Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሕክምና ጥናት ዘርፉን ለመደገፍ ያለመው የዘለቄታ በጎ አድራጎት ድርጅት

የሕክምና ጥናት ዘርፉን ለመደገፍ ያለመው የዘለቄታ በጎ አድራጎት ድርጅት

ቀን:

በሔፒታተስ ቫይረስ መንስዔ በሚከሰተው የጉበት በሽታ ላይ ለሚደረጉ ጥናትና ምርምሮችን በገንዘብ መደገፍ ዋነኛ ዓላማ ያደረገው የሲስተር ቆንጂት መታፈሪያ የዘለቄታ በጎ አድራጎት ድርጅት (ፋውንዴሽን) ነው፡፡ እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪያቸውንና ከዚያም በላይ ትምህርታቸውን ለመግፋት ፈልገው የገንዘብ እጥረት ለሚያጋጥማቸው ወጣት ሴት ተማሪዎች የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ሌላኛው ዓላማው ነው፡፡  

 በቅርብ ዓመታት የተቋቋመው ፋውንዴሽኑ ሲስተር ቆንጂት መታፈሪያ በሕይወት እያሉ በሕክምና ዘርፉ ላይ ያቅዷቸው የነበሩትን ሥራዎች ለመሥራት ያለመ መሆኑን፣  ሐምሌ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. በሒልተን አዲስ አበባ በተዘጋጀው ሥርዓት ላይ የፋውንዴሽኑ አባላት አስታውቀዋል፡፡

የፋውንዴሽኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ ወርቁ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሕክምና ሙያ ላይ ተሰማርተው የድኅረ ምረቃ ጥናታቸውን በ‹‹ጉበት በሽታ›› ላይ ለሚያደርጉ ተማሪዎች ለምርምር የሚያስፈልጋቸውን ግብዓቶችን እንዲያሟሉ የገንዘብም ሆነ የቁሳቁስ ድጋፍ ያደርጋል፡፡

ፋውንዴሽኑም 1.5 ሚሊዮን ብር ተቀማጭ ያለው መሆኑን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ የተቋቋመበት ዓላማውን ለማሳካትና በዘርፉ ላይ ያሉትን ችግሮች ለመግታት በሕይወት እያሉ ያፈሩትን ንብረት ሙሉ በሙሉ ለዘላቂ በጎ አድራጎት ድርጅት እንዲውል ኑዛዜያቸውን ትተው ማለፋቸውን አስረድተዋል፡፡

የበጎ አድራጎት ድርጅቱ በ100 ሚሊዮን ብር ሕንፃ ለመገንባት ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁንም አክለው ገልጸዋል፡፡

ተቋሙም የራሱ የሆነ ገቢ እንዳለው የተናገሩት አቶ ደረጀ፣ የሕንፃውን ግንባታ ዕውን የሚሆነው ሲስተር ቆንጂት መታፈሪያ በሕይወት እያሉ ኑዛዜ ከሰጡት ሁለት የተለያዩ ቦታዎች መካከል በአንዱ ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

የሕክምና ትምህርት በሚሰጡ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚማሩ ሴት ተማሪዎችና ተመራማሪዎች ድጋፍ የማድረግ እንቅስቃሴ በ2012 ዓ.ም. መጀመሩንም አስታውሰዋል፡፡

በድኅረ ምረቃ መርሐ ግብር ላይ ተሳታፊ ከሆኑ ተማሪዎች በተጨማሪ፣ የምርምር ሥራ ለሚሠሩ ሴት ተመራማሪዎችም ማኅበሩ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ዓለሚቱ ዑመድ፣ ‹‹የሲስተር ቆንጂት መታፈሪያ የዘለቄታ በጎ አድራጎት ድርጅት ሁሉም በተሰማራበት መስክ ውጤታማ ሥራን በመሥራት እንዲሁም ደግሞ ማኅበረሰቡ በተሰማራበት የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ትምህርት ሰጪ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የበጎ አድራጎት ድርጅቱም ላለፉት ሁለት ዓመታት በሥልጠና ላይ በማተኮር፣ ሴት ሙያተኞችን በጉበትና ከጉበት ጋር ተዛማጅነት ላላቸው የምርምር ሥራዎች ያደረገው ድጋፍ ይህ ነው የማይባል እንደሆነ ሚኒስትር ዴኤታዋ አብራርተዋል፡፡

በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ ችግሮችን በማውጣት ለችግሩ የመፍትሔ አካል በመሆን፣ አገርንና ወገንን በከፍተኛ ሁኔታ መጥቀም የሚያስችል በመሆኑ፣ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን መወጣት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ፋውንዴሽኑም በተቋቋመበት ወቅት ሲስተር ቆንጂት መታፈሪያ የሠሩትን ሥራዎች ያካተተ መጽሐፍ በወቅቱ ለምርቃት በቅቷል፡፡

ከአራት አሠርታት በላይ በነርስነት፣ በተለያዩ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ያገለገሉት ሲስተር ቆንጂት መታፈሪያ (1927-2009)፣ በማኅበረሰብ ነርስነት የሠለጠኑት በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የጤና ጥበቃ ኮሌጅና የማሠልጠኛ ትምህርት ቤት (ጎንደር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ) ነው፡፡

በሥራ ዓለምም ከጤና ኮሌጁ ሆስፒታል በመቀጠል ከ1953 እስከ 1962 ዓ.ም. ድረስ በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታልና በመቀጠልም በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ክሊኒክ ለሦስት አሠርታት አገልግለዋል፡፡ ጡረታ ከወጡበት ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ እስካረፉበት 2009 ዓ.ም.፣ በጡረታ ጊዜያቸው ለሕዝብ አገልግሎት የሰጡት በመኖሪያ ቤታቸው ባቋቋሙት የፊዚዮ ቴራፒ ክሊኒክ መሆኑ ‹‹ለሌሎች የተረፈ ሕይወት›› የተሰኘው ስለሕይወት ታሪካቸው በተጻፈው መጽሐፍ ላይ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...