሮት የሚሆነው በሚያደርጉት የነቃ የድጋፍ አቀራረብና አገራዊ ባለቤትነትን በማረጋገጥ አስፈላጊነት መካከል ተገቢውን ሚዛን አለመጠበቅ ነው።

የችግሩ አንዱ መገለጫ አገር፣ ክልላዊና የባለብዙ ወገን ድርጅቶች፣ እንዲሁም የውይይቱ አከናዋኝ አገሮች በብሔራዊ ሕገ መንግሥታቸው ወይም በቻርተራቸው ውስጥ በተደነገጉ አንዳንድ መርሆዎች፣ ደንቦችና እሴቶች የታሰሩ መሆናቸው ነው። ይህም የውጭ ተዋናዮች ከሁሉም አግባብነት ካላቸው ብሔራዊ ተዋናዮች ጋር በኢገለልተኝነት እንዳይሳተፉ መከላከል አለበት፡፡ ለምሳሌ በሕግ አገር ውስጥ እንዳይንቀሳቀሱ ከተከለከሉ ወይም በአሸባሪነት ከተፈረጁ ቡድኖች ጋር ሲገናኙና የአካባቢ እውነታዎችን በሚገባ ከመረዳት/ካለመረዳት የሚኖር ጣልቃ ገብነትና የአገራዊ እሴት ሥርዓቶችን ከማክበር/ካለማክበር አንፃር በአግባቡ መታየት ይኖርበታል፡፡

እንዲሁም በውስጣዊ ተዋንያን በኩል የውይይቶች የአገር ባለቤትነት መርህ ከውጫዊ ተዋንያን የታወቀ ጥቅም አንፃር ሚዛን ተዛብቶ በፍፁም መመናመን እንደሌለበት ሊታመን ይገባል። ለዚህም ዓይነተኛ ማሳያ የሚሆነው የኢራቅ ብሔራዊ ውይይት ነው፡፡ ይህ አገራዊ ውይይት በተለይም የአሜሪካና የአጋሮቿን ስትራቴጂካዊ ፍላጎት፣ ወታደራዊ ጥቅሞችና መሥፈርታዊ ፍላጎቶች በሚገባ ለማስጠበቅ የተዘጋጀ በመሆኑ፣ በአብዛኛው ክንውኑ በውጫዊ ኃይሎች የሚገፋና በእነዚህ አካላት አጀንዳዎች አቀባይነት የተመራ ነበር። በዚህ ምክንያት ሒደቱ በአገር ውስጥና በአካባቢው ባለድርሻ አካላት ዘንድ ተዓማኒነትን አጥቷል፡፡

በአጠቃላይ በብሔራዊ ውይይት ሒደት የውጭ ኃይሎችን ተሳትፎና ፍላጎቶችን በጥንቃቄና በአሠራር ላይ ተመሥርቶ በመገደብ፣ የውጭ ኃይሎችን ፍላጎት ለአገራዊ ፍላጎት የማስገዛት መርህ (The Principle of Sub sidiarity) መተግበር ይገባል፡፡ ስለሆነም ይህ የማስገዛት መርህ በብሔራዊ ውይይቶች ውስጥ የውጭ ተሳትፎዎች ላይ በጥብቅ መተግበር አለበት፡፡ ይህ ማለት የውጭ አካላት በአገር አቀፍ ተዋንያን በብቃት ሊሟሉ የማይችሉ ተግባራትን ብቻ ያከናውናሉ፡፡ ሆኖም በቅርበት በመሥራት፣ ግልጽና የማያሻማ የትብብር ማዕቀፍ በመፍጠርና በአሠላለፍ መርህ በመመራት የውጭ ተዋናዮች በውይይት ሂደቶች ውስጥ የብሔራዊ ባለድርሻ አካላትን ሥራ በጎን ማሟላት ሊኖርባቸው ይችላል።

የውጭ ኃይሎች ተሳትፎና የገንዘብ ድጋፍ

በተጨባጭ ካየነው አንድን የፖለቲካዊ ውይይት ሒደት ፋይናንስ ማድረግ ‘የግንዱን ዝቅተኛ ወይም የቅርቡን የደረሰ ፍሬ’ ያለ ምንም ድካም ቀጥፎ እንደ መወሰድ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ይህ ከፖለቲካ ፍላጎት ውጪ የሚመስለው የፋይናንስና የሎጂስቲክስ የድጋፍ ተሳትፎ መንገድ እንኳ የአገሪቱ ልሂቃንን የፖለቲካ ፍላጎትና ፈቃድ ሙሉ በሙሉ ለመተካት ሥራ ከዋለ ሒደቱን ፍፁም ሊያበላሸው ይችላል።

ስለሆነም እነዚህ ኃይሎች በሚሰጡት የፋይናንስ ድጋፍ ላይ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ቁጥብነትና የምንጭ ምርጫ ሊኖር ይገባል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ለውይይቱ ግብዓት የሚውል የገንዘብ ድጋፍ አቅርቦት ቋት (ፈንድ) በቀላሉ መገኘት፣ በግጭቱ መሠረታዊ ነገረ ጉዳዮች ላይ ዘላቂ መግባባትን ሳያመጣ የአጭር ጊዜ የሰላም ግኝት ድርሻን መፍጠር ያስችላል።

በዚህ ረገድ በሚገኘው የገንዘብ ድጋፍና በደጋፊዎቹ ተጠባቂ ጫና መካከል ተመጣጣኝ ሚዛን መምታት ሁልጊዜ ከአደጋ የሚጋርድ ነው። በመሆኑም እንደ ነባራዊ ሁኔታው ተለዋዋጭ፣ የአገር የቅድሚያ-ቅድሚያ መሠረታዊ አጀንዳዎች ላይ ያተኮረና ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የሚቀርብ የገንዘብ ድጋፍ ለውይይት ሒደቱ ስኬታማነት የበለጠ ጠቃሚ ሊሆን ቢችልም፣ ለጋሾች (አብዛኛዎቹ መንግሥታት፣ የፋይናንስ ተቋማትና ዓለም አቀፍ/ክልላዊ ድርጅቶች) በግብር ከፋይ ዜጎቻቸው በኩል ዘወትር ተጠያቂ በመሆናቸው አብዛኛውን ጊዜ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ ውጤቱን እንዲያሳዩ ግፊት ይደረግባቸዋል። ይህም ከላይ የጠቀስነውን የአጭር ጊዜ የሰላም ሁኔታና የሽግግር ውጤቶች ላይ እንዲያተኩሩ ያደርጋቸዋል፡፡

ሆኖም በታዳጊ አገሮች ውስጥ የሚፈጠሩ ፖለቲካዊ የሽግግር ምዕራፎች ካለባቸው ፈርጀ ብዙ ውስብስብነትና የከረመ አለመግባባት የተነሳ፣ ሁሉም ሊባል በሚችል ሁኔታ የረጅም ጊዜ ሁሉን አቀፍ የድጋፍ ተሳትፎ የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ በዚህ ሒደትም በተለምዶ ወጥ የሆነ መስመር በሌለው መንገድ የሚጓዙ፣ መሻሻላቸው ሳይታወቅ የኋሊት የሚመለሱ መሆናቸው አይቀርም። ስለሆነም ለአገራዊ ውይይቶች የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ እነዚህን መሠረታዊ ወጣ ገባ ባህሪያትን ባማከለ መንገድ ተለዋዋጭ መሆን አለበት። ከዚሁ ጎን ለጎን ከተለያዩ አካላት የሚገቡ የድጋፍ ቃል ኪዳኖች የሚደረጉት በቀጥታ ከለጋሽ ክበቦች የሚቀርብ ጥያቄን በመቀበል ብቻ ሳይሆን፣ ከአገራዊ ባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከርና በሒደቱ በማሳተፍ መሆኑ በጣም አስፈላጊ ነው። ይኸውም በምክክር የተሰጡ እነዚህ የገንዘብ ድጋፍ ውሳኔዎች ብሔራዊ ውይይቶችን የሚመሩ አካላት ላስቀመጧቸው መሥፈርቶች ተገቢ ምላሽ መሰጠቱን ያረጋግጣሉ። እንደ ሃርትማን አገላለጽ ከሆነ በአጠቃላይ የብሔራዊ ውይይቶችን የአገራዊ ባለቤትነትን ዕሳቤ ለማጉላት፣ ከአካባቢው ሕዝብ ዕይታ አንፃር ከመጠን በላይ የለጋሽ አገር ጥገኛ አለመሆናቸውን ማስገንዘብ በጣም አስፈላጊ ነው።

የውጭ ኃይሎች ተሳትፎና ቅንጅት

በፖለቲካዊ ሽግግር፣ በሰላም ማስፈንና መግባባት ግንባታ ሒደት ውስጥ በብዙ ባለድርሻ አካላት በሚደረጉ የድጋፍ የተሳትፎ ማዕቀፎች አካሄድ መካከል፣ የቅንጅታዊነት ማነስ በጣም የተለመደ ችግር ነው፡፡ ሆኖም እንደ ማናቸውም መሰል ሒደቶች ብሔራዊ ውይይቶችም ከእነዚህ መሰል የተዛቡ የድጋፍ ሥልቶችና ቅንጅታዊነት ማነስ ተፅዕኖ ፍፁም ነፃ አይደሉም። በአገራዊ ውይይት ላይ ሰፊ ጥናት ያደረገው ፕሮፌሰር ሲበርት እንደሚገልጸው፣ በምያንማር የብሔራዊ ውይይቱን ለማዘጋጀት በተደረገው የቅድመ ውይይት ስብሰባ ከ126 ያላነሱ የውጭ ድርጅቶች ተሳትፈዋል፡፡ በእነዚህ አካላት መካከል ስለአገሪቱ ባላቸው ውስጣዊ ዕሳቤ፣ የነባራዊ ሁኔታ አረዳድ ወጥነት ማነስና ስለፖለቲካዊ ዓውዱ የጋራ ግንዛቤ ማጣት የተነሳ ውጤታማ ቅንጅትን አሳጥቷል።

በዚህ ረገድ እንደ የወዳጅ ቡድኖች (ለምሳሌ የወዳጆች ማኅበራት፣ የልማት አጋሮች ስብስብ) እና መንግሥታዊ የድጋፍ ቡድኖች ያሉ ስብስቦች የማስተባበር ችግሮችን በእጅጉ ለማቃለል ይረዳሉ። የየመንን ጉዳይ እንደ ምሳሌ ብንመለከት አምስቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አባላት፣ ከአውሮፓ ኅብረት፣ እንዲሁም ከባህረ ሰላጤው የትብብር ምክር ቤት የተውጣጡ የአሥር አገሮች አምባሳደሮች (G10) ቡድን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ጋር በቅርበት አንድ ወጥ በመሆን መሥርተው ሠርተዋል። እነዚህ ቡድኖች ባሳዩት ቅንጅታዊ አሠራርና አንድነት በበርካታ ዓለም አቀፍ አካላት የተመሠገኑ ሲሆን፣ በብዙዎች ዘንድም ብሔራዊ የውይይት ኮንፈረንሱ በሰላም እንዲጠናቀቅ ያስቻሉ ናቸው ተብለዋል። በአንፃሩ ደግሞ ይህ አንድነት ከጊዜ በኋላ በተለያዩ አገራዊና ቡድናዊ ጥቅሞች የመሳሳብና የፍላጎት ግጭት የተነሳ በመላላቱ፣ የቡድኑ መፈራረስ ለሰፊው የውይይት ሒደት መበላሸትና እንደ ግመል ሽንት ወደኋላ መንሸራተት ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ስለሆነም በብሔራዊ ውይይቶች ውስጥ በተገቢው ሚዛናዊነት መጠበቅ ያለበት በጣም አስፈላጊው የማስተባበር ገጽታ፣ ሒደቱን በሚደግፉ የውጭ አካላትና ሒደቱን በሚመሩ ብሔራዊ ባለድርሻ አካላት መካከል ነው። የውጭ ኃይሎች ሥልታዊ ፍላጎቶቻቸውና አገር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገረ ጉዳዮች ሊጣጣሙ የሚገቡ ሲሆን፣ የውጭ ተዋናዮችም ተሳትፏቸውን ብሔራዊ ውይይቶችን ለሚመሩት ዜጎችና አገር ፍላጎት በሚስማማ መንገድ ማስተካከል አለባቸው። በአጠቃላይ አገላለጽ የውጭ ኃይሎች የሚሰጧቸው ድጋፎች በእነሱ አቅርቦት ላይ የተመሠረተና ትዕዛዛዊ ሳይሆን፣ በአገር ፍላጎት ላይ የተመሠረተና ባለብዙ ከፊል አቀራረብ በሆነ መንገድ ከሆኑ በጣም ውጤታማ የውጭ ድጋፍን ማረጋገጥ ያስችላቸዋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...