Tuesday, November 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኦሮሚያ ባንክ የኤልሲ ጥያቄዎችን በኦንላይን መፈጸም ሊጀምር ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኦሮሚያ ባንክ የብድርና የሌተር ኦፍ ክሬዲት ጥያቄዎችን በኦንላይን በራሱ መፈጸም እንዲችልና ተያያዥ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ግዥ ከሁለት ቴክኖሎጂ አቅራቢ ኩባንያዎች ጋር ተፈራረሙ፡፡

ባንኩ ባለፈው ሐሙስ ስምምነቱን በማስመልከት እንዳስታወቀው፣ የባንኩን የአገልግሎት አሰጣጥ ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ የሚያሸጋግረውና ለአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ዕድገት ጉልህ ሚና የሚጫወተውን፣ የተቀናጀ የአገልግሎት ማዕቀፍ መስጠት የሚያስችል የኦምኒ ቻናል የዲጂታል ባንኪንግ ቴክኖሎጂ፣ ዓለም አቀፍ የሲአር2 የዲጂታል ባንኪንግ ቴክኖሎጂና አገር በቀሉ ሞጌታ ቴክኖሎጂ ከተባሉ ኩባንያዎች ነው፡፡

ይህ ትልቅ ኢንቨስትመንት የሚጠይቀው የኦምኒ ቻናል የዲጂታል ባንኪንግ ቴክኖሎጂ በጥቂት ወራት ውስጥ ተሠርቶ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር፣ ባንኩ አጠቃላይ የክፍያ ሥርዓት በእጅጉ የሚያግዝ መሆኑንም ባንኩ ገልጿል፡፡

የኦምኒ ቻናል የዲጂታል ባንኪንግ ቴክኖሎጂ ከዚህ በፊት በናሽናል ኦምኒ ቻናል ቴክኖሎጂ ሲሰጡ የነበሩ የክፍያ አማራጮችን፣ ወደ አንድ ቋት አቀናጅቶ በመምጣት አገልግሎቱን ፈጣን፣ ዘመናዊና ምቹ እንደሚያደርገውም ተጠቁሟል፡፡

‹‹ይህ የዲጂታል ባንኪንግ ቴክኖሎጂ ለደንኞቻችን የፍጆታ ክፍያዎችን ከማሳለጥ ባለፈ፣ ከባንክ ውጪ ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ወደ ባንክ ኢንዱስትሪ የማምጣት ትልቅ አቅም አለው ተብሎ ይታመናል፤›› ተብሏል፡፡ በተለይም የባንኩ ቅርንጫፎች ባልደረሱበት የገጠሩ ክፍል ለአርሶ አደሮችና ለአርብቶ አደሮች በቀላሉ ተደራሽ በመሆኑ፣ ፈጣን የባንክ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ይሆናል፡፡ በተጨማሪም አርሶ አደሩ ለግብርና ግብዓትና መሰል ወጪ የሚያስፈልጉን አነስተኛ ብድሮችን በኦንላይን እንዲያገኙ ቴክኖሎጂው ትልቅ ዕገዛ እንደሚያደርግ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ተፈሪ መኮንን ገልጸዋል፡፡

‹‹ይህ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራውና በአገር አቀፍ ደረጃ የወጣውን የናሽናል ዲጂታል ፔይመንት ስትራቴጂ ለማሳካት በእጅጉ ያግዛል፤›› ያለው የባንኩ መግለጫ፣ ቴክኖሎጂው አገራችን እየተፈተነችበት ያለውን ውጭ ምንዛሪ እጥረት ከመቅረፍ አንፃርም በጎ አስተዋጽኦ ያበረክታል ይላል፡፡

ድንበር ዘለል ግብዓቶችና የውጭ ምንዛሪ ግኝት ቴክኖሎጂ በቀጥታ ከውጭ የሚላከውን ገንዘብ ያለምንም አስተላላፊ ድርጅቶች ጣልቃ ገብነት ወደ ባንኩ ገቢ በማድረግ፣ ለተጠቃሚው የሚመጥነውን የአገልግሎት እንደሚያገኝ የተገለጸ ሲሆን፣ በተለይ የባንኩ የተለያዩ አገልግሎቶች በዘመናዊ መንገድ ለመስጠት የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡ በተለይ እስካሁን በኦንላይን ያልተሞከሩ የባንክ አገልግሎቶች በዚህ ቴክኖሎጂ ዕውን ይሆናል የሚል እምነት ያለው ኦሮሚያ ባንክ፣ ከእነዚህም መካከል የብድርና የሌተር ኦፍ ክሬዲት አገልግሎት በቀጥታ በኦንላይን አገልግሎት የሚሰጥባቸው ይሆናል ተብሏል፡፡  

ከዚህም ሌላ የዲጂታል ባንኪንግ ቴክኖሎጂ የባንኩን የውስጥ አሠራርም በእጅጉ የሚያዘምን፣ እንዲሁም የባንኩ ደንበኞች ቅርንጫፍ ሳይሄዱ አገልግሎቶችን በማንኛውም ጊዜና ቦታ በኦንላይን በራሱ መፈጸም የሚያስችል ዕድል ይፈጥራል ተብሏል፡፡

እንደ ባንኩ ፕሬዚዳንት ገለጻ፣ የኦምኒ ባንኪንግ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ከማንኛቸውም የአገራችን ባንኮች ከሌላ ሦስተኛ ወገን ጋር በ‹‹ፔይመንት ጌት ዌይ›› ጋር በቴክኖሎጂ በመታገዝ በማንኛውም ክፍያ ከየትኛውም ባንክ መክፈል የሚያስችል ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው የፍጆታ ክፍያውን መክፈል ፈልጎ ኦሮሚያ ባንክ ሒሳብ ባይኖረው እንኳን፣ ደንበኛው ሒሳቡን ለሌላ ባንክ በመጠቀም የፍጆታ ክፍያውን መክፈል የሚችልበት ዕድል ይፈጥራል፡፡

ይህ ስምምነት የቴክኖሎጂ ግዥ ብቻ ሳይሆን እሴት የሚጨምር የአጋርነት ስምምነትም ይጨምራል፡፡ በመሆኑም ተግባሩ የባንኮችን የዲጂታል ባንኪንግ ቴክኖሎጂ አቅም መገንባት ብቻ ሳይሆን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ አቅማችንን ያጠናክራል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች