በኢትዮጵያ የባንኮች ቁጥር 30 የደረሰ ቢሆንም ከጥቂቶቹ በስተቀር የአብዛኞቹ ባንኮች ካፒታል አነስተኛ በመሆኑ ካፒታላቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡
ይናገር (ዶ/ር) ይህንን የገለጹት፣ ፀሐይ ባንክ በይፋ ሥራ መጀመሩ በተበሰረበት ፕሮግራም ላይ ነው፡፡ በገበያ ውስጥ ከ16 እና 17 ዓመታት በላይ የቆዩ አንዳንድ ባንኮች ሳይቀሩ ካፒታላቸውን ማሳደጋቸውን ያስታወሱት ገዥው፣ ባንኮች ካፒታላቸውን ማሳደግ አለባቸው ብለዋል፡፡ ካፒታላቸውን ያላሳደጉ ባንኮች ከዚህ በኋላ የሚወዳደሩት ከውጭ ባንኮች ጋር ጭምር በመሆኑ፣ ካፒታላቸውን በማሳደግ በሁሉም ዘርፍ ዝግጁ መሆን እንዲሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ የባንኮች ቁጥር 30 መድረሱን የገለጹት ይናገር ደሴ፣ ከእነዚህ ባንኮች ጥቂቶቹ ብቻ የተሻለ ካፒታል እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ፀሐይ ባንክን ሥራ ለማስጀመር ካፒታሉ በቂ ቢሆንም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተሻለ ካፒታል እንዲኖረው በማድረግ ረገድ የባንኩ አመራሮች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ይናገር (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡ ባንኮች ካፒታላቸውን የማሳደግ አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት የሰጡት፣ የውጭ ባንኮች ሲገቡ ተወዳዳሪ ለመሆን አንዱ አስፈላጊው ነገር ካፒታል በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡
‹‹የውጭ ባንኮች እንዲገቡ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው፡፡ እነዚህ ባንኮች የኢትዮጵያን የባንክ ገበያ ከተቀላቀሉ ውድድሩ ቀላል ይሆናል ተብሎ አይታሰብም፤›› በማለት የባንኮች ካፒታል ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ይህንን ውድድር ለማለፍ ፀሐይ ባንክም ሆነ ሌሎች ባንኮች ከዚህ በኋላ ከአገር ውስጥ ባንኮች ጋር መወዳደር ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ከውጭ ባንኮች ጋር ጭምር በመሆኑ፣ ለዚህ የሚሆን በቂ ዝግጅት በሁሉም መስክ ማድረግ እንደሚኖርባቸው የብሔራዊ ገዥው ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡
አዳዲስ ባንኮች ኢንዱስትሪውን እየተቀላቀሉ መሆናቸውን በማስመልከት ሲናገሩ፣ አዳዲስ ባንኮች ወደ ባንክ ኢንዱስትሪው እየገቡ መሆናቸው ጥሩ ነው ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እስካሁን ባለው ደረጃ ወደ 30 ባንኮች፣ 40 የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት እንዳሉት፣ የሊዝ ፋይናንሲንግ ተጨምሮ ወደ 89 የፋይናንስ ተቋማት ይገኛሉ ብለዋል፡፡ ከ30 ባንኮች በተጨማሪ የተወሰኑ በምሥረታ ላይ እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡ ካለፉት አራት ዓመታት ወይም ከለውጡ ወዲህ በርከት ያሉ ባንኮች እየተቋቋሙ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡
በመሆኑም የባንኮች ቁጥር መጨመር ለማኅበረሰቡ የሚጠቅም እንጂ ምንም የሚጎዳ ነገር የለውም ብለዋል፡፡ ከይናገር (ዶ/ር) ንግግር መረዳት እንደተቻለው፣ ባለፈት አራት ዓመታት ብቻ 12 አዳዲስ ባንኮች ተቋቁመዋል፡፡ ከ1983 ዓ.ም. እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ የተቋቋሙ የግል ባንኮች 16 ነበሩ፡፡ ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች ጋር አጠቃላይ የባንኮች ቁጥር 18 እንደነበር ይታወሳል፡፡
‹‹ስለዚህ ዘግይታችሁ የገባችሁም ብትሆኑ የእኛ አገር የባንክ ተደራሽነት ገና በመሆኑና ገበያውም ስላለ የፋይናንስ ተቋማት የሚያሠጋቸው ነገር አይኖርም፤›› ብለዋል፡፡
የባንክ አገልግሎት ዓይቶ የሚያውቅ የኅብረተሰብ ክፍልን ተደራሽ ለማድረግ ባንኮች፣ የማይክሮ ፋይናንስ፣ የኢንሹራንሽና የሊዝ ኩባንያዎችን ማቋቋም መሠረታዊ ተደርጎ የሚታይ በመሆኑ በገበያ ደረጃ የሚያስፈራ ምንም ነገር እንደማይኖር፣ አዳዲስ የፋይናንስ ተቋማት ቢገቡ ገበያው እንደሚኖራቸው ጠቁመዋል፡፡
‹‹ፀሐይ ባንክ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በኋላ የሚቀቋቋሙ ባንኮች ስለሚኖሩ የገበያ ችግር የለባቸውም፤›› ያሉት ይናገር (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያን የንግድ ሕግና የብሔራዊ ባንክ መመርያዎችን መሠረት አድርጎ ለሁሉም ማኅበረሰብ በመላ ኢትዮጵያ አገልግሎቱን በተሻለ ቅልጥፍና እየተሰጠ ከተሄደ፣ ዘግይቶ የተቋቋመም ባንክ ቢሆን ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ዕድሉ ሰፊ ስለመሆኑ አመልክተዋል፡፡ ገበያው ውስጥ የቆዩ ቁጭ ያሉ ባንኮች መኖራቸውን፣ ካፒታላቸው ብዙም ያላደገ ባንኮች እንዳሉ ገልጸው፣ ‹‹ከእነዚህ ባንኮች በተሻለ ሁኔታ የቴክኖሎጂ አቅም፣ የተሻለ የሠራተኛና የተሻለ የአገልግሎት አሰጣጥ ይዛችሁ ወደ ገበያ መግባት ከቻላችሁ ስኬታማ መሆን ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡
የፀሐይ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ታዬ ዲበኩሉ በበኩላቸው፣ ባንካቸው የካፒታል አቅሙን ከፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ እንዳመለከቱም የባንኩን ካፒታል ከማሳደግ አንፃር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያስመቀጠውንና ዝቅተኛ መነሻ ካፒታል የሆነውን አምስት ቢሊዮን ብር፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማሟላት ዕቅድ ይዞ በመሥራት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
‹‹በአገራችን የባንክ አገልግሎት ተደራሽነት፣ አካታችነት፣ እንዲሁም በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዙሪያ ሰፊ ክፍተት እንዳለ ይታወቃል፤›› ያሉት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ ይህንን ክፍተት በመመልከት ከዘመኑ ጋር የሚሄድ የባንክ አገልግሎት በመስጠት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የራሱን ተፅዕኖ የማሳረፍ ተልዕኮን አንግቦ የባንክ ኢንዱስትሪውን የተቀላቀለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ፀሐይ ባንክ ባለፈው ቅዳሜ 30 ቅርጫፎቹን በአንዴ በማስጀመር ሥራ የጀመረ መሆኑን የገለጹት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ያሬድ መስፍን፣ ቅርንጫፎቹ 50 እንደሚደርሱና ለበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ ደግሞ 100 ቅርንጫፎች ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ባንኩ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በተለይ ለአነስተኛ ተበዳሪዎች ብድር በማቅረብ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ፀሐይ ባንክ ከሌሎች የአገሪቱ ባንኮች በተለየ 373 ባለአክሲዮኖችን ይዞ የተቋቋመ ሲሆን፣ ወደ ሥራ የገባውም በእነዚሁ ባለአክሲዮኖች በተከፈለ 734 ሚሊዮን ብርና በተፈረመ 2.9 ቢሊዮን ብር ካፒታል ነው፡፡ ፀሐይ ባንክ አገልግሎት መጀመሩን አስመልክቶ አራት የተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች 1.6 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡