Thursday, September 21, 2023

ሰርጌይ ላቭሮቭ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን በኢትዮጵያ ለማጠናቀቅ አዲስ አበባ ገቡ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ትናንት ከሰዓት አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የደረሱ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አቻቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኰንን አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ ላቭሮቭ ዛሬ ረቡዕ በአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ አገሮች አምባሳደሮችን ሰብስበው በማወያየት የአራት ቀን ጉብኝታቸውን ያጠናቅቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ላቭሮቭ እሑድ ሐምሌ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. ከግብፅ አቻቸው ሳሚ ሹክሪ ጋር የዓረቡ ዓለም በዩክሬን ጦርነት ላይ የጠራ አቋም እንዲይዝ፣ በጦርነቱ የተስተጓጎለው የነዳጅ፣ ስንዴ፣ ማዳበሪያ፣ የዘይትና የተለያዩ ሸቀጣሸቀጦች ግብይት እንዲጀመርና እንዲሁም ሩሲያ ለግብፅ የምታስገነባውን የኑክሌር ኃይል ግንባታን በተመለከተ ተመካክረዋል፡፡ በቀጥታም ኮንጎንና ዩጋንዳን የጎበኙ ሲሆን፣ ኡጋንዳም በተመሳሳይ የኑክሌር ኃይል እንዲገነባላት ጠይቃለች፡፡

ላብሮቭ አገራቸው በጦርነት መሀል እያለች ወደ አፍሪካ ጉዞ ማድረጋቸው ምዕራባውያን፣ የአፍሪካን ልብ ለማሸፈት የብድር ማስተካከያና የዕርዳታ ዲፕሎማሲ መጠቀም ጀምረዋል፡፡ አለፍ ሲልም ከሩሲያ ጋር የሚተባበሩ አገሮችን የሚቀጣ ረቂቅ አዘጋጅተዋል፡፡  በባለፈው ሳምንት ብቻ አሜሪካ ለምሥራቅ አፍሪካ የ1.3 ቢሊዮን ዶላር ዕርዳታ ለመስጠት ቃል ገብታለች፡፡

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪም በበኩላቸው የአፍሪካ አገሮች ሩሲያና እንዲያወግዙና ከሩሲያ ጋር ግንኙነት እንዲያቆሙ ሲወተውቱ መሰንበታቸው ይታወሳል፡፡

ምዕራባውያን በተለይ ሩሲያን ለመቅጣት ተመድን የሚጠቀሙ ከሆነ፣ የ54ቱ የአፍሪካ አገሮች ድምፅ አስፈላጊ መሆኑ ስለማይቀር፣ ሩሲያ በአፍሪካ ካላት ተሰሚነት ጋር ፉክክር ውስጥ መግባታቸው አፍሪካን ከሁለቱም ጎራ ተጠቃሚ ያደርጋታል፡፡

ሩሲያ ኢትዮጵያን ከትግራዩ ጦርነት ጋር በተገናኘ በተደጋጋሚ ከምዕራባውያን ማዕቀብ ያስጣለቻት ሲሆን፣ ሩሲያ በምላሹ ከኢትዮጵያ ታማኝነቷን ትጠይቃለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይሁን እንጂ ላቭሮቭ ለግብፅ የኑክሌር ኃይል ለማስታጠቅ መወሰናቸው ኢትዮጵያ በዓባይ ጉዳይ ካለባት እሰጥ አገባ አንፃር የሦስቱን አገሮች ግንኙነት አዲስ ቅርቃር ውስጥ ከቷል፡፡

ላቭሮቭ በቆይታቸው በኢትዮጵያና ታዳጊ አገሮች ላይ ጫና እየፈጠረ ያለውን የግብርና ግብዓትና መሠረታዊ ምርቶች ላይ መፍትሔ ይሰጣሉ ተብሎ በዋናነነት ይጠበቃል፡፡ ላቭሮቭ በ2010 ዓ.ም. ኢትዮጵያን የጎበኙ ሲሆን ባለፈው ዓመት ደግሞ አቶ ደመቀ ሩሲያን ጎብኝተዋል፡፡ ላቭሮቭ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን መጠናቀቅ አስመልክተው ዛሬ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -