ሐምሌ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. በሶማሌ ክልል በአፍዴር ዞን ቆህሌ ወረዳ ኢትዮጵያና ሶማሊያ በሚዋሰኑበት የሁልሁል አካባቢ ጥቃት ለመክፈት ሰርጎ የገባ የአልሸባብ ኃይል 254 አባላት መደምሰሳቸው ተነገረ፡፡ የክልሉ ልዩ ኃይልና የመከላከያ ሠራዊት በሰርጎ ገቡ የአልሸባብ ቡድን ላይ በወሰዱት ዕርምጃ አሸባሪዎቹ መደምሰሳቸውን የክልሉ ባለሥልጣናት አረጋግጠዋል፡፡
አልሸባብ ከዚህ በተጨማሪም በሸበሌ ዞን ፌርፌር ወረዳ አካባቢ ሌላ ዙር ጥቃት ለመክፈት ከትናንት በስቲያ ተንቀሳቅሶ እንደነበር ተነግሯል፡፡ በመከላከያና በክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ የተቀናጀ ኦፕሬሽን ወደ 200 የሚጠጉ ተጨማሪ የሽብር ቡድኑ አባላት መደምሰሳቸውን የክልሉ ባለሥልጣናት ገልጸዋል፡፡
አልሸባብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግሮ አዲስ የሽብር ህዋስ ለመፍጠር ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን የሶማሌ ክልል ባለሥልጣናት አመልክተዋል፡፡ የክልሉ የፀጥታ ምክር ቤት የአልሸባብን ሰርጎ ገብ ህዋስ ለመበጣጠስ በወሰደው ዕርምጃ፣ ከ100 በላይ የቡድኑ አባላትና ቡድኑን ሲረዱ የነበሩ ግለሰቦች ቀደም ብሎ መያዛቸው ተነግሯል፡፡ በኤልከሬ አካባቢ ቡድኑ አስቀድሞ የቀበረው በርካታ የጦር መሣሪያ መያዙንም የክልሉ ባለሥልጣናት ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡
አልሸባብ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚፈጥረው ህዋስ በአመራርነት ያጨው ሼክ መሐመድ ሁሴን ኡስማን፣ በአፍዴር ዞን ኤልከሬ ወረዳ በደው ቀበሌ ሐምሌ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ከ60 ታጣቂዎች ጋር በሶማሌ ክልል የፀጥታ ኃይሎች መደምሰሱን ክልሉ ይፋ አድርጓል፡፡ ባለፈው ሳምንት ከረቡዕ ጀምሮ አልሸባብ በተከታታይ ቀናት በየድና በአቶ መንደሮች፣ እንዲሁም በኤልከሬ በኩል የከፈታቸው ጥቃቶችም የአመራሩን መገደል ለመበቀል ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡
ይሁን እንጂ እነዚህን ጥቃቶች ለመከላከል የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ በርካታ ታጣቂዎች የተማረኩ ሲሆን፣ ከእነዚህ የተማረኩ ታጣቂዎች ውስጥ ደግሞ አብዛኞቹ ኦሮሚኛ ተናጋሪ መሆናቸው አልሸባብ በኤልከሬ በኩል ከኦነግ ሸኔ ኃይሎች ጋር የመቀናጀት እንቅስቃሴ መጀመሩን እንደሚያመለክት የክልሉ ባለሥልጣናት ተናግረዋል፡፡
ወደ 18 ተሽከርካሪዎች ሦስት የሞተር ብስክሌቶች ታጣቂዎችን ይዞ በሶማሊያው በኮል ዞን በኩል በየድና በአቶ መንደሮች የኢትዮጵያን ድንበር ለመሻገር የሞከረው 254 የአልሸባብ ኃይል እንደ አመጣጡ ተመልሷል ሲሉ ለሪፖርተር የተናገሩት የክልሉ ባለሥልጣናት፣ ባዙቃን ጨምሮ የቡድንና የግል መሣሪያዎች ከታጣቂዎቹ መማረካቸውን አረጋግጠዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፋ መሐመድ ኡመርን ጨምሮ ከፍተኛ የክልሉ አመራሮች በግንባር ተገኝተው በዘመቻው የተሳተፉ የፀጥታ ኃይሎችን ማበረታታታቸው ተነግሯል፡፡ የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ትናንት በጎዴ ከተማ የጎሳ መሪዎች፣ ኡጋዞችና የአገር ሽማግሌዎች የተሳተፉበት የፀጥታ ጉባዔ የመሩ ሲሆን፣ አልሸባብ ከሶማሊያ ጋር ሰፊ ድንበርን በሚጋራው የሶማሌ ክልል ሊያደርስ የሚችለውን ጥቃት ኅብረተሰቡ በንቃት እንዲጠብቅ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ክልሉ ይፋ አድርጓል፡፡
ከዚሁ አልሸባብን የማፅዳት ተልዕኮ ጋር በተያያዘ በሶማሌ ክልል የተቋቋመውን የጋራ የፀጥታ ግብረ ሰናይ የሚመሩት የአገር መከላከያ ሠራዊት አመራር ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው በአልሸባብ ሽብር ቡድን አባላት ላይ የተቀናጀ ዕርምጃ መወሰዱን ይፋ አድርገዋል፡፡ በየድ፣ በአቶ፣ በኤልባርዴ፣ በወቀሾና በፌርፌር በኩል የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው ጥቃት ለማድረስ የሞከሩ የአልሸባብ ኃይሎች ላይ የማፅዳት ዘመቻ መካሄዱን ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ መግለጻቸው ተሰምቷል፡፡