Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹እሹሩሩ ድምቡል ቦቃ›› በዓለም የጨረቃ ቀን

‹‹እሹሩሩ ድምቡል ቦቃ›› በዓለም የጨረቃ ቀን

ቀን:

‹‹የሰሎሞንም አባባል ‹ከቶ አዲስ ነገር የለም›

‹ከአርያም ግርጌ ካንጦርጦርስ በላይ› ሲባል የነበረ

አረጀና ተሻረ፤

ባዳዲስ ነገሮች ተሟረ

ኮምፒዩተርስ ኤሌክትሮኒክስ ከሰው ኅሊና ናረ

እነ አፖሎ እነኮዝሞስ ሰማያትን መርምረው

ምሥጢርነቱ ቀረ፤

ሰው በሠራው አክናፍ በረረ፤

ፍጡርም ፍጡሩን ፈጠረ፤

ምናልባትም ይኖር ይሆናል፤ ኋላ በነጁፒተር ሰፊ ዓለም፡፡

 ይህ የግጥም አንጓ ‹‹ገሞራው›› በተሰኘ የብዕር ስሙ ይታወቅ የነበረው ኃይሉ ገብረዮሐንስ በ1961 ዓ.ም. በዚህ ሰሞን ከገጠመው ‹‹እሹሩሩ ድምቡል ቦቃ›› ግጥሙ የተገኘ ነው፡፡

ገሞራው ለዚህ ግጥሙ መነሻ የሆነው ከ53 ዓመት በፊት ኒል አርምስትሮንግና ቡዝ አልድሪን በጨረቃ ላይ በማረፍ የመጀመርያዎቹ ሰዎች በመሆን ታሪክ በመሥራታቸው ነው፡፡

የቲኤን ሳይንስ የሰሞኑ ዘገባ እንደሚያሳየው አፖሎ 11 የተባለችው መንኮራኩር ሐምሌ 14 ቀን 1961 ዓ.ም. ከአሜሪካ ምድር ወደ ሰማይ ስትመጥቅ ሁለቱን ጠፈርተኞች ይዛ ሲሆን፣ ለ6 ሰዓት ከ39 ደቂቃ በመንኮራኩሩ ላይ ከቆዩ በኋላ ቀድሞ ጨረቃ ላይ ያረፈውና የተራመደው ኒል አርምስትሮንግ ነው፡፡ ከ19 ደቂቃ በኋላ ቡዝ ተከትሎታል፡፡

ጨረቃን በማሰስ የመጀመርያ ሰዎች የሆኑት ሁለቱ ጠፈርተኞች ለ2.5 ሰዓታት ያህል የጨረቃን ገጽታ አስሰዋል፡፡ ወደ መንኮራኩሩ ፓይለት ከመመለሳቸው በፊት 21.5 ኪሎ ግራም የጨረቃ ቁሳቁስ ሰብስበዋል፡፡ በአጠቃላይ በጨረቃ ወለል ላይ የቆዩት ወደ 21 ሰዓታት የሚጠጋ ነው፡፡

በወቅቱ የሮም ፖፕ የነበሩት ጳውሎስ 6ኛ በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ የዓለማችን ሰዎች፣ ሴቶች ወንዶች እና ሕጻናት ጋር ሆነው ሐምሌ 13 ቀን 1961 ዓ. ም. የሰው ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ጨረቃን ለመርገጥ ያደረገውን የጠፈር ጉዞን መከታተላቸውን ቫቲካን ኒውስ በወቅቱ ዘግቦታል።

ዘገባው አክሎም ጠፈርተኞቹ የተጓዙባት መንኮራኩር ወደ ጨረቃ በተቃረበችበት ወቅት፣ ምን ይከሰት ይሆናል በማለት የዓለም ሕዝብ በቴሌቪዥን ይከታተል እንደነበርና ፖፕ ጳውሎስ 6ኛም በካስቴል ጋንዶልፎ በተባለ የበጋ ወቅት መኖሪያ ቤታቸው ሆነው  መከታተላቸውንም አውስቷል።

ይህን ታሪካዊ ክስተትን በአግባቡ የዓመቱ መዘከር አስፈላጊነቱን የተረዳው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጠፈር ከባቢ ለሰላማዊ አጠቃቀም ኮሚቴ ዓምና ባፀደቀው መሠረት ‹‹ጁላይ 20›› ሐምሌ 13 ቀን ዓለም አቀፍ የጨረቃ ቀን ሆኖ እንዲከበር አውጇል፡፡

በዚህም መሠረት ዘንድሮ ቀኑ ለመጀመርያ ጊዜ በተለያዩ አገሮች ተከብሮ ውሏል፡፡ በኢትዮጵያ በሚመለከተው ተቋም ስለመከበሩ አልተሰማም፡፡

ከአምስት አሠርታት ጥቂት እልፍ ካሉ ዓመታት በፊት ናሳ የሚባለው ብሔራዊ የጠፈርና የኅዋ አስተዳደር በአፖሎ ፕሮግራም የመጀመርያዎቹን ሰዎች ወደ ጨረቃ ልኳል፡፡ አሁን ናሳ የአርቴምስ ፕሮግራም አካል በመሆን የመጀመርያዋን ሴትና የመጀመርያ ከነጭ ውጭ ወደ ጨረቃ ለመላክ በዝግጅት ላይ መሆኑ ተዘግቧል፡፡

ገሞራው ‹‹ፍንደታ›› ብሎ ባሳተመው የግጥም መድበሉ አንድ ክፍል ያደረገው ጨረቃን የተመለከተው እሹሩሩ ድምቡል ቦቃን ግጥሙን ነው፡፡

ግጥሙን ለሰው ልጆች ከፍተኛ ምኞትና አርያማዊ ተምኔት መታሰቢያ ይሆን  ዘንድ የቀረበ፣ አሜሪካዊው አርምስትሮንግ ጨረቃን ረገጠ በተባለበት ሰሞን የተገጠመ ሲል በመዘክር ገጹ ከትቦታል፡፡

ገሞራው እንዲህ ሲል ግጥሙን ቀጠለ፡-

‹‹ግና… ከዚያ ወዲህ ጨረቃ ሆይ

  • ለደራሲ ሐሳብ ማመንጫው፣
  • ለባለቅኔ መምጠቂያው
  • ለፍቅርኞችም መተጫጫቸው

ምን ይሆን ብለሽ ድንገት ተማረክሽ፣

ምንስ ተካሽ ለዚያ ሰማይ?››

ሲል ጨረቃን ይጠይቃታል፡፡ በአመሥጥሮ ምሥጢርም ይዘልቅባታል፡፡

‹‹ጨረቃ እንቺ በሶ

በንጥር ቅቤና በወለላ ማር ተለውሶ››

ይባልልሽ የነበረው ምናልባት ተቀልብሶ

እኔስ የምፈራው እንዳይሉሽ፤ በምናምንቴ

መርዝ ተለውሶ!››

ድሮም ሆነ ዘንድሮ የነባሩና አሁንም ያሉ ሕፃናት ከጨረቃ ጋር የተዛመደ መዝሙራዊ ጨዋታ አላቸው፡፡ ከነሱው ከትውፊቱ የቀዳው ገሞራው ከግጥሙ ጋር አሰናስሎታል፡፡

‹‹ድሮማ ትባይ ነበር ጨረቃ ድምቡል ቦቃ

ካጤ ቤት ገባች አውቃ፤

ዛሬም ቢሆን የገባሽው ካልጠፋ ቤት ካላጣሽው

ከምናውቀው እንዲያ ካለው፤

እኛ ግን የጠበቅነው፣

ትገቢያለሽ ብለን እምነት የጣልነው

ነበራ ከገነት መች ከነዚያ ሀገር ነው!

ገሞራው ከካሌንደር ጓዳ በመግባትም ሲባል የነበረው የጨረቃ ድብቅ ነገር መሰበሩንም ያትታል፡፡

እንዲህ ሲል፡-

‹‹ፍካሬ ነቢያት፣ ፍካሬ ሊቃውንት፣

ስለ ጨረቃችን የተነበዩላት፣

አልነበረም የሚል የ‹‹አሸዋ ዱቄት››

ድሜጥሮስም ሆነ አቡሻህር፣ የወልደ አሚዱም ጊዮርጊስ፤

ዑመር ካያምን ጨምረው የነበራቸው ነባር መንፈስ፤

ባሕረ ሐሳብ ነው እንጅ፤ ጨረቃን ማን አስቧት እንደየብስ፡፡

ዛሬ ግን የብስነቷ መታወቁ ተነገረ፤

የኖረውም ኅቡዕ ምሥጢር፤ በጠንካራው ክንድ ተሰበረ፤

‹ዐውደ ወርኅ ሠላሳም› እንደቀመርነቱ ቀረ፡፡›

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...