የፍትሕ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት በቅርቡ የሰጡት መግለጫ የማንነት ጥያቄን የተከተለ ቀውስን በጉልህ የሚያወሳ ነበር፡፡ ለምሳሌ በደቡብ ክልል የአሪ ብሔረሰብ ከ16 ብሔረሰቦች ጋር አንድ የአስተዳደር ዞን እየተጋራ ለረዥም ዓመታት ኖሯል፡፡ ይሁን እንጂ ጂንካ ከተማን በመጠቅለል ከሌሎች ብሔሮች ተነጥሎ የራሱ የዞን አስተዳደር መመሥረት ይገባዋል ያሉ የብሔሩ ተወላጆች ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር ጥያቄው መቅረቡ ምንም ኃጢያት እንደሌለው ነው በመግለጫው ያመለከተው፡፡ የፍትሕ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ፈቃዱ ፀጋ እንዳመለከቱት ከሆነ፣ ጥቂቶች ጥያቄውን በኃይልና በአመፅ ለማስመለስ ነበር ጥረት ያደረጉት፡፡ ከፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምርያ ኃላፊ አቶ ሙሊሳ አብዲሳ ጋር በመሆን በሰጡት መግለጫ፣ የአሪ ብሔረሰብን የማንነት ጥያቄ ለማስመለስ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የሕግ አካላት፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ወጣቶች ጭምር በወንጀልና በብጥብጥ ውስጥ ተሳታፊ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
የዞኑ አስተዳዳሪዎችና የሥራ ኃላፊዎች ሸኮን (ወጣት) የሚል ኢመደበኛ አደረጃጀት በመፍጠር በጂንካ ከተማና በዙሪያዋ ብጥብጥ መጀመራቸውን፣ በዋናነት ጥያቄያቸው እንዳይመለስ እንቅፋት ሆኑብን የሚሏቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎችን ዒላማ በማድረግ ጥቃት ማድረሳቸውን፣ በተለይ ዋና ጠላቶች ተብለው የአማራ ተወላጆች ጥቃት እንደተከፈተባቸው የፍትሕ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት መግለጫ ያስረዳል፡፡
በጂንካና በዙሪያዋ የአሪ ብሔረሰብ የማንነት አስተዳደር ጥያቄን በተንተራሰው የጥቃት ዘመቻ የሰው ሕይወት ባይጠፋም 1,550 ዜጎች መፈናቀላቸው፣ 46 ቤቶች ተጎድተው 144 ቤቶች መቃጠላቸው፣ አንድ መስጊድ መቃጠሉ፣ 232 ንግድ ቤቶች መዘረፍና መውደማቸው፣ በአጠቃላይ ከ247 ሚሊዮን ብር በላይ የንብረት ውድመት መድረሱን ነው ባለሥልጣናቱ በመግለጫቸው የዘረዘሩት፡፡
በዚህ የማንነት ጥያቄን ተገን ባደረገ አመፅና ብጥብጥ ይህ ሁሉ ውድመት ሊደርስ የቻለው ደግሞ፣ የአካባቢው ባለሥልጣናት የፌዴራል ፀጥታ ኃይሎች ወደ ቦታው እንዳይገቡ በመከልከላቸው ነው ተብሏል፡፡ የመንግሥት ካዝናን ገልብጠው የሕዝብ ሀብትና ንብረትን ለአመፅ ተግባሩ እንዲውል የአካባቢው ባለሥልጣናት ማድረጋቸውም ተነግሯል፡፡ ይህ በተጠና፣ በተደራጀና፣ የጥቃት ሰለባዎችን በማንነታቸው እየመረጠ የተካሄደ ጥቃት በፀጥታ አካላት ርብርብ ባይበርድ ኖሮ ጉዳቱ ከዚህ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ነበር የፍትሕ አካላቱ በመግለጫቸው ያወሱት፡፡
‹‹ወንጀል ማንንም አይወክልም፡፡ ወንጀል የሃይማኖት ቡድንም ሆነ ብሔር የለውም፡፡ ሚዲያዎች ወንጀል ሲፈጸም የምትዘግቡትን ያህል ወንጀለኞችን ለሕግ ተጠያቂ ስናደርግም ሒደቱን ተከታትላችሁ ዘግቡ፤›› በማለት ነበር አቶ ፈቃዱ በመግለጫው ወቅት የተናገሩት፡፡ ከሁሉም ጎልቶ የሚሰማውና መልስ ያላገኘው ጥያቄ ግን የማንነትም ሆነ የአስተዳደር ጥያቄዎች በኢትዮጵያ ለምን ብጥብጥና ደም መፋሰስ የሚያስከትሉ ሆኑ የሚለው ጉዳይ ይመስላል፡፡
የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥትና የፌዴራል ሥርዓተ መንግሥቱ የብሔር ማንነት ጥያቄን የመለሰ ነው ቢባልም፣ የማንነት ጥያቄ ግን እስካሁንም ለረዥም ዓመታት እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ዕድል የሰጠ ነው ቢባልም፣ ነገር ግን የአስተዳደር ጥያቄ በየቦታው አልተቋረጠም፡፡ ይህ ጥያቄ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ መሠረት በሕጋዊ መንገድ መመለስ የሚችል መሆኑ ቢነገርም፣ ነገር ግን ውጤቱ ውድመትና ዕልቂት ሲሆን ይታያል፡፡ ይህን መሰሉን ቀውስ በዘላቂነት መቅረፍና አገሪቱን ከቀውሱ ማዳን የሚቻለው እንዴት ነው ለሚለው በርካታ ምሁራን የተለያየ ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡
‹‹እነዚህ ለዝንተ ዓለም ይዘው ሲያባሉን የቆዩ ችግሮችን መፍታት ማስቀደም አለብን፡፡ አሁን ያለውን ቀውስ በማስቆም ኢትዮጵያ ምን ዓይነት የፖለቲካ ሥርዓት ይኑራት በሚለው ላይ መምከር አለብን፡፡ ነገሮችን አርግበን እንደ ከዚህ ቀደሙ የብሔር ፖለቲካን እንከተል? ወይስ ሌላ የተለየ የፖለቲካ ሥርዓት እንፍጠር? በሚለው ላይ በሰፊው መወያየት አለብን፡፡ በተግባር ሊሆን እንደማይችል እያወቅነው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 ብሔሮች የራሳቸውን ክልል መፍጠር ይችላሉ ብለን አስቀምጠናል፡፡ በመሆኑም ቀበሌው ወረዳ፣ ወረዳው ዞን፣ ዞኑ ክልል ካልሆንኩ ማለቱ ይቀጥላል፤›› በማለት የኢዜማ መሪና የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ይናገራሉ፡፡
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አባሉና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋም ዳይሬክተሩ ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)፣ የብሔርና የዘር ፖለቲካ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ካወሳሰቡ ችግሮች አንዱ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ በደርግ፣ በአፄ ኃይለ ሥላሴ፣ በአፄ ምኒልክ፣ በዮሐንስና በቴዎድሮስ ዘመን የነበረው ፖለቲካ የዘር ጭቆና የሰፈነበት ነበር ተብሎ ተደመደመ፡፡ ለብሔር ጭቆና መልስ የሚሆነው ደግሞ የብሔር ፖለቲካ ነው ተብሎ መጣ፡፡ ይህ ከመነሻው ጀምሮ ስህተት የሆነ አረዳድና ድምዳሜ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የነበረውን የፖለቲካ ችግር የፈጠረው ብዙ ምክንያት እንዳለ እየታወቀ፣ የዘር መድሎን ብቻ ምክንያት ማድረግ ስህተት ነው በማለት የሚናገሩት ዮናስ (ዶ/ር)፣ ሰዎች የዘር ብቻ ሳይሆን ብዙ የማንነት መሠረቶች እንዳሏቸው ይጠቅሳሉ፡፡
‹‹በዚህ ባለንበት ዘመን ከ193 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገሮች ውስጥ የዘር ፖለቲካን በሕገ መንግሥት ደንግጋ የምትመራ አገር ኢትዮጵያና ኢትዮጵያ ብቻ ናት፤›› ሲሉ የሚያክሉት ዮናስ (ዶ/ር)፣ ይህም በአገር ውስጥ ለሚፈጠሩ ግጭቶችና ለችግሮች መወሳሰብ ዋና ምክንያት እየሆነ እንደመጣ ነው የጠቆሙት፡፡
የቀድሞ የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና የሕግ ባለሙያው አቶ ታረቀኝ አበራ፣ ኢትዮጵያ አሁን የገጠሟትን ቀውሶች ለማስቆም ከሕገ መንግሥት ማሻሻል ጀምሮ ብዙ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ የዘርና የማንነት ፌዴራሊዝም ይከተሉ የነበሩ እንደ ናይጄሪያና ህንድ የመሳሰሉ አገሮች ከመበተን የዳኑት ሥርዓታቸውን በማሻሻል መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
‹‹ናይጄሪያዎቹ በቢያፍራ ጦርነት ለመገነጣጠል የሚያደርስ ቀውስ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ ልክ የትግራይ ጦርነት እንደ ገጠመን በናይጄሪያ ብዙ የደም መፋሰስ ተፈጥሮ ነበር፡፡ በፌዴራሊዝም ሥርዓት ውስጥ ማዕከላዊ መንግሥቱ ጠንክሮ መውጣት አለበት፡፡ ያለበለዚያ ማንም እየተነሳ አገር ልሁን ይላል፡፡ ተራማጅ በሆነ የፌዴራል ሥርዓት ውስጥ ጠንካራ የፌዴራል መንግሥት ያስፈልጋል፡፡ ህንድም ቢሆን የማንነት ፌዴራሊዝም ነው፡፡ ነገር ግን የፍትሕ ተቋሙ፣ ፀጥታውና ፍርድ ቤቱ በማዕከላዊ መንግሥት ሥር በመሆኑ ብዙ ተጠቅመዋል፡፡ እነዚህ አገሮች ከመፈራረስ የዳኑት የክልል በሚል ጨዋታ ሳይሆን የፌዴራል መንግሥታቸውን በማጠናከር ነው፡፡ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ በሚል ጨዋታ ሳይሆን ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት በመፍጠር ነው የምንድነው፤›› በማለት ነው አሁን ኢትዮጵያ ከገባችበት ቀውስ ልትወጣ የምትችልበትን መንገድ አቶ ታረቀኝ የተናገሩት፡፡
‹‹ፌዴራሊዝም ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ለ30 ዓመታት ኢትዮጵያን የግድያ ቤተ ሙከራ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ይህን እንዲቀጥል መፍቀድ የለብንም፤›› በማለትም አቶ ታረቀኝ አክለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ምን ዓይነት የፖለቲካ ሥርዓት ይበጃታል የሚለውን ጥያቄ አሁን የሚታዩ የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄ ቀውሶች ዳግም እንዲስተጋባ እያደረጉት ነው፡፡ ፌዴራላዊ ሥርዓተ መንግሥት ወይም ያልተማከለ አስተዳደር ኅብረ ብሔራዊ ብዝኃነት ላላት ኢትዮጵያ አዋጭ ነው ተብሎ ለ30 ዓመታት ቢተገበርም፣ ነገር ግን ግጭትና ደም መፋሰሶችን እስካሁን ማስቆም አልተቻለም፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ (በተለይ ለውጡን ተከትሎ) በዋናነት በደቡብ ክልል እየተነሳ ያለው የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄ እጅግ በርካታ ሆኗል፡፡ ሲዳማ ራሱን የቻለ ክልል እንዲሆን የፈቀደው መንግሥት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልን በመፍጠር በርካታ ብሔሮች ተሰባስበው አንድ ክልላዊ መስተዳድር እንዲፈጥሩ ዕድል ማመቻቸቱን ይገልጻል፡፡ ይሁን እንጂ ልክ እንደ ሁለቱ አዳዲስ ክልሎች የራሳችን ክልል ይኑረን የሚሉ የብሔረሰብ ዞኖች አስተዳደሮች ጥያቄዎቻቸውን በተጠናከረ ሁኔታ እየገፉት ይገኛል፡፡ መንግሥት ለሲዳማና ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የሰጠውን ፈጣን ምላሽ ለሌሎች የክልልነት ጥያቄ ላቀረቡ ዞኖች እየሰጠ አይደለም የሚል ትችት ከብዙዎች ይሰማል፡፡
ከሰሞኑ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ጉባዔ ስብሰባ ሲደረግ ጎልተው ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል፣ የአስተዳደር ይገባኛል አጀንዳዎች በአግባቡ ይመለሱ የሚል ጥያቄ ይገኝበታል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ለምክር ቤቱ በሰጡት ምላሽ፣ አሁን ባለው የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ የአስተዳደር ጥያቄዎችን ረገብ ማድረግ እንደሚገባ ነበር ያሳሰቡት፡፡ ‹‹ጥያቄያችን የሞት የሽረት ጉዳይ ነው ይላል፡፡ ደግሞ መልሶ ሰላም አጥቻለሁ ይላል፡፡ አርሶ አደሩ ግን የማዳበሪያ ጥያቄ እንጂ የአስተዳደር ጉዳይ ጉዳዩ አይደለም፤›› በማለት የተናገሩት አቶ ርስቱ፣ ብዙዎቹ የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄዎች የጥቂት ፖለቲካ ልሂቃን ፍላጎት የተከተሉ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
‹‹ገበሬው ፖለቲካዊ መብቱ እስከተከበረ፣ በቋንቋው መናገርና በባህሉ መኩራት ከቻለ፣ በማንነቱ እስካልተገለለ ድረስ መልካም አስተዳደር ነው የሚፈልገው፡፡ ስንነጠል ችግሮቻችን ሁሉ ይፈታሉ ወይም መና ይወርድልናል ብለን ባናስብ ይሻላል፡፡ ቀበሌም፣ ወረዳም፣ ዞንም ሆነ ክልል ቢኮን ሀብትና ገንዘቡ በቀመር ነው የሚደርሰን፤›› ሲሉ አቶ ርስቱ አስረድተዋል፡፡
መንግሥት በተደጋጋሚ ጊዜ በደቡብ ክልል የራሳችን አስተዳደር ይሰጠን የሚሉ ጥያቄዎች እንዲረግቡ ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡ አዳዲስ የአስተዳደር ወሰኖችን በክልሉ ለመፍጠር ያመቻሉ ያላቸውን የመፍትሔ አማራጮችም በተደጋጋሚ አስጠንቶ ሲያቀርብ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህም ቢሆን ጥያቄዎቹ ሲረግቡም ሆነ ሲቆሙ አልታየም፡፡
የጌዲዮ፣ የወላይታ፣ የሃዲያ፣ የከምባታ፣ የጋሞ ጎፋ፣ የሰገን ዞኖችና ወረዳዎች ውዝግብና ጥያቄዎች አሁንም በእንጥልጥል ላይ ይገኛሉ፡፡
ከሰሞኑ ጠንከር ብሎ የመጣው ጥያቄ ደግሞ ራሳቸው ርዕሰ መስተዳድሩ የወጡበት የጉራጌ ዞን የክልልነት ጥያቄ ሆኗል፡፡ እስካሁን እንደታየው ከሆነ በደቡብ ክልል የተመለሱት የሲዳማና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ጥያቄዎችን ጨምሮ ያልተመለሱ የአስተዳደር ጥያቄዎች ጉዳቱ ይለያይ እንጂ፣ ግጭትና ደም መፋሰስን ያስከተሉ ነበሩ፡፡ ጥያቄዎቹ እየጨመሩ ከመምጣታቸው ጋር ተዳምሮ ወደፊት ምን ሊያስከትሉ ይችላሉ የሚለው ጉዳይ ደግሞ ከወዲሁ በእጅጉ እንደሚያሳስብ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡
በፌዴራላዊ አወቃቀርና በማንነት ጉዳይ ያጠኑ ምሁራን ይህ ማንነትን ተገን ያደረገ የፖለቲካ ችግር፣ ረዥም ዘመናትን የተሻገረ አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን ያወሳሉ፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችን የሚገልጥ ጥናታዊ መዘክር›› የሚል ጥናታዊ መጽሐፍ በ2008 ዓ.ም. ያበረከቱት ፍሰሐ አስፋው (ዶ/ር)፣ የማንነት ጉዳይ ከደርግ ዘመን ጀምሮ መጠናት እንደጀመረ ይናገራሉ፡፡ የብሔረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት ተብሎ በደርግ መንግሥት ስለኢትዮጵያ ብሔሮች ጥልቅ ጥናት በጊዜው መካሄዱን በመጽሐፋቸው አመልክተዋል፡፡
‹‹ምንም እንኳን የብሔረሰቦች ጥናት ቢባልም ሥራው ብዛታቸውን፣ ዓይነታቸውንና አሠፋፈራቸውን ብቻ አጥንቶ ለማቅረብ ሳይሆን በሕዝብ ፈቃደኛነት ላይ የተመሠረተ ዘለቄታ ያለው የአስተዳደር ክልልና ሕገመንግሥት ለመንደፍ እንዲውል›› ተብሎ የብሔረሰቦች ጥናት ተቋም ጥናት በባለሙያዎች መካሄዱን ፍሰሐ (ዶ/ር) በመጽሐፋቸው መግቢያ ከትበዋል፡፡
ደርግ ወድቆ በኢሕአዴግ ሲተካ ያልተማከለ አስተዳደር የሰፈነባት ኅብረ ብሔራዊ ብዝኃነትን ያከበረች አገርን የመፍጠሩ ጉዳይ ዋና አጀንዳ ሆኖ ሲመጣ፣ በሕዝቦች ስምምነትና በጋራ መግባባት አሁን ያለው የፌዴራላዊ ሥርዓተ መንግሥት ተፈጠረም ተባለ፡፡
ይሁን እንጂ ስለዚሁ ፌዴራላዊ አስተዳደር በማጥናት ‹‹የዘር ፖለቲካና የቋንቋ ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ›› የሚል መጽሐፍ በ2012 ያበረከቱት ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) እወክላቸዋለሁ የሚላቸውን የብሔር ተወካዮችንም ይሁንታ ያላገኘ ሥርዓት ነበር ሲሉ ያስቀምጡታል፡፡
‹‹የፊስካል ፌዴራሊዝምን ወይም ኢኮኖሚን መሠረት ያደረገ ፌዴራላዊ አስተዳደር ኢትዮጵያ እንደሚያዋጣት አጥንቻለሁ›› ሲሉ የሚናገሩት ጫኔ (ዶ/ር) አሁን ያለው ፌዴራላዊ አስተዳደር በደርግ ዘመን ተጠንቶ የቀረበውን ምክረ ሐሳብ ያልተቀበለና የዜጎችን ይሁንታ ያላገኘ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡
ከሀብት አጠቃቀም፣ አሰባሰብና በጀት አመዳደብ ጀምሮ ፌዴራላዊ መዋቅሩ የዜጎችን ተንቀሳቅሶ የመሥራት፣ ሀብት የማፍራትና የመነገድ መብት በሚያከብር መንገድ እንዲደራጅ ይመክራሉ፡፡ ‹‹የዜጋ መብት ሳይከበር እንዴት የቡድን መብት እናስከብራለን ይባላል?›› ሲሉ የጠየቁት ጫኔ (ዶ/ር) ዜጋ የአገሩ ባለቤት መሆን አቅቶትና በየቦታው በሚፈነዳ የአስተዳደር ጥያቄ ሕይወት እየተቀጠፈ፣ ይህን ችግር የፈጠረውን ፌዴራላዊ ሥርዓትና ሕገ መንግሥት አለመቀየር ትልቅ አገራዊ አደጋ ነው ሲሉም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በቅርብ ጊዜ በደቡብ ክልል የተስፋፋውን የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄ በተመለከተ ጥያቄ ቀርቦላቸው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ‹‹ጥያቄዎቹ በአብዛኛው ለሥልጣን ወይም ለገንዘብ ቅርምት›› በሚል የሚቀርቡ መሆናቸውን እንደተናገሩ ይታወሳል፡፡
ከሰሞኑ ይህንኑ ጥያቄ በተመሳሳይ ያስተናገዱት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ፣ ‹‹ክልል እንሁን እያሉ የዓመት በጀታቸውን በአምስት ወራት ይቀራመታሉ፤›› በማለት ነበር የአስተዳደር ይገባናል ጥያቄዎችን የተቹት፡፡
በፌዴራላዊ አስተዳደሩ ላይ ጉድለቶቹን ያጠኑት ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) ግን ከፊስካል ወይም ከኢኮኖሚ ፌዴራሊዝም እኩል ለአስተዳደራዊ አመቺነት የሚሆኑ እርሾዎችን መፈለግ እንደሚገባ ነው ያስረዱት፡፡ ራስ ገዝ አስተዳደር አመቺ ለሚሆንባቸው አካባቢዎች ራስ ገዝ አስተዳደር መፍጠርን አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመው፣ ፌዴራላዊ መዋቅሩ ዘር ወይም ቋንቋን ብቻ ሳይሆን አስተዳደራዊ አመቺነትንም ያማከለ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ እንደ አንቀጽ 39 ያሉ መገንጠልና መለያየትን የሚያበረታቱ ሕጎችን የያዘ ሕገ መንግሥት በአገሪቱ እስከሰፈነ ድረስ ይህ የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄ ሊቋረጥ እንደማይችልና በዚህ የተነሳ ግጭቶች ተባብሰው አገሪቱ መፍረሷ የማይቀር አደጋ መሆኑን ነው ግምታቸውን የተናገሩት፡፡