Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ሕገ መንግሥቱ ካልተሻሻለ ይህች አገር አሁን በምናያት መንገድ አትኖርም›› ጫኔ ከበደ (ዶ/ር)፣ የኢዜማ ሊቀመንበር

ለረዥም ጊዜ በዘለቀው የፖለቲካ ሕይወታቸው ይታወቃሉ፡፡ በቅርቡ በተካሄደው የኢዜማ ምርጫም የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል፡፡ የተለያዩ ጥናቶችን በማበርከት የሚታወቁም ሲሆን፣ በተለይ በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ላይ በ2012 ዓ.ም. ባበረከቱት ጥናታዊ መጽሐፍ ይጠቀሳሉ፡፡ ‹‹የዘር ፖለቲካና የቋንቋ ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት በዚህ መጽሐፍ፣ ከዘርና ከቋንቋ ይልቅ በኢኮኖሚ መደራጀት ያለውን ጠቀሜታና የግለሰብ ነፃነትን የማስቀደም አስፈላጊነትን በሰፊው አውስተዋል፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ የሚታዩ የማንነት ጥያቄዎችን የተከተሉ ግጭቶችና ደም መፋሳሶች የሚቆሙበትን መፍትሔ በተመለከተም፣ ‹‹ሕገ መንግሥቱ ይቀየር›› ሲሉ ነው ሐሳብ የሚያቀርቡት፡፡ የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄን በተመለከተ በሚነሱ ግጭቶችና መፍትሔዎቻቸው ላይ ዮናስ አማረ ከጫኔ ከበደ (ዶ/ር) ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡ 

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓትን ካጠኑና መጽሐፍ ከጻፉ ሰዎች አንዱ ነዎት፡፡ እርስዎ ይህን ሥርዓት ለማጥናት እንዴት ተነሱ? ጥናቱን ማድረግስ ለምን አስፈለገ?

ጫኔ (ዶ/ር)፡- ‹‹ኢትዮጵያ የምትገኝበት ምስቅልቅልና ቀውስ የዘር ፌዴራሊዝም ፖለቲካ ያመጣው ነው›› በሚል መነሻነት ነው ወደ እዚህ ጥናት የገባሁት፡፡ ኢትዮጵያ የሚበጃት የፌዴራላዊ ሥርዓት የቋንቋ፣ የዘር፣ ወይስ ሌላ የቱ ዓይነት ነው? የሚለውን ለማጥናት ሞክሬያለሁ፡፡ ታች ያለው ኅብረተሰቡ ጋ ወርጄ የሚፈልገው ያልተማከለ አስተዳደር ዓይነት ምን እንደሆነ ለማወቅ ሞክሬያለሁ፡፡ ከለውጡ በፊት ነው ጥናቱን ያጠናሁትና መጽሐፍ የጻፍኩት፡፡ ብዙ የኢትዮጵያ አካባቢዎችንም አካልያለሁ፡፡ ፖለቲከኛ በመሆኔም በማኅበራዊ ጉዳዮች ሳልወሰን ፖለቲካዊ ችግሮችንም በተጨባጭ በፌዴራሊዝሙ ውስጥ ለመፈተሽ ሞክሬያለሁ፡፡ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ዘላቂ የፖለቲካ ሥርዓት ምን ዓይነት ነው የሚለውን ጉዳይ መልስ ለማፈላለግ ሞክሬያለሁ፡፡ አሁን ያለውን ፌዴራላዊ ሥርዓት የተከሉ ሰዎች የተለያዩ ክልሎችና ሕዝቦችን ፍላጎቶች መልሰዋል ወይ የሚለውን መርምሬያለሁ፡፡ የውጭ አገሮች ተሞክሮዎችንም አቅርቤያለሁ፡፡

ኢትዮጵያ 86 ብሔሮች አሏት፡፡ የእነዚህ ብሔሮች በእኩልነት የመኖር፣ ሀብት የማፍራትና ከቦታ ወደ ቦታ ተንቀሳቅሶ የመኖር ወይም የመነገድ ጥያቄያቸው አሁን ባለው የፌዴራል ሥርዓት እንዳልተመለሰ እያየን ነው፡፡ እንዲያውም ሥርዓቱ የእኔ ነው የሚል ስሜት የፈጠረ ነው፡፡ አንተ ከዚህ መለስ አያገባህም፣ የአንተ አይደለም የሚል ስሜት ተፈጥሯል፡፡ ይህ እያደገ ሄዶ ደግሞ ግጭትና ግድያ፣ እንዲሁም ማፈናቀል በየቦታው ተስፋፍቷል፡፡ በአንድ ጀንበር አንድ ከተማ የወደመበትን አጋጣሚ ጨምሮ ብዙ ግጭቶችና መፈናቅሎች ሲደርሱ ያየነው ፌዴራሊዝሙ ባመጣው ችግር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ስለፌዴራላዊ አወቃቀር አስፈላጊነት ተጠንቷል፡፡ በደርግ ዘመን ከተደረገው የብሔረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት ጀምሮ በሽግግሩ ዘመን ሕገ መንግሥቱ ሲዋቀርና አሁን ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓት ሲመሠረት ብዙ ጥናቶችና የሕዝብ መጠይቆች ተደርገዋል፡፡ ሆኖም የፌዴራል ሥርዓቱ ነው ዋናው የአገሪቱ ችግር የሚባለው ለምንድነው?

ጫኔ (ዶ/ር)፡- ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ሲደራጅ ጥናት አልተደረገም፡፡ በደርግ ጊዜ የነበረው የብሔረሰቦች ጥናት ተቋም እንኳ ያቀረበውን ትልቅ ጥናትና ምክረ ሐሳብም ከግምት ውስጥ አላስገባም፡፡

ሪፖርተር፡- ሕዝብ ሳያወያይበት የተደረገ ነው?

ጫኔ (ዶ/ር)፡- አዎን ሕዝቦችን አላወያየም፡፡ የተለያዩ ብሔረሰቦችንና ተወካዮችን እንኳን አላማከረም፡፡ በተሳሳተ መንገድ ነው አሁን ባለው መንገድ የተደራጀው፡፡ በሽግግሩ ወቅት የነበረው አሁን ካለው አደረጃጀት በጣም የተለየና የተሻለም ነበር፡፡ አሁን ከምናየው ፍፁም በተለየ ሁኔታ ክልል አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት እያለ በቁጥር ነበር የተደራጀው፡፡ በእኔ ጥናት ላይም የተለያዩ ወገኖችን ሳነጋግር ያገኘሁት ምክረ ሐሳብ እንደዚያ ዓይነት አደረጃጀት ቢመለስ ይሻላል የሚል ሐሳብ ይገኝበታል፡፡ ሕዝቦች ባልመከሩበትና ይሁንታ ባልሰጡበት ሁኔታ ይህን ዓይነት አደረጃጀት መፍጠሩ ስህተት ነው፡፡ ይህ የክልል አደረጃጀት የተዛባ የኢትዮጵያዊነት ትርጉምና ማንነትን በትውልዱ ላይ የፈጠረ ነው፡፡ ሥርዓቱ ቡድናዊ ማንነትን ከፍ በማድረጉ የብሔረሰብ እንጂ ግለሰባዊ መብቶች እንዲጨፈለቁ አድርጓል፡፡ በአንድ ክልል ወይም አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች የዚያ ክልል ወይ አካባቢ ብሔረሰባዊ ማንነት ከሌላቸው መብታቸው ይጨፈለቃል፡፡ ይህ ዓይነቱ አደረጃጀት ብሔረሰባዊ ወይም ክልላዊ ማንነትን እንጂ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎላም አይደለም፡፡ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ወዘተ የሚል ክልልን እንጂ ትውልዱ የሁሉም የሆነችውን ኢትዮጵያን ሳያውቅ ለማደግ ተገዷል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያዊነት እየደበዘዘ የብሔር ወይም የክልል ማንነቶች እየገነኑ መጥተዋል፡፡ 

ክልሎች የበላይ ሆነው የሚታዩበት አደረጃጀት ደግሞ አገርን ሊበታትን የሚችል አደገኛ አካሄድ መሆኑን ዓይተናል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ይህ አካሄድ እንዲስተካከል ጥቆማ ሲቀርብ ቢቆይም ነገር ግን ማንም አልሰማም፡፡ ክልሎች የተሰጣቸውን ሥልጣን ባልተገባና አደገኛ በሆነ ሁኔታ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል፡፡ ባንክ፣ የመኪና ሰሌዳና የአካባቢ ስም መቀያየርና አዲስ ማንነት መስጠት የተጀመረው በዚህ ዓይነቱ የተበላሸ አካሄድ ነው፡፡ ክልሎች ራሳቸውን አንድ ቀን ሉዓላዊ አገር ለመፍጠር በሚያዘጋጅ መንገድ ነበር ፌዴራሊዝሙ ሲሠራበት የቆየው፡፡ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ ወይ ሌላ አንድ የሆነ ክልል ሄደህ ‹‹ግለሰባዊ መብቴና ነፃነቴ ይከበርልኝ›› ብለህ መጠየቅ፣ ኬንያ ወይ ሌላ አገር ሄደህ እንደ መጠየቅ ዓይነት እስኪመስል ድረስ ዜጎች በአገራቸው ነፃነት አጥተዋል፡፡ በየክልሉ ብትሄድ ልክ ደቡብ ሱዳን የሄድክ ይመስል ‹‹የእኔ ነው›› ወይም ‹‹ዜጋዬ ነው›› ብሎ አቅፎ የሚይዝህ አካል ማግኘት ከባድ ነው፡፡ በአገርህ እየኖርክ ፍርድ ቤት የምትዳኘውና አገልግሎት የምታገኘው በአስተርጓሚ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ኬንያም ሆነ ሌላ ውጭ አገር ሄደህ ከምታገኘው አገልግሎት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ፌዴራላዊ አስተዳደር ኢትዮጵያ እንደማይመጥናት፣ ልማቷንና ዕድገቷን የሚጎትት መሆኑን ብዙ ምሁራን መክረዋል፡፡ ንግድን፣ የሰው ሀብት አጠቃቀምንና የሰዎችን ተንቀሳቅሶ የመሥራት መብትን የሚገድብ መሆኑ በግልጽ ታይቷል፡፡ እዚህ ክልል ላይ የንግድ ድርጅት ፈጥሬ እሠራለሁ ለማለት የዚያ ክልል ብሔረሰብ ካልሆንክ አታስበውም፡፡ ይህ ደግሞ የኢኮኖሚ ትስስራችንን የሚያላላ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊ በየትም ተንቀሳቅሰህ ለመሥራት አዳጋች ሆኗል፡፡ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ዕውቀትና ሀብትን ወስደህ ለመጠቀም ዕድሉ ጠቧል፡፡ በዚህ የተነሳ ብዙ ክልሎች ከበጀት ተደጓሚነትና ከድህነት መውጣት ሳይችሉ፣ ሕዝባቸውን በድህነት አስቀርተዋል፡፡ ክልሎች የተደጎሙትን ያህል የተማረ ሕዝብ ካለበት እያነፈነፉ መውሰድና መጠቀም ቢችሉ ኖሮ፣ ድህነትን ማሸነፍ በቻሉና ከተደጓሚነትም በተላቀቁ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊ መሬትና ሀብት አላት፡፡ ይህንን ለመጠቀምና ለማደግ አመቺ የሆነ የፖለቲካ ሥርዓት ባለመኖሩ ግን ድህነትን ማሸነፍ አቅቶናል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጥያቄ ደጋግሞ ይነሳል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ሕገ መንግሥት ለማሻሻልም ሆነ ለመቀየር ፈታኝ አይሆንም ብለው ያስባሉ?

ጫኔ (ዶ/ር)፡- ሕገ መንግሥትን ለማሻሻል የፖለቲካ ልሂቁ አዕምሮውን ሰብስቦ መግባባት ላይ መድረስ መቻል አለበት፡፡ አሁን ባለው ሕገ መንግሥት ‹‹ኢትዮጵያን እናስቀጥላለን›› የሚሉ የብሔር ማንነት ፖለቲካን አቀንቃኝ ኃይሎች ፍላጎታቸው ኢትዮጵያን ‹‹መበታተን›› ወይ ‹‹መከፋፋል›› ነው ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የቋንቋና የዘር ፖለቲካ አደረጃጀትን የሚደግፉ የፌዴራሊስት ኃይሎች ነን የሚሉ ወገኖች ብዙዎቹ ኢትዮጵያን የማፈራረስ ፍላጎት እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡ በእነሱ በኩል የሚነሳው ሥጋት ኢትዮጵያን አስቀድማለሁ የሚሉ ኃይሎች የኢትዮጵያን ብሔሮች ቋንቋና ባህላቸውን ለመደፍጠጥ፣ እንዲሁም ማንነታቸውን ለመርገጥ ፍላጎት አላቸው የሚል ነው፡፡ ሁለቱን ኃይሎች አስታርቆ ሕገ መንግሥቱንም ሆነ ፌዴራላዊ ሥርዓቱን አሻሽሎ የአገሪቱን ህልውና ማስቀጠል የሚቻለው በምንድነው?

ጫኔ (ዶ/ር)፡- ቀናነቱ ካለ ማስታረቅ የሚቻልበት ዕድል አለ፡፡ የፌዴራሊስት ኃይሎች አገሪቱ አሁን ባለው ሕገ መንግሥትና አደረጃጀት እንድትቀጥል ፍላጎት አላቸው፡፡ አሁን ባለው ፖለቲካ ‹‹የብሔርና የማንነት ጥያቄ ተመልሷል›› ብለው የሚያምኑም ናቸው፡፡ ይህ ግን በጣም አደገኛ ነው፡፡ አካሄዱ ለረዥም ጊዜ ተሞክሮ ምን ዓይነት ውጤት እንዳስከተለ ዓይተነዋል፡፡ አሁንም ድረስ የሰዎችን ዕልቂት እየፈጠረ ያለው የዘር ፌዴራሊዝሙ ነው፡፡ በዚህ መንገድ እንሂድ የሚሉ ኃይሎች በእኔ እምነት ከበስተጀርባው ተገንጥሎ አገር የመሆን ልምምድ የያዙ፣ ወይም ኢትዮጵያ የምትባለዋን አገር አፍርሰው በእነሱ ፍላጎት ለመሥራት የሚያልሙ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የአንድነት ኃይሉስ ግማሽ መንገድ መምጣት የለበትም ወይ?

ጫኔ (ዶ/ር)፡- የአንድነት ኃይሉ እኮ የብሔረሰብ ማንነትን ልጨፍልቅ አላለም፡፡ የብሔር ፖለቲከኞች ሥጋት ተጨባጭነት የለውም፡፡ እነሱ በወጣትነታቸው የብሔር ፖለቲካን በማራገብ ሲነሱ በዋናነት የአንድነት ኃይሉ ጨቋኝ፣ በዝባዥና ጨፍላቂ ነው በሚል የውሸት ትርክት ነው፡፡ የአንድነት ኃይሉ የአገር አንድነት ያስፈልጋል ሲል፣ የብሔር ማንነት ይረገጥ ማለቱ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች በሚፈልጉት መንገድ ቋንቋቸውን፣ ባህላቸውንና ማንነታቸውን ማሳደግ አለባቸው፡፡ ራሳቸውን በራሳቸውም ማስተዳደር አለባቸው፡፡ ይህን ማንም አይከለክላቸውም፡፡

የአንድነት ኃይሉም ቢሆን የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ ሲደራጅ የብሔር ማንነት፣ ቋንቋና ባህል በሚያበለፅግ መንገድ መደራጀት እንዳለበት አምናለሁ፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱም ልክ እንዲሁ መሄድ አለበት፡፡ አብሮ መኖርን፣ መተሳሰርን፣ አብሮ ማደግን፣ እርስ በእርስ መነገድን፣ በወሰንና በሀብት አጠቃቀም መተሳሰርን ባማከለ መንገድ መደራጀት እንዳለበት አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ማኅበረሰብ ከፌዴሬሽኑ ጋር አልቀጥልም፣ ወይም ኢትዮጵያ በቃችኝ ብሎ ባመነ ጊዜ መገንጠል የሚችልበት ዕድል መነፈግ አለበት ወይ?

ጫኔ (ዶ/ር)፡- የ86 ብሔሮች አገር በሆነችው ኢትዮጵያ ሁሉም ብሔር እንዲህ ይላል ማለት መንግሥት የለም ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን የምናየው በማንነት ፖለቲካ የሚፈጠር ግጭትና ውጥረት የዚሁ ፖለቲካ ፍላጎት ውጤት አይመስልዎትም?             

ጫኔ (ዶ/ር)፡- ይህ በፍፁም ተገቢነት የሌለውና መንግሥት በአስቸኳይ መቅረፍ ያለበት ችግር ነው፡፡ 86 ብሔሮች መገንጠል ይፈልጋሉ በሚል አስተሳሰብ ብቻ አገር እንዲፈርስ በፍፁም መፈቀድ የለበትም፡፡ ‹‹እንገንጠል›› የሚሉም ሆነ ‹‹የራሳችን ማንነት የሚከበርበት አስተዳደር ይሰጠን›› የሚሉ ኃይሎች በጥቂት ፖለቲከኞች ፍላጎት ነው የሚመሩት፡፡ ታች ማኅበረሰቡ ዘንድ ስትሄድ ሕዝቡ አብሮ በመኖሩ ችግር እንደሌለበት ነው የምታየው፡፡ መንግሥት ይህን ችግር መፍታት የሚቻልበትን ዓውድ መፍጠርና ታች ኅብረተሰቡ ጋር ወርዶ የሕዝቦችን ትስስር የበለጠ ለማጠናከር መጣር አለበት፡፡

አሁን የምናየው የትጥቅ ቡድኖችና ኢመደበኛ አደረጃጀት እየተባሉ የሚወራጩ ኃይሎች መስፋፋት የተፈጠረው፣ የሕዝብ ትስስርና የአገር አንድነትን ለመፍጠር በቂ የማንቃት ሥራ ባለመሠራቱ ነው፡፡ ሰምተነውና ዓይተነው በማናውቀው ሁኔታ በአማራ ክልል ጭምር ‹‹የኢመደበኛ ኃይል ተፈጠረ›› የሚል ነገር መፈጠሩ የዚህ ውጤት ነው፡፡ መንግሥት የአገር አንድነትን አሁንም በጊዜ መሰብሰብ ካልቻለ፣ ብሔሮች የራሳቸውን ኃይል እየፈጠሩ መንቀሳቀሳቸው ገና ይቀጥላል፡፡ ስለዚህ አሁን በቅርቡ ሊጀመር በታቀደው አገራዊ የምክክር መድረክ ላይ የሕገ መንግሥቱ መሻሻልና የአገር አንድነት መጠናከር ጉዳይ በተገቢው ሁኔታ ሊነሳና ምላሽ ሊያገኝ ይገባል፡፡ ሁሉም ይቀበለዋል ባይባልም፣ ዴሞክራሲያዊ መንገድ መከተል አስፈላጊ ነውና 60 ወይም 75 በመቶ የሚቀበለው ከተገኘ ሌላው በዚያ ስምምነት መገዛት መለማመድ አለበት፡፡ ሕገ መንግሥቱ ካልተሻሻለ ይህች አገር አሁን በምናያት መንገድ አትኖርም፡፡ ብዙው ማኅበረሰብ ሕገ መንግሥቱ ይሻሻላል የሚል ተስፋን ታሳቢ በማድረግ እንጂ ዛሬ ዝም ብሎ የሚያዳምጠው፣ በአገሪቱ ያለው የፖለቲካ ውዥንብር የተረጋጋ ሕይወት ለመምራት የሚያስችለው ሆኖ አይደለም፡፡ 

ሪፖርተር፡- የትኛው የፌዴራላዊ ሥርዓት ነው የሚበጀው? በዘር፣ በቋንቋ፣ በአካባቢ፣ ወይስ እርስዎ በጥናቶች እንደጠቆሙት በኢኮኖሚ መደራጀት ነው የሚበጀው? በኢኮኖሚም ቢሆን በስፔን ካታላን ግዛት የሚታየው ዓይነት ውዝግብ አይገጥምም ወይ?

ጫኔ (ዶ/ር)፡- በኢትዮጵያ የነበረው የፌዴራላዊ ሥርዓት የተወሰነ ቡድንን ወይም የማኅበረሰብ ክፍል በፖለቲካ ታማኝነት ብቻ የሚጠቅም ሥርዓት ነበር፡፡ ብዙኃኑ ሕዝብ ከኢኮኖሚው ተገልሎ ከተለያዩ ቡድኖች ወይም ክልሎች በፖለቲካ የተሰባሰቡ ኃይሎች ነበሩ ሲጠቀሙ የኖሩት፡፡ ሕወሓት በስፋት ተንሰራፍቶ ቢታይም፣ ነገር ግን ሁሉም ከኢኮኖሚው የራሱን ጥቅም ለማጋበስ ሲጥር ቆይቷል፡፡ ሁሉም የራሱን የኢኮኖሚ ለመዋቅር ለመዘርጋት ሲጣጣር ነው የቆየው፡፡ በዚህ ጉዳይ ያልገባ ክልልም ሆነ ብሔር የለም፡፡ እኔ በጥናቴ ያየሁት አንዱ ችግር የኢኮኖሚ መዋቅሩም መበላሸቱን ነበር፡፡

አሁን ‹‹የራሴ ክልል ይሰጠኝ›› ወይ ‹‹አስተዳደር ይፈጠርልኝ›› የሚለው ጥያቄ የበዛው በዚህ የቆየ ችግር መነሻነት ነው፡፡ እኔ በጥናቴ ‹‹ፊሲካል ፌዴራሊዝም›› የሚባል ኢኮኖሚን መሠረት ያደረገ ፌዴራላዊ ሥርዓት አስፈላጊ መሆኑን ለመጠቆም ሞክሬያለሁ፡፡ ፌዴራላዊ ሥርዓቱን ለማስተካከል የኢኮኖሚ ሥርዓቱን ማቃናት አስፈላጊ መሆኑን አስቀምጫለሁ፡፡ እኔ ካልተጠቀምኩ፣ የእኔ ካልሆነ ወይም ሌሎች አይጠቀሙ የሚል ስሜትን እየፈጠረ ያለው በተዛባ ፌዴራላዊ ሥርዓት በተፈጠረው የተዛባ የኢኮኖሚ ሥርዓት ነው፡፡ ከታክስ አሰባሰብ ጀምሮ በፌዴሬሽን ምክር ቤት እስከ የሚደረገው የበጀት አመዳደብና የሀብት አጠቃቀም ድክመት የኢኮኖሚ ሥርዓቱ የፈጠረው ድክመት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የፖለቲካ ድክመትና የማስተዳደር አቅም ችግር የሚፈጥር ነው፡፡

ስለፊስካል ፌዴራሊዝም ባቀረብኩት ጥናት የክልሎችን የሀብት አሰባሰብና በጀት አደጓጎም ተመልክቻለሁ፡፡ ታክስ በአግባቡ የሚሰበስቡ ክልሎች በኢትዮጵያ አሉ፡፡ በአግባቡ ታክስ ሳይሰበስቡ ሁሌም እየተደጎሙ የሚኖሩ ክልሎችም አሉ፡፡ አንድ ቢሊዮን ብር የማይሞላ ታክስ እየሰበሰበ እስከ መቼ ድረስ ነው ታዳጊ ክልል እየተባለ የሚደጎመውና አሥር ቢሊዮን ብር በጀት እየተመደበለት የሚቀጥለው የሚለውን ወሳኝ ጥያቄ አንስቻለሁ፡፡ አንድ ቢሊዮን ብር መሰብሰብ የማይችል ክልል የአምስት ቢሊዮን ብር ስታዲየም የሚገነባ ከሆነ፣ የሌሎችን ክልል ሀብት በድጎማ ስም ወደሌላ ክልል እያዛወርክ ነው ማለት ነው፡፡ ታዳጊ ናቸው፣ በኢኮኖሚ ተጎድተው ስለነበር ነው እየተባለ ዕድገት ለማመጣጠን ተብሎ ድጎማው መጀመሩ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን አሁንም ድረስ የቀጠለ ሲሆን፣ እስከ ስንት ዓመት በዚህ መንገድ ይቀጥላል የሚለውም አልተመለሰም፡፡

የኢኮኖሚ ሥርዓቱ መስተካከል የሚችለው ደግሞ ሕገ መንግሥቱና የፖለቲካ ሥርዓቱ ሲስተካከል ነው፡፡ ክልሎች ራሳቸውን የሚችሉበት መንገድ አልተፈጠረም፡፡ የተፈጥሮ ሀብት በገጸ ምድርም፣ በከርሰ ምድርም አለን፡፡ ይሁን እንጂ የእኔ ብቻ ነው ባይነት ስለበዛ ይህንን ሀብታችንን በአግባቡ ለመጠቀም አልቻልንም፡፡ ለምሳሌ በሶማሌ ክልል ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ተገንጥለን አገር ስንሆን እንጠቀምበታለን ብሎ በግልጽ የሚናገር የፖለቲካ ቡድን እናያለን፡፡ ሕግ መውጣት አለበት፡፡ ሥርዓት ሊበጅለት ይገባል፡፡ የውኃ ሀብታችን ለመጠቀም ‹‹በወንዜና በሐይቄ አትምጣብኝ›› የሚል አለ በየቦታው፡፡ ይህን መሰሉን ችግር ለመቅረፍ የሀብት አጠቃቀም ድልድል በሕግ ማበጀት ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- የግለሰብና የቡድን መብቶችን አስታርቆ መሄድ ባለመቻሉ ዜጎች የአገር ባለቤት መሆን አቅቷቸዋል ይባላል፡፡ አሁን ባለው የፖለቲካ ሥርዓት ይህን ማስታረቅ ይቻላል ወይስ ሌላ መፍትሔዎች ያስፈልጋሉ?

ጫኔ (ዶ/ር)፡- በእኔ በኩል ሌሎች መፍትሔዎች ያስፈልጉናል ነው የምለው፡፡ የግለሰብን መብት ጥሰህ የቡድን መብትን ማስከበር ማለት መሠረታዊ ነገር መሳት ነው፡፡ የቡድን መብት ይከበር ስትል ብዙ ጊዜ የግለሰቦችን መብት እየጣስክ ነው የምትሄደው፡፡ ለምሳሌ ትግራይ ክልል ውስጥ 12 ብሔረሰቦች ይኖራሉ፡፡ አሁን ባለው አወቃቀር ግን ከትግራይ ተወላጆች ውጪ የሌሎች ብሔሮች በክልሉ የሚከበርበት ዕድል አለ ለማለት አይቻልም፡፡ የግለሰቦች መብት የሚከበርበት ካልሆነ በስተቀር ከተጋሩ ውጪ የሌሎች ጎሳዎች መብቶች ሊከበር አይችልም፡፡ ሌላው ቀርቶ በራሳቸው በክልሎች ሕገ መንግሥት ላይ ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ዕውቅና ሰጥቶ መብታቸውን የሚያከብር ሕግ ብዙም አታገኝም፡፡

ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የፖለቲካ ውክልና ሊኖረው ይገባል፡፡ ክልል ብቻ ሳይሆን በክልል ውስጥ ያሉ ሁሉም ብሔሮች፣ ማኅበረሰቦችና ነዋሪዎች በየደረጃው የፖለቲካ ውክልና ማግኘታቸው መረጋገጥ ይገባዋል፡፡ በሌሎች አገሮች ይህ ቢሠራበትም በእኛ አገር ግን ተጨፍልቋል፡፡ ለምሳሌ ድሬዳዋና ሐረርን ተመልከት፡፡ ብዙ ዓይነት ቅይጥ ሕዝብ የሚኖርባቸው ከተሞች ናቸው፡፡ ሆኖም የተወሰኑ ወገኖች አፓርታይዳዊ ሥርዓት በሚመስል ሁኔታ የፖለቲካ ውክልናውን 80 በመቶና ከዚያ በላይ ይቆጣጠሩና የሌሎቹ ጉዳይ ይተዋል፡፡ ይህ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግር ብቻ ሳይሆን፣ አንድ ቀን የሚፈነዳ የተጠመደ ችግር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ከተሞች በቻርተር መተዳደር እንዳለባቸውና ሁሉም የሚወከልበት ሥርዓት መፈጠር እንደሚገባው ምክር አቅርቤያለሁ፡፡ ሐዋሳን የመሰለች ኅብረ ብሔራዊ ትልቅ ከተማ ለአንድ ክልል በመስጠት ከተማዋን ኦና ያደረጋት ችግር ተፈጥሯል፡፡

አቅም ያላቸውና የራሳቸውን ገቢ በማመንጨት ራሳቸውን ማስተዳደር የሚችሉ አካባቢዎች ክልል መፍጠር የሚፈልጉ መሆን አለመሆኑ መጠናት አለበት፡፡ ከፌዴራል ተደጉሞ ለመኖር ወረዳ፣ ዞን ወይም ክልል ይሰጠኝ የሚለውም ራሱን መፈተሽ አለበት፡፡ ራስን ችሎ ለመቆምና በሌሎች ሳይደጎሙ የራስን ሕዝብ ማስተዳደር የመቻል አቅም እየተጠና፣ ራስን የማስተዳደር ጥያቄ ቢከበር ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን ይህ እየተደረገ አይደለም፡፡

የብሔረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት ያኔ ያጠናውና ምክረ ሐሳብ የሰጠበት ጉዳይ አቅም አለመፍጠር መቻልን ነው፡፡ እኔም የፊስካል ፌዴራላዊ አስተዳደር አዋጪነትን ሳጠና ያየሁት ብዙዎቹ አካባቢዎች ራስን በራስ ለማስተዳደር በቂ የኢኮኖሚና የመሠረተ ልማት አቅም የሌላቸው መሆኑን ነው፡፡ ለብቻቸው እየተገነጣጠሉ ክልል ወይ ዞን ከመሆን ይልቅ፣ ከሚጎራበቷቸው ማኅበረሰቦችና አካባቢዎች ጋር ተሰባስበው ጠንካራ የራስ ገዝ አስተዳደር ቢፈጥሩ የተሻለ መሆኑን ኅብረተሰቡን በመጠየቅ ያገኘሁትን ሐሳብ አስቀምጫለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በደቡብ ክልል በርካታ አዳዲስ የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄዎች እየቀረቡ ነው፡፡ እርስዎ በጥናትዎ እነዚህን ጥያቄዎችና የመፍትሔ አማራጭ የሚሉትን ሐሳብ አስቀድመው አንስተው ነበር፡፡ እነዚህ የራስ አስተዳደርና የይገባኛል ጥያቄዎች ግን በየቦታው ደም መፋሰስ ሲፈጥሩ ይታያል፡፡ ችግሩ እንዴት መቀረፍ ይችላል?

ጫኔ (ዶ/ር)፡- እነዚህ ግጭቶች የተነሱት ቀበሌ የነበረው ወረዳ፣ ወረዳ የነበረው ዞን፣ ዞን የነበረው ደግሞ ክልል ብንሆን የተሻለ ሥልጣንና በጀት እናገኛለን በሚሉ የማንነት ጥያቄዎች የተፈጠሩ ናቸው፡፡ አንዳንዱ ወገን በኃይል ጥያቄዬ ይመለሳል ብሎ በማመኑ ግጭቶቹ ደም አፋሳሽና አደገኛ ሲሆኑ ይታያል፡፡ የማንነት ጥያቄዬ ካልተከበረልኝ የሚለው ኃይል የዚያ አካባቢ ነዋሪዎችን ፍላጎት ጨፍልቆ ይሆናል ጥያቄዬ ካልተመለሰ የሚለው፡፡ በደቡብ ክልል እያየናቸው ያሉ የማንነት ጥያቄዎችና ግጭቶች አሁን ያለው ሕገ መንግሥት እስከ ቀጠለ ድረስ ይቀጥላሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከሁሉ ቀድሞ የሚሻሻልበት መንገድ በአገራዊ ምክክሩ ካልተፈጠረ ወይም ችግሩን ማብረድ የሚችል ሌላ ሰላማዊ መንገድ ካልተገኘ በስተቀር ጥያቄዎቹን ማቆም አይቻልም፡፡ በደቡብ ያለው ሁኔታ አሁን ከምናየው በላይ የሚመር ነው፡፡ ያለነው እጅግ አደገኛ ሁኔታ ላይ ነው፡፡ ጉራጌ እየጠየቀ ነው፣ ወላይታ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ካስገባ ቆይቷል፣ ሐዲያም በተመሳሳይ መንገድ ጠይቋል፣ ወደ ጋሞ ጎፋና አርባ ምንጭ አካባቢዎችና ሌሎችም እየጠየቁ ነው፡፡ እኔ በጥናቴ ዛሬ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ተብሎ የተፈጠረውን አመቺ ነው ብዬ ምክረ ሐሳብ አቅርቤ ነበር፡፡ ከጋሞ ጀምሮ ጂንካን ይዘህ ወደ ደቡብ ጫፍ ያሉ አካባቢዎችን አንድ ላይ ሰብስቦ ክልል የማድረግ ሐሳብም አቅርቤ ነበር፡፡ አሁን እያሰቡት ይመስላል፡፡ ዳውሮ በአጋጣሚ ወደ ደቡብ ምዕራብ ሄደ እንጂ፣ በዚህ አካባቢ የሚገኙ ማኅበረሰቦች የም ብሔረሰብን ጨምሮ፣ ጋሞ፣ ወላይታ የመሳሰሉት አንድ ላይ ተሰባስበው የራሳቸው አስተዳደር መፍጠር የሚችሉ፣ በተፈጥሮ ሀብት የታደሉና ተጎራብተው የሚኖሩ ናቸው፡፡ ሌላው ያቀረብኩት በደቡብ ዕንብርት የሚገኙት አላባ፣ ከምባታ፣ ሐዲያ፣ ጉራጌና አጎራባቾቻቸው አንድ የአስተዳደር ክልል ቢፈጥሩ አዋጪ እንደሚሆን አስቀምጫለሁ፡፡ እነዚህ በመሀል ደቡብ ያሉ አዋሳኝ ዞኖች በኢኮኖሚ ሊፈጥሩ የሚችሉትን ዕድገት ሐሳብ ሰጥቻለሁ፡፡ አንዱ የኢንዱስትሪ፣ ሌላው የቱሪዝም፣ የፖለቲካና የግብርና ማዕከል በመፍጠር መበልፀግ ይችላሉ፡፡ ይህ ሐሳብ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሲንሸራሸር እየሰማሁ ነው፡፡

እኔ እነዚህን ሐሳቦች ከለውጡ በፊት አጥንቼ ስጽፍ ከራሴ ፈጥሬ ሳይሆን፣ ታች ማኅበረሰቡ ዘንድ ወርጄ የሕዝቡን ስሜት በመጠየቅ የሰጠኝን ምክር መሠረት አድርጌ ነው ያስቀመጥኩት፡፡ ራሱ ሕዝቡ በየአካባቢው ወርደህ ስትጠይቀው ከዚህ ወረዳ ወይ ዞን ጋር ብንሆን አካባቢያችን ይለማል/ይለወጣል ሲል ትሰማለህ፡፡ ለምሳሌ የማጃንግ ማኅበረሰብ ከጋምቤላ ጋር ሳይሆን ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ጋር ቢሆን እንደሚሻለው ብዙ ሰዎችን ጠይቄ ነግረውኛል፡፡ ዲማ የሚባል በሚዛን ቴፒ በኩል ተኪዶ የሚገኝ የደቡብ ሱዳን ጠረፍ ከተማ አለ፡፡ ይህ አካባቢ በሚዛን ቴፒ በኩል ካሉ አካባቢዎች ጋር መደራጀትን እንደሚፈልግ ዓይቻለሁ፡፡ ይህን ደግሞ ራሱ ሕዝቡ ነው የሚያቀርበው፡፡ ቅድም ሕዝቡ ያላመነበትና ያልመከረበት ፌዴራሊዝም ስል ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከመወሰን በፊት ራሱ ሕዝቡ በየአካባቢው ሕዝበ ውሳኔ እንዲያደርግ መፍቀድ አስፈላጊ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሪፈረንደም ከዚህ ቀደም በሶማሌና በኦሮሚያ፣ እንዲሁም በአፋርና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ተሞክሮ የለም ወይ? ሪፈረንደም በማድረግና አካባቢዎችን ከአንዱ አስተዳደር ወደ ሌላው አስተዳደር በማቀያየር፣ በማንነት ጥያቄ የሚፈጠሩ ግጭትና ደም መፋሰሶችን ማስቆም እንደማይቻል በእነዚህ አጋጣሚዎች አልታየም ወይ?

ጫኔ (ዶ/ር)፡- እነዚህ ትክክለኛ ሕዝበ ውሳኔዎች አልነበሩም፡፡ የፖለቲካ ውሳኔዎች ነበሩ እላለሁ፡፡ ማኅበረሰቡ በነፃነት ምርጫው ቀርቦለት ወይም የሪፈረንደሙ ምንነት በበቂ ሁኔታ እንዲገባው ተደርጎ አልነበረም የተካሄዱት፡፡ የፖለቲካ ልሂቃኑ በመጓተትና ተፅዕኖ በመፍጠር የእነዚህን ሪፈረንደሞች ውሳኔ በማስቀየራቸው ችግሮቹን ማስቀረት አልተቻለም ብዬ እገምታለሁ፡፡ ለምሳሌ አርጎባ ብሔረሰብን አፋርና አማራ ክልሎች ብሎ ከመክፈል ይልቅ፣ ራሱን የቻለ አንድ የማኅበረሰብ ወሰን ለመፍጠር ለምን አይቻልም? በሁለቱም አቅጣጫ መጓተት ስላለ እንጂ ራሱን የቻለ አስተዳደር በሕግ መፍጠር ይቻላል፡፡ ትግራይ ክልል ለምሳሌ ከኢሮብ ማኅበረሰብ ውስጥ የተወሰኑት ከኤርትራ ጋር ብንሆን ይሻላል የሚል ስሜት አላቸው፡፡ አንድ ሕዝብ በተወሰነ አስተዳደር ክልል መኖሩ ወይም መቆየቱ እንደሚጠቅመው እንዲያውቅ ካልተደረገ አስቸጋሪ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩ እንደሚጠቅመው በተጨባጭ ካላስተማርክና ጥቅሙን በማረጋገጥ ካላሳየህ በስተቀር ተመሳሳይ ችግር ይፈጠራል፡፡

የራስ ገዝ አስተዳደር እንዲሰጠው የሚጠይቀው ማኅበረሰብ በየአቅጣጫው ብዙ ነው፡፡ በሁለቱ ጉጂዎችና በቦረና ባደረግኩት ጥናት የራስ ገዝ አስተዳደር ፍላጎት መኖሩን ዓይቻለሁ፡፡ ሞያሌ አካባቢ ሶማሌና ኦሮሚያን የሚያጋጭ የወሰን ከተማ ነው፡፡ ብዙ ብሔሮች ያሉበትና ሞቅ ያለ ንግድ የሚታይበት ከተማ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ከተማ የራስ ገዝ አስተዳደር ቢሆን ከግጭት ተላቆ ብዙ ማደግ ይችላል፡፡ በሶማሌ ክልል ከሊበን መለስ ያለው አካባቢ ከጅግጅጋ ይልቅ ለጉጂና ለቦረና የቀረበ ነው፡፡ የተነጣጠሉ አካባቢዎችን በአንድ አስተዳደር ሥር ይሁኑ ብሎ ከማስገደድ፣ የአካባቢ አስተዳደር አመቺነትን ባማከለ ሁኔታ ቢካለሉ በእጅጉ ይጠቀማሉ፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ግጭቶች በሰብዓዊ ዕርዳታ ሥራዎቻችን ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተፅዕኖና እየተከሰተ ያለውን ሥቃይ እያየን ነው›› ሆላንደር ሆላንደር፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያና የጂቡቲ ዋና...

ከበርካታ የአፍሪካ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ለአሜሪካ የቅርብ ወዳጅ እንደሆነች ይነገርላታል፡፡ ክፍለ ዘመንን የተሻገረው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ሰሞኑን ዲፕሎማቲክ ግንኙነት የጀመሩበትን 120ኛ ዓመት ክብረ በዓላቸውን...

‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖሩንን እንቅስቃሴዎች ሊያግዙ የሚችሉ ተቋማት ያስፈልጉናል›› ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ/ር)፣ የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያንና የምሥራቅ አፍሪካን የፋይናንስ ተቋማት መሠረት በማድረግ በየዓመቱ የሚካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ፣ በበርካታ አጀንዳዎች አማካይነት በተለይ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓቶችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ጎን...

‹‹ኢትዮጵያ ብዙ ፈተና እየገጠማት ቢሆንም ከፈተናው ውስጥ ቀስ እያልን እንወጣለን ብዬ አስባለሁ›› ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር

ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ መካሄዱን ተከትሎ  በቀደሙት ጊዜያት ከተቋማዊ ስሙ ባለፈ በሚያከናውናቸው ተግባራት፣ ተቋሙን ይመሩት በነበሩ ኮሚሽነሮች፣ እንዲሁም በአጠቃላይ ተቋማዊ ባህሪው ከአስፈጻሚው...