Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊጎንደር በከፍተኛ የውኃ ዕጦት ችግር ውስጥ በመሆኗ ሕዝቡ የዝናብ ውኃ መጠቀም ጀመረ

ጎንደር በከፍተኛ የውኃ ዕጦት ችግር ውስጥ በመሆኗ ሕዝቡ የዝናብ ውኃ መጠቀም ጀመረ

ቀን:

የጎንደር ከተማ ሕዝብ ከፍተኛ የውኃ ችግር ውስጥ እንዳለና በወር አንድ ቀን ለሰዓታት ብቻ የቧንቧ ውኃ እያገኘ እንደሆነ ታወቀ፡፡ ሕዝቡ የዝናብ ውኃ እየተጠቀመ ነው፡፡

የውኃው ችግር የተከሰተው በ1978 ዓ.ም. የተሠራውና የጎንደር ዋነኛ የቧንቧ ውኃ ምንጭ እንዲሆን በታሰበው የአንገረብ ግድብ በከፍተኛ ደለል መሞላቱ፣ እንዲሁም በደንቢያ በ2000 ዓ.ም. የተሠራው የከርሰ ምድር ውኃ ማውጫ ጣቢያ የአቅም ማነስ ምክንያት መሆኑ ታውቋል፡፡

ከአንድ ወር በፊት ሰኔ 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ከፍተኛ ዝናብ የአንገረብ ውኃ ማጠራቀሚያ ግድብ በደለል በመሞላቱ ምንም ውኃ ላይዝ እንደቻለና ይህም የግድቡን አቅርቦት ጥያቄ ውስጥ ከቶታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ዝናቡ ባይኖር የግድቡ አገልግሎት ላይኖር እንደሚችል፣ የከተማው ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ታምራት መኩሪያ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ለ20 ዓመታት እንዲያገለግል ተብሎ የተሠራው የአንገረብ ግድብ ለበርካታ ዓመታት ማገልገሉ አንደኛው ምክንያት መሆኑንም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ማገዣ ተብሎ ዘመናዊና ባለ ስምንት ትልልቅ ጉድጓዶች ያሉበት በደንቢያ የተሠራው የከርሰ ምድር ውኃ ማውጫ፣ 17,000 ሜትሪክ ኪዩብ ውኃ በቀን እንዲያመርት ታቅዶ፣ በተመረቀ በሳምንታት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከ3,000 ሜትሪክ ኪዩብ ውኃ የበለጠ ማምረት አልቻለም፡፡

‹‹ከእነዚህ አማራጮች ውጪ ምንም ዓይነት ሌላ አማራጭ ለሕዝቡ ውኃ ማቅረቢያ መንገድ የለም፤›› ሲሉ አቶ ታምራት ገልጸዋል፡፡

የከተማው አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ ጥሩዬ አታክልት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በከተማዋ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ አንደኛው ለውኃ አቅርቦት አለመጣጣም ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የውኃ ማቅረቢያ ጣቢያዎች አቅም እየተመናመነ መምጣት፣ ከከተማው የሕዝብ ቁጥር ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነው ያለው፤›› ሲሉ ወ/ሮ ጥሩዬ ገልጸዋል፡፡

የጎንደር ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ ወደ 750,000 እንደሚጠጋ የሚገመት ሲሆን፣ የውኃ ፍላጎቱም በቀን ከ70,000 ሜትሪክ ኪዩብ በላይ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ሁለቱ ዋነኛዎቹ የቧንቧ ውኃ ምንጮች በአንድ ላይ ከክረምቱ ዝናብ ጋር 13,000 ሜትሪክ ኪዩብ ውኃ ያመርታሉ፡፡ ክረምቱ አልፎ ዝናብ መዝነብ በሚያቆም ጊዜ፣ ሕዝቡ ቀጥታ ከዝናብ መጠቀም አለመቻልና የግድቡም አለማምረት ተደምሮ ከተማዋን ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚከታት ይመታናል፡፡

ከሕዝቡም ባሻገር በከተማዋ የሚገኙት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በከፍተኛ ሁኔታ መቸገራቸው ይነገራል፡፡ ጎንደር ዩኒቨርሲቲና የዩኒቨርሲቲው ሪፈራል ሆስፒታልም አንደኛው ነው፡፡

ከ20,000 በላይ ተማሪዎች ያሉት ዩኒቨርሲቲው ከጥቂት ጊዜያት በፊት ጀሪካን በመሸከም አመፃቸውን በዩኒቨርሲቲው መግለጻቸውንና የዩኒቨርሲቲውም ኃላፊዎች ከተማዋ ሙሉ በሙሉ በዚህ ችግር ውስጥ መሆኗን አስረድተው፣ ማረጋጋታቸውን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሥራት አፀደወይን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹ወደ 900 የሚጠጉ ተኝተው የሚታከሙ ሕሙማን ያሉበት ሪፈራል ዩኒቨርሲቲያችን ሆስፒታል ውስጥ የምንሰጠው አገልግሎት በከፍተኛ ሁኔታ ተስተጓጉሏል፤›› ሲሉ ዶ/ር አሥራት ሆስፒታሉ የሚያስፈልገውን ንፅህና እያገኘ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

የከተማው አስተዳደር ወደ አራት የሚጠጉ ኮሚቴዎችን በማዋቀር አስፈላጊውን መረጃ ማሠራጨትና ሀብት ማሰባሰብ ሥራዎች በመሥራት ለከተማዋ ተጨማሪ የውኃ ፕሮጀክቶች ማቀዱ ታውቋል፡፡ የዚህም ፕሮጀክቶች አካል የሆነው ከጣና ጎርጎራ ጎንደር የሚደርስ 60 ኪሎ ሜትር የሚረዝም መስመር በመዘርጋት ሲሆን፣ እስከ 2.6 ቢሊዮን ብር ይፈጃል ተብሎ ተገምቷል፡፡        

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...