Saturday, July 13, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የከተማችን የቤት ችግር የፖለቲከኞች መደለቢያና ቁማር መጫወቻ ከመሆን ይላቀቅ

በበላይ ወልደየስ (ፕሮፌሰር)

በአገራችን የሕዝብ ቆጠራ ለብዙ ዓመታት ያልተካሄደ በመሆኑ፣ ትክክለኛውን የከተማ ነዋሪ ቁጥር በአሁኑ ጊዜ መናገር ባይቻልም፣ እ.ኤ.አ. በ2015 የወጣ ጽሑፍ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ ከሕዝቧ ውስጥ 21 በመቶ በከተማ ውስጥ እንደሚኖር፣ የከተማ ነዋሪ ዕድገትም በዓመት ከ3.8 እስከ 5.4 በመቶ እንደሆነ፣ የአዲስ አበባ ነዋሪ ቁጥር ከ2000 እስከ 2015 ድረስ በ37 በመቶ እንዳደገ ተመልክቷል፡፡ በዚህ ሥሌትም መሠረት በ2015 የአዲስ አበባ ነዋሪ ብዛት 3.8 ሚሊዮን እንደነበረ ተጽፏል፡፡ ይሄ ቁጥር ምናልባት በከተማው ውስጥ ለሚኖሩ መታወቂያ ለተሰጣቸው እንደሆነ እንጂ መታወቂያ ያልያዘ ብዙ ነዋሪ ስላለ፣ እነዚህ ቢጨመሩ ቁጥሩ በከፍተኛ ደረጃ ሊያሻቅብ ይችላል፡፡ የሕዝብ ቁጥሩን ባናውቅም አብዛኛው የከተማ ነዋሪ የመኖሪያ ቤት ችግር እንዳለበት በቀላሉ ልንስማማ እንችላለን፡፡ ችግሩ እንዴት እንደመጣ ለማወቅ፣ በኅብረተሰብ ሳይንስ ያሉ ምሁራን ጥናት ቢያቀርቡ የሚሻል ቢሆኑም፣ እኔ በአዲስ አበባ ያደግኩኝ ስለሆንኩ፣ የቤት አቅርቦትና ፍላጎት እንዴት አንደነበረ ካየሁትና ከኖርኩበት ተነስቼ መተረክ አያቅተኝም፡፡

በኢትዮጵያ የመሬት ሥሪት በጥቅሉ እስካሁን ድረስ በከተማም ሆነ በገጠር፣ በግል ይዞታና በንጉሡ/በኋላ ዘመናዊ አስተዳደር ሲመጣ በመንግሥት ነበር፡፡ በንጉሡ ጊዜ የአዲስ አበባ መሬት የተያዘው ከንጉሡ ውጪ በባለቤትነት በአብዛኛው በእቴጌ፣ በንጉሡ ልጆች፣ በመሳፍንቱ፣ በመኳንንቱ፣ በቤተ መንግሥት አገልጋዮች፣ በከፍተኛ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሹሞች ወዘተ ነበር፡፡ እቴጌ በስማቸው የመሬት ይዞታ እንዳላቸው ያወቅሁት፣ ፍል ውኃ ያለው ኢዮቤልዩ (ብሔራዊ) ቤተ መንግሥት ሲሠራ፣ ቦታው ላይ ለነበሩ ባለመሬቶች፣ ንጉሡ ራሳቸው እቴጌን በመለመን፣ ‹‹እቴጌ መስክ›› የሚባለው ቦታ ላይ ምትክ እንደተሰጣቸው፣ የመሬት ባለቤቶች ሲያወሩ በመስማቴ ነው፡፡ የእነዚህ መሬቶች የይዞታ ማረጋገጫ እንደ ዛሬው ካርታ ሳይሆን፣ የሚሰጠው ከማዘጋጃ ቤት የቦታው ባለቤት ስም፣ ቦታው የሚገኝበት ሥፍራ፣ የቦታው ስፋት በካሬ ሜትር ወዘተ የያዝ አንድ ገጽ ጽሑፍ ነበር፡፡ ኤምባሲዎች፣ መሳፍንት፣ መኳንንት፣ የሃይማኖት ተቋማት የሠሩት ቤት አንድ ራሱን የቻለ ዘመናዊ ቤት  (ቪላ)  አድርገው ሲሆን፣  ሰፊው ነዋሪ መሬትን ከመሬት ባለሀብቶች በጭሰኝነት በመመራት ወይም በመግዛት፣ በጭቃ ዛኒጋባ ቤት ሠርቶ ይኖር ነበር፡፡ እነዚህ ቤቶች ሲሠሩ በፕላን በማዘጋጃ ቤት ፈቃድ ካለመሠራታቸው በላይ መሠረታዊ ነገር እንደ መብራት ውኃና መንገድ ወዘተ ያላሟሉ በመሆናቸው አዲስ አበባን ገና ከመጀመርያዋ በፕላን ያልተሠራች በዘመናዊ ዕይታ መንደር የሆነች፣ ደቃቃ ቤቶች (Slums House) የበዙባት አደረጋት፡፡ በዚህ ዓይነት የተገነቡት የመኖሪያ ቤቶች፣ ምንም እንኳ የከተማን የመኖሪያ ቤት መሥፈርት ያሟላሉ ባንልም እንደ አገሪቱ የዕድገት ደረጃና የነዋሪው የኑሮ አቅም፣ የራሱ የሆነ ቦታና ቤት በግዥ ወይም  የኪራይ ቤት ያገኝ ነበር፡፡ የመሬት ዋጋ በንጉሡ ጊዜ በ1940 ዓ.ም. አካባቢ በአሁኑ ጊዜ ቦሌ ማተሚያ ቤት ተብሎ ከሚጠራው ሥፍራ በካሬ ሜትር አሥር ሳንቲም በቀላል ይገኝ እንደነበረ፣  የንጉሡም አገዛዝ ወደ ማክተሙ አካባቢ በ1964 ዓ.ም. በአሁኑ ሳሪስ ቀይ መስቀል ማሠልጠኛ አካባቢ በካሬ ሜትር ከ1.50 እስከ ሦስት ብር መሬት የገዛ እንደ ነበረ የሚያወሩ ምስክሮች ነበሩ፡፡ በሌላ በኩልም ከመሀል ከተማ አንስቶ እስከ ዳር ከ100 እስከ 500 ካሬ ሜትር ለጭሰኝነት መሬት ከ100 አስከ 300 ብር እና በዓመት ግብር 30 እሰከ 50 ብር ጭሰኛው ለባለ ርስቱ ይከፈል ነበር፡፡ እነዚህም ዋጋዎች የከተማው ነዋሪ ካለ ብዙ ችግር የራሱን ቤት በባለቤትነት ወይም በኪራይ እንዲያገኝ ረድተውት ነበር፡፡ በየደጃፉም ‹‹የሚከራ ቤት አለ›› የሚል ተለጥፎ ማየት የተለመደ ነበር፡፡ በዚህም የከተማ ነዋሪ ተከራይ ብዙ አቅርቦት ስለ ነበረለት በየጊዜው ለመሻሻል ቤት ስለሚቀይር ‹‹እንደ አዲስ አበባ ቤት ዕቃ ያንከራትትህ›› ይባል ነበር፡፡ እዚህ ላይ መነሳት ያለበት፣ የሚሠሩት ቤቶች አንድ የከተማ ነዋሪ ከሚኖርበት ቤት ማግኘት የሚጋባውን ግልጋሎት አለሟሟላታቸውን ወይም የከተማ መኖሪያ ቤት መሥፈርቱን ያልጠበቁ መሆናቸውን ነው፡፡ ይሄም የመጣው በዚያን ጊዜ በነበረው የነዋሪው የኑሮ ደረጃ፣ አስተሳሰብና የዕውቀት ችግር ነው፡፡ በዚህም አዲስ አበባን የገነባነው እኛ ኢትዮጵያውያን ባለን ገንዘብና ዕውቀት ነው ብለን መናገር እንችላለን፡፡ በዚህም እንኮራለን፡፡ ሌሎቹን የአፍሪቃ አገሮች ከተሞቻቸው የተገነቡት ቅኝ ገዥዎቻቸው ለራሳቸው ብለው፣ ባላቸው ሀብትና ዕውቀት የራሳቸው መሥፈርት አውጥተው ነው፡፡ እነ ናይሮቢ፣ ዳካር፣ ሌጎስ፣ ካይሮና አክራ ወዘተ ከአዲስ አበባ ያምራሉ፡፡ ንፁህ ናቸው ብሎ ማወዳደር አይቻልም፡፡  ዜጋዎቹ አልሠሩዋቸውም፡፡ ኤርትራ ከእናት አገሯ ኢትዮጵያ በነበረችበት ጊዜ አንዳንድ ሰዎች ነገሩን ሳያውቁ አስመራ ከአዲስ አበባ ንፁህ ነች ወዘተ ብለው ያወራሉ፡፡ እውነት ሊሆን ይችላል፡፡ ግን የዘነጉት አስመራ የተቀየሰችው/የተገነባቸው በጣሊያን ነው፡፡ በሰው ልብስ ማጌጡ አያኮራም፡፡ እኛ ያልተደባለቀ የአፍሪካውያን ባህልና አኗኗር ማሳያ መሆናችን ያኮራናል፡፡ በአጠቃላይ በንጉሡ ጊዜ ቤት እንደ ሰው አቅም በሽ ነበር፡፡ ከማዕድ ቤት (ኩሽና) አንስቶ እስከ ደረጃውን የጠበቀ መኖሪያ ቤት ለማግኘት ብዙም ችግር አልነበረም፡፡ አነስተኛ ኑሮ የሚኖሩ ግለሰቦች ካላቸው ቤት በመክፈል ወይም ኩሽናቸውን በማከራየት ደባል በማስገባት ይጠቀሙ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ቤቶች፣ የጋራ ሽንት ቤት፣ ኩሽና፣ ውኃና መብራት ወዘተ ነበር ያላቸው፡፡ ይሄም የመጣው ከነዋሪው አስተሳሰብ ነው፡፡ ለምሳሌ ሽንት ቤት በቤቱ ውስጥ ያለው አባወራ  ‹‹እንዴት ሚስቴ ፊት ዕዳሪ እቀመጣለሁ ብሎ ወደ ወንዝ ጠጠር ይዞ የሚሄድ፣ ወንድ ኩሽና መግባት የለበትም በማለት ከዋናው ቤት ውጭ አርቆ የማዕድ ቤት የሚሠራ ወዘተ ነበር፡፡ በአጠቃላይ በዚያን ጊዜ የነበረው የከተማ ቤት ሥሪትና አኗኗር በአሁኑ መነጽር ብዙ የጎደለው የከተማን አናናር መስፈርት የማያሟላ እንደነበረ ብረዳም ያኔ ግን የነበረውን ተቀብለን የከተማ ቤት ሥሪት ብዛት ወዘተ ላይ ጥያቄ አቅርበን ሰላማዊ ሠልፍ የወጣንበት ጊዜ ትዝ አይለኝም፡፡ ይኼም የሆነበት አከራይም ሆኑ ተከራይ ባላቸው ዕውቀትና ልምድ በአንድ ላይ ምንም ልዩነት ሳይፈጥሩ ትንሽ ክፍልም ብትኖር ተዳብለው አብረው ተባብረው ይኖሩ ስለ ነበረ እኛ በአጀንዳ ይዘነው አልወጣንም፡፡ ትዝ የሚለኝ ሁሉም እኩል እንደሚኖር የማስታውሰው፣ በአካባቢያችን አንድ በልመና የሚተዳደር ሰው አንድ ኩሽና ተከራይቶ ይኖር ነበር፡፡ ይሄ ሰውዬ ለምኖ የሚያመጣውን ፍርፋሪ ቤተሰቡን ከመገበ በኋላ የተረፈውን እንዳይበላሽበት አውጥቶ በመንደሩ መሀል ሲያሰጣው፡፡ ‹‹ፍርፋሪው ከማጓጓቱ በስተቀር››  ማንም እዚህ ለምን ታሰጣለህ ብሎ ሳይጠይቅ የአካባቢው ነዋሪ አክብሮት አብሮ ይኖር ነበር፡፡

ንጉሣዊው አገዛዝ ተወግዶ የወታደራዊው አገዛዝ ሲመጣ የነበረውን አሠራር የሚያናጋ ‹‹የከተማ ትርፍ ቤት  እና ቦታ አዋጅ›› ደነገገ፡፡ በዚህም አዋጅ የከተማ ቦታ ሁሉ የመንግሥት እንደሆነና ነዋሪው በከተማው ውስጥ በይዞታ ሊይዝ የሚችለው መሬት እስከ 500 ካሬ ሜትር  በታጠረ ቦታ አንድ ቤት ብቻ እንደሆነና የተቀረውን ትርፍ ቤት ማስረክብ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ በዚህም አዋጅ በኪራይ ላይ የነበሩ የግለሰብ ቤቶች በሁለት ተከፍለው እስከ 100 ብር የሚከራዩ አነስተኛ ቤቶች ‹‹ቀበሌ››  ከ100 ብር በላይ የሚከራዩትን ‹‹ኪራይ ቤት›› የሚባሉ ድርጅቶች ተቋቁመው እንዲያስተዳድሩ በመወሰን ለተከራዮች ተሰጡ፡፡ ይሄን አዋጅ ኢፍትሐዊ ያደረገው በአከራዮች ላይ የደረሰው ድርጊት ነው፡፡ አብዛኛው ቤት አከራዮች ያከራዩት ቤት ከአከራዩ ቤት ጋራ በልጣፊ የተሠሩ ወይም ካላቸው ቤት በደባልነት ያስጠጉ ከመሆኑም በላይ የቤት ኪራዩ  ከመቶ ብር በታች ስለሆነ ገንዘብ እያስፈለጋቸውም፡፡ ገንዘብ በማነሱ ብቻ ተከራዮቹን ውጡ ብለው አስወጡ፡፡  ተከራዮች የነበሩ በዚህ አዋጅ ቤት አልባ ሆኑ፡፡ በአዲስ አበባ ‹‹አንተ ትብስ – አንቺ ትብሺ›› ተባብሎ የሚኖረው ሕዝብ በመደብ እንዲከፋፈል ተደረገ፡፡ ለተወሰኑ ዓመታትም የሚከራይ ቤት ጠፋ፡፡ አዲስ ለሚመጣም ሆነ በአዋጁ ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች በመዲናዋ የሚያስጠልል ቤት ጠፋ፡፡ የመኖሪያ ቤት እጥረት በከተማዋ በዚህ አዋጅ ምክንያት ተጀመረ፡፡ ደርግም የመኖሪያ ቤትን ችግር ለመቅረፍ ለከተማው ነዋሪ እስከ 500 ካሬ ሜትር ቦታ በመስጠትና የባንክ ብድር በማመቻቸት ቤት እንዲሠራ አመቻቸ፡፡ ራሱም በኪራይ ቤቶች ድርጅት አማካይነት ቤት እየሠራ፣ በዕጣ ለከተማው ነዋሪ፣ በተለይ ከውጭ ትምህርታቸውን አጠናቀው ለተመለሱ ምሁራን ወዘተ ሰጠ፡፡ ይህም ቢሆን አብዛኛው አነስተኛ ገቢ ያለው የከተማ ቤት ፈላጊ በመሥፈርቱ ምክንያት ሳያሟላ በመቅረቱ ቤት ሊሠራ ወይም ከመንግሥት ሊከራይ አልቻለም፡፡ ይሄን ክፍተት ለመሙላት በንጉሡ ጊዜ የቤት ባለቤትና በደርግ ጊዜ የቤት ተከራዮች የነበሩ በድብቅ ካላቸው ቤት ላይ ክፍሎች እየቀነሱ በደባልነት እንዲሁም በግቢያቸው ውስጥ ካለው አነስተኛ ትርፍ መሬት፣ የጨረቃ ማዕድ  ቤቶችን፣ ግድግዳውን በቆርቆሮና በሰሌን በመሥራት፣ ለቤት ፈላጊዎች አከራዩ፡፡ ይሄም ቢሆን የአዲስ አበባ ነዋሪ ቁጥር በከፍተኛ ቁጥር እያሻቀበ በመምጣቱ የቤት አቅርቦትና ፍላጎት ባለመጣጣሙ  በጥቂት ዓመታት ውስጥ የቤት ችግር እየጨመረ መጣ፡፡ ደርግም ለአንድ ሰው የሚሰጠውን ቦታ በማከታተል  ከ500 ወደ 250 ቀጥሎ እስከ 150 ካሬ ሜትር ዝቅ አድርጎ እስከ አንድ ፎቅ ይሠራ በማለት ከዓለም ባንክ በ4.5 በመቶ የቤት መሥሪያ ወለድ ቢያመቻችም በጊዜው የነበሩ ቢጠቀሙም በዘላቂነት ችግሩን ሊቀርፈው አልቻለም፡፡ እዚህ ላይ መካድ የሌለበት ደርግ በተለይ ለከተማው ሠራተኛ መሬት በነፃ በመስጠት ቤት እንዲኖረው በማድረጉ የሚያመሠግኑት እንዳሉ ሁሉ፣ በሌላ በኩል በተሳሳተ ፖሊሲ ምክንያት የመደብ ትግል ፈጥሮ አብሮ የኖረውን ሕዝብ አለያይቶ የቤት ችግር ፈጥሯል ብለው የሚያማርሩት አሉ፡፡

የኢሕአዴግ  መንግሥት የትግራይ፣ የኦሮሞ፣ የአማራና የደቡብ ሕዝቦች ተወካይ ነኝ ብሎ ሥልጣን ሲይዝ ካለፉት መንግሥታት ለየት ባለ ሁኔታ ‹‹ኢትዮጵያ ያላት ሀብት መሬት ነው፡፡ እሱም የብሔሮች ነው፡፡ እነሱም በቅድሚያ ማግኘት ይገባቸዋል፤›› የሚል የኢኮኖሚ ፍልስፍና በማምጣት ብሔርተኞችን አነሳሳ፡፡ በዚህም በዋናነት በመንግሥት ሥልጣን የያዘው የትግራይ ሕዝብ ነፃነት ግንባር (ትሕነግ/ሕወሓት) በመካከል ከተማ ነዋሪ የሆኑትን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በልማት ስም እያፈናቀለ ለራሱ ደጋፊዎች የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ ሌሎቹ ድርጅቶች እንደ አቅማቸው በማዳረስ የአዲስ አበባን ቁልፍ ቦታዎችን ተቆራምቶ ዘመናዊ ቤቶች እና ፎቆች (አፓርታመት) ሠርቶ ከተማዋን አስዋብኩ አለ፡፡ በሌላ በኩል በከተማው መሀልና ዳር ገንዘብ ላለው ለቤት ፈላጊ ጥቂት የከተማ ነዋሪ በከተማው ጽሕፈት ቤት አማካይነት የጋራ መኖሪያ ቤት (ኮንዶሚኒየም)  እየሠራ ለማከፋፈል ሞከረ፡፡ እነዚህ ቤቶች ግን የታደሉት ሙሉ በሙሉ ለችግሩ ሰለባዎች ሳይሆኑ ለልማት ተፈናቃዮች፣ ለካድሬዎችና ለዘመዶቻቸው ነበር፡፡ የቤት ፈላጊዎች የከተማ ነዋሪዎች እየበዙ በመምጣታቸው ከዓመት ወደ ዓመት የቤት እጥረት እያደገ መጣ፡፡ ይሄንን አቃልላለሁ ብሎ ለምርጫ እንዲረዳው  በተለይ በ2004 ዓ.ም. ‹‹በባንክ ተመዝግቦ ለቆጠበ 20/80 እና 40/60 የሚባሉ የመኖሪያ ቤቶች በብዛት ሠርቼ እሰጣለሁ፤›› እያለ ለፈፈ፡፡ በዚህም ኢሕአዴግ ‹‹ለምርጫ  የፖለቲካ ቁማር መጫወቻ›› የከተማ ቤትን እንደመያዣ ማድረግ ጀመረ፡፡ በተለይ መሥፈርቱን የሚያሟላ ቤት ፈላጊ የከተማ ነዋሪ ወጣት ሆ ብሎ ተመዘገበ፡፡ እነዚህ ቤቶች መጠናቀቅ ሲቃረቡ የገባውን ቃል አጥፎ የኢሕአዴግ አባዜ ክንትው ብሎ ብቅ አለ፡፡ ይኸውም በዕጣ ለደርሳቸው ጥቂት በባንክ ለቆጠቡ ተመዝጋቢዎች ሲሰጥ አብዛኛው ግን ላልተመዘገቡ ካድሬዎች፣ ተፈናቃይ ለሚባሉ ገበሬዎች፣ በመሀል ከተማ ላሉ ለልማት ተነሺዎች፣ ለፓርቲ አባሎችና ለደላሎች በአጠቃላይ ለራሴ ሰዎች ለሚላቸው በመስጠት ያ በስሙ  ባንክ ከፍቶ እየከፈለ ያለ የከተማ ነዋሪ የቁማር ተብዬ ሆነ፡፡ ቤት ፈላጊው ግን ይህ ድርጊት ቢያሳዝነውም ተስፋ ሳይቆርጥ በባንክ መቆጠቡን ቀጠለ፡፡

የኢሕአዴግ መንግሥት በአመፅ ሲናጥ ለውጥ ፈላጊ ከራሱ ውስጥ በመውጣት  ‹‹የብሔር የሚለውን በጋራ ኢትዮጵያዊነት›› በሚል ፍልስፍና መጣ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ብለው የሚያቀነቅኑትም በደስታ ድጋፍ አደረጉለት፡፡ ከፍተኛ ድጋፍ ከሰጡትም በዋነኝነት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ሲሆኑ፣ ከነዚም ቤት አጦች 20/80 እና 40/60 በሚባለው ልማት ሥር በባንክ ቁጠባ እያደረጉ ያሉ ይገኙበታል፡፡ እነሱም የደገፉት ቢያንስ በስማችን ከባንክ ተወስዶ እየተሠራ ያለው የመኖሪያ ቤት እናገኛለን በማለት ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን ‹‹ቤቱ አለቀ ሊሰጠን ነው ሲሉ ያገኙት  ይሄ የተሠራው ቤት የተፈናቀሉ ገበሬዎች ሀብት ነው ማንም አይወስደውም፤›› የሚል በገጀራ የሚደገፍ አዲስ ኢሕጋዊ የከተማ አስተዳደር ቡድን መልስ ነበር፡፡ ይሄም ድርጊት ብዙዎቹን እንዳስቆጣ ከመታመኑም በላይ ለብዙዎቹ አዲስ የሆነ ክስተት ‹‹አዲስ አበባ በሁለት አስተዳዳር ማለትም በከተማው የብልፅግና ፓርቲና በሕገወጥ መንገድ በፓርቲው ተሸሽገው ያሉና ከውጭ ግለሰቦች ተከፋፍለው የሚያስተዳድሯት መሆኑን እንዲያምኑ አደረጋቸው፡፡ ለዚህም ምክንያት የሆናቸው ሁለቱ አስተዳደር በየፊናቸው ገንዘብ በመቆጠብ ቤት ለማግኘት ተራ እየጠበቀ ያለውን ትተው በሚያሳፍር ሁኔታ ቤቶቹን ለደጋፊዎቻቸው፣ ለወንዜ አደጎቻቸው፣ አዲስ አበባ ላልኖሩ ዘመዶቻቸውና በፖለቲካ ለተሰገሰጉ ካድሬዎች ወዘተ አከፋፍለዋል በማለት ስለተጠረጠሩ ነበር፡፡ እነዚህ መደበኛና ኢመደበኛ አስተዳዳሪዎች ቤትና ቦታ ለመዝረፍ የተጠቀሙበት ዘዴ ‹‹የተፈናቀሉ ገበሬዎችን እንክስበታለን›› በማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ በግልጽ መቀመጥ ያለበት ‹‹በከተማው መስፋፋት ምክንያት፣ የተፈናቀሉ ገበሬዎች ለምን ተሰጣቸው ተብሎ ማንም ሰው አይጠይቅም፡፡ እነሱ በኢሕአዴግ ዘመን ተዘርፈዋል፡፡ ካሳም ይገባቸዋል፡፡  ‹‹ሕዝቡን ያስቆጣው በገበሬዎች ልጆችና የልጅ ልጆች (አንዳንዶቹ ኢትዮጵያም የሌሉ) ስም እያወጡ አየር በአየር መሬቶቹን በመሸጥ ለገበሬዎቹ ትንሽ ገንዘብ በመስጠት ቀሪውን በመከፋፈል ሚሊየነሮች እንደሆኑ መታየቱ ነው፡፡  ይህ ኢመደበኛ ረዥም እጁን በመሰንዘር በከተማው ውስጥ አንዱን መጤ፣ ሌላውን ባላገር የሚል አስተሳሰብ ፈጥሯል፡፡ ነዋሪው ቤት ፈላጊ በፖለቲካ ድርጅት ወይም በብሔር ካልታቀፈ አዲስ አበባ ቢወለድም፣ ቢያድግም መሬትና ቤት እንደማያገኝ እያሳየ ነው ብለው የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን እንዲያምኑ አድርጓቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ቀላል የማይባል የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪም ሆነ ቤት ፈላጊ ‹‹ከአራት ዓመት በፊት የመጣው ብልፅግና ፓርቲ  ከድጡ ወደ ማጡ ከተማዋን አስገብቷታል፤›› ብሎ እንዲያስብ አድርጎታል፡፡

ዝርፊያው አሁንም አልቆመም፡፡ ሐምሌ 1 ቀን ጥቂት የተረፈ የ20/80 እና 40/60 ለከተማ ቤቶች ለቆጠቡት አስተላልፋለሁ ብሎ ዕጣ ቢያወጣ በዝርፊያ ላይ የሚንቀሰቀሰው ማፍያው ቡድን በቴክኖሎጂ በመጠቀም አስተጓጎለ፡፡ እንደሰማነው ለዕጣ ብቁ ናቸው ተብለው ከባንክ የተላኩትን በ70 ሺሕዎች አካባቢ ሰዎች ላይ የባንክን መሥፈርቶች የማያሟሉ በሌብነት የተሰጣቸውን/የሚሰጣቸውን ከ100 ሺሕ ሰዎች በላይ ጨምሮ ዕጣ እንዲወጣ ተደረገ፡፡ መስተዳድሩ ቶሎ አውቆ ዕጣውን ባይሰርዘው ኖሮ የባንኩን መሥፈርት ያሟሉት ሕጋዊ ቤት ጠባቂዎች  ወደ አንድ ሦስተኛው ብቻ ነበሩ የማግኘት ዕድላቸው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ያለው ዝርፊያ በመኖሪያ ቤት ብቻ የሚቆም ሳይሆን፣ በመሬት ላይም ይበልጣል ተብሎ ይታማል፡፡ ለዚህም በአሁኑ ጊዜ ሌብነቱ አድጎ የአስተዳደሩ ሠራተኞች ሦስት መሬት ለአንድ ለሚፈልጉት ‹‹ፖለቲከኛ፣ ካድሬና የወንዜ ልጅ ወዘተ እየሰጡ ነው ተብሎ በከተማው ይወራል፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት አንድ ቦታ ብቻ ቢሰጠው በእነሱ አስተሳሰብ ቤት የሚሠራበት ስለሌለው ሁለቱን ሸጦ በሦስተኛው ላይ ቤት በመሥራት እንዲጠቀም ስለተፈለገ ነው ይባላል፡፡ የሕዝብን ሀብት እየሰረቁ ማማረጥ ‹‹አይ ጊዜ ምን አመጣህብን?›› ነው የሚባለው፡፡

እዚህ ላይ በአዲስ አበባ በልማት ስም በግፍ የተፈናቀሉ የልማት ተነሺ ገበሬዎችን አንስተን፣ ሌሎች አስታዋሽ ያጡ በመሀል አዲስ አበባ ይኖሩ የነበሩ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ በልማት ስም የተፈናቀሉትን የጥንት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የልጅ ልጆች፣ ሳናስታወስ ማለፍ የለብንም፡፡ እነዚህን የአሁኑ ተፈናቃዮች ደርግ መጥቶ ቦታቸውንና ቤታቸውን ወርሶ ገደላቸው፡፡ ኢሕአዴግ  ደግሞ ደርግ ያስቀረላቸውን ቤትና ቦታ ካለ ተመጣጣኝ ካሳ አፈናቅሎ ከመሀል ከተማ አውጥቶ ሰው በሌለበት አካባቢ በመውሰድ በቁማቸው ቀበራቸው፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያውያን የሚጠይቅላቸው የተደራጀ ኃይል ስለሌላቸው የጡረታ ጊዜያቸውን በድህነት እየኖሩ ስለሆነ ፍትሕ እንደሚያስፈልጋቸው ቢታወቅላቸው ጥሩ ነው፡፡

እንግዲህ የአዲስ አበባ የቤት ችግር የመጣው በፖለቲከኞች መሆኑን ብንቀበልም የቤት አቅርቦት አካሄዳችንም ችግር አለበት፡፡ የፖለቲከኞችን ችግር በዴሞክራሲያዊ ሒደት ብንፈታም አሁን እየሠራንበት ያለውን አሠራራችን እስካልለወጥን ድረስ የቤት እጥረት መፍትሔ ወደ ማይገኝለት አረንቋ መሸጋገራችን አይቀርም፡፡ የዚህ ጽሑፉም ዋና ዓላማም ፖለቲካው ‹‹የእኔ ነው›› የሚለው ቀርቶ ‹‹የእኛ ነው›› በሚለው ይቀየራል ብሎ ተስፋ በማድረግ የቤት አቅርቦት አሠራር ችግርን ለመፍታት የመፍትሔ ሐሳብ ለማቅረብ ነው፡፡ የቤት ችግር እንቀርፋለን ስንል ሀብት ያላቸው በራሳቸው መንገድ የማዘጋጃ ቤቱን መመርያ ተከትለው ይሠራሉ ተብሎ ስለሚታመን የእነዚህ አሠራር ችግሩን ከመፍታት የበለጠ ሌላ ችግር ያመጣሉ ብለን አናካትታቸውም፡፡ ስለዚህ የቤት ችግር አለባቸው የምንለው ቤት ለመሥራት ገቢያቸው የማይበቃቸውን ማለታችን ነው፡፡

እዚህ ላይ በቅድሚያ ተሰምሮበት መታወቅ ያለበት ሁሉም የከተማ ዜጋ የራሱን ቤት ገንብቶ/አግኝቶ ይኑር ማለት አይደለም፡፡ ይህንን በፖለቲከኞች ምክንያት ታስቦ አልተሳካም፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱ ሰው ቦታ ተሰጥቶት ይሥራ ቢባል አገሩ በሙሉ ከተማ ነው የሚሆነው፡፡ አቅምም የለም፡፡ ማንም አገር የከተማን ቤት ችግር በዚህ ዓይነት አልፈታም፡፡ ቤት ለመሥራት ገቢያቸው የማይበቃቸውን ስንል ከደመወዛቸው ለምግብና ለመኖሪያ አውጥተው ብዙም የማይተርፋቸው (የመካከለኛና ዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል) ማለታችን ሲሆን፣ እነዚህ ደግሞ በእኛ አገር ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ ከ75 በመቶ በላይ በከተማ የሚኖረውን ሠራተኛ ኅብረተሰብ ነው፡፡ ለዚህ ኅብረተሰብ እስካሁን ድረስ የከተማ ቤት ለማቅረብ የሄድንበትን አካሄድ ቀይረን፣ የዓለም ከተሞች የመኖሪያ ቤትን ችግር ለመፍታት የተጠቀሙትን አካሄድ መውሰድ አለብን፡፡ ለዚህም በመጀመርያ አዲስ አበባ የመኖሪያ ቤት ልማቷ በምን መሥፈርት እንደምትገነባ  ከዓለም አቀፍ ለከተማ መኖሪያነት ተቀባይነት ያገኘውን መንደፍ አለባት፡፡  መሥፈርቶቹም ‹‹የከተማ ነዋሪው በተፈላጊ ቦታ አስተማማኝና ተመጣጣኝ መኖሪያ ቤት ማግኘት አለበት የሚሉ ናቸው፡፡ ‹‹የመሥፈርቶቹም ትርጓሜም በተፈላጊ ቦታ ማለት ለነዋሪው ፍላጎት በአቅራቢያው መሠረተ ልማት፣ የመሥሪያ ቤት፣ ትምህርት ቤትና የጤና ጣቢያ መኖር፣ አስተማማኝ ማለት የነዋሪው ቤት ሁሉንም ያሟላ መሆን፣ ከቤቱ የሚያሰወጣው አለመኖር ወዘተ፡፡ ተመጣጣኝ ማለት የመኖሪያ ቤት ኪራይ በምንም ዓይነት ተከራዩ ከሚያገኘው ገቢ ከሚያወጣቸው ወጪዎች የአንበሳውን ድርሻ የያዘ እንዳይሆን (ይኸም ከተከራዩ ገቢ ከ20 በመቶ መብለጥ የለበትም የሚለው ለተመጣጣኝ ኪራይ ቤት ዋጋ ተቀባይነት ያገኘ ይመስላል) ማለት ነው፡፡  መሥፈርቶቹን ለሟሟላት በመጀመርያ አገሮች ማንኛውም የከተማ ነዋሪ መኖሪያ (መጠለያ) ማግኘት በፖለቲካ ችሮታ ሳይሆን፣ ሰብዓዊ መብቱ ነው ብለው ተነሱ፡፡ እዚህ ላይ ለመጥቀስ የተፈለገው የራሱን ቤት ለመሥራት አቅም የሌለውን የከተማ ዜጋ መኖሪያ ቤት ማግኘት እንደለበት ለማስገንዘብ ነው፡፡ እዚህ ላይ በግልጽ መቀመጥ ያለበት አገሮች (የከተማ መስተዳድር) ቤት ሠርተው በነፃ ለከተማ ነዋሪው ያቀርባሉ ማለት አይደለም፡፡ ሊባል የተፈለገው የከተማ መስተዳድሩ የመኖሪያ ቤት አሠራር ፖሊሲ አውጥቶ አልሚዎችን አነቃቅቶ በአነስተኛ ኪራይ ለነዋሪዎች ቤት እንዲያገኙ ያመቻቻል ለማለት ነው፡፡ በመቀጠልም የከተማ መስተዳድሩ ለነዋሪው ቤት ለመስጠት አልሚዎች በአነስተኛ ገንዘብ መሬትና የባንክ ወለድ ከቀረጥ ነፃ የግንባታ ዕቃዎች ወዘተ እንዲያገኙ በማመቻቸት የመኖሪያ ቤትን በኪራይም ሆነ በግዥ እጅግ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያወርዱት አደረጉ፡፡ በተጨማሪም መስተዳድሩ በከተማቸው ለሚገኙ ገቢያቸው በጣም አነስተኛ ለሆኑ የከተማው ነዋሪዎች የቤት ኪራይ ድጎማ በማድረግ ሁሉም የከተማ ነዋሪው ፍትሐዊ በሆነ ሁኔታ መኖሪያ ቤት አግኝቶ የተረጋጋ ኑሮ እንዲኖር አስቻለ፡፡   

ለምሳሌ የአውሮፓን አገሮች የቤት ችግርን እንዴት እንደቀረፉት ማየቱ የሚጠቅመን ይሆናል፡፡  የመኖሪያ ቤትን ችግር በሁለት ዓይነት ነው የቀረፉት፡፡ በግል ቤት ለሚያቀርቡና ለከተማው ሰፊ ሕዝብ የሚያቀርቡ፡፡ በግል ቤት ለሚያቀርቡ መሬት የገዙ ወይም የወረሱ ሀብታሞች (እንደነዚህ የሉ የቤት ባለቤቶች ከከተማ ነዋሪው አንፃር በጣም ጥቂቶች ናቸው) ለራሳቸውና ለቤት ኪራይ በጠበቀ ውል (ማለትም የቤት ኪራይ ውል፣ የማስወጫ ኪራይና የመጨመሪያ ግዴታ) እንዲተዳደር አደረጉ፡፡ አብዛኛው ከተሜ ቤት የሚያገኘው ማዘጋጃ ቤቱ ከሚያመቻቸው ነው፡፡ ማዘጋጃ ቤቱም እንደ እርሾ የሚጠቀምበትን ገንዘብ ከአገሪቷ ጠቅላላ ገቢ (ጂዲፒ) ከመንግሥት የተወሰኑ መቶኛ በመያዝ ለተጋነነ ትርፍ ያልተቋቋሙ የመኖሪያ ቤቶች አልሚዎች (ሪልስቴት) እንደ ከተማ ማኅበራት የሃይማኖት ተቋማት የግል ኩባንያዎችና የውጭ ኩባንያዎች በጣም በጠበበ ሕግ የመኖሪያ ቤቶችን፣ የገበያ ሱቆችን፣ የጥቃቅንና አነስተኛ አዳራሾችን፣ ሆቴሎችን፣ የቱሪዝም ማዕከላትን ወዘተ  እንዲያለሙ ይሰጣል፡፡

የቤት ዋጋ እንዲወርድም ማዘጋጃ ቤቱ መሬት በማዘጋጀት መሠረተ ልማትን በመገንባት ከግል ባንኮች ዝቅ ያለ ወለድ በማምጣት ወዘተ ያበረታታል፡፡ በዚህ ልማት የመጣውን የከተማ ነዋሪዎች ቤት በተቋቋመው የቤቶች አስተዳደር መሠረት ማንኛውም የከተማ ነዋሪ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ቤት አመልክቶ በተራው አግኝቶ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ እንዲኖር በጠበቀ ውል የሚያገኝበት አሠራር ተጠብቆለታል፡፡ ይህም ማለት ነዋሪው ከደመወዙ ወይም ከጡረታው በማያናጋ ሁኔታ በየወሩ አነስተኛ ገንዘብ እየከፈለ በሕይወት እስካለ ድረስ እንደሚኖር ሲሞት ለሕግ ባለቤቱ እስከ ሕይወቷ ፍጻሜ ልጅ እስከ 18 ዓመት ኑረውበት ቤቱን ለሌለ ዜጋ እንደሚያስተላልፍ ሕጉ ያረጋግጥለታል፡፡

እንግዲህ ይህ አሠራር ባለበት ጀርመን ወይም እንግሊዝ ላለ የከተማ ነዋሪ ቦታ/ቤት ግዛ ስትሉት ግራ ይገባዋል፡፡ ‹‹እኔ ሀብታም አይደለሁም ምን ሊያደርግልኝ  አገዛለሁ፡፡ ነገ እኮ ከዚህ መሥሪያ ቤት ለቅቄ በመቶ ኪሎ ሜትር እርቄ እሄዳለሁ፡፡ ቤቱን ተሸክሜ አልሄድም፡፡ አሁን ያለሁበትን የኪራይ ቤት እንደ እራሴ ቤት ቆጥሬ ነው የምኖረው፡፡ በሕይወቴ እስካለሁ ድረስ እንድኖርበት ውል አለኝ፡፡ ማንም ሊያስወጣኝ አይችልም፡፡ የራሴ ቤት ነው፤›› ብሎ ያስረዳችኋል፡፡

በዚህ ዓይነት ለሚተዳደር የቤት አቅርቦት አንድ የከተማ ቤት ፈላጊ ማድረግ ያለበት ሄዶ የሚፈልግበት ቦታ ካለው የቤት አስተዳደር ጋር ሰነድ (ፎረም) መሙላት ነው፡፡ አስተዳዳሪውም ተከራዩ ቤት የማግኘት መብት እንዳለው ካረጋገጠ በኋላ መዝግቦ ቤት የሚያገኝበትን ጊዜ ነግሮት እንዲጠባበቅ ያስረዳዋል፡፡ ቤት ፈላጊም እስከዚያ በግል ቤት የሚያከራዩት ጋር በመሄድ መርጦ ይከራያል፡፡ እንደዚህ ነው እንግዲህ አገሮች የከተማ መኖሪያ ቤት ፍላትን ቀላል ያደረጉት፡፡ ይሄንን ስንል፣ አንዳንድ ሰዎች፣ እኛ ደሃ አገር ነን፣ እንደዚህ ልናደርግ አንችልም የሚሉ አሉ፡፡ አቅም እንደሌለን ባምንም መጀመር ግን አለብን፡፡ ግባችን መሆን ያለበት በአንድ ወቅት እንደርስበታለን ነው፡፡

ኃይሌ 10 ሺሕ ሜትር ሮጦ ሪኮርድ የሰበረው በመጀመርያ ዕርምጃ ጀምሮ ነው፡፡ ስለዚህ አገራችን ለፖለቲካ ቁማር መጫወቻ ያደረገችውን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ጥቂቶችን ከመጥቀም በስተቀር ብዙኃኑን የከተማ ነዋሪ የመኖሪያ ቤት አሳጥቶ  ከመንግሥት ጋራ እንደ አይጥና ድመት ትንቅንቅ ያስገባ በመሆኑ እስካሁን የሄድንበትን እርግፍ አድርገን ዓለም እየተከተለ ያለውን የከተማ ቤት ለነዋሪዎች ማዳረስ ዘዴ መከተል አለብን፡፡  ለዚህም በመጀመርያ መሬት ሁሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ነው የሚለውን ደግሞ ማረጋገጥ አለበት፡፡ በዚህም መንግሥት አጉል የነፃ ገበያ የሚለውን ፈሊጥ ትቶ የመሬት ዋጋ (ከፓሪስ ከተማ በላይ ዋጋ የሚያወጣውን!) በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ ከሕዝቡ አቅም ጋራ ማስተካከል አለበት፡፡ ይህም መሬት የሚሸጡ የግል ባለቤቶችን መጨመር አለበት፡፡ እናውቃለን መሬት በሕግ እንደማይሸጥ፡፡ እየተደረገ ያለው ግን 10 ሺሕ ብር የማያወጣ ቤት ያለበት ቦታ በብዙ  እየተሸጠ ነው፡፡ የሽያጭ ውሉ ቤቱ አወጣ ተብሎ ይሸጣል፡፡ ቦታው ነው የተሸጠው፡፡ ሁለተኛው መንግሥት ማረጋገጥ ያለበት ቤት ለሌላቸው የከተማ ነዋሪዎች ቤት የማቅረብ ግዴታ እንዳለበትና ሥራው እንደሆነ በዓለም አቀፍ የተደነገገውንና አገራችን ኢትዮጵያ የተቀበለችውን መቀበል እንዳለበት ማረጋገጥ አለበት፡፡ ይህም ድንጋጌ ከያዛቸው ውስጥ ‹‹ማንኛውም ሰው ለራሱና ለቤተሰቡ በቂ የሆነ መኖሪያ ቤት፣ ምግብ፣ ልብስ፣ ሕክምና፣ ትምህርት፣ መጦሪያ፣ የኑሮ ዋስትና ወዘተ ማግኘት አለበት የሚለው ይገኝበታል፡፡

ተመሳሳይ ድንጋጌ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንድነት በኩልም ከዚህ ላይ በመነሳት የአገራችን በተለይም የአዲስ አበባ አስተዳደር ለነዋሪዎች የከተማ ቤቶችን ለማልማት ዓለም አቀፍ ለከተማ መኖሪያነት ተቀባይነት የተገኘውን መሥፈርቶች በመውሰድ ማለትም ‹‹የከተማ ነዋሪው በተፈላጊ ቦታ፣ አስተማማኝና ተመጣጣኝ መኖሪያ ቤት ማግኘት አለበት የሚሉትን በመውሰድ ሰፊ ተግባር ይጠብቁታል፡፡ ለዚህም የሚከተሉትን ተግባሮች ከብዙ በጥቂቱ ማከናወን አለበት፡፡ 

የከተማ  መኖሪያ  ቤቶች  ልማት ፖሊሲ ሕግና መመርያዎችን ማዘጋጀት

በዚህ ርዕስ ውስጥ የከተማ መኖሪያ ቤትን ለመገንባት ለማከፋፈልና ለማስተዳደር የሚያስፈልጉ ሕጎች መመርያዎችና ኮዶች ይዘጋጃሉ፡፡ ከሚወጡትም ውስጥ የመሬትና የገንዘብ አቅርቦት፣ የከተማ አስተዳደሩና አልሚዎች፣ የአልሚዎችና የተከራዮች ወዘተ ይገኙበታል፡፡

የተጠናከረ የቤት መሥሪያ ገንዘብ ማደራጀት

የከተማ አስተዳደሩ ቦታን በሞተ ዋጋ (የአገልግሎት ክፍያና ዓመታዊ ግብር) በማቅረብና ለቤት አልሚዎች ከራሳቸው ወይም ከአስተዳደሩ፣ ለቤቶች ብሎ ከተያዘው ወይም ቦንድ በመሸጥ ወይም ከገንዘብ ተቋማት በአነስተኛ ወለድ እንዲያገኙ ያመቻቻል፡፡

የቤት መሥሪያ ግብዓትን ማደራጀት

ለቤት ዋጋ መናር አንዱ የቤት መሥሪያ ግብዓት መወደድ ነው፡፡ እነዚህን ግብዓቶች የሚያዘጋጁ የከተማ ልማት ቤቶች ኢንዱስትሪዎችን ያቋቁማል፡፡ ለኢንዱስትሪዎቹ ግብዓት የሚያቀርቡትን አስተዳደሩ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ ከታክስ ነፃ ያደርጋቸዋል፡፡

በከተማው ውስጥ መገንባት ያለባቸውን ቤቶች ዓይነትና ዋጋቸውን መወሰን

የከተማ ቤት መሥፈርቶች የሚያመሟሉ እንደ የአንድ ሰው መኖሪያ (ስቱዲዮ አፓርትመንት)፣ ዘመናዊ ቤቶች፣ ፎቆች፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶችና የንግድ ማዕከላት ብሎ በመለየት አብሮ ተመጣጣኝ የቤት ኪራይ ዋጋ ይወሰናል፡፡

የተሠሩትን የመኖሪያ ቤቶች እንዴት እንደሚዳረሱ ፍትሐዊና ግልጽ በሆነ ሁኔታ መደንገግ

በአገራችን  ሌብነት ነውር ከመሆን ይልቅ የሚከበርበት እንደሆነ እያየን ነው፡፡ አንድ ደመወዙ/ገቢው አነስተኛ የሆነ ሠራተኛ ሁለት ፎቅ ሠርቶ ለምርቃት ሲጠራን ገንዘቡ ተሰርቆ እንደተሠራ እያወቅን ‹‹ጎበዝ ነህ በርታ›› ብለን እንመርቃለን፡፡ አንድ ጀማሪ ነጋዴ ዓመት ባልሞላው ዘመኑ ያመጣውን አዲስ መኪና ሲገዛ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ቤት ሲሠራ ምስጢሩ ኮንትሮባንድ ወይም ገንዘብ አዘዋዋሪ ወይም ዕቃ ደብቆ በውድ ዋጋ የሚሸጥ ወይም አየር ባየር ነጋዴ መሆኑን እያወቅን ‹‹በሦስተኛ ዲግሪ ከመመረቅ እነዚህ ድርጊቶች ክብር አላቸው፤›› እንላለን፡፡ በአሁኑ ጊዜ አንዱ መክበሪያ ‹‹ቤትና ቦታ›› ነው፡፡ ፖለቲከኞች ለራሳቸውና ለዘመዳቸው ቦታና ቤት ያድላሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ ቤት እያላቸው በስንት መከራ በከተማ አስተዳደሩ የተሠራን ቤት ይሸጣሉ፡፡ ሌብነት ከሚስተዋሉበት አንዱ ይህ ቦታ ነው፡፡ ስለዚህ አስተዳደሩ የመኖሪያ ቤቶች ከሌቦች በመጠበቅ እንዴት እንደሚዳረሱ ፍትሐዊና ግልጽ በሆነ ሁኔታ ማዘጋጀት አለበት፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በላይ ወልደየስ (ዶ/ር-ኢንጂነር) የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ስፔሻላይዝድ ያደረጉት ደግሞ በፔትሮኬሚካል ኢንጂነሪንግ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2015/16 የአስተማሪነት ልዕልና ሽልማትን (Distinguished Teaching  Award) ተቀብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ መሥራች አባልም ናቸው፡፡  ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]  ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles