Saturday, December 9, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ፖለቲከኞች ሕዝቡን ለቀቅ አድርጉት!

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከሚታወቅባቸው አኩሪ ባህሪያቶቹ መካከል የሚጠቀሱት፣ ሕግ አክባሪነቱና ሰላም ወዳድነቱ ናቸው፡፡ ከሕግ አክባሪነቱና ከሰላም ወዳድነቱ ጋር ደግሞ ለዘመናት በጋራ የገነባቸው ትውልድ ተሻጋሪ ማኅበራዊ እሴቶቹ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ እርስ በርስ በሚያደርጋቸው የዕለት ተዕለት መስተጋብሮቹ ተዋዶና ተከባብሮ መኖር ብቻ ሳይሆን፣ የብሔርና የሃይማኖት ልዩነቶች ሳይገድቡት በጋብቻ ጭምር የተሳሰረ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት ውስጥ በሚገኙ መልክዓ ምድሮች ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ አንዳቸውን ከሌላቸው ለመለየት እስከሚያስቸግር ድረስ ተመሳሳይ ሕይወት ነው ያላቸው፡፡ በተለይ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮችም ሆኑ አርብቶ አደሮች በተመሳሳይ የኑሮ ዘይቤ ውስጥ ሆነው ነው የሚኖሩት፡፡ አንዱ ደጋ ሌላው ቆላ፣ አንዱ ወይና ደጋ ሌላው በረሃ ውስጥ ቢኖሩም ከአለባበስ እስከ አመጋገብ ድረስ የሚስተዋለው ተመሳሳይነት በጣም አስገራሚ ነው፡፡ ይህንን እርስ በርሱ በሰላምና በፍቅር ሲኖር የነበረ ተመሳሳይ ሕዝብ ነው፣ ፖለቲከኞች መሀሉ እየገቡ ልዩነቶችን በአጉሊ መነጽር እየፈለጉ ማፋጀት የሚፈልጉት፡፡

ከኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ አኩሪ መገለጫዎች መካከል የብሔር፣ የእምነት፣ የቋንቋ፣ የባህልና ሌሎች ልዩነቶችን ዕውቅና በመስጠት ተሳስቦና ተከባብሮ መኖር ትልቁ እሴት ነው፡፡ የዘመኑ ፖለቲከኞችና አጋፋሪዎቻቸው ግን ለዘመናት የተገነባውን የአብሮነት እሴት በመናድ፣ አንዱ በሌላው ወገኑ ላይ ጭካኔ የተሞላበት ወንጀል እንዲፈጽም መገፋፋት ትልቁ ተግባራቸው ሆኗል፡፡ ልዩነቶችን ጌጦቹ አድርጎ ሳያፍር ለዘመናት አብሮ የኖረ ሕዝብ ውስጥ ጥላቻ በመዝራት ቅራኔ መፍጠር፣ የዘመኑ ትውልድ ባልኖረበት ዘመን ትርክት መወንጀል፣ የገዛ ወገንን መጤና ባለቤት በማለት መከፋፈል፣ ተፈጥሯል ለተባለ ክስተት ዕዳ መክፈያ ይመስል በጭካኔ መጨፍጨፍና ለማመን የሚከብዱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸም ተለምዷል፡፡ ይህ ሁሉ ግፍና ሰቆቃ ሲፈጸም ግን ከፖለቲከኞችና ከአጃቢዎቻቸው ውጪ ማኅበረሰቡ ውስጥ የሚታወቅ ጠብም ሆነ ጥላቻ የለም፡፡ በተደጋጋሚ በሚፈጸሙ ግድያዎች፣ ማፈናቀሎችና ዘረፋዎች ውስጥ በፖለቲከኞች ግፊት እንዲሳተፉ የሚደረጉት፣ በዕድሜም ሆነ በአዕምሮ ብስለት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ናቸው፡፡ ከዚያ ውጪ ኢትዮጵያውያን አንዳቸው በሌላቸው ላይ የሚጨክን አንጀት የላቸውም፡፡

ጀግኖቹ የኢትዮጵያ አትሌቶች አገራቸውን በዓለም የስፖርት አደባባይ በሜዳሊያ ሲያንቆጠቁጡና በሰንደቅ ዓላማቸው ሲዋቡ፣ በተልካሻ የፖለቲካ ዓላማ የሚያነክሱ ወረበሎች ደግሞ የሚሠሩትን እየታዘብን ነው፡፡ እናት አገራቸውን ኢትዮጵያን ወክለው ታሪክ የሠሩትን ጀግኖች አትሌቶች፣ መንደርና ጎጥ ውስጥ በመሸጎጥ ሊያሳንሷቸው መከራቸውን ያያሉ፡፡ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ለብሰው ታላላቅ ድሎችን የተጎናፀፉ ጀግኖችን ለክብራቸው የማይመጥን ደረጃ ሊሰጧቸው ይጋጋጣሉ፡፡ በሌሎችም መስኮች ሌሎች ወገኖችንም አገርን ከምታህል ደረጃ አውርደው በማሳነስ፣ የኢትዮጵያዊነትን ክብር በተደጋጋሚ ሲዳፈሩ ተስተውለዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ከራሳቸው በፊት ለአገርም ሆነ ለሕዝብ ምንም ደንታ የሌላቸው ስለሆኑ፣ የእነሱ ፍላጎት እስካልተሳካ ድረስ ሚሊዮኖች ቢያልቁ ደንታቸው አይደለም፡፡ እንኳንስ ለወጣቱ መማርና መለወጥ፣ ለአጠቃላይ ሕዝቡ የኑሮ ዕድገት ቀርቶ ለአገር ህልውናም ደንታ የላቸውም፡፡ እነሱ ቀንና ሌሊት የሚማስኑት ለሥልጣንና ይዞት ለሚመጣው ጥቅም ብቻ ስለሆነ፣ የእነሱን ፍላጎት እስካረካ ድረስ ኢትዮጵያ ዘጠኝ ቦታ ብትሸነሸን ድጋፋቸውን ከመስጠት ወደኋላ አይሉም፡፡ አዋጭ ሆኖ ካገኙትም የሽንሸናው ዋና መሐንዲስ ከመሆን አይመለሱም፡፡ በዚህም ምክንያት በሕዝብ ስም እየነገዱ ፍላጎታቸውን ለማርካት ማንኛውንም ወንጀል ይፈጽማሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ ከወረዳነት ወደ ልዩ ወረዳነት፣ ከልዩ ወረዳነት ወደ ዞንነት፣ እንዲሁም ከዞንነት ወደ ክልልነት ለማደግ በሚደረገው ፉክክር አንድም ጊዜ የሕዝብ ጥያቄ ስለመሆኑ መረጃ ሲቀርብ አይታወቅም፡፡ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው ግን ፍላጎታቸውን በሕዝብ ስም ሲያቀርቡ፣ ሌላው ቀርቶ ሰላማዊውንና ሕጋዊውን መንገድ ለመከተል ሲቸገሩ ይታያሉ፡፡ የሚያስተዳድሩት ሕዝብ በምግብ፣ በውኃ፣ በኤሌክትሪክ፣ በመጠለያ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በትራንስፖርትና በመሳሰሉት ከፍተኛ ችግር ውስጥ ሆኖ ዞንና ክልል ለመሆን ሲሉ ብቻ የሕዝቡ ዋነኛ ጥያቄ አድርገው ያቀርባሉ፡፡ ሰፊ ለም መሬት፣ በርካታ የውኃ ሀብትና የሰው ኃይል ይዘው ሕዝቡን ለሥራ ከማነሳሳት ይልቅ በድጎማ በጀት ለሚመራ ሥልጣን ሲሉ አመፅ ይቀሰቅሳሉ፡፡ ወደ ዞንም ሆነ ወደ ክልል ሽግግር ቢደረግ ተጠቃሚዎች እነሱና ከበስተጀርባ ሆነው ፋይናንስ የሚያደርጓቸው ባለሀብቶች እንጂ፣ ሕዝብ ከመከራ ይልቅ ምንም ጠብ የሚልለት ነገር እንደሌለ አዳዲሶቹን ክልሎችና ዞኖች ዞር ዞር ብሎ ማየት በቂ ነው፡፡ ሕዝብ የሚተርፈው ነገር ቢኖር በስሙ እየነገዱ ሥልጣን ላይ የተንጠላጠሉና የሀብት ማማ ላይ የወጡ ግለሰቦችንና ቢጤዎቻቸውን ማየት ብቻ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡ እጅግ በጣም ሰላማዊና ለሕግ ትልቅ ትኩረት ስለሚሰጥ ለአመፅና ለብጥብጥ ሥፍራ የለውም፡፡ የፀጥታ አስከባሪዎች በሌሉበት አጋጣሚ ራሱን በሥርዓት ለመምራትም አይቸግረውም፡፡ ነገር ግን ፖለቲከኞች ያገኙትን አጋጣሚ በመጠቀም ከተለመደው አኗኗሩ ውጪ፣ የተውሶ ፖለቲካዊ ዕሳቤዎችንና ርዕዮተ ዓለሞችን እንደ ወረዱ እያመጡ ሕይወቱን ያመሰቃቅላሉ፡፡ በውስጣቸው ያዳበሩዋቸውን የዓመታት ጥላቻዎች፣ ክፋቶች፣ ጭካኔዎችና አስነዋሪ ድርጊቶች በሕዝብ ስም እያግበሰበሱ የዘመናት መልካም እሴቶችን ለማጥፋት ይወራጫሉ፡፡ ፖለቲከኞች ለዓመታት የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም የሚያሠራጩዋቸው መርዞች በሕዝቡ ውስጥ ተቀባይነት ቢኖራቸው ኖሮ፣ ኢትዮጵያን ዛሬ በዚህ ይዘቷና ቅርጿ ማግኘት አይቻልም ነበር፡፡ ይሁንና ከጊዜ ወደ ጊዜ ሃይ ባይ በማጣታቸው ምክንያት ወጣቱን ትውልድ እንዳይበክሉት ግን ፍራቻና ሥጋት አለ፡፡ እነሱ የማይጠረቃውን ፍላጎታቸውን ለማርካት ሲሉ ማንኛውንም ዓይነት ጥፋት ከመደገስ ስለማይመለሱ፣ አገር ወዳድ ዜጎች በሙሉ ተባብረው ሊያስቆሟቸው ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ህልውና አደጋ የሚያጋጥመው አገር ወዳዶች በይሉኝታ ተሸብበው አገር አጥፊዎች እንዳሻቸው ሲፈነጩ እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡

ኢትዮጵያ ሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ትልቁን የውኃ ሀብት፣ ክረምት ከበጋ ምርት የሚሰጡ የአየር ፀባዮች፣ ተዝቀው የማያልቁ የማዕድን ሀብቶች፣ በርካታ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ሃይማኖታዊ የቱሪዝም መስህቦችና ሌሎች የተፈጥሮ ፀጋዎችና በረከቶች ታድላ ሕዝቧ ለምን ይራባል? በመኖሪያ ቤት ዕጦት ለምን ይሰቃያል? በትምህርት፣ በጤና፣ በኤሌክትሪክ ኃይል፣ በንፁህ የመጠጥ ውኃ፣ በትራንስፖርትና በሌሎች መሠረተ ልማቶች ከዓለም ወለል በታች ለምን ሆነ? በተፈጥሮ ፀጋዎች ሀብታም የሆነች አገር ውስጥ እየኖረ ለምን ምፅዋት ጠባቂ ይሆናል? ጥንታዊ ኢትዮጵያውያን በጥበብና በሥልጣኔ አሻራዎችን ጥለው አልፈው፣ በዚህ ዘመን የድህነትና የኋላቀርነት ተምሳሌት መሆን አያሳፍርም ወይ? እነዚህ ጥያቄዎች በቀጥታ የሚመለከታቸው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ተዋናይ የሆኑትን ሁሉንም ፖለቲከኞች ነው፡፡ ፖለቲከኞች በመሀላቸው የሚፈጠሩ ልዩነቶችን በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ መልክ አስይዘው፣ የታፈረችና የተከበረች አገር እንድትኖር ከማድረግ ይልቅ ለሥልጣን ሲሉ ብቻ ሕዝቡን ለምን ያምሱታል? አንዴ በብሔር ሌላ ጊዜ በሃይማኖት እየከፋፈሉ የዘመናት አብሮነቱን ሊነጥቁት ለምን ያሴራሉ? ፖለቲከኞች እናንተ ከአገርና ከሕዝብ አትበልጡምና አደብ ግዙ፣ ሕዝቡንም ለቀቅ አድርጉት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...