Thursday, December 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከትግራይ ውጭ የሚገኙ የክልሉ ግብር ከፋዮች ግብር በፌዴራል መንግሥት ሊሰበሰብ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ትግራይ ክልል ውስ በፌዴራልና በክልል ታክስ ከፋይነት የተመዘገቡ፣ ነገር ግን አሁን ከትግራይ ክልል ውጪ የሚገኙ ግብር ከፋዮች፣ መክፈል ይገባቸው የነበረውን ግብር፣ አዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የገቢዎች ሚኒስቴር ሰሜን ምዕራብ ቅርንጫፍ ተገኝተው እንዲከፍሉ ሊደረግ ነው፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር በክልሉ መሰብሰብ የነበረበትን የፌዴራል ገቢ በቀጥታ የሚሰበስብ ሲሆን፣ ለክልሉ መንግሥት ገቢ መሆን የነበረበትን ግብር ደግሞ በአደራ የባንክ አካውንት እንዲቀመጥ ይደረጋል ተብሏል፡፡

ገቢዎች ሚኒስቴር ይኼንን ጊዜያዊ አሠራር በገንዘብ ሚኒስቴር ፈቃድ የዘረጋው ከትግራይ ክልል ውጪ ያሉ የክልሉ በታክስ ከፋይነት የተመዘገቡ ድርጅቶችና ግለሰቦች፣ የንግድ እንቅስቃሴያቸውን ለመቀጠል በመቸገራቸው መሆኑን፣ የሚኒስቴሩ የታክስ ማስታወቅ ዳይሬክተር ወ/ሮ ዓባይነሽ አባተ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፣ ግብር ከፋዮቹ አሁን ባሉበት ቦታ ሥራቸውን መቀጠል ቢፈልጉም፣ የንግድ ፈቃድ፣ የተሽከርካሪና የኮንስትራክሽን መሣሪያዎች ዕድሳት ማግኘት አልቻሉም፡፡

በዚህም የተነሳ ብድር ማግኘት፣ በጨረታ መሳተፍና ሌሎች መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ማግኘት እንዳልቻሉ የጠቀሱት ወ/ሮ ዓባይነሽ፣ ‹‹አንዳንዶቹ ንግድ ፈቃዳቸው ስላልታደሰ የሚከራዩበት መቸገራቸውን በማስታወቅ ቅሬታ አቅርበዋል፤›› ብለዋል፡፡ ከ100 በላይ ግብር ከፋዮች ለሚኒስቴሩ ቅሬታ እንዳቀረቡ፣ ከአቅራቢዎቹ ውስጥም አብዛኞቹ ለክልሉ መንግሥት ግብር የሚከፍሉ መሆናቸውን አክለዋል፡፡

መሥሪያ ቤታቸው ይኼንን ቅሬታ ለገንዘብ ሚኒስቴር በማሳወቅ ንግግር በኋላ፣ ግብር ከፋዮቹ በተዘረጋ ጊዜያዊ አሠራር ጊዜያዊ የታክስ ክሊራንስ እንዲያገኙና ከፈለጉ በሌላ ቦታ በግብር ከፋይነት እንዲመዘገቡ መፈቀዱን አስረድተዋል፡፡

ገንዘብ ሚኒስቴር ባለፈው ወር ሰኔ 2014 ዓ.ም. ለገቢዎች ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ፣ የትግራይ ክልልን የግብር ገቢ የመሰብሰብ ሥልጣን ያለው የክልሉ መንግሥት መሆኑን ጠቅሷል፡፡ ይኼንን ለማስረዳት የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 96 የጠቀሰው ሚኒስቴሩ፣ ‹‹ከግለሰብ ነጋዴዎችና ከክልል መንግሥት የልማት ድርጅቶች የሚሰበሰብ ገቢ የክልል ገቢ በመሆኑ፣ ግብሩን ሊጥልና ሊሰበስብ የሚችለው የክልል መንግሥት መሆኑ ግልጽ ነው፤›› ብሏል፡፡

በአንፃሩ በክልል ከሚገኙ የግል ድርጅቶች የሚሰበሰብ ግብር የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የጋራ ገቢ በመሆኑ፣ የሚጣለውና የሚሰበሰበው በፌዴራል መንግሥት እንደሆነ፣ በክልል ከሚገኙ የፌዴራል የልማት ድርጅቶች የሚሰበሰብ ገቢ የፌዴራሉ መንግሥት ገቢ እንደሆነ ደብዳቤው ያስረዳል፡፡

እነዚህ የሕግ መንግሥቱ ድንጋጌዎች የተጠበቁ ቢሆንም፣ በትግራይ ክልል የተመዘገቡ የፌዴራልና የክልል ግብር ከፋዮች በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት የሥራ እንቅስቃሴያቸውን ለመቀጠል ችግር ስላጋጠማቸው ጊዜያዊ አሠራር መዘርጋት አስፈላጊ እንደሆነ ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

በዚህም መሠረት በአዲስ አበባ ከተማ ልደታ አካባቢ የሚገኘውን የሰሜን ምዕራብ ቅርንጫፍን የመደበው ገቢዎች ሚኒስቴር፣ እነዚህ ግብር ከፋዮች የታክስ ክሊራንስ እንዲያገኙ እንደሚደረግ ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ዓባይነሽ ተናግረዋል፡፡ ለክልሉ ገቢ መሆን የነበረበትን ግብር የሚያሳውቁ ክፋዮች ገቢ የሚያደርጉበት የአደራ የባንክ አካውንት እንዲከፈት ለገንዘብ ሚኒስቴር ጥያቄ መቅረቡን አስረድተዋል፡፡ ‹‹በአደራ ነው የሚቀመጠው፣ ወደፊት ለክልሉ እንዲተላለፍ ይደረጋል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ይሁንና ሚኒስቴሩ የክልሉ ግብር ከፋዮች ምን ያህል ዕዳ እንዳለባቸው የሚያረጋግጥበት መንገድ ባለመኖሩ፣ ከፋዮቹ የሚያሳውቁትን ግብር ብቻ እንደሚሰበስብ ወ/ሮ ዓባይነሽ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የለንም ካሉም የምናረጋግጥበት ምንም መረጃ የለንም፡፡ በዚያ ደረጃም ማድረግ አንችልም፡፡ ነገሮች ሲስተካከሉ መረጃዎች በአግባቡ ይታያሉ፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ዳይሬክተሯ እንደገለጹት፣ ከፋዮቹ የታክስ ክሊራንስ ካገኙ በኋላ የሥራ ቦታቸውን አሁን ወደሚገኙበት አድራሻ መቀየር ከፈለጉ ቀደም ሲል በወሰዱት የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር በሚፈልጉት አድራሻ ምዝገባ ይከናውንላቸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር የድርጅት አድራሻ ሲቀየር የመመሥረቻ ጽሑፍ መስተካከል እንዳለበትና ቃለ ጉባዔም ማቅረብ ግዴታ እንደነበረባቸው፣ ከዚህም በላይ አድራሻ ቅያሪውን የሚፈቅደው የክልሉ መንግሥት እንደነበር ወ/ሮ ዓባይነሽ አስረድተዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ይኼንን ማድረግ እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የተመዘገቡት የፌዴራልም ሆነ የክልሉ ግብር ከፋዮች ከገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ክሊራንስ ሰርቲፊኬት የሚሰጣቸው ቢሆንም፣ ንብረት መሸጥ አይችሉም፡፡ ይኼም የሆነው አሁን የሚፈለግባቸው የግብር ዕዳ ይኑር አይኑር ማረጋገጥ የማይቻል በመሆኑ እንደሆነ በገንዘብ ሚኒስቴር ደብዳቤ ላይ ሠፍሯል፡፡

ቅሬታ ካቀረቡት ግብር ከፋዮች ውስጥ 97 ያህሉ ለክልሉ የሚከፍሉ 12 ያህል ደግሞ ለፌዴራል መንግሥት ግብር የሚከፍሉ መሆናቸውን የገለጹት ዳይሬክተሯ፣ ይኼ ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ መሥሪያ ቤታቸው የከፋዮቹን ቅሬታ ሲቀበል ስልክ ቁጥራቸውን በመያዙ እያንዳንዱን ግብር ከፋይ እየጠራ ሥራውን እንደሚያከናውን ገልጸዋል፡፡

ሚኒስቴሩ አዲስ አበባ ውስጥ የከፍተኛ ግብር ከፋዮች፣ መካከለኛ ግብር ከፋዮች፣ ምዕራብ፣ ምሥራቅና ሰሜን ምዕራብ የሚባሉ ቅርንጫፎች አሉት፡፡ እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፣ የሰሜን ምዕራብ ቅርንጫፍ የተመረጠው ከሌሎቹ ቅርንጫፎች አንፃር አነስተኛ ግብር ከፋዮችን ስለሚያስተናግድና የሥራ ቦታው ምቹ በመሆኑ ነው፡፡

ገቢዎች ሚኒስቴር በ2014 የበጀት ዓመት በ2013 የበጀት ዓመት ከተሰበሰው አጠቃላይ ገቢ የ57.4 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው 336.7 ቢሊዮን ብር ገቢ ሰብስቧል፡፡ ይሁንና ይህ ገቢ የበጀት ዓመቱ ሲጀመር ለመሰብሰብ ካቀደው 360 ቢሊዮን ብር በ23 ቢሊዮን ብር ያነሰ ነው፡፡

እንደ ሚኒስቴሩ ገለጻ፣ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአገሪቱ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሳቢያ ብዙ ተቋማት ከሥራ ውጪ በሆኑበት፣ የንግድ እንቅስቃሴዎች በተቀዛቀዙበትና በሌሎችም አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ሳቢያ ተቋማት በአግባቡ ሥራቸውን ለመሥራት የተቸገሩበት ነው፡፡ ይሁንና በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የተሰበሰበው ገቢ የተሻለ የሚባል መሆኑን ጠቅሷል፡፡

ገቢዎች ሚኒስቴር ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. የፌዴራል መንግሥት ከትግራይ ክልል በመውጣቱ፣ የ2014 በጀት ዓመትን ዕቅድ የያዘው የትግራይ ክልልን ሁኔታ ከግምት ውስጥ አስገብቶ መሆኑን ከዚህ ቀደም ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች