Tuesday, February 20, 2024

የፌዴራል መንግሥት በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች የተከሰተውን ድርቅ በይፋ እንዲያሳውቅ ኢሰመኮ ጠየቀ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከ300 ሺሕ በላይ ተማሪዎች በድርቅ ምክንያት ከትምህርት ውጪ ሆነዋል

የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ምክር ቤት ሕግ በሚያዘው መሠረት በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች ስለተከሰተው ድርቅ የፌዴራል መንግሥት በይፋ ለሕዝብ እንዲያሳውቅ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጠየቀ፡፡

በብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ማቋቋሚያ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 363/2008 መሠረት፣ አደጋዎች ተከስተው በአጥጋቢ ሁኔታ ለመቋቋም ካልተቻለ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ምክር ቤት አደጋ መከሰቱን በይፋ ለሕዝብ ማሳወቅ እንዳለበት ቢደነግግም፣ ይኼ አለመፈጸሙን ኢሰመኮ አስታውቋል፡፡

መንግሥት የተከሰተውን ድርቅ በወቅቱ ባለማሳወቁ ምክንያትም ድርቅ ባለባቸው አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍና አገር በቀል ድርጅቶች፣ ካለው ችግር ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ሀብት አሰባስበው ድጋፍ ማድረግ አለመቻላቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡ ከዚህ ባሻገር የድርቁን አደጋ ቅነሳ፣ ቅድመ ማስጠንቀቂያና የዝግጅት ሥራዎች በይፋ አለመከናወናቸውን የጠቀሰው ኢሰመኮ፣ ለድርቅ አደጋው የተሰጠው ምላሽ የዘገየ እንዲሆን ምክንያት መሆናቸውን አስረድቷል፡፡

ኢሰመኮ ይህንን ያስታወቀው በሁለቱ ክልሎች የተከሰተውን ድርቅና ያደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ በየካቲት ወር ያደረገውን ምርመራ ውጤት፣ ማክሰኞ ሐምሌ 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ ባደረገበት በባለ 50 ገጽ ሪፖርቱ ነው፡፡

ሪፖርቱ እንደሚያሳየው፣ በሁለቱ ክልሎች 4.2 ሚሊዮን ሰዎች ለውኃ እጥረት ተዳርገዋል፡፡ ምግብን በሚመለከት ደግሞ በሶማሌ ክልል ብቻ 3.3 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው አስታውቋል፡፡

በድርቁ ሳቢያ በተከሰተው የምግብና የውኃ እጥረት ምክንያት የሰዎች የበሽታ የመቋቋም አቅም የተዳከመ በመሆኑ፣ በተለይም ሕፃናት፣ አረጋውያንና ከተለያዩ በሽታዎች ጋር  የሚኖሩ ሰዎች ለጤና ችግር መዳረጋቸውን ኢሰመኮ ገልጿል፡፡ ከዚህም የተነሳ በሕፃናት፣ በሚያጠቡ ሴቶች፣ በነፍሰ ጡር እናቶችና በአረጋውያን ላይ የሰውነት መቀነስና ማበጥ መከሰቱን ከጤና ተቋማትና ከተጎጂዎች ባሰባሰባቸው መረጃዎችና ማስረጃዎች ማረጋጋጥ መቻሉን በሪፖርቱ አካቷል፡፡

በተጨማሪም በሶማሌ ክልል ነዋሪዎች ከመንግሥት ነፃ የሕክምና አገልግሎት እያገኙ እንዳልሆነ ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡ ሪፖርቱ አክሎም፣ ‹‹ይህ የሚሆነው ማኅበረሰቡ ለጤና መድን ሽፋን ተብሎ 400 ብር እንዲያዋጣ በተደረገበት ዓውድ መሆኑን የማኅበረሰቡ አባላት ይገልጻሉ፤›› ሲል ግኝቱን አስረድቷል፡፡

የኮሚሽኑ ሪፖርት እንደሚያሳየው ክትትል እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ ብቻ፣ በሁለቱ ክልሎች የተከሰተው ድርቅ ከ1.3 ሚሊዮን በላይ እንስሳት እንዲሞቱ ምክንያት ሆኗል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ብቻ የሞቱት እንስሳት የገንዘብ ተመን 7.3 ቢሊዮን ብር እንደሆነ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ በዞኑ መከናወን የነበረበት የድርቅ ምላሽ የከብቶች መኖን በነፃ ማከፋፈልን የሚያካትት ቢሆንም፣ በቦረና ዞን ያሉ ማኅበረሰቦች የከብቶች መኖ የሚያገኙት በግዥ እንደሆነ መግለጻቸውን የኢሰመኮ ሪፖርት ገልጿል፡፡

ድርቁ ያስከተለው የምግብ እጥረትና በድርቁ ምክንያት በደረሰባቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና የሥነ ልቦና ጉዳት የተነሳ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በመቀጠል ረገድ ተግዳሮት እንደገጠማቸውን ሪፖርቱ አስረድቷል፡፡

በተለይ በሶማሌ ክልል ካሉት 11 ዞኖች በዘጠኙ ድርቁ በመከሰቱ ጉዳቱ ከፍ ብሎ መታየቱን ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡ በክልሉ ከሁለት ሺሕ በላይ ትምህርት ቤቶች በድርቁ ተፅዕኖ እንደ ደረሰባቸው የገለጸው ኢሰመኮ፣ ከእነዚህም ውስጥ 915 በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ መዘጋታቸውን አስረድቷል፡፡ በዚህም ምክንያት 300 ሺሕ የክልሉ ተማሪዎች ትምህርት እንዳቋረጡ በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች ባደረገው ምርመራ የደረሰውን ጉዳት ከማሳወቅ ባሻገር፣ በክልሎቹና በፌዴራል መንግሥት ደረጃ የሚመለከታቸው አካላት ያደረጓቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ዳሷል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ድርቁ ከመከሰቱ በፊት በነሐሴ ወር 2013 ዓ.ም. ከድርቅ ተዛማጅ ሚና ያለው ግብረ ኃይል በቦረና ዞን ደረጃ ተቋቁሞ ድርቁ በሰዎችና በእንስሳት ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት፣ መደረግ ያለበትን ቅድመ ማስጠንቀቂያና ዝግጅትን በተመለከተ የዳሰሳ ጥናት ማካሄዱን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ የጥናቱን ግኝትም የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ በክልሉ ለሚመከታቸው መሥሪያ ቤቶች በወቅቱ እንዳሳወቀ ተጠቅሷል፡፡

ይሁንና የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ለቀረበው ፈጣን የዳሰሳ ጥናት አፋጣኝ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፣ ጥናቱን ወደ ጎን በመተው ሌላ የዳሰሳ ጥናት ለመሥራት ጊዜ በመውሰዱ ለተጎጂዎች የቀረበው ድጋፍ እንዲዘገይ ማድረጉን ኢሰመኮ አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም የክልሉ መንግሥት ምላሽ መስጠት የጀመረው ችግሩ ተባብሶ በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት ማድረሱን የሚያመለክቱ መረጃዎች በተለያዩ አካላት በማኅበራዊ ሚዲያዎች መሠራጨት ሲጀምሩ መሆኑን ሪፖርቱ አስረድቷል፡፡

የሶማሌ ክልል መንግሥት በአንፃሩ ድርቁን የሚመለከቱ የዳሰሳ ጥናቶች በማድረግ የድርቅ አደጋ ምላሽ ዕቅድ ማዘጋጀቱን፣ በጀት መመደቡንና ምላሽ አሰጣጡን በተመለከተ የማስተባበርና የመቆጣጠር ተግባራትን የሚያከናውኑ ጥምር ግብረ ኃይሎች ከመንግሥትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ተውጣጥቶ እንደተመሠረተ ተገልጿል፡፡ ድርቁ መከሰቱ እርግጥ መሆኑ ሲታወቅ፣ የክልሉ መንግሥት የመጠባበቂያ በጀቱን በሙሉ ለድርቁ ምላሽ እንዲውል መወሰኑን፣ እንዲሁም 500 ሚሊዮን ብር ከፌዴራል ግምጃ ቤት መበደሩን፣ በአጠቃላይም ለድርቁ 1.5 ቢሊዮን ብር መመደቡ ታውቋል፡፡

ኢሰመኮ በሪፖርቱ፣ ‹‹ድርቁ በሰው ላይ ጉዳት ያላደረሰው የክልሉ መንግሥት በተሰጠው ወቅታዊና የተቀናጀ ምላሽ አማካይነት ነው›› የሚል እምነት አለው፡፡ ይሁንና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በበኩላቸው፣ ‹‹ድርቁ መምጣቱን በተመለከተ ቅድመ ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውንና በዚህ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ላይ ተመሥርቶ ተገቢው ዕርምጃ ተወስዶ ቢሆን ኖሮ፣ ቢያንስ የድርቁን ጉዳቶች መከላከልና መቀነስ ይቻል እንደነበር፤›› መግለጻቸውን ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ኢሰመኮ፣ ‹‹የፌዴራል መንግሥት የተከሰተውን ድርቅ ሕጉ በሚደነግገው መሠረት በወቅቱ እንዳላሳወቀ፣ ይህም በሚሰጠው ምላሽ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ያሳደረ መሆኑን ተገንዝቧል፤›› ሲል ፌዴራል መንግሥትን ወቅሷል፡፡

የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብና የብሔራዊ የአደጋ ክስተት ሥጋት ሥራ አመራር ፖሊሲና ስትራቴጂ ካካተቷቸው ጉዳዮች አንዱ፣ የድርቅ አደጋን ማሳወቅን የሚመለከት መሆኑን ሪፖርቱ አስታውሷል፡፡

የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 363/2008 አንቀጽ 2 (10) እና 9 (5) እንደ ድርቅ ዓይነት አደጋዎች ተከስተው የሌሎች ድጋፍ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፣ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ምክር ቤት አደጋ መከሰቱን በይፋ ሕዝብ እንዲያውቅ ማድረግ እንዳለበት ስለመደንገጉ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

ነገር ግን በድንጋጌዎቹ መሠረት ድርቁን የማሳወቅ ሥራ በይፋ ባለመከናወኑ፣ በክትትል ሥራው ማረጋገጡን ኢሰመኮ አስታውቋል፡፡ የኮሚሽኑ ሪፖርት የዕርዳታ ድርጅቶች በሚፈለገው መጠን ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ገንዘብ መሰብሰብ አለመቻላቸውን ጠቁሟል፡፡

ድርጅቶቹ ዕርዳታ ለማድረስ የሚጠቀሙትን የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙት ከዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች መሆኑን የጠቀሱ ሲሆን፣ ነገር ግን መንግሥት ድርቁን ባለማሳወቁ ዕርዳታ የሚሰጧቸው አካላት ‹‹የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ አንችልም›› እያሉ መሆናቸውን መግለጻቸው በሪፖርቱ ተካቷል፡፡

በተጨማሪም ድጋፍ ሰጪዎች ለተጎጂዎች በቀጥታ ዕርዳታ ለማድረስ ሲሞክሩ፣ ከመንግሥት በቂ መረጃ ስለማያገኙ ወደ የትኛው የኅብረተሰብ ክፍል መሄድ እንዳለባቸው ለማወቅ እንደሚቸገሩና አንድ ቦታ ምላሽ ሳያገኝ ሌላው ዳግም ምላሽ የሚያገኝበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ሪፖርቱ አስረድቷል፡፡

ኢሰመኮ ድርቁን በተመለከተ በፌዴራል መንግሥት በአፋጣኝ ሊተገበሩ የሚገባቸው ምክረ ሐሳቦች ሲጠቅስ፣ ድርቁን በይፋ የማሳወቅን ጉዳይ በቀዳሚነት አስቀምጦታል፡፡ የድርቁን  አስቸኳይ አደጋነት ማሳወቅ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ያወሳው ኮሚሽኑ፣ ‹‹የድርቁ አደጋ አሁንም ያልተቀረፈ በመሆኑ መንግሥት አግባብነት ያላቸው ሕግጋትና ፖሊሲዎች በሚደነግጉት መሠረት ድርቁን በተመለከተ በይፋ የማሳወቅ ተግባር ሊፈጽም ይገባል፤›› በማለት አሳስቧል፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -