Monday, February 26, 2024

መንግሥት ለተመድ ሰብዓዊ መብት መርማሪዎች ፈቃድ ለመስጠት በቅድመ ሁኔታዎች ላይ እየተነጋገረ ነው

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች የባለሙያዎች ኮሚሽን ከትግራይ ጦርነት ጋር ተያይዘው የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር ያቀረበውን ጥያቄ፣ መንግሥት በድጋሚ እያጤነው መሆኑን አስታወቀ፡፡ መንግሥት ባስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎችና ዝርዝር የእንቅስቃሴ አቅጣጫዎች ላይ ከተስማማ፣ ኮሚሽኑ ምርመራውን መጀመር የሚችልበት ዕድል መኖሩ ተገልጿል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት የተሾሙት ሦስት ኮሚሽነሮች ሰኞ ሐምሌ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ለመጀመርያ ጊዜ ኢትዮጵያ የገቡ ሲሆን፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ጋር ተገናኝተዋል፡፡ በስድስት ቀናት ቆይታቸው ከመንግሥትና ከተለያዩ አካላት ጋር በሚያደርጉት ድርድር፣ የምርመራው መጀመርና አለመጀመር የሚወሰን ይሆናል ተብሏል፡፡

ከኢትዮጵያ በኩል የፍትሕ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አብረው ይሠራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ‹‹ከኮሚሽነሮቹ ጋር ተገናኝተናል፡፡ ነገር ግን የሥራ ትብብርን በተመለከተ ሥራውን እንዲጀምሩ ከተፈቀደላቸው በኋላ ነው የምንወያየው፤›› ሲሉ የኢሰመኮ አንድ ኃላፊ ስማቸው እንዳይገለጽ ጠይቀው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ኮሚሽኑ መርማሪዎቹን አምጥቶ ሥራ መጀመር የሚችሉበት ዕድል የሚኖረው፣ ‹‹ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ መንግሥትን መሠረታዊ አቋም ባገናዘበና የብሔራዊ ሕግ ሥርዓቱ ጋር የሚሄድ መርሆዎችን ሲያሟላ፣ ተገቢነት ከሌላቸው የፖለቲካ ፍላጎቶች ከነፃ፣ ከዚህ ቀደም በኢሰመኮና በተመድ የተደረጉ የጥምር ምርመራዎችን የማይደግም ከሆነና የኢትዮጵያ መንግሥት ተጠያቂነትን ለማስፈን እየወሰዳቸው ያሉ ዕርምጃዎችን በማያስተጓጉል መንገድ የሚንቀሳቀስ›› ከሆነ፣ እንዲሁም ‹‹በዝርዝር የእንቅስቃሴ አቅጣጫዎች ማዕቀፍ (Modalities of Engagement)›› ላይ ከተስማማ ብቻ መሆኑን፣ የመንግሥት የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

መንግሥት ከዚህ ቀደም ከነበረው አሉታዊ አቋም አንፃር የውሳኔ መለሳለስ ያሳየ ሲሆን፣ ኮሚሽኑ በቀጥታ ከሕወሓት ጋር የመሥራት አዝማሚያ እስካላሳየ ድረስ ፈቃድ ሊሰጠው እንደሚችል ማሳያ ነው ሲሉ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ ሕወሓትና የኤርትራ መንግሥት በበኩላቸው ኮሚሽኑ እስኮሁን እንዳላማከራቸውና እነሱን ያላካተተ ምርመራ ውጤታማ አይሆንም የሚል አቋም አንፀባርቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ በፓርላማ በአሸባሪነት የተፈረጀውን ሕወሓት በምርመራው ሳያካትት እንዴት ተጠያቂ ሊያደርገው እንደሚችል፣ ኮሚሽኑ ከመንግሥት ጋር እንደሚነጋገርበት ይጠበቃል፡፡

ተመድ መርማሪ ኮሚሽነሩን በመስከረም 2014 ዓ.ም. የትግራዩ ጦርነት በተጀመረ በዓመቱ ያቋቋመው ቢሆንም፣ ኮሚሽኑ እስካሁን ሥራውን ሳይጀምር ቆይቷል፡፡ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ተቀባይነት ሳያገኝ ከመቆየቱም ባሻገር፣ ከተመድ በኩልም በቂ በጀት እንዳልተመደበለት የኮሚሽኑ ዋና ኃላፊ ኬንያዊቷ ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ ባለፈው ወር ተናግረው ነበር፡፡ ጽሕፈት ቤቱን እንቴቤ ያደረገውን ኮሚሽን ሦስት ኮሚሽነሮች ሲኖሩት ሁለተኛዋ ከስሪላንካ፣ እንዲሁም ሦስተኛው ከአሜሪካ የተመረጡ ናቸው፡፡

በኮሚሽነሮቹ ሥር ከሕግ፣ ከወታደራዊ ጉዳዮች፣ ከምርመራና ከትንተና ባለሙያዎች በተጨማሪ የቋንቋ ተርጓሚዎችን ጨምሮ የተለያዩ ባለሙያዎች ይኖሩታል፡፡ ኢትዮጵያ ለኮሚሽኑ በጀት እንዳይመደብ ያቀረበችው አቤቱታ በድምፅ ብልጫ ውድቅ ከተደረገ በኋላ ባለፈው ግንቦት መለሳለስ የጀመረች ሲሆን፣ የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በጄኔቫ ተገኝተው ሦስቱ ኮሚሽነሮች ወደ አዲስ አበባ መጥተው እንዲወያዩ ከጋበዙ በኋላ ነገሮች መሻሻላቸውን ሙሩንጊ ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው አለመግባባትና በዚህ ሳምንት ይፈታል ተብሎ የሚጠበቀው የምርመራው አድማስ ሲሆን፣ የቦታና የጊዜ እንዲሁም የመረጃ አሰባሰብ ሒደቱን የተመለከተ መሠረታዊ ጥያቄ ነው፡፡

መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ከትግራይ ከወጣበት ከሰኔ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የተፈጸሙትን የሰብዓዊ ጥሰቶች ኮሚሽኑ እንዲመረምር ይፈልጋል፡፡ ይህም ከዚያ በፊት ያለው በጥምር ሪፖርቱ የተሸፈነ በመሆኑ ነው፡፡

ኮሚሽኑ ምንም እንኳ የጥምር ሪፖርቱን እንደ መነሻ የሚጠቀም መሆኑን የገለጸ ቢሆንም፣ ምርመራውን የሚጀምረው የትግራዩ ጦርነት ከተጀመረበት ጥቅምት 2013 ዓ.ም. እንደሚጀምር፣ ከትግራይ በተጨማሪ በቅርቡ በምዕራብ በኦሮሚያ ክልል የተፈጸሙ ጥሰቶችን ምርመራው እንደሚያካትትና አገር ውስጥ ካሉ ባለድርሻዎች በተጨማሪ ስደተኞችን ያስጠለሉ ጎረቤት አገሮችንም እንደሚያነጋግር ገልጿል፡፡ ለዚህም ተጎጂዎችንና ቤተሰቦችን፣ የዓይን እማኞችንና ከጥቃት ያመለጡ ሰዎች ያሉባቸው አካባቢዎች ገብቼ መረጃ እንድሰበስብ ይፈቀድልኝ በማለት መንግሥትን ጠይቋል፡፡

ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች፣ የበጎ አድራጎትና የስደተኞች መብት ተጥሷል ያለ ሲሆን አንዳንዶቹ እስከ ጦር ወንጀልና በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ሊደርሱ እንደሚችሉ ሲያስታውቅ ነበር፡፡

‹‹የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ፣ የአማራና የትግራይ ኃይሎች ሁሉም ለወንጀሎቹ ተሳታፊ ናቸው፡፡ እኛ የምንመረምረው ወካይ የሆኑና ከመለኪያዎቻችን ጋር የሚሄዱትን ጉዳዮች ነው፡፡ በአዲስ አበባ የምናደርገው ቆይታና ንግግር ወንጀሎቹ የተጸሙበትን ቦታ እንድናይና ሰለባዎችን እንድናገኝ በመፍቀድ ይጠናቀቃል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፣ ሲሉ ሙሩንጊ አስረድተዋል፡፡

‹‹አሁን የሚኖረው በሒደት (Procedure) ላይ የሚደረግ ውይይት ሲሆን፣ ጄኔቫ ላይ የነበረው ውይይት ቀጣይ እንጂ ኮሚሽኑ ሥራ እንዲጀምር ተፈቀደለት ማለት አይደለም፤›› ሲሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -