ሃገር
ሃገር መገኛ ናት
ሃገር የልብ ምት
ሃገር ህልውና
ደግሞም አደራ ናት
ያጌጥንባት ጦብያ
የኛዋ መለያ
አምሮባት ስናያት
በአደባባይ ደምቃ
ደስታውን በእንባ
ድሏን በፍንደቃ
ትከሻችን ሆኖ
የሰንደቅ ምሰሶ
ያነባል በፍቅር
ባንዲራዋን ለብሶ
- ቀሲስ አሸናፊ ገብረማርያም
******
እንኳን ደስ አለን!
ደሞ እንደገና
በድሉ ጎዳና
ባለመድነው መንገድ ዝላይ ገባንና
ይኸው መዝለል ያዝን መች ያቅተንና
ቀስ በቀስ እንዲሉ የእንቁላሉ ዘይቤ
በብሯ ተስቤ
ነሐሷን ደርቤ
ደሞ ለከርሞ ዓመት ነገርኩት ለልቤ
ወርቋን ለእምዬ ላመጣት አንግቤ
ቃል ገባሁ ለራሴ ቃል ገባሁ ለእምዬ
አሁን እልል በሉ ጉሮ ወሸባዬ
ወርቅም ብሩም አለን ነሐሱን መች ጥዬ
በየዓይነቱ አድርገነው አረ እናንተ ሆዬ
ሳቂልኝ ኢትዮጵያ ሳቂልኝ ሀገሬ
ከመንደር እሳቤ ወጥተሻል ለዛሬ
****
‹‹አቤቱ ስማን!››
ባለድሎቹ አትሌቶች ለተሰንበት ግደይ እና ጎተይቶም ገብረሥላሴ፣ ወርቅ ውኃ ጌታቸው እና መቅደስ አበበ ከድላቸው በኋላ በእምነታቸው መሠረት ጸሎታቸውን ሲያደርሱ ታይተዋል፡፡
- ፎቶ ድረ ገጽ
****
ጀግናዋ ጀግኖችን ስታከብር
በኦሪገን (አሜሪካ) እየተካሄደ ያለው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ሐምሌ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. ይጠናቀቃል፡፡ እስከ ትናንት በስቲያ ሐምሌ 15 ቀን ድረስ ኢትዮጵያ ባገኘቻቸው ሦስት ወርቅ፣ አራት ብር እና አንድ ነሐስ ሜዳሊያዎች አሜሪካን ተከትላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በተከታታይ ዕለታት ወርቅ በወርቅ የሆኑት አትሌቶችን ስታተጋ የነበረችው የብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኦሊምፒኗ ደራርቱ ቱሉ፣ በአትሌቶቿ ድል ደስታዋን የገለጸችባቸው መንገዶች የዓለምን ትኩረት የሳቡ፣ ሚዲያዎችም በሜዳቸው ሽፋን የሰጡበት ነው፡፡
******
‹‹ስፖርት ለወዳጅነት››
የኦሪገኑን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመከታተል ከተገኙት የተለያዩ አገሮች ደጋፊዎች መካከል ምሥራቅ አፍሪካውያኑ ኢትዮጵያና ዑጋንዳ ይገኙባቸዋል፡፡
***
የመሠናክሉ መሠናክል
በኦሪገን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የ3000ሜ መሠናክል ፍጻሜ፣ ባለፈው ሐሙስ ንጋት ላይ ተወዳዳሪዎቹ ሩጫቸውን ሲጀምሩ፣ ከመሃላቸው የገባው በቪዲዮ ይቀርፃቸው የነበረ አንድ የሚዲያ ሰው መሠናክል ሆኖባቸው ነበር፡፡