ክተለያዩ ሚዲያዎች የተውጣጡ ባለሙያዎች በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አሰባሳቢነት በህዳሴ ግድብና በሌሎች የውኃ ሀብቶች ላይ በአንድነት የሚሠራ የሚዲያ ፎረም ተመሠረተ።
ፎረሙ ሌሎች አገሮች የኢትዮጵያን ጥቅም በሚነካና በሚያዛንፍ መንገድ ለሚያነሱትም አጀንዳ፣ በአንድነት የአገርን ጥቅም ለማስጠብቅና ለመመከት በትብብር የሚሠራ ነው ተብሏል፡፡
ማክሰኞ ሐምሌ 19 ቀን 2014 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል በተደረገ የፎረሙ ምሥረታ ላይ ቢያንስ በሦስት ወራት አንድ ጊዜ እንዲሰበሰብና በወር አንድ ጊዜም የበይነ መረብ ስብሰባዎችን እንዲያካሂድ ሐሳቦች ቀርበው ውይይት ተደርጓል፡፡ ፎረሙ በዚህ መሠረት ስብሰባውን እንደሚያካሄድ ውሳኔ ላይ ተደርሷል። አባላትም የተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችና የኢሜይል አድራሻዎች በአንድነት ሐሳባቸውን በየጊዜው እንዲገልጹ፣ እንዲሁም ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱን ማዕከል በማድረግ መረጃዎችን ማሠራጨት እንዲቻል ሐሳብ ቀርቦ ተወስኗል።
በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን በሚመለከት ከውጭ አገሮች (በተለይም ከግብፅ) የሚወጡ ዘገባዎችና የሚቀረፁ አጀንዳዎች ላይ በተደጋጋሚ መልስ ለመስጠት በሚደረጉ ሒደቶች ላይ እንደምትጠመድ በመጥቀስ፣ ከሚዲያ ባለሙያዎች ጋር በተመሠረተው ፎረም ግን ራሱ የተለያዩ አጀንዳዎችን በመቅረፅ መሥራት እንዳለበት፣ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢንጂነር) በውይይቱ ወቅት ገልጸዋል፡፡
ከኢትዮጵያና ከተፋሰሱ አገሮች የሚመነጨው የዓባይ ውኃ ግብፅን አልፎ ሜድትራንያን ባህር ውስጥ እንደሚገባ በተጨማሪም ሌሎች እጅግ በርካታ ተያያዥ ኢትዮጵያን በትርክት ሊያግዙ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ መነጋገር እየተቻለ በበቂ መጠን ያለማንሳት ችግር እንዳለ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
‹‹ይህን ደግሞ ለማድረግ ብቃትም፣ ሰዎችም፣ የመገናኛ ዘዴዎችም ያሉን ሲሆን ያጣነው ነገር ቢኖር መሰባሰብና አብሮ ቁጭ ብሎ መነጋገር ነው፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ አስረድተዋል። ምን መደረግ እንዳለበት፣ ከጋዜጠኛችስ ምን እንደሚጠበቅ፣ ከኃላፊዎችም ምን እንደሚጠበቅና ምን ምን ዓይነት አጀንዳዎች መውጣት እንዳለባቸውም በውይይት መስማማቶች ላይ መደረስ እንዳለበት አብራርተዋል።
ተሳታፊ የነበሩት በርካታ የሚዲያ ባለሙያዎች ሐሳባቸውንና በዚህ ፎረም አማካይነት ምን ምን ዓይነት ተግባራት መከናወን እንዳለባቸው ሐሳባቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም የተለያዩ መረጃዎችን ሲጠየቁ ያለ ማጋራት፣ እንዲሁም በሚያስፈልግ ጊዜ በፍጥነት አለማሠራጨት እንደ ችግር ተነስተዋል።
የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ዓለም አቀፍ ተቀባይነት አለማግኘትና ለዚያም አለመጣር፣ የሥራ ኃላፊዎችም ሆኑ አንጋፋ ባለሙያዎች በዓለም አቀፍ ሚዲያ በበቂ ሁኔታ ቀርበው የኢትዮጵያን አቋም በደንብ አለመግለጻቸው እስከ ዛሬ ድረስ ከነበሩት ተግዳሮቶች ዋነኛዎቹ መሆናቸውንም የሚዲያ ባለሙያዎች ገልጸዋል።
በሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ የኃይል ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሡልጣን ዎሊ (ዶ/ር/ኢንጂነር) በበኩላቸው፣ የመረጃ ክፍተት እንዳለ በመግለጽ ከእነዚህም ውስጥ ዋነኛው ምን ዓይነት የውኃ ሀብት እንዳለና ይህንን በመረጃ የማጠናከር ችግር እንዳለ ጠቁመዋል፡፡
በመድረኩ ተሳታፊ የነበረውና በተለያዩ የዓረብኛ ሚዲያዎች ላይ በኢትዮጵያ ጉዳይ በተደጋጋሚ በመከራከር የሚታወቁት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ መሐመድ አልአሩሲ፣ የአገር ውስጥ ሚዲያዎች በውጭ የሚገኙ ሚዲያዎች ለሚቀርፁዋቸው አጀንዳዎች መልስ በመመለስ ሥራ ላይ ብቻ መጠመዳቸውን ገልጸዋል። ‹‹በኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘሩት አጀንዳዎች ከክብደታቸው የተነሳ ወገባችንን የሚሰብሩ ናቸው፤›› ሲሎ አቶ መሐመድ አስረድተዋል፡፡
በዓለም ላይ የሚገኙት ትልልቅ ሚድያዎች በኢትዮጵያና በሱዳን ጉዳዮች ላይ ብቻ ፕሮግራም ሲሠሩ ምንም የማያገባቸውን ግብፃውያንን እንደሚጋብዙ አቶ መሐመድ ገልጸው፣ እሳቸውም ምንም እንደማይሠሩ በመግለጽ የሚሳተፉባቸው እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ሚዲያዎቹ ስለኢትዮጵያ በደንብ እንደሚያውቁና እንደሚያጠኑ አስረድተዋል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከኢትዮጵያ የሚቀርቡ እንግዳዎችን ለማጨናነቅና ለማሳነስ እንደሚሞክሩ ገልጸዋል።
‹‹እኔ ከዚህ በፊት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንግዳ ሆኘ ስቀርብ ከአንድ ብሔር በኩል ብቻ በማያያዝ ለመላው አገሪቱ ምንም እንደማያገባኝ፣ አንተ የዚህ ብሔር ወኪል ሆነህ ለዚህኛው ምንም አያገባህም በማለት ክርክሮች ገጥመውኛል፤›› በማለት ተቃራኒ ሆነው የሚገጥሙዋቸው ሚዲያዎችና ተከራካሪ እንግዶች ምን ያህል አጥንተውና ተዘጋጅተው እንደሚመጡ አብራርተዋል፡፡