በ18ኛው የኦሪገን ዓለም አሻምፒዮና ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ አትሌቲከስ ቡድን ዛሬ በሚያደርጉት የፍፃሜ ውድድሮች ቆይታውን ያጠናቅቃል፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ በኦሪገን በነበረው ቆይታ ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ አዲስ ታሪክ ማኖር የቻለችበትን ገድል የፈጸመበት አጋጣሚ ነበር፡፡
ቡድኑ በሴቶች 10,000 ሜትር ርቀት ወርቅ ጀባ ካለ በኋላ፣ በርካታ ርቀቶችንም በድል አጠናቋል፡፡ በሻምፒዮናው ሜዳልያ ከማግኘት ባሻገር በርቀቶች አዳዲስ ክብረ ወሰኖችን ያስመዘገበበት ሻምፒዮና ሆኖም ነበር፡፡
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከተሳተፉባቸው ርቀቶች መካከል በማራቶን በሁለቱም ፆታ የሻምፒዮናውን ክብረ ወሰን በማሻሻል ጭምር አሸናፊ ሲሆኑ፣ በተለይ በ3,000 ሜትር ርቀት ሴቶች መሰናክል ወርቅውኃ ጌታቸው ዘጠኝ ደቂቃ በታች የገባችበት ሌላው አጋጣሚ ነበር፡፡
በቶኪዮ ኦሊምፒክ በ800 ሜትር ርቀት ኢትዮጵያን ወክላ ወደ ጃፓን አምርታ የነበረው ወርቅውኃ በውስጧ የነበረው የቴስቴስትሮን መጠን ከፍተኛ በመሆኑና ርቀት ቀይራ መሮጥ እንዳለባት በተወሰነው መሠረት፣ በ3,000 ሜትር ፊቷን አዙራ አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ ችላለች፡፡
ከዘጠኝ ደቂቃ በታች በገቡበት በ3,000 ሜትር መሰናክል ፍፃሜ ወርቅውኃ ጌታቸው 8፡54፡01 በመግባት በርቀቱ ለኢትዮጵያ አዲስ ክብረ ወሰን ማስመዝገብ ችላለች፡፡
አትሌቷ ቀድሞ ኢትዮጵያዊቷ ሶፊያ አሰፋ እ.ኤ.አ. በ2012 ለንደን ኦሊምፒክ ያጠናቀቀችበትን 9፡09፡04 ጊዜ ማሻሻል ችላለች፡፡
በኦሪገኑ የሴቶች 3,000 መሰናክል ፍፃሜ ላይ ሦስቱም አትሌቶች ከዘጠኝ ደቂቃ በታች ማግባት የቻሉ ሲሆን፣ ወርቅውኃ ብሔራዊ ክብረ ወሰን በእጇ መጨበጥ ስትችል፣ ሌላዋ ኢትዮጵያዊት መቅደስ አበበ 8፡56፡08 በሆነ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ የራሷን ምርጥ ሰዓት ማስመዝገብ ችላለች፡፡ ርቀቱን ትውልደ ኬንያዊቷ ለካዛኪስታን የምትሮጠው ሮራ ጀሮቶ 8፡53፡02 በማጠናቀቅ የሻምፒዮናው ክብረ ወሰን በማሻሻል ጭምር አሸንፋለች፡፡
ኢትዮጵያ እምብዛም በማትታወቅበት በዚህ ርቀት በቀጣይ ለሚከናወኑት ዓለም አቀፍ ሻምፒዮኖች ተስፋን የሚሰንቅ ውጤት መሆኑ ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል ሐሙስ ንጋት በተደረጉ የሴቶችና የወንዶች 5,000 ሜትር ማጣሪያ ውድድሮች ኢትዮጵያ አትሌቶች ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያን በወንዶች 5,000 ፍፃሜ በሰለሞን ባረጋ ዮሚፍ ቀጄልቻና ሙክታር እድሪስ የምትወክል ሲሆን፣ በሴቶች በለተሰንበት ግደይ በጉዳፍ ፀጋይና ዳዊት ሥዩም የምትወከል ይሆናል፡፡ በወንዶች 10,000 ሜትር እንደሚያሸንፍ ታላቅ ግምት ተሰጥቶ የነበረው ሰለሞን ባረጋ በ5,000 ሜትር ፍፃሜ ከወዲሁ ግምት ተሰጥቶታል፡፡
ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያ በሦስት ወርቅ፣ በአራት የብር ሜዳልያና በአንድ ነሐስ በአጠቃላይ በስምንት ሜዳልያዎች አሜሪካን ተከትላ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
ኢትዮጵያ የኦሪገኑን ዓለም ሻምፒዮና ጨምሮ መካፈል ከጀመረች ጊዜ አንስቶ 32 ወርቅ፣ 34 የብር ሜዳልያና 27 የነሐስ ሜዳልያ መሰብሰብ ችላለች፡፡