ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት
የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ ዓመታት በፊት ያወጣውን የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ፡፡ ረቂቅ አዋጁ መንግሥት ከቫት ታክስ የሚሰበስብበትን መሠረት የሚያሰፋ ስለሚሆን ለውይይት ቀርቧል፡፡
በሥራ ላይ ያለው አዋጁ በ1994 ዓ.ም. ከወጣ በኋላ በ2001 ዓ.ም. እና በ2011 ዓ.ም. ለሁለት ጊዜያት መጠነኛ ማሻሻያዎች ተደርጎበት የቀጠለ ሲሆን፣ አዲስ እየወጣ ያለው የተጨማሪ እሴት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ሲፀድቅ የበፊቱን ይሽራል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር ያቀረበው ረቂቅ አዋጅ 15 በመቶ የሆነውን የቫት ማስከፈያ ምጣኔ ባለበት ሲያስቀጥል፣ አቅራቢና ሻጮች ለተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲመዘገቡ ግዴታ የሚያደርገውን ዓመታዊ የአቅርቦትና የሽያጭ የገንዘብ መጠን ወደ አምስት ሚሊዮን ብር አሳድጓል፡፡
በረቂቅ አዋጁ ላይ ከታክስ ነፃ የሆኑ አቅርቦቶችን በተመለከተ መሠረታዊ የሆነ ለውጥ ባይኖረውም፣ ከዚህ ቀደም ሙሉ ለሙሉ ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል አሁን ገደብ ተቀምጦለታል፡፡ በረቂቁ መሠረት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ቫት የማይጣልበት፣ ወደፊት በሚያወጣው መመርያ ከሚወሰን ወርኃዊ ፍጆታ ያልበለጠ ከሆነ ነው፡፡
በተመሳሳይ ከዚህ ቀደም ሙሉ በሙሉ ከቫት ነፃ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት አሁን ቅድመ ሁኔታዎች ተቀምጠውበታል፡፡ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪን ሳይጨምር፣ ከእነ ሾፌሩ ከስምንት ሰው በታች የመጫን አቅም ያላቸው ታክሲዎች፣ ተሽከርካሪዎች ማከራየት፣ ከእነ ሾፌሩ የሚሰጥ የኪራይ ተሽከርካሪ አገልግሎት፣ እንዲሁም ቱሪስቶችን የማጓጓዝ አገልግሎት ከቫት ነፃ አይሆኑም፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ከቫት ነፃ የሆነው ‹‹ኬሮሲን››፣ ረቂቅ አዋጁ ከቫት ነፃ አድርጎ ያስቀመጣቸው አቅርቦቶች ዝርዝር ውስጥ አልተጠቀሰም፡፡
ረቂቅ አዋጁ በመሠረታዊነት ያመጣው ለውጥ በኤሌክትሮኒክ የግብይት ሥርዓት ከሚከናወኑ ግብይቶች ቫትን መሰብሰብ የሚያስችል አሠራር በመዘርጋት ነው፡፡ ረቂቁ ድረ ገጽ፣ የኢንተርኔት ፖርታል፣ ጌትዌይ፣ መደብር፣ የማከፋፈያ መድረክ ወይም ሌላ ተመሳሳይ መድረክን በመጠቀም በኤሌክትሮኒክ የመገበያያ ዘዴ አማካይነት ከሩቅ የሚከናወን አቅርቦት ቫት እንደሚጣልበት ደንግጓል፡፡
የኤሌክትሮኒክ መገበያያውን ሥራ የሚያከናውነው ባለሙያ (ሰው) በኢትዮጵያ ውስጥ የንግድ ሥራ ቦታ የሌለው እንደሆነ በረቂቅ ውስጥ ሠፍሯል፡፡ ይህም ምንም እንኳን መሸጫ ሱቅ ባይኖርም፣ ውጭ ባለም ሆነ በአገር ውስጥ አቅራቢ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለ ደንበኛ የሚቀርብ አገልግሎትም ሆነ ዕቃ ቫት እንዲጣልበት ያደርጋል፡፡
በረቂቁ መሠረት የንግድ ሥራ ቦታ የሌለውን ወይም እውነተኛው አቅራቢ ተብሎ ከሚጠራው አካል አቅርቦቱን የማድረስ ሥራ (Delivery) የሚሠሩ አካላትም ቫት ይጣልባቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የንግድ ሥራ ቦታ የሌለው ሰው የሚያከናውነው የአገልግሎት አቅርቦት ተቀባይ ያልተመዘገበ ሰው ከሆነ፣ ሥራውን እንዳከናወነ ተቆጥሮ ቫቱን የሚቀበሉት አቅርቦቱን ለደንበኛ የማድረስ ሥራ የሚሠሩት አካላት ናቸው፡፡
እውነተኛው አቅራቢና የኤሌክትሮኒክ መገበያያውን ሥራ የሚያከናውነው በጽሑፍ ከተስማሙ ግን፣ ታክስ የሚከፈልባቸው አቅርቦቶች ላይ ሊከፈል የሚገባውን የተጨማሪ እሴት ታክስ የመክፈል ኃላፊነት የእውነተኛው አቅራቢ ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ላለ ደንበኛ አገልግሎቱን የሚያቀርበው አካል ከኢትዮጵያ ውጭ ከሆነ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የተጨማሪ እሴት ታክስ ወኪል መሾም ወይም ለገቢዎች ሚኒስቴር ዋስትና እንዲያቀርብ ይገደዳል፡፡ ወኪል ሆኖ የተሾመ ግለሰብም ለቫት ለመመዝገብ ማመልከቻ ማቅረብ፣ የገቢ ማስታወቂያ ማቅረብና ቫት መክፈልን ጨምሮ ወካዩ ያሉበትን ግዴታዎች የመወጣት ኃላፊነት ይጣልበታል፡፡
ውክልና የተሰጠው ግለሰብ የወከለው አካል ለሚኖርበት የተጨማሪ እሴት ታክስ ዕዳም በግሉ ተጠያቂ እንደሚሆን ረቂቁ ውስጥ ተቀምጧል፡፡
በተጠናቀቀው የ2014 በጀት ዓመት 336.7 ቢሊዮን ብር ገቢ ግብር የሰበሰበው የፌዴራል መንግሥት፣ በበጀት ዓመቱ የሰበሰበው ገቢ ካለፈው ዓመት አንፃር የ57.4 ቢሊዮን ብር ብልጫ ቢኖረውም ካቀደው በ23 ቢሊዮን ብር ያነሰ ነው፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው ከ2011 እስከ 2013 ዓ.ም. በነበሩት ሦስት ዓመታት አጠቃላይ የመንግሥት የታክስ ገቢ የ18.3 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት አሳይቷል፡፡ የታክስ ገቢ ከአጠቃላይ የመንግሥት ገቢ 79.3 በመቶ ድርሻ ያለው ቢሆንም፣ በአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ላይ ያለው ድርሻ ግን በሦስት ዓመታት ውስጥ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ በ2010 ዓ.ም. የታክስ ገቢ ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ 10.7 የነበረ ሲሆን፣ ይህ ድርሻ በ2013 ዓ.ም. ወደ ዘጠኝ በመቶ ወርዷል፡፡
በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው መሥሪያ ቤታቸው ለ2015 በጀት ዓመት ያዘጋጀውን በጀት ያቀረቡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ፣ የታክስ ገቢን ለመጨመር የሕግ ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ ተናግረው ነበር፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክስ ሕግ፣ የኤክሳይስ ታክስና የንብረት ታክስ ማሻሻያ ከሚደረግባቸው ሕጎች መካከል እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
የሚኒስቴሩ የታክስ ፖሊሲ ዳይሬክተር አቶ ሙላይ ወልዱ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ አዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ ረቂቅ አዋጅ በተቋም ደረጃ በገቢዎችና በገንዘብ ሚኒስቴር ንግግር ተደርጎበት፣ የሕግ ምሁራንና ባለሙያዎችም አስተያየት ሰጥተውበታል፡፡ ከታክስ ከፋዩ ማኅበረሰብና ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር የሚደረግ ውይይት እንደሚቀጥል አክለዋል፡፡