የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት ያወጣው አዲስ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች የትርፍ ሰዓት ሥራና ክፍያን የሚመለከት መመርያ፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሠሩ ሾፌሮች በትርፍ ሰዓት ሥራ የሚያገኙትን ቁርጥ አበል በእጥፍ አሳደገ፡፡
ባለፈው ሳምንት ዓርብ ሐምሌ 15 ቀን 2014 ዓ.ም. በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) ከተፈረመ ደብዳቤ ጋር ለ185 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተላላፈው መመርያ እንደሚያሳየው፣ የሾፌሮች የትርፍ ሰዓት ሥራ አበል ከአምስት መቶ እስከ ሰባት መቶ ብር አድጓል፡፡
ኮሚሽነሩ ለመሥሪያ ቤቶች በላኩት ደብዳቤ እንዳሳወቁት፣ በመመርያው ላይ የተቀመጠው አሠራር ተግባራዊ መሆን የሚጀምረው ከነሐሴ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. አንስቶ ነው፡፡
በመመርያው መሠረት ሁሉም የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች፣ ከመደበኛው የሥራ ሰዓት ውጪ የሚሠሩት የሥራ ሰዓት ክፍያ ከዚህ ቀደምም በነበረው ሥሌት መሠረት ነው፡፡ የሠራተኞቹን የአንድ ቀን ደመወዝ በተለያዩ ሁኔታዎች ከ1.25 እስከ 2.50 በማባዛት የሚሠራ ነው፡፡ ሠራተኞቹ በትርፍ ሰዓት ሥራ ከፍተኛውን ክፍያ የሚያገኙት በሕዝብ በዓላት ቀን በሚሠሩበት ጊዜ የአንድ ቀን ደመወዛቸው በ2.50 ተባዝቶ ሲከፈላቸው ነው፡፡
ይሁንና መመርያው ከዚህ ቀደም አንድ ሠራተኛ በአንድ ወር ውስጥ በትርፍ ሰዓት የሚሠራበት የሰዓት ገደብ በእጥፍ በማሳደጉ የመንግሥት ሠራተኞች በወር ከትርፍ ሰዓት ሥራ የሚያገኙት ክፍያ እንዲጨምር አስችሏል፡፡ ከዚህ ቀደም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አንድ ሠራተኛ በአንድ ወር ውስጥ ከ60 ሰዓት በላይ በትርፍ ሰዓት ማሠራት የማይችሉ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ይህ ገደብ ወደ 120 ሰዓት አድጓል፡፡
ከሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች በተለየ ሁኔታ የሾፌሮች የትርፍ ሰዓት ክፍያ የሚከፈለው በሥሌት ሳይሆን፣ አስቀድሞ በኮሚሽኑ በሚወስነው ቁጥር አበል የገንዘብ መጠን ነው፡፡ ይህም ሾፌሮች በማንኛውም ጊዜ አገልግሎት የመስጠት ግዴታ ስላለባቸው መሆኑን መመርያው ደንግጓል፡፡ መመርያው አክሎም፣ ‹‹በየወሩ ከመደበኛ ደመወዝ ጋር በቁርጥ አበል የሚሰጣቸው ክፍያ የትርፍ ሰዓት ማካካሻ ታሳቢ ተደርጎ ስለሆነ ተጨማሪ የትርፍ ሰዓት ክፍያ አይከፈልም፤›› በሚል አስቀምጧል፡፡
ይህ የሾፌሮች ቁርጥ አበል ለመጨረሻ ጊዜ የተሻሻለው ከስድስት ዓመት በፊት በ2008 ዓ.ም በተላለፈ ሰርኩላር ሲሆን፣ በጊዜው የበላይ አመራር ሾፌር የሆነ ሠራተኛ የትርፍ ሰዓት ሥራ አበል 800 ብር ተደርጎ ነበር፡፡ አዲሱ መመርያ ይህንን የበላይ አመራር ሾፌሮች የትርፍ ሰዓት ሥራ አበል ወደ 1,500 ብር አሳድጎታል፡፡
መመርያው 600 ብር የነበረውን የሌሎች ሾፌሮች የትርፍ ሰዓት ሥራ አበል ከእጥፍ በላይ አድጎ ወደ 1,300 ብር አድርሷል፡፡
በመመርያው መሠረት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ሾፌር የሆኑ ሠራተኞች ደመወዝ ያለው ሥሌት ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዚዳንቶችና ምክትል ፕሬዚዳንቶች ሾፌሮች በትርፍ ሰዓት ሥራ አበል ያገኙት የነበረው 900 ብር ወደ 1,500 ብር አድርጓል፡፡ በእነዚሁ ተቋማት ውስጥ ያሉ ሌሎች ሾፌሮች ለትርፍ ሰዓት ሥራ የሚከፈላቸው 800 ብር በአምስት መቶ ብር አድጎ 1,300 ብር እንደሚሆን መመርያው ደንግጓል፡፡
ከዚህ ውጪ ለሾፌር ረዳቶችም የሚከፈለው አበል ተሻሽሎ በ400 ብር በመጨመር ወደ 800 ብር አድጓል፡፡
የጥበቃ ሠራተኞችን በተመለከተ መመርያው፣ በ2001 ዓ.ም. በወጣው መመርያ መሠረት እስካሁን ሲሠራበት የነበረው የትርፍ ሰዓት ሳይከፈል፣ 24 ሰዓት እየሠሩ 48 ሰዓት እንዲያርፉ የሚያደርግ አሠራር እንዲቀጥል አድርጓል፡፡
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ያወጣው መመርያው፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያ ከፍተኛ ወጪ ሊያስከትል ስለሚችል ማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት በትርፍ ሰዓት አፈቃቀድ ላይ ኃላፊነት የተሞላበት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳስቧል፡፡
በፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች ደመወዝ ስኬል ለመጨረሻ ጊዜ የተሻሻለው ከሶስት ዓመት በፊት በ2011 ዓ.ም. ነበር፡፡
ይሁንና ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የታየው የዋና ንረት በማስመልከት፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጨምሮ የተለያዩ አካላት መንግሥት የደመወዝ ስኬልን እንዲጨምርና የዝቅተኛ ደመወዝ ወለልን የሚወስን ቦርድ እንዲያቋቁም መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት እንግሊዝኛው ዘ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ንግሥት ጌታቸው፣ ኮሚሽኑ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች የዋጋ ንረቱን የሚቋቋሙበት ስትራቴጂካዊ መንገዶችን በመለየት ላይ መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡