Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየነዋሪዎችን አቅል ያሳተው የኑሮ ውድነት

የነዋሪዎችን አቅል ያሳተው የኑሮ ውድነት

ቀን:

በየጊዜው እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት ለብዙዎች በልቶ የማደርን  ፍላጎት ከባድ አድርጎታል፡፡ በተለይ በምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ በየቀኑ የሚጨምረውን ዋጋ የሚመጥን ገቢ ማግኘት እንደ ሰማይ ርቋል፡፡

የተሻለ ቀርቶ በነበሩበት እንኳን መኖር ስላልተቻለ፣ ነዋሪዎች ደረጃቸውን ወዳልጠበቁና ወደማይፈልጉት እንዲሁም ለብስጭት፣ ለሃሳብና ጭንቀት እየተጋለጡ ስለመሆናቸውም በተለያዮ መድረኮች ተሰምቷል፡፡

በየመሥሪያ ቤት ኮሪደሮች፣ ካፌዎች ሆነ ገበያ ቦታዎች ነዋሪው የሚያነሳውም ይህንኑ አላባራ ያለ የኑሮ ውድነት ከአቅም በላይ መሆኑን ነው፡፡  ከብዙዎች ጥቂቶች መብላት ቢችሉም፣ የሚራቡ ግን የትየለሌ ናቸው። ረሃብ ደግሞ ለስርቆትና ለተለያዩ ወንጀሎች ምንጭም ነው።

- Advertisement -

የኑሮ ውድነቱ እጅግ የሚጎዳቸው በዝቅተኛ ገቢ ላይ የሚገኙ ወገኖችን ነው፡፡ ጉሊት የዘረጉ፣ ጥቃቅን ዕቃዎችን የሚቸረችሩ፣ በጠዋት ያደፈና ያረጀ ካፖርታቸውን ለብሰው በትራፊክ መብራቶች አካባቢ የሚለምኑ አዛውንቶች፣ ልመናውን ፈልገውት ሳይሆን የኑሮ ውድነት ከቤት ገፍትሮ ያስወጣቸው እናቶች፣ አባቶች፣ ጡረተኞችና ልጆችን ማየት የተለመደ ሆኗል።

በኑሮ ውድነት ምክንያት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከማማረርም አልፎ በሁሉም ነገር ተስፋ እየቆረጠ እንደሆነ ብዙ ማሳያዎች አሉ። 

መሠረታዊ ከሚባሉት ልብስ፣ መኖሪያ ቤትና ምግብን ጨምሮ፣ ሁሉም አገልግሎቶችና ዕቃዎች ከመወደዳቸው የተነሳ ሕዝቡ ሥጋት ውስጥም ገብቷል። 

ምን ውስጥ ኖሬ?፣ ምን በልቼ አድራለሁ? የሚለው የብዙዎች ጭንቀት እየሆነ መምጣቱን ካለው ሁኔታ ለመረዳት አይከብድም።

በተለይ የመንግሥት ሠራተኞች፣ በቀን ሥራ የሚተዳደሩ እንዲሁም ገና በሥራ ፍለጋ ያሉትንም ጨምሮ አብዛኛው ሕዝብ በኑሮ ውድነቱ ምክንያት ችግር ውስጥ ገብቷል።

የሚያኙትን ገቢ ለቤት ኪራይና ለቀለብ ለማብቃቃት የማይችሉ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡

 የዕቃዎቹ መወደድ፣ የዘይትና ምግብ ነክ ነገሮች መናር፣ የታሪፍ መጨመር፣ የቤት ኪራይ ዋጋ መጨመር፣  አብዛኛውን ሕዝብ ተስፋ እያስቆረጠ ሲሆን፣ ቀጣዩ ጊዜ ደግሞ አስፈሪ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ።

በጦርነት፣ በድርቅ፣ በውጭ ተፅዕኖና ለተለያዩ አገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ባለመሰጠቱ፣ የኑሮው ውድነቱ ቅጥ ያጣ፣ መቆሚያ የሌለውና አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርጓል፡፡ 

በይበልጥ የዚህ ገፈት ቀማሽ ደግሞ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ነዋሪዎች መካከል የሦስት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ፈንታ ዓለማየሁ ይገኙበታል፡፡

የራሳቸውንና የልጆቻቸውን የዕለት ጉርሳቸውን የሚሸፍኑበት ሽንኩርትና ቲማቲም በመሸጥ ነው፡፡ የሦስት ልጆች እናት እንደሆኑ የሚናገሩት ወ/ሮ ፈንታ ስድስት ኪሎ አካባቢ የሚገኘው ቸሬ ሠፈር ነዋሪ ናቸው፡፡

የጉሊት ሥራ ከጀመሩ ረዥም ዓመታት ያስቆጠሩ ቢሆንም፣ ከዕለት ጉርስና ከልጆች ትምህርት ቤት ውጪ እንደማያልፍ ይናገራሉ፡፡

እንደ አብዛኛው የቀዬው ነዋሪ ሕይወታቸውን እንደነገሩ የሚኖሩ ሲሆኑ፣ የዓምናና የዘንድሮ የዋጋ ጭማሪ አቅላቸውን እንዳሳጣቸው በብስጭት ይናገራሉ፡፡

ነጋዴዎች የተሻለ ሕይወት ለመኖር የሚሠሩ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ፈንታ፣ ‹‹እሳቸውና መሰሎቻቸው የዕለት ጉርስ ለማግኘት ነው የምንሠራው፤›› ብለዋል፡፡

ወጪና ገቢን ማወቅ የነጋዴ የዕለት ተዕለት ሥራ መሆኑን፣ የንግድ እንቅስቃሴያቸው ለዕለት ጉርስ የሚሆን ብቻ ማግኘት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቸሬ ሠፈር እንደ አብዛኛው የመዲናው ነዋሪዎች የተጠጋጉ ቤቶች የሚገኙበት ነው፡፡ ምንም እንኳን የነዋሪዎችን ቁጥር ለመገመት ቢከብድም፣ ኑሮ ለከበደውና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚኖር የተሻለ መሆኑን ነገር ግን አንዳንዴ ልጆቻቸውን  የሚመግቡት እንደሚያጡ ይናገራሉ፡፡

ማኅበራዊ ኑሮው፣ የትራንስፖርትና ሌሎችም ወጪዎች ላይ የዋጋ መናር እንደ ወ/ሮ ፈንታ ልጆቻቸውን ብቻቸውን ለሚያሳድጉ እናቶች ብቻ ሳይሆን እስከ መካከለኛ ገቢ ያለውንም ፈተና ውስጥ የከተተ ነው፡፡

በዚህ የኑሮ ውድነት ዋጋን ያረጋጋሉ ተብለው የተከፈቱትና አብዛኛውን ሸቀጣቸውን ከውጪው ገበያ እኩል ከሚሸጡት ሸማቾች መግዛት ‹‹ቅንጦት›› የሆነባቸው ዜጎች ቁጥር መበራከቱን የወ/ሮ ፈንታ ኑሮ ማሳያ ነው፡፡

‹‹ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ለመጣው የኑሮ ውድነት መንግሥት መፍትሔ ካላበጀለት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖች ወደ ጎዳና መውጣታቸው አይቀሬ ነው፤›› የሚሉት ወ/ሮ አያልነሽ ጉግሳ ናቸው፡፡

ወ/ሮ አያልነሽ በመንገድ ዳር ላይ ሸራ ወጥረው ድንች፣ ቲማቲምና ሌሎች ነገሮችን እየሸጡ መኖር ከጀመሩ ስድስት ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ እየሸጡ የሚተዳደሩበት ሥራ የዕለት ጉርሳቸውን ከመቻል ውጪ ሌላ ትርፍ እንደሌለው የሚናገሩት ወ/ሮ አያልነሽ፣ አንድ ልጃቸውን ለማሳደግ ማጥ ውስጥ እንደገቡ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በተለይም በሸቀጣ ሸቀጦችም ሆነ በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ የሚታየው የዋጋ ንረት አይደለም ጉሊት ሸጦ ለሚተዳደር ቀርቶ ቋሚ ሥራ ለሚሠሩ ዜጎች እንደሚከብድ አስረድተዋል፡፡

ወ/ሮ አያልነሽ ከልጃቸው አባት ጋር ከተለያዩ በኋላ ብዙ ውጣ ውረዶች ማሳለፋቸውን፣ በአንድ ወቅትም የቤት ኪራይ መክፈል አቅቷቸው ጎዳና ላይ መውጣታቸውን አስታውሰዋል፡፡

የኑሮ ውድነቱ በዚህ ከቀጠለ አሁንም ቢሆን ጎዳና ላይ መውጣታቸው እንደማይቀርና መንግሥት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖችን ታሳቢ ያደረገ አሠራር መዘርጋት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

‹‹በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች በድጎማ መልክ ለምግብነት የሚውሉ ነገሮችን መስጠት አለበት፤›› የሚሉት ወ/ሮ አያልነሽ፣ ወቅቱ ክረምት እንደመሆኑ መጠን እንደ ልባቸው የያዙትን ዕቃ ሸጠው ለመጨረስ እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡

የሚኖሩበት አካባቢ የሚገኙት የማኅበረሰብ ክፍሎች ማኅበራዊ አኗኗር ላይ የተሻሉና እንዳንድ ጊዜም ችግር በሚያጋጥማቸው ወቅት እንደሚደርሱላቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ልጃቸው የሰባተኛ ክፍል ተማሪ እንደሆነ የሚናገሩት ወ/ሮ አያልነሽ፣ ለትምህርት የሚሆኑ ግብዓቶችን በመንግሥት ወጪ በመሸፈኑ፣ ኑሯቸው ላይ ዕፎታን እንደፈጠረላቸው አስረድተዋል፡፡

የኑሮ ውድነት እየተባባሰ የመጣው ቅርብ ጊዜ መሆኑን፣ መንግሥትም ጉዳዩን በጊዜያዊ መፍትሄዎች በመሸፋፈን እያለፈ በመሆኑ፣ የኑሮ ውድነቱ አብዛኛውን የማኅበረሰብ ክፍሎች ሊያስጨንቅ ችሏል ብለዋል፡፡

ሌላዋ የጡረታ አበል እየጠበቁ ኑሯቸውን እየገፉ ያሉት ወ/ሮ አስናቁ በዳዳ እንደሚሉት፣ የኑሮ ውድነትና የእርስ በርስ ጦርነት የእሳቸውን የኑሮ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን የልጅ ልጆቻቸውን ሕይወት ጭምር አሳሳቢ አድርጎታል፡፡

‹‹ከዚህ በፊት የኑሮ ውድነት ከታየ መንግሥት አፋጣኝ የሆነ ምላሽ ይሰጣል፤›› የሚሉት ወ/ሮ አስናቁ፣ ለአብነት ያህል ደርግ ሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ይህንን አሠራር ይከተል እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ወ/ሮ አስናቁ 58 አካባቢ አራት በአራት በሆነች የቀበሌ ቤት ውስጥ መኖር ከጀመሩ 15 ዓመታት ማስቆጠራቸውን፣ በየወሩ ተቆራጭ የሚደረግላቸውን የጡረታ አበል ለምን እንደሚያውሉት ግራ እንደሚባቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ዘይት፣ ሽንኩርት፣ በርበሬ፣ ጤፍና ሌሎች ነገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ ዋጋቸው እየናረ መምጣቱን የሚናገሩት ወ/ሮ አስናቁ፣ ‹‹መንግሥት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ፈጣን የሆነ ምላሽ መስጠት አለበት፤›› ብለዋል፡፡

ወ/ሮ አስናቁ ከባለቤታቸው ከአቶ መገርሳ አያሌው ሁለት ልጆችን ማፍራታቸውን፣ አሁን ላይ ግን ባለቤታቸውን በሕይወት በማጣታቸው ኑሮ እየከበዳቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከባለቤታቸው ጋር እያሉ የተሻለ ኑሮ ይኖሩ እንደነበር ያስታወሱት ወ/ሮ አስናቁ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕድሜያቸው እየገፋ በመምጣቱ እንደሌሎች ወጥቶ ለመሥራት መቸገራቸውን አስረድተዋል፡፡

ከባለቤታቸው ያፈሯቸው ሁለት ልጆች አልፎ አልፎ ተቆራጭ እንደሚያደርጉላቸውና ልጆቻቸው ከእሳቸው የተለየ የተሻለ ኑሮ እንደማይኖሩ ገልጸዋል፡፡

የኑሮ ውድነት በዚህ ከቀጠለ የሚላስ የሚቀመስ ሊያጡ እንደሚችሉና ይህም ከፍተኛ የሆነ ሥጋት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡

ዕድሜያቸው እየገፋ መምጣቱን፣ ልጆቻቸው ደግሞ ምን ያህል ችግር ውስጥ ሊወድቁ እንደሚችሉ ከወዲሁ ግምታቸውን አኑረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ የኑሮ ውድነትን ያረጋጋል የተባለው  96 ቦታዎች ‹‹የእሑድ ገበያ››  ቢቋቋምም ፣ የሕዝቡ የመግዛት አቅም መጣጣም አልቻለም፡፡ የህዝቡ በተለይም የተቀጣሪው ደመወዝ ለዓመታት ያህል ባልጨመረበት፣ ለሁሉም ሸቀጦች መናር መሰረታዊ ምክንያት የሚባሉት የነዳጅና የትራንስፖርት ዋጋ መጨመር ችግሩን አባብሶታል፡፡

በሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ የሰብልና የአትክልት አቅራቢዎች፣ የጅምላ ነጋዴዎችና በምግብ ማቀነባበሪያ የተሰማሩ ፋብሪካዎች እንዲሁም የኅብረት ሥራ ማኅበራትን በማሳተፍ በየሳምንቱ የእሑድ ገበያን በከተማዋ በተመረጡ 96 ቦታዎች በማቅረብ እንዲሁም የመሠረታዊ ፍጆታ ሸቀጦች ለከተማችን ነዋሪ በተመጣጠኝ ዋጋ በማቅረብ የኑሮ ውድነት ችግር ለማቃለል ጥረት  እየተደረገ መሆኑን መንግሥት በተደጋጋሚ ቢናገርም፣ ውጤቱ ግን የተገላቢጦሽ እንደሆነ ሸማቾች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡

ዘይት ለአብነት ቢታይ ዘንድሮ አጋማሽ ላይ ተወደደ ተብሎ የአዲስ አበባ አስተዳደር፣ ክልሎች እና ይመለከተናል የሚሉ አካላት ‹‹ የተደበቀ ያዝን፣ ህገወጦችን በቁጥጥር ሥር አዋልን፣ ችግሩ የሥርዓት አልበኝነት ነው›› ሲሉ ቢከርሙም፣ ዛሬ ላይ አምስት ሌትር ፈሳሽ የሱፍ ዘይት ደረሰኝ ተቆርጦለት እስከ 1,140 ብር ድረስ እየተሸጠ ነው፡፡

በወቅቱ የተሰቀለው የሸቀጦች ዋጋ ሰው ሠራሽ ነው ተብሎ በየመድረኩ መግለጫ ቢሰጥበትም፣ ዋጋው በወራት ልዩነት ውስጥ መደበኛ ሆኗል፡፡ የምግብ ሸቀጦች ዋጋ እንደ አይነቱ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ እጥፍ፣ ሁለት እጥፍና ከዚህ በላይ ጨምሯል፡፡

 የመንግሥት ሠራተኛ፣ የፋይናንስ ተቋማትን ሳይጨምር በአብዛኛው የግል ተቀጣሪ ደመወዝ ላይ ጭማሪ አለመደረጉ፣ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ዋጋ ሲጨምሩና ለመጨመር ጥናት እያደረግን ነው ሲሉ፣ መንግሥት የነዳጅ ድጎማን እንደ ኪሳራና ቅንጦት ቆጥሮ ጭነቱን ወደ ሕዝብ ያወረደ ያለውን ያህል የደመወዝ ማስተካከያ እንዲደረግ አለመትጋቱ፣ በየቦታው የሚሰማው የሰላም እጦትና የፖለቲካው በቅጡ አለመረጋጋት ከፈጠረበት ሥጋት ላይ የኑሮ ውድነቱ ተጨምሮ ነዋሪው የከፋ ችግር ውስጥ ገብቷልና መንግሥት መላ ይበል የብዙኃን ድምፅ ነው፡፡

በሔለን ተስፋዬና በተመስገን ተጋፋው

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...