Tuesday, December 5, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ለተቋማት ግንባታ ትኩረት ሳይሰጥ ውጤት መጠበቅ ከንቱ ልፋት ነው!

ኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ታሪክ ያላት አገር እንደሆነች ቢነገርም፣ በዕድሜዋ ልክ የሚመጥን የአገረ መንግሥት ግንባታ ባለመከናወኑ ምክንያት ለበርካታ ችግሮች የተጋለጠች ሆናለች፡፡ ጠንካራ አገረ መንግሥት እንዲኖር ከሚረዱ አስፈላጊ ግብዓቶች ውስጥ የተቋማት ግንባታ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ መንግሥት ሥራውን በአግባቡ እንዲመራ ከሚያግዙ መንግሥታዊ ተቋማት በተጨማሪ የዴሞክራሲ ተቋማት የሚባሉትም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ መንግሥት የሚባለው አካል የአገር መከላከያ ሠራዊትን፣ ብሔራዊ ደኅንነትን፣ ፖሊስን፣ ዓቃቤ ሕግን፣ ፍርድ ቤትንና የመሳሰሉትን አካላት ሲያደራጅ የአገሪቱን ሕግ መሠረት በማድረግ መሆን አለበት፡፡ ሕገ መንግሥት በሕዝብ ይሁንታና ፈቃድ በፀደቀባቸው አገሮች የመንግሥት ሦስቱ ቅርንጫፎች ማለትም ሕግ አውጭው፣ ሕግ ተርጓሚውና ሕግ አስፈጻሚው በእርስ በርስ ቁጥጥርና መናበብ ስለሚመሩ ተቋማት የማንም መጫወቻ አይሆኑም፡፡ አስፈጻሚው አካል የሚያደራጃቸው ተቋማት በሕጉ መሠረት ብቻ ስለሚመሩ፣ ማንም እየተነሳ ፍላጎቱን የሚያስፈጽምባቸው መሣሪያዎች አይሆኑም፡፡ ሕግ ባለበት አገር ሕገወጥነት የበላይ ሆኖ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አይጣሱም፡፡ የመንግሥት ዋና ሥራም የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት መጠበቅ ይሆናል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ብዙዎች የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ደጃፋቸው ላይ ዓላማቸውና ራዕያቸው ባሸበረቁ ሰሌዳዎች በግልጽ ቢሠፍርም፣ ውስጣቸው ሲገባ ያለውን ጉድ የሚያውቁት አገልግሎት ፍለጋ ሄደው ፍዳቸውን የሚያዩ ዜጎች ናቸው፡፡ ከተራ ጉዳይ ማስፈጸሚያ ጉቦ ጀምሮ በብልሹ አሠራሮቻቸው ተገልጋዮችን የሚያማርሩ ተቋማት፣ ከአመራር ጀምሮ እስከ አገልጋዮች ድረስ የሚስተዋልባቸው ኋላቀርነት ለዘመኑ የሚመጥን አይደለም፡፡ መሪነት በአርዓያነት አመራር መስጠት መሆኑን የማይረዱና በብሔርና በፖለቲካ ወገንተኝነት የተሰባሰቡ ኃይሎች የተከማቹባቸው ደካማ ተቋማት፣ አገርን በጠራራ ፀሐይ የሚዘርፉ ወረበሎች ጭምር የሚርመሰመሱባቸው ለመሆናቸው እማኝ መጥራት አስፈላጊ አይሆንም፡፡ በተደጋጋሚ ስለተቋማት ግንባታ አስፈላጊነት ማሳሰቢያ ቢሰጥም፣ ተቋማቱ የታለመላቸውን ግብ እንዲያሳኩ ሳይሆን የግለሰቦች መፈንጫ እንዲሆኑ የተፈለገ ይመስል አዳማጭ የለም፡፡ የመንግሥት ዕርካብ የጨበጡትም ሆነ የሌሎች የፖለቲካ ተዋንያን ትኩረት ሥልጣን እንጂ፣ የተቋማት ግንባታ አስፈላጊነት ላይ ሊሆን አልቻለም፡፡   

የአገርን ህልውና ለማፅናት የተቋማት ግንባታ አስፈላጊነት አጠራጣሪ አይደለም፡፡ የተቋማት ግንባታ ጉዳይ ሲነሳ ትኩረት መስጠት ካልተቻለ፣ የግለሰብ ባለሥልጣናትን መረን የለቀቁ ድርጊቶችን ማስቆም አይታሰብም፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የካቢኔ ሚኒስትሮች፣ የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ የከተማ ከንቲባዎችና በተለያዩ ኃላፊነቶች የተሰየሙ ሹማምንት ሥራቸውን በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መወጣት የሚችሉት ጠንካራ ተቋማት ሲኖሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የዘመናዊ መንግሥት ግንባታ ከተጀመረ ወዲህ የግለሰቦች ተክለ ሰብዕና ብቻ ገዝፎ የወጣው፣ ለተቋማት ግንባታ የተሰጠው ትኩረትም ሆነ ቁርጠኝነት እዚህ ግባ የማይባል በመሆኑ ነው፡፡ መንግሥታዊ ተቋማት በጠንካራ መሠረት ላይ ባለመገንባታቸው፣ እጅግ በጣም ጥቂት ከሚባሉት በስተቀር የግለሰቦችና የተደራጁ ቡድኖች መጫወቻ ከመሆን የዘለለ ሚና አልነበራቸውም፡፡ የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ደኅንነት፣ ፖሊስ፣ ፍርድ ቤትና ሌሎች የፀጥታና የፍትሕ አካላት የሕዝብ አገልጋይ መሆን የሚችሉት ተቋማዊ ጥንካሬ ኖሯቸው በነፃነት ሲደራጁ ነው፡፡ ይህ ዕውን መሆን የሚችለው መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችና የአገር ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ ወገኖች ተሳትፎ ሲታከልበት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ያለችበት ውጥንቅጥቅ ራሱን የቻለ ታሪካዊ ዳራ እንዳለው መረዳት ሳይቻል፣ በጊዜያዊና በአጣዳፊ ጉዳዮች ላይ ብቻ በመንተራስ በሁሉም ወገኖች የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ወይም የሚቀርቡ የመፍትሔ ሐሳቦች የተቋማት ግንባታን ጉዳይ የዘነጉ ይመስላሉ፡፡ በአገራዊ ምክክሩም ሆነ በሌሎች ግንኙነቶች ትልቅ ግምት ከሚሹ ጉዳዮች መካከል አንዱ የተቋማት ግንባታ መሆን ካልቻለ፣ ሕዝብና አገርን እያስጨነቁ ያሉ ሥጋቶችን ለመቅረፍ አዳጋች ይሆናል፡፡ ሰዎች በነፃነት እየተንቀሳቀሱ መኖር የሚችሉት ሕግ ሲከበርና ሕግ አስከባሪ ተቋማትም ሲጠናከሩ ነው፡፡ ዜጎች መንግሥታዊ አገልግሎቶችን በሥርዓት ማግኘት የሚችሉት ተቋማቱ ሕግ አክብረው የሚሠሩበት ተቋማዊ ጥንካሬ ሲኖራቸው ነው፡፡ ተሿሚዎች በሕግ የተሰጣቸውን ሥልጣን በአግባቡ ሊሠሩበት የሚችሉት ተቋማቱ ከሕግ ውጪ ዝንፍ እንዳይሉ አቅሙ ሲኖራቸው ነው፡፡ በሥልጣን መባለግ፣ ዝርፊያ፣ ማናለብኝነትና ሥርዓተ አልበኝነት የሚሰፍኑት ተቋማቱ ሲሽመደመዱ ነው፡፡ ተቋማት ብቁ ሆነው በጠንካራ ቁመና ላይ እንዲገኙ ጥረት ሳይደረግ፣ ተሿሚዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ውጤት ይገኛል ማለት ዘበት ነው፡፡ በሥልጣን መባለግና ሕዝብን መናቅ ሙያ የሚሆነው፣ ለተቋማት ግንባታ በተሰጠ ዝቅተኛ ምልከታ መሆኑን መተማመን ይገባል፡፡

ተራው ዜጋም ሆነ ልሂቃኑ ስለተቋማት ግንባታ ጉዳይ በሚገባ ግንዛቤ ሳይዙ ግለሰቦች ላይ የሚያተኩሩ ከሆነ፣ ሥልጣን በአጋጣሚ እጃቸው የገባ ሁሉ ለሕግ የበላይነትም ሆነ ለፍትሕ የሚኖራቸው ዕሳቤ ከደረጃው የወረደ ይሆናል፡፡ የተቋማት ግንባታ አስፈላጊነት ላይ መግባባት ሳይኖር ሲቀር፣ አስፈጻሚው አካል ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚፈልገው በተመቸው መንገድ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነው የመንግሥት አሠራር ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት እንዲኖርበት ለተቋማት ግንባታ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠት አለበት የሚባለው፡፡ ከዚያ በመለስ ግን የአገሪቱ ተቋማት ከዘመናት ድብርታቸው ውስጥ ሳይወጡ፣ ብቃት ያላቸው አመራሮችና ባለሙያዎች ወደ ጎን ተገፍተውና ለሕግ የበላይነት የሚሰጠው ክብር በወረደበት ሁኔታ ውስጥ ውጤት መጠበቅ ከስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ አለመሆንን ያሳያል፡፡ እያንዳንዱ መንግሥታዊ ተቋምና የሚመራው ተሿሚ በሕግ የተሰጠው ኃላፊነትና ተጠያቂነት ተረስቶ፣ ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት እየተንሰራፋ ያለው ከተቋማት ግንባታ ይልቅ ግለሰባዊ ተክለ ሰብዕና ሰፋ ያለ ቦታ ስለተሰጠው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አንድ ችግር ሲከሰት ከክስተቱ ይልቅ የግለሰቦች ጉዳይ ጎልቶ ይሰማል፡፡

በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ፍትሕ እንደ ሸቀጥ እየተቸበቸበ ነው ሲባል ለብዙዎች ቀልድ ሊመስል ይችላል፡፡ የደረሰባቸው ግን ሕመሙን ያውቁታል፡፡ መብታቸውን በአግባቡ ማግኘት ያለባቸው ዜጎች በጉልበተኞች ከሕግ ውጪ ሲንገላቱ፣ ንብረታቸውን ሲቀሙ፣ ሕይወታቸውን ሲያጡና ተስፋቸው ሲጨልም ሕግ ሊከላከልላቸው የማይችለው ተቋማቱ ስለተሽመደመዱ ነው፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማት የሚባሉት እንደ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በነፃነትና በገለልተኝነት ሥራቸውን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሌሎች በሕግ የተቋቋሙ መንግሥታዊ ተቋማትም በሕጉ መሠረት በተሰጣቸው የሥልጣን ወሰን ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ ብቃት ባለው አመራር፣ በሠለጠነ የሰው ኃይል፣ በከፍተኛ ሥነ ምግባርና ዘመኑ ባፈራቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ታግዘው መሥራት መቻል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ተቋማት ከአምባገነኖች፣ ከዘራፊዎችና ከሥርዓተ አልበኞች መፅዳት የሚችሉት ለዘመኑ አስተሳሰብ ብቁ ሆነው ሲደራጁ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው ፋይዳ ቢስ እንቅስቃሴ ለአገር አይጠቅምም፡፡ ለተቋማት ግንባታ ትኩረት ሳይሰጥ ውጤት መጠበቅ ከንቱ ልፋት ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...

በሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ የታየው ተሞክሮ በሌሎች ምርቶች ላይም ይስፋፋ!

ሰሞኑን በኢትዮጵም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ግዙፍ ስለመሆኑ የተነገረለትን የለሚ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...