Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የአዲስ አበባ ትራንስፖርትን ዘርፍ የሚመራ የመንግሥት አካል ራሱን ይመልከት!

በአዲስ አበባ ከተማ ሥር ከሰደዱ ብርቱ ችግሮቻችን አንዱ የትራንስፖርት አገልግሎት ነው፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያለው የትራንስፖርት እጥረትና አማራሪ የአገልግሎት አሰጣጥ የከፋ ከሚባል ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ችግሩ የቆየ ነው። ነገር ግን የችግሩን ግዝፈት ያህል ሁነኛ መፍትሔ ሳይገኝለት ቆይቷል፡፡ በዚህ ሳቢያም የከተማው ማኅበረሰብ በእጅጉ እየተማረረ ኑሮውን ለመግፋት ተገዷል፡፡ የትራንስፖርት እጥረቱ ሳያንስ የአገልግሎት አሰጣጥ ግድፈቱ ሲታከልበት በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚፈጥረውን ቀውስ መገመት አያቅትም። በሕዝብ ትራንስፖርት ማመላለሻዎችና በታክሲዎች የሚገለገሉ የመዲናዋ ነዋሪዎች በተለይ በክረምት ወቅት ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባቸዋል፡፡ 

ትራንስፖርት ለማግኘት በተለይ በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ብቻ የሚጠፋው ሰዓት በገንዘብ ቢተመን የትየሌለ ነው፡፡ እንግልቱ አማራሪ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም በሚፈለገው ሰዓት አገልግሎቱን ማግኘት የማይችሉ ሠራተኞች ወደ ሥራ ቦታ ለመድረስ የሚፈጅባቸው ጊዜ እየረዘመ በመምጣቱ በወቅቱ ሥራ ገበታ ላይ ባለመገኘታችን ብዙ ሥራ ይስተጓጎላል፡፡ ትራንስፖርት ለማግኘት ያለው ውጣውረድና መንገላታትም በሠራተኞች የሥራ አፈጻጸምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የራሱ ተፅዕኖ እየፈጠረ ይገኛል፡፡  

ያለውን ትራንስፖርት እጥረት ተገን አድርገው ያልተገባ የትራንስፖርት ታሪፍ በማስከፈል ነዋሪውን የሚበዘብዙ አገልግሎት ሰጪዎች በመበራከታቸው የከተማ ነዋሪው 

በቅጥር ከሚያገኘው የወር ደመወዝ ጋር የማይጣጣም የተጋነነ የትራንስፖርት ወጪ እንዲከፍል እየተገደደና የኑሮ መዛባት እየደረሰበት ነው። 

በመንግሥት የወጣውን የትራንስፖርት ታሪፍ አክብረው የሚያስከፍሉ አገልግሎት ሰጪዎች ከመጥፋታቸው እኩል በወጣው የጉዞ ታሪፍ አገልግሎት መስጠታቸውን የሚከታተልና የሚቆጣጠር የመንግሥት አካል ባለመኖሩ ብዝበዛው አይሎ ቀጥሏል። ዝናብ ጠብ ሲል የአምስት ብር መንገድ አሥርና አሥራ አምስት ብር ይጠየቅበታል፡፡ መሸት ካለ ደግሞ ይኸው የአምስት ብር መንገድ 30 ብር እየተጠየቀበት ነው፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ነዳጅ ጨመረ በሚል ሰበብ የሚጠየቀው ዋጋ ሕዝብን የበለጠ እያማረረ ነው፡፡ ከትርፍ በላይ ጭነሃል ብሎ የሚጠይቅ ተቆጣጣሪ ጠፍቷል፡፡

ስለዚህ የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት እጥረት እጅግ ውስብስብና የበለጠ አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ በዋጋ ንረትና በኑሮ ውድነት የተማረረው ኅብረተሰብ በትራንስፖርት እጥረትና ያልተገባ የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ የመፍትሔ ያለህ እያለ ነው፡፡ 

በጣም የሚገርመው አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ያደርሳሉ የተባሉ እንደ ታክሲ ያሉ ተሽከርካሪዎች የነዳጅ ድጎማ እየተደረገላቸው መሆኑ እየታወቀ ነዳጅ ጨመረ በሚል ሰበብ መቶና ሁለት መቶ ፐርሰንት ዋጋ መጨመራቸው ሕገወጥ ተግባር መሆኑ እየታወቀ ዕርምጃ የሚወስድ የመንግሥት አካል የለም፡፡ መንግሥት ለሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የነዳጅ ዋጋ ድጎማ ያደረገው ኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የትራንስፖርት አገልግሎት እዲያገኝ ቢሆንም በተግባር እየታየ ያለው ግን በተቃራኒው ነው፡፡ በመሆኑም የነዳጅ ድጎማ የሚደረግላቸው የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በአግባቡ ኅብረተሰቡን እያገለገሉ መሆኑን በመከታተልና በቆጣጠር ማስተካከል ካልተቻለ በመንግሥት የተፈቀደው የነዳጅ ድጎማ መና መቅረቱ አጠያያቂ አይደለም። ይህም ከወዲሁ እየታየ ነው። መንግሥት የነዳጅ ድጎማን መሠረት ያደረገ የትራንስፖርት ታሪፍ ማውጣትና ከሥር ከሥር እያየ ማስተካከያ ማድረግ አንዱ ተግባሩ እንደሆነው ሁሉ፣ ከዚሁ ጎን ለጎን የተወሰነው የትራንስፖርት ታሪፍ ምን ያህል እየተሠራበት መሆኑን ማረጋገጥም ግዴታ ነው፡፡

የአዲስ አበባ የትራንስፖርት እጥረት የቆየና ሥር የሰደደ የመሆኑን ያህል፣ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ የሚያበጅ የመንግሥት አካል መጥፋቱ ደግሞ ነገሩን አሳዛኝ ያደርገዋል። ችግሩን ለማቃለል ይረዳሉ ተብለው የሚወሰዱ ዕርምጃዎችም መፍትሔ ማምጣት አለመቻላቸው የመፍትሔ አፍላቂውን የመንግሥት አካል የእይታ አድማስ ውሱንነት የሚገልጡ ናቸው። በከተማዋ ጎዳናዎች ላይ ትራንስፖርት ለማኝኘት የሚታዩት ረዣዥም ሠልፎች የሚነግሩን ይህንኑ ነው፡፡

ስለዚህ ችግሩን በዘለቄታ ለመፍታት እንዲሁም በየጊዜው እያደገ የሚመጣውን የከተማውን ነዋሪ የሚመጥን ዕቅድ ተይዞ መሥራት ቀዳሚና ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ጉዳይ መሆን አለበት፡፡ በዚህ ደረጃ ታስቦ የማይሠራ ከሆነ የከተማዋ የትራንስፖርት እጥረት የሚያስከትለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየከፋ መሄዱ አይቀሬ ነው፡፡

የከተማውን የትራንስፖርት ችግር ከማቃለል አንፃር መወሰድ የነበረባቸው ዕርምጃዎች የተምታቱ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ለምሳሌ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በጉዞ ርቀት ለሚያስከፍሉ እንደ ራይድና መሰል የታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች ተሽከርካሪዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡና የተለያዩ ማበረታቻዎችን እንዲያገኙ መንግሥት በአንድ በኩል ሲወስን፣ ብዙኃኑን ሊያስተናግዱ የሚችሉ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ዘርፎችን ማስተዋል አለመቻሉ ለትራንስፖርት ችግሩ የሚሰጡ መፍትሔዎች ሸውራራ መሆናቸውን ያሳያል።

ከ12 በላይ የሚጭኑ ታክሲዎችና ሌሎች የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችን በማስገባት ችግሩን ለማቃለል የሚደረግ ጥረት ባለመኖሩ ትራንስፖርትን በተመለከተ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ቅድሚያ ለማን ይሰጥ? የሚለውን ያላገናዘቡ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ 

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ችግር  የሚሊዮኖች በመሆኑ እንደ አንበሳና ሸገር ባስ ባሉ የመንግሥት የትራንስፖርት ድርጅቶች ብቻ አሁን ያለውን ችግር መቅረፍ አይችልም፡፡ አነስተኛ ታክሲዎችን በማበርከትም የሚቃለል አይደለም፡፡ በመሆኑም በርከት ያሉ ተጓዦችን የሚጭኑ ተሽከርካሪዎች ወደ አገልግሎት እንዲገቡ የሚያስችሉ አሠራሮችንና ማበረታቻዎችን ያቀፈ የትራንስፖርት ችግሩን ቀርፎ አግልግሎቱን ለማዘመን የሚያስችል ጥልቅ ፖሊሲ መቅረጽ ያስፈልጋል። በቴክኖሎጂ ታግዘው የትራንስፖርት አግልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ታክሲዎች ያለመንግሥት ድጋፍ ራሳቸውን አደራጅተው የባንክ ብድር ጭምር እያገኙ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ላስተዋለ፣ በሚኒ ባስና ከዚያ በላይ በሆኑ ተሽከርካሪዎች የትራንስፖርት አገልግልት የሚሰጡትን እንዲደራጁና አገልግሎታቸውን እንዲያዘምኑ ማድረግ አዳጋች ነው ብሎ ሊከራከር አይቻለውም። ጭምር ሊኖር ይገባል፡፡ በግለሰብ ደረጃ ከሚሰጥ የትራንስፖርት አገልግሎት መውጣትና በባለንብረቶች የሚመሠረቱ የትራንስፖርት ኩባንያዎች እንዲፈጠሩ ማድረግ አንዱ የችግሩ መፍቻ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል። እንደዚህ ያሉና ሌሎች ዘላቂ የመፍትሔ ሐሳቦችን አፍልቆ መተግበር የማይችል የመንግሥት አካል የትራንስፖርት ዘርፉን ለመምራት ብቁ አይደለምና ይወገድ። 

አነስተኛ ታክሲዎችና በተለያዩ መንገዶች ለማስገባት የተደረገው ጥረት ለምን ብዙኃኑን የሚያገለግሉ የከተማ የሕዝብ ሰጪዎች ላይ እንደማይታይ መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ 

የከተማ የሕዝብ ማመላለሻ የትራንስፖርት አገልግሎትን አንዳንዶች አያዋጣም ቢሉም አሁን ላይ በደንብ የሚያዋጣበት ብዙ ዕድል አለ፡፡ ስለዚህ አንዱ የከተማዋ የትራንስፖርት ችግር ወደ ትራንስፖርት ዘርፉ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ማነስ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ በጣም አሳሳቢው ጉዳይ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ያሉ በተለይ የሚኒባስና መሰል የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ዓመት ዓመት እያነሰ መምጣቱ ነው፡፡ ወደ ዘርፉ የሚገቡ ባለሀብቶችም የማይበረታቱ በመሆኑ ችግሩ ይብሳል፡፡

በመሆኑም ነጋ ጠባ ችግሩን በመናገር ብቻ መጠበቅ ስለማይቻል የከተማና የሕዝብ ማመላለሻ የትራንስፖርት ዘርፍ በልዩ ሁኔታ ተበረታቶ እንዲገባ መደረግ አለበት፡፡ ችግሩ እስካሁን በተመጣበት መንገድ መፍታት አይቻልም፡፡ ቢያንስ አሁን ያሉ ከ12 ሰዎች በላይ የሚይዙ ታክሲዎችን አደራጅቶ አዲስ የሚገቡትን እያበረታቱ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡበትን አሠራር መተግበር ለምን ከባድ እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያሉ አማራጮችን መጠቀም የማይቻል ከሆነ ችግሩ መቼም እንደማይፈታ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ 

ሌላው የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት ለሠራተኞቻቸው ሰርቪስ የማዘጋጀት ልምድ ቢያዳብሩ ችግሩን በማቃለል ረገድ ቀላል የማይባል ጠቀሜታ አለው፡፡ አሁን የምናየው ግን ሰርቪስ ማቅረብ የሚችሉ ተቋማት ሳይቀር ይህንን ሲያደርጉ አይታይም፡፡ ስለዚህ አቅም ያላቸው ተቋማት ቢያንስ ጠዋትና ማታ ሠራተኞችን ከቤት ወደ መሥሪያ ቤት ከመሥሪያ ቤት ወደ ቤት  ሊያደርሱ የሚችሉ የሰርቪስ አገልግሎቶችን እንዲያቀርቡ ማስገደድ ዘርፉን የሚመራ የመንግሥት አካል ሚና ነው። ይህ አሠራር ለምርታማነት ጭምር ይጠቅማል፡፡

እንዲህ ያለውን አሠራር ደግሞ ወጪን በመጋራት ጭምር መተግበር ይቻላልና ችግሩን ለማቃለል ሲባል የተለያዩ መፍትሔዎችንና አማራጮችን መጠቀም የግድ ይላል፡፡ ካልሆነ ችግሩ እየባሰ መሄዱ አይቀርም፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት