Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርለኢትዮጵያና መሰል አገሮች የሚያስፈልጉ አብዮቶች

ለኢትዮጵያና መሰል አገሮች የሚያስፈልጉ አብዮቶች

ቀን:

በአብረሃም ይሄይስ

አገራችን ይበልጥም ከ1960ዎቹ አጋማሽ በኋላ በአብዮት ተጠምዳ የዜጎቿ ኑሮ ከድጡ ወደ ማጡ ሆኗል፡፡ ከዚያ በኋላ በአገራችን የተፈጠሩ፣ የተደራጁ፣ በየጫካውና በየዱሩ የሚንቀሳቀሱ ነፃ አውጪ ግንባሮች ሻል ብሏቸው በከተማ መተዳደሪያ ደንብ ቀርፀው ፓርቲ መሥርተው ምርጫ በመጣ ሰሞን ሕይወት እየዘሩ የሚወዳደሩ ፓርቲዎች ለዚህች አገር የፈየዱትን በጎ ነገር መናገር ከባድ ይሆናል፡፡ የነፃነትንና የዴሞክራሲ ፍቺን ከመጠን በላይ ለጥጠውና አወዛግበው ለሁሉ ነገር መነሻ ጥያቄ፣ ‹‹ዴሞክራሲያዊ መብቴ አልተከበረልኝም፣ ነፃነቴ ታፍኗል፣ በማንነቴ እንድሸማቀቅ ሆኛለሁ፤››  የሚሉ አደረጉብን፡፡

በደርግ ጊዜ ሕዝቡን በመደብ በመለያየት ሠራተኛው፣ ጭቁኑ፣ ባላባቱ፣ ቡርዣው፣ ፊውዳሉ እየተባለ አንዱን ጨቋኝ አንዱን ተጨቋኝ፣ አንዱን በዝባዥ አንዱን ተበዝባዥ በማድረግ አኢወማ፣ አኢሴማና፣ መኢገማ፣ ወዘተ እየተባለ ለሥራ ሳይሆን ለስብሰባ የሚሆኑ አደረጃጀቶች ተፈጥረው አገራችንን የጋለ ምጣድ ላይ ጣዷት፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ያሉት መንግሥታት በአገራችን እየተስተዋሉ ላሉ ችግሮች መፍትሔ ሕዝቡን በብሔርና በሃይማኖት በመለያየት አንዱን ጨቋኝ፣ አንዱን ተጨቋኝ፣ አንዱን በዝባዥ አንዱን ተበዝባዥ እያደረጉ አገሪቱን የጦርነት፣ የብጥብጥ፣ አነስ ሲልም የስድድብ ዓውድማ አደረጓት፡፡

ሁሉም ዓይነት እንቅስቃሴዎች ለተራበ ዜጋቸው ዳቦ አላመጡም፣ ለታረዘ ልብስ አላለበሱም፣ ሥራ ላጣው ወገናቸው ሥራ አልላስገኙለትም፣ ሥልጣኔ ለራቀው ሥልጣኔን አላመጡለትም፣ ሰላም ላጣው ዜጋቸው ሰላም አላስገኙለትም፣ እንዲሁ ‹‹ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ›› ኑሮን በሕዝባቸው ላይ ፈርደው አሉ፡፡ ለዚህ ስለአስፈላጊ አብዮቶች የጽሑፍ መነሻ በአንድ ስብሰባ ላይ በሻይ ሰዓት ከአንድ ጓደኛዬ ጋር የተጨዋወትነው ነው፡፡ ‹‹ህንድ ከአንድ ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎቿን ቀልባ የተረፋትን ለውጭ አገሮች እየላከች ከፍተኛ ገቢ ስላገኘችባቸውና በተለያዩ ቀለሞች ስለሰየመቻቸው አብዮቶች ብታነብ ትገረማለህ፤›› አለኝ፡፡ ጓደኛዬ ማስተርሱን ህንድ መሰለኝ የተማረው፡፡

አንዳንድ ጊዜ ለረዥም ጊዜያት በተለያዩ አገሮች ዲግሪያቸውን፣ ማስተርሳቸውንና ዶክትሬታቸውን የሚሠሩ ዜጎቻችን ከሚማሩት ትምህርት በተጨማሪ ያዩትን፣ የተረዱትንና ይጠቅማል የሚሉትን የአገሮችን የሥልጣኔ፣ የውጣ ውረድ ልምድ የሚያካፍሉበት፣ አገራችን በምን ዓይነት ዘዴ መድረስ እንደምትችል የሚያስረዱበት መድረክ በቋሚነት ቢመቻች የሚል የውስጥ ፍላጎት አለኝ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይቶች ቢካሄዱ ጥሩ ነው፡፡ ጓደኛዬ ብታነብ ትገረማለህ ስላለኝ የህንድ የቀለም አብዮቶች አንብቤ ተደንቄአለሁ፡፡ ይህን ጉዳይ ለራስ ብቻ ማስቀረት ንፉግነት ስለሚሆን እንዲህ ጫጭሬዋለሁ፡፡ የግብርና ሚኒስቴርን ብቻ ሳይሆን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የንግድ ሚኒስቴርን ይበልጥ የሚመለከት ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

የግብርና  አብዮቶች  በህንድ  

የእርሻ አብዮት በግብርናው ዘርፍ የተደረጉ መሠረታዊ ለውጦችን፣ አዳዲስ አሠራሮችን፣ ሳይንሳዊ ግኝቶችን፣ ቴክኖሎጂ አጠቃቀሞችን በሥራ ላይ አውሏል፡፡ ይህም በምርትና በአመራረት ዘይቤ ላይ ዕድገትን አስመዝግቧል፡፡ በግብርናው ዙሪያ የተለያዩ አብዮቶች የተካሄዱ ሲሆን፣ በግብርናው መስክ ፍፁም የሆነ የአዲስ ዘመን ጅማሬ ሆኗል፡፡ የግብርና አብዮት በህንድ የግብርናው ዘርፍ በእጥፍ እጥፍ እንዲያድግና ብዙ ዕድሎችን እንዲፈጥር አድርጓል የግብርና አብዮቶች ዝርዝር (በእንግሊዝኛ ፊደል ቅደም ተከተል)፡፡

ሰማያዊው አብዮት (Blue Revolution)

ይህ አብዮት በገንዳዎችና በኩሬዎች ውስጥ ዓሳ ማርባት ምን ያህል ውጤታማና ትርፋማ እንደሆነ ያስመሰከረ ነው፡፡ ሰማያዊ አብዮት በመንግሥት አነሳሽነት የተጀመረና የውኃ ግብርና (Aquaculture) የዓሳ ሀብት ኢንዱስትሪን በአገሪቱ ለማሳገድ ያለመ ነው፡፡ ይህ የተጀመረው በቻይና ሲሆን፣ በዓለም ሁለት ሦስተኛውን የአኳካልቸር ምርት ታመርታለች፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም የአኳካልቸር ኢንዱስትሪ በዓመት በአማካይ ዘጠኝ በመቶ  እያደገ ሲሆን፣ ህንድ ከፈጣን ዕድገት ካሳዩ አገሮች አንዷ ነች፡፡ ሰማያዊ አብዮት በህንድ የኢኮኖሚ ብልፅግና በማስገኘት ዘላቂ ልማትን፣ የሥነ ሕይወት ጥበቃና የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮችን አካቶ የሚተገበር ነው፡፡ ሰማያዊ አብዮት በህንድ የተጀመረው በሰባተኛው የአምስት ዓመት ዕቅድ (እ.ኤ.አ. ከ1985 እስከ 1990) በዓሳ አምራች ልማት ኤጀንሲና በማዕከላዊ የህንድ መንግሥት ወጪ ስፖንሰርነት ነው፡፡

በመቀጠልም በ8ኛው የአምስት ዓመት ዕቅድ (እ.ኤ.አ. 1992 እስከ 1997) የባህር ላይ አሳ አጥማጆች መርሐ ግብር ተስፋፋ፡፡ የእርሻና የገበሬዎች ደኅንነት ሚኒስቴር ከእንስሳት እርባታ፣ የወተት ልማትና የዓሳ ልማት ዲፓርትመንት ከሰማያዊ አብዮት መርሐ ግብር ጋር ተጣምሮ እንዲተገበር ሆኗል፡፡ መርሐ ግብሩ የሚያተኩረው በብሔራዊ ዓሳ ማምረት ልማት ቦርድ ሥር ባለው በዓሳ ማምረት ዕድገትና አስተዳደር ነው፡፡

በሰማያዊ አብዮት መርሐ ግብር የሚካተቱት ዋና ዋና ክፍሎች

ብሔራዊ የዓሳ ዕርባታ ልማት ቦርድና ተግባራቱ የዓሳ ዕርባታ ዘርፍ የሥነ ምድር መረጃ ሥርዓትና ዳታ ቤዝ በተጠናከረ መንገድ መያዝ፣ የአገር ውስጥ የዓሳ ዕርባታና የአኳካልቸርን ማልማት፣ ብሔራዊ የዓሳ አርቢዎችን ደኅንነት ጉዳይ፣ የባህር ላይ ዓሳ ማጥመድ ልማት፣ መሠረተ ልማትና ድኅረ ምርት ሥራ፣ የክትትል፣ ቁጥጥርና ፍላጎትን መሠረት ያደረገ ጣልቃ ገብነትን ማጠናከርና የዓሳ ዕርባታ ዘርፍን ተቋማዊ አደረጃጀት ማየት፡፡  

የሰማያዊ አብዮት ዓላማዎች

ሰማያዊ አብዮት ዓላማ አድርጎ የተነሳው የህንድን የኢኮኖሚ ዕድገት የዓሳ ዕርባታን በማሳደግና የምግብና የንጥረ ምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ማሳደግ ነው፡፡ በምድር (በሐይቆች፣ በኩሬዎችና በወንዞች) እንዲሁም በባህር ላይ ያለውን ዓሳ የማርባት አቅም በመጠቀም የዓሳ ምርትን በ2020 በሦስት እጥፍ ማሳደግ ነው፡፡ የዓሳ ዕርባታውን ዘርፍ ወደ ዘመናዊ ኢንዱስትሪ እንዲሸጋገር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና የአሠራር ሒደቶችን መጠቀም፡፡ ምርትን በማሳደግና የድኅረ ምርት የገበያ ሁኔታዎችን ማለትም የኤሌክትሮኒክ ግብይትን (E-commerce)፣ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምና በዓለም ላይ ያሉ ምርት ግኝቶችን በመጠቀም የዓሳ ዕርቢዎችን ገቢ በእጥፍ ማሳደግ፣ እ.ኤ.አ. በ2020 በውጪ ንግድ የምንዛሪ ግኝትን በሦስት እጥፍ ማሳደግና ህንድን በምግብ አቅም ራስን መቻልና የንጥረ ምግብ ፍላጎትን ማሳደግ

የሰማያዊ አብዮት ውጤት (ትሩፋት)

ሰማያዊ አብዮት በህንድ ከዓሳ አርቢ ገበሬዎች ልማት ኤጀንሲ ጋር በመሆን የአኳካልቸርንና የዓሳ ዕርባታ ዘርፍን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስረፅ፣ የአገር ውስጥ ገበያን፣ የዓሳ ምርት ወደ ውጭ መላክንና ዓሳ ማርባት ላይ የተሻለ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ጥቂቶችን ለመጥቀስ፣ በአሁኑ ጊዜ የዓሳ ዕርባታው ዘርፍ (በባህርና በአኳካልቸር) ዓመታዊ ምርት 4.7 ሚሊዮን ቶን ሲሆን፣ ከ50 ዓመታት በፊት 60 ሺሕ ቶን የነበረው በአኳ ካልቸር ብቻ የሚለማው በአሁኑ ጊዜ 1.6 ሚሊዮን ቶን ደርሷል፡፡ ህንድ በዓሳና በዓሳ ምርት ላይ የ14.8 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት ስታስመዘግብ በዓለም ደረጃ የተመዘገበው ግን 7.5 በመቶ ነው፡፡ የዓሳ ምርት ህንድ ባለፉት አምስት ዓመታት ወደ ውጭ ከላከቻው የግብርና ምርቶች ትልቁን ድርሻ ሲይዝ ከስድስት እስከ አሥር በመቶ ድርሻ ነበረው፡፡

አረንጓዴው  አብዮት  (Green  Revolution)

በ1960ዎቹ መጀመርያ የአረጓዴው አብዮት መጀመርያ ነው፡፡ በተሻሻሉ እርሻ ተኮር ቴክኖሎጂዎች ምክንያት ከፍተኛ ምርት የሚያመርቱ ዝርያዎች እየበዙ ሄደዋል፡፡ ይህም በማደግ ላይ የነበረችውን ህንድ ከኋላ ቀር የእርሻ ምርት እንድትላቀቅ አድርጓል፡፡ በህንድ መንግሥት ኃላፊነት በ2018 እስከ 2019 በጀት ተመድቦለት በቲማቲም፣ በሽንኩርትና በድንች የተጀመረ ዘመቻ ነው፡፡ ይህ ዘመቻ የነጩ ዘመቻ ውጤታማነት ላይ መሠረት ያደረገ ነው፡፡

የአረንጓዴው ዘመቻ የኋላ ታሪክ

የህንድ የገንዘብ ሚኒስትር ከ2018 እስከ 2019 በጋራ በፀደቀ 500 ቢሊዮን የህንድ ሩፒ የአረንጓዴው ዘመቻ መጀመሩን ለሕዝብ ይፋ አደረጉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የአረንጓዴው አብዮት በምግብ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ሚኒስትር (Ministry of Food Processing Industries) ሥር ነው ያለው፡፡ የአረንጓዴ ዘመቻ ሥራ የጎርፉ ዘመቻ እየሄደ ባለበት መንገድ የሚሄድ ሲሆን፣ ዓላማው አምራች ገበሬዎችና ድርጅቶችን ማበረታታት፣ የምግብ ማምረቻ አቅርቦቶችን፣ የእርሻ መሣሪያዎችንና በዘርፉ ያለውን ሙያ ከፍ ለማድረግ ነው፡፡

አረንጓዴው ዘመቻ ምንድነው?

አረንጓዴው ዘመቻ ገበሬዎች ላመረቱት ምርት ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡ ይበልጥ ትኩረት የሚያደርገው በቲማቲም፣ ሽንኩርትና ድንች ምርቶች ላይ የተደራጀ የገበያ ዕድል መፍጠር ላይ ነው፡፡ በዚህ ዘመቻ መንግሥት ለተደራጁ አምራች ገበሬዎች፣ ለመንግሥት የእርሻ ድርጅቶች፣ ለማኅበራት፣ ለምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች፣ ለራስ አገዝ ቡድኖች የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ በ‹‹E-NAM Platforms›› የእርሻ ምርት ገበያ ኮሚቴ (APMC) ጋር ተገናኝቶ (ተሳስሮ) አደረጃጀትና በመሠረተ ልማት በመደገፍ የአረንጓዴ ዘመቻ መርሐ ግብርን ለማሳካት ጥረት ተደርጓል፡፡ መንግሥት በዚህ መስክ 22,000 የእርሻ ገበያዎችን መዝግቧል፡፡

የእርሻ ምርት ገበያ ኮሚቴ (APMC) በመንግሥት የተቋቋመና በተወሰኑ የእርሻና፣ የከብት እርባታና የፍራፍሬ ምርት ገበያ ላይ ሕጎችንና ደንቦችን የሚያወጣ አካል ሲሆን በሕግ የተቋቋመ ነው፡፡ ‹‹The e-National Agriculture Market (E-NAM)›› በህንድ መንግሥት የተዘጋጀ የኤሌክትሮኒክ ንግድ ፖርታል ሲሆን፣ ጨረታና ሥራዎች ይካሄዱበታል፡፡ የእርሻ ምርቶችም በአገር አቀፍ ደረጃ በአንድ በኩል ይከናወንበታል፡፡

የአረንጓዴው ዘመቻ ዓላማ

የቲማቲም፣ የሽንኩርትና የድንች ምርቶች ዕቅድን በክላስተር በማምረት ለተጠቃሚውና ለአምራቹ የተረጋጋ ዋጋ ማቅረብ፣ የቲማቲም፣ የሽንኩርትና የድንች አምራች ገበሬዎችን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል፣  የአምራች ገበሬዎች ማኅበራትን በማጠናከር የምርትና ግብይት ትስስርን መፍጠር፣ ከእርሻ ቦታ የሚነሱ መሠረተ ልማቶችን በማጠናከር፣ ተገቢ መጋዘኞችን (ማቆያ ቦታ) በማዘጋጀት፣ ዘመናዊ እርሻ መሣሪያዎችን በማቅረብና ከተጠቃሚ ጋር የሚያገናኝ ሰንሰለቶችን በመዘርጋት በድኅረ ምርት የሚደርሰውን ኪሳራ መቀነስ፣ የድንች፣ የቲማቲምና የሽንኩርት ምርቶችን በፋብሪካ ደረጃ የሚያቀነባብሩ ድርጅቶችን በማሳደግ ከገበያ ጋር ትስስር የሚፈጥሩበትን አሠራር መዘርጋትና የገበያውን እውነተኛ ዋጋ፣ ፍላጎትና አቅርቦትን የሚያጠናና ወደ መረጃ ቋት የሚያስገባ ኔትወርክ መሥራት ናቸው፡፡

የአረንጓዴው ዘመቻ አስፈላጊነት

ከአረንጓዴው ዘመቻ ጀርባ ያለው ዋና ዕቅድ በ2022 የገበሬዎችን ገቢ በእጥፍ ማሳደግ ነው፡፡ ይህ ዘመቻ የተበሰረው የጎርፉ ዘመቻ ያመጣውን ውጤት በአትክልትና ፍራፍሬ ለመድገም ነው፡፡ ለገበያ የሚቀርበው የአትክልት ምርት በከፍተኛ ፍጥነት ሲያድግ ዋጋው በፍጥነት አሽቆለቆለ፡፡ ምክንያቱም የአትክልት ምርት የሚያቆይ ተስማሚ መጋዘን ስላልነበረ ነው፡፡ በዚህም ቀጣይ ሥራ ዘመናዊና ተስማሚ መጋዘን ማዘጋጀት ሆነ፡፡

አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ምርታቸውን የሚሸጡበት ዋጋና በላተኛ ደንበኛ ምርታቸውን ከነጋዴ የሚገዛበት ዋጋ አንድ አራተኛ ነው፡፡ ይህ ከፍተኛ ልዩነት የተፈጠረው በአምራቹና በተጠቃሚው መካከል ባለው የተወሳሰበ የዕዝ ሰንሰለትና የደላሎች ተፅዕኖ ነው፡፡ በአረንጓዴው ዘመቻ መርሐ ግብር ከላይ የተጠቀሱና በዋና ዋና ምርቶች ላይ የተጋረጡ ችግሮችን ለመፍታት በሚያመች መልኩ ተዘጋጅቷል፡፡

የአረንጓዴ ዘመቻ ስትራቴጂ

የአረንጓዴ ዘመቻ መርሐ ግብር ሁለት ዘላቂ ስትራቴጂዎች አሉት፡፡  በአጭር ጊዜ የገበያ ዋጋን ማረጋጋትና በረዥም ጊዜ በዘርፉ ያሉትን የእሴት ሰንሰለት ልማትን ማሻሻል

በአጭር ጊዜ የገበያ ዋጋን የማረጋጋት ዕርምጃዎች

ለአትክልትና ግራፍሬ ምርት ማቆያ ተገቢ የሆኑ መጋዘኖችን በኪራይ ማግኘት፣ የብሔራዊ የእርሻ ማኅበር ገበያ ፌዴሬሽን የዋጋ ማረጋጋቱን ሥራ በበላይነት እንዲሠራ ተደረገ፡፡ የምግብ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ሚኒስቴር አትክልትና ፍራፍሬዎች ከምርት ቦታቸው ወደ ገበያ ሥፍራ ሲሄዱ የሚወጣውን የትራንስፖርት ወጪ 50 በመቶ ይደጉማል፡፡

የረዥም ጊዜ የእሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጄክቶች አደረጃጀት

የእርሻ መሣሪያ አቅርቦት፣ የአምራች ገበሬ አደረጃጀቶችን አቅም መገንባት፣ የምርት ጥራት፣ ከምርት በኋላ ባሉ እንደ ገበያና የንግድ ትስስር ባሉ የአሠራር ሒደቶች መፍትሔዎችን ማምጣት፣ በአትክትልና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ ያለውን የፍላጎትና የአቅርቦት መረጃ ለማስተዳደር የሚያመች የኤሌክትሮኒክስ በይነ መረብ መዘርጋት ናቸው፡፡

የአረንጓዴ ዘመቻ ቀጣይ ዕቅድ

በምርትና በተጠቃሚዎች  መካከል ያለውን ግንኙነት ማሳጠርና የድለላ ተግባርን መቀነስ ያስፈልጋል፡፡ ምርቱ ከፍ እያለ በመሄዱ ከምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህም ቢያንስ የምርቱ አንድ አራተኛ ወደ ምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች እንዲገባ ተደርጓል፡፡ መንግሥት ለተጠቃሚው ማኅበረሰብ ምርቶችን በዝቅተኛ ዋጋ እንዲገዛ፣ ገበሬው ደግሞ ከፍተኛ የገበያ ድርሻ እንዲኖረው በማድረግ ዘላቂና ከፍ ያለ ተጠቃሚ እንዲሆን አስችሎታል፡፡ በዚህም የዋጋ መዋዤቅን ተቆጣጥሯል፡፡ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች እንዲቋቋሙና እንዲበረታቱ የበጀት ድጋፍ ተደርጓል፡፡ 

ግራጫው አብዮት (Grey Revolution)

ይህ የአፈር ማዳበሪያ ምርትን ከፍ ያደረገ አብዮት ነው፡፡ ይህ በአረንጓዴው አብዮት ጊዜ በአፈር ለምነት ላይ የተፈጠሩ ጉዳቶችን ለመቀነስና የተሻሻሉ የእርሻ መሣሪያዎች ያመጡትን ጉዳት ይቀንሳል፡፡

ወርቃማው አብዮት (Golden Revolution)

ከ1991 እስከ 2003 ያሉ ዓመታት የወርቃማው አብዮት ጊዜያት ይባላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ህንድ በሙዝ፣ በማንጎና በመሳሰሉት ምርቶች ዓለምን የመራችበትና ለዜጎቿ በቂ የንጥረ ምግብ አማራጮችን ያቀረበችበት ጊዜ ነው፡፡ ይህ አብዮት ከማርና ከፍራፍሬ ምርቶች ጋር ይያያዛል፡፡ በህንድ ከተካሄዱ አብዮቶችም በጣም አስፈላጊው እንደነበር ይታመናል፡፡ ኒርፓክ ቱቴጅ የወርቃማው አብዮት አባት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

የፍራፍሬ ምርት ኢንቨስትመንት በከፍተኛ ደረጃ ውጤታማ የተሆነበት ጊዜም ነው፡፡ ህንድ በተለያዩ የፍራፍሬ ምርቶች ከዓለም አገሮች መሪ ሆነች፡፡ ለምሳሌም በኮኮናት፣ በማንጎ፣ በለውዝና በተለያዩ ምርቶች፡፡ ዘርፉ ዘላቂ የኑሮ አማራጭና ሁለተኛው ከፍተኛ የአትክልትና ፍራፍሬ አምራች ሆኗል፡፡ የብዙ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት የታቀፉ ገበሬዎች ኢኮኖሚ ያደገበትና በማኅበረሰቡ ዘንድ በበታችነት የሚታዩ የኑሮ ደረጃቸው የተሻሻለበት ነው፡፡

በወርቃማው አብዮት ወቅት የአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍን የተገዳደሩ ሁኔታዎች

እስከ 1990 ድረስ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ቅድሚያ የተሰጠው ጉዳይ አልነበረም፡፡ ከ1948 እስከ 1980 ድረስ ዋና የግብርና ትኩረት በእህል ዘሮች ላይ ነበር፡፡ ጥናትን መሠረት በማድረግ የወርቃማው አብዮት ከአረንጓዴው አብዮት የተለየ መሆኑን አሳይቷል፡፡ የአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ዕድገትን የወሰኑ ተግዳሮቶች ከፍተኛ ምርት የሚያስገኙ ዘሮችን እንደተፈለገው አለመገኘት፣ የማምረቻ ቦታዎችን ማሳደግና የምርት ማሻሻያ ቴክኒኮች ናቸው፡፡

አትክልትና ፍራፍሬን ለውጭ ገበያ ማቅረብን በተመለከተ

የአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ብዙ መሰናክሎች ተጋርጠውበት ነበር፡፡ ቀዝቃዛ መጋዘኖችና የምርታማነት መቀነስ ይጠቀሳሉ፡፡ ነገር ግን የምግብ (አመጋገብ) ባህል ለውጥና ከፍተኛ ገቢ ማግኘት፣ ለጤና ያላቸው ጠቀሜታን በተመለከተ በተደረገው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ሕዝቡ የአትክልትና የፍራፍሬ ምርቶችን በከፍተኛ ደረጃ ለወጠ፣ የንግድ ዕሳቤም ከፍተኛ ነበር፡፡ 

ህንድ እ.ኤ.አ. በ2004 እስከ 2005 ለውጭ ገበያ ካቀረበቺው አትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ‹‹6308.53 Crores›› ያገኘች ሲሆን፣ በ2014 እስከ 2015 ግን ‹‹286,286.1 Crores›› ደርሷል፡፡ ይህ ከፍተኛ ለውጥ የመጣው ዘርፉ እጅግ በተደራጀና በተቀናጀ ዕቅድ በመመረቱና በወርቃማው አብዮት ጊዜ ለዘርፉ የወጡት ፖሊሲዎችና ሕግ ማዕቀፎች ጭምር ነው፡፡

ብሔራዊ  የአትክልትና የፍራፍሬ ተልዕኮ

የህንድ መንግሥት የብሔራዊ የአትክልትና ፍራፍሬ ተልዕኮ የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት እንዲወጣ አስፈላጊ የገንዘብና የአቅርቦት ፍላጎቶችን ለማሟላት ወስኖ ተንቀሳቅሷል፡፡ ክልሎች ለዘርፉ የተሰጡ አዎንታዊ ዕርምጃዎችን እንዲጠቀሙ አድርጓል፡፡

የወርቃማ ጭረቶች አብዮት (Golden Fiber Revolution)

የቃጫ ተክል ላይ ያተኮረ ሲሆን ይበልጥ ጆንያ፣ ከረጢትና የመሳሰሉ ምርቶችን ለማምረት ሲሆን ከኢንዱስትሪ አብዮት ጊዜና እስካሁን ተፈላጊነቱ ከፍተኛ ነው፡፡

ሐምራዊው አብዮት  (Pink Revolution)

ለውጭ ገበያ የሚቀርብ የሥጋ ምርትንና ጥራትን ከፍ ያደረገ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ይህ አብዮት በዶሮ እና ሥጋ ማቀነባበር ዘዴ ላይ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን ከፍ ያደረገ ነው፡፡ የሐምራዊ አብዮት ትኩረት በዶሮና በሥጋ ምርትና ማቀነባበሪያ ላይ ሲሆን፣ በሽንኩርትና በመድኃኒትም ላይ ነበር፡፡ ህንድ በዶሮና በከብት ሀብት ከፍተኛ ፀጋ ያላት አገር ስለሆነች በዚህ ዘርፍ የማደግ ዕድሏን ተጠቅማለች፡፡

ሐምራዊው አብዮት በህንድ

ኢንዱስትሪ መርና የዘመኑ ቴክኖሎጂዎች ዓለም ዓቀፍ መሥፈርቶችን ለማሟላት ለሁሉም የህንድ ተቋማት ያስፈልጋሉ፡፡ በተጨማሪም በብዛት የማምረት ብቃትም ኢንዱስትሪዎችን ምርታማ ያደርጋቸዋል፡፡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ህንዳውያን ከውጪ ታሽጎ ከሚመጣ ሥጋ የበለጠ በአገራቸው የተመረተ ሥጋን ስለሚመርጡ፣ በሥጋ ማምረትና ማቀነባበር ላይ የተመሠረቱ ድርጅቶች ገበያ አላቸው፡፡ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ  በመጨመራቸው፣ ህንድ ጥራት ያለውንና ዓለም አቀፍ የጥራት መሥፈርቶችን በማሟላት የምታመርተው የሥጋ ምርት የውጪ ገበያዋን አሳድጎላታል፡፡

የሐምራዊው አብዮት ፈተናዎችና ዕድሎች

የሐምራዊ አብዮት ኃላፊነት የወደቀው በብሔራዊ የሥጋና የዶሮ ዕርባታ ማቀነባበሪያ ቦርድ ሲሆን፣ ይህ ቦርድ ተጠሪነቱ ለምግብ ማቀነባበሪያ ሚኒስቴር ነው፡፡  ፈተናዎቹም የሚከተሉት ናቸው፡፡ በህንድ ከፍተኛ የዶሮና የከብት ቁጥር ቢኖራትም ለዓለም አቀፍ ገበያ የምታውለው ሁለት በመቶ ብቻ ነው፡፡ የሥጋና የዶሮ ጥራትና የደኅንነት መሥፈርትን ማሟላት ግዴታ መሆን፣ የሥጋ ምርትና ወደ ውጭ መላክ ላይ መሥፈርቶችን ማዘጋጀት፣ የሥጋ ጥራት መፈተሻ መሣሪያዎች አቅርቦት እጥረት፣ በፍጥነት እያደጉ ለመጡት የሥጋና የዶሮ ምርቶች የቀዝቃዛ መጋዘኖች እጥረት፣ ለዘመናዊ ቄራዎች የመሠረተ ልማት አለመሟላትና በየጊዜው ለዘርፉ የሚጠይቀው ኢንቨስትመንት እየጨመረ መምጣት፣ ለሥጋና ለዶሮ ማቀነባበሪያ የሚያስፈልጉ የጤና ጉዳዮች መወሳሰብ፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ተግዳሮቶች እንዳሉ ሆነው ህንድ በሥጋና በዶሮ ማቀነባበሪያ ዘርፍ ከፍተኛ አለኝታ አላት፡፡ በህንድ በአሁኑ ጊዜ ሥጋን የመጠቀም ልምድ በቀን ስድስት ግራም ሲሆን፣ በቀጣይ አሥር ዓመት 50 ግራም ለማድረስ ታቅዷል፡፡ ይህ የዕድገት ዕቅድ ዘርፉ በፍጥነት እንደሚያድግ ምስክር ነው፡፡

ሐምራዊውን አብዮት ያስተዋወቁ የመንግሥት ፖሊሲዎች

በህንድ የዶሮ ዕርባታ ኢንዱስትሪ ከ700 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሀብት የሚያንቀሳቅስ  ዘርፍ ነው፡፡ በዓመትም ከስምንት እስከ 15 በመቶ ያድጋል፡፡ መንግሥት ዘርፉን ለመደገፍ የሚጠቀማቸው በሥጋና በዶሮ ዕርባታ ለተሰማሩ ድርጅቶች የታክስ ሥርዓቱን ነፃ ማድረግ (ኤክሳይዝ ታክስና ከአገር ውስጥ ገቢ ግብር ነፃ ማድረግ)፣ በዶሮ ማርባትና ምርት ላይ ገደቦችን ማንሳትና ከመንግሥት ትራንስፖርት ድጋፍ ማግኘት ነው፡፡  በሥጋ ምርት ላይ የሚደርሰውን ብክነት ለመቆጣጠር፣ የጥራት መሥፈርቶችን ማዘጋጀት፣ በመበከል የሚፈጠረውን ኪሳራ ለመታደግ መንግሥት ሁሉን አቀፍ መርሐ ግብር ለሁሉም ቄራዎች አዘጋጅቶ አሠራጭቷል፡፡ የህንድን ሥጋ የሚቀበሉ አገሮች ማሌዥያ፣ ታይላንድ፣ ቬትናም፣ አውስትራሊያ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና ግብፅ ሲሆኑ ሥጋን ወደ ውጭ የሚልኩ ግዛቶች ፑንጃብ፣ ማሃርሺትራና ኡታር ፕራዴሽ ናቸው፡፡ ከቄራ የሚገኙ ተረፈ ምርቶችን እሴት በመጨመር ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙና ተረፈ ምርቶቹን በማስወገድ ሊደርስ የሚችሉ የአካባቢ መበከልና ወጪ ተቀንሷል፡፡ የሥጋ ምርትን ለማሳደግ በከብቶች ዝርያ ላይ የተለያዩ ማሻሻያዎች ተወስደዋል፡፡

ብርማው አብዮት  (Silver Revolution)

ይህ አብዮት ተጀመረበት ጊዜ የእንቁላል ምርት በሚያስገርም ፍጥነት ያደገበት ዘመን ነው፡፡ የእንቁላል ምርቱ ያደገበት ምክንያቶች በእንስሳት ሕክምና የተደረጉ መሻሻሎችና በፕሮቲን ይዘታቸው ከፍተኛ የሆኑ ምግቦችን ለዶሮዎች መመገብ ነው፡፡ በህንድ በስፋት እያደገ የመጣውን የእንቁላል ምርት በቴክኖሎጂና በምርጥ የአመራረት ሒደት በማሻሻል ለተሻሻለ ውጤት ማብቃት ነው፡፡ ይህ አብዮት ዘጠኝ ዓመታትን የፈጀ ሲሆን፣ አዳዲስ የሳይንስ ግኝቶችና በሕክምና ሳይንስ የተደረገው ዕገዛ ከፍተኛውን ድርሻ ተጫውተዋል፡፡ የህንድ መንግሥትና የግል ድርጅቶች፣ እንዲሁም የእንስሳት ጤና ባለሙያዎች  የእንቁላል ምርት እጅግ በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ህንድን በእንቁላል ምርት ከቻይናና ከአሜሪካ ቀጥላ በሦስተኛነት እንድትቀመጥ አድርጓታል፡፡

የብርማ አብዮት አስፈላጊ መለያ ባህሪያት

እንቁላልን የማምረት ሥራ ጤናማ ምግብን መጠቀም ከማሳዳግ አንፃር ስለሚታይ በሥሩ ብዙ ዓላማዎች አሉት፡፡ ብርማው አብዮት የተለያዩ በሽታዎችን ለመከላከል ከፍተኛ ቴክኖሎጂዎችን ማስረፅና ሥነ ሕይወታዊ ፕሮቶኮሎችን መከተል ይገባዋል፡፡ ብርማው አብዮት ተግባራዊ ሳይንስን በመጠቀም ዶሮችን ማግኘት አስችሏል፡፡ ብርማው አብዮት እንቁላልን በማምረት ሒደት የጥራት ደረጃዎችን ማሟላት የግድ ስለሚል፣ በዶሮ ዕርባታ ኢንዱስትሪ ጥሩ ገበያ ያላቸውን አገሮችን መሥፈርት አሟልቷል፡፡ ምግብን የመመገብ ፍላጎትን ለማሳደግ የእኩለ ቀን ምግብ መርሐ ግብርን የእንቁላልን ምርት በመጨመርና ‹‹ዘላቂነት ያለውን ምግብ ለሁሉም›› በሚለው መርህ ተዋውቋል፡፡ የተመረቱ እንቁላሎች ለገበያ በሚቀርቡበት ጊዜ በጥሩ ሁኔታ ታሽገውና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው እንዲጻፍ ተደርጓል፡፡ እንቁላል በቀላሉ ሊሰበር የሚችል ከመሆኑ አንፃር ረዥም ርቀት ላለ ገበያና ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ታምኖበታል፡፡

የብርማ አብዮት ተግዳሮቶች

ትክክለኛውን የማስወገድ ሒደት ያልተከተሉ የዶሮዎች ኩሶች የአካባቢ ብክለት  በማስከተል፣ ጎጂ ኬሚካሎችና ባክቴሪያዎችን እንዲፈጠሩ አደረጉ፡፡

ነጩ አብዮት (White Revolution) 

ቨርጌስ ኩሬይን የነጩ አብዮት አባት ነው፡፡ ቢሊዮን ሊትር የሚለው ሐሳብ ህንድን በጎርፉ ዘመቻ (Operation Flood) በዓለም ቁጥር አንድ የወተት አምራች አገርና በወተት ተዋጽኦ ራሷን የቻለች አገር እንድትሆን አድርጓል፡፡ ነጩ አብዮት በአረንጓዴው አብዮት በሩዝና በስንዴ ላይ የታዩትን አመርቂ ውጤት በማየት የጎርፍ ዘመቻ በሚል መርህ መንግሥት የነጩ አብዮትን ማካሄድ ጀመረ፡፡ ይህ አብዮት ከፍተኛ የወተት ምርትን በማምረትና በማቅረብ ህንድን ከዓለም ከፍተኛ ወተት አምራች አገር አንዱ ማድረግ ፍላጎቱ ነው፡፡

ነጩ አብዮት ምንድነው?

የጎርፍ ዘመቻ (Operation Flood) መርሐ ግብር ወደ ነጩ አብዮት የመራ ነው፡፡ ይህ የብሔራዊ የወተት ቋት በመፍጠር በ700 ከተሞች የሚገኙ ወተት አምራቾችን በማስተሳሰር፣ ወደ ተጠቃሚዎች የሚያደርስና ወተት አምራቾችን ከፍተኛ ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥርዓት በመፍጠር በቦታና በወቅቶች ምክንያት የሚፈጠርን የዋጋ መለያየት ያስቀረና በመሀል የደላሎችን ሚና ያስቀረ አብዮት ነው፡፡ የጎርፉ ዘመቻ መርሐ ግብር የሚጀምረው መንደር ውስጥ ካሉ ወተት አምራቾች ሲሆን፣ እነሱን በማኅበር በማደራጀት፣ ስለ አመራረትና አስተዳደር፣ እንዲሁም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ነው፡፡ ነጩ አብዮት ህንድን በወተት ምርት ራሷን የቻለች አገር የማድረግና ከወተት አምራች አገሮች ከፍተኛ አገር ማድረግ ነው፡፡

የነጩ አብዮት ታሪካዊ ዳራ

ከ1964 እስከ 1965 የከብት ማርባት መርሐ ግብር በህንድ ተዋውቆና የከብት ባለቤቶች በከብት ርቢ ማዕቀፍ ውስጥ ገብተው፣ የተሸሻሉ ዝርያ ያላቸውን ከብቶች በማግነት በምርት ላይ ለውጥ በማስመዝገብ ላይ በነበሩበት ጊዜ ነጩ አብዮት ወደ ሥራ ገባ፡፡ የጎርፉ ዘመቻም በ1970 ሲጀመር ዓላማውም ብሔራዊ የወተት ቋት መሥራት ነበር፡፡ ይህን በብሔራዊ የወተት ተዋጽኦ ልማት ቦርድ አሳሳቢነት የተጀመረ ነው፡፡

የነጩ አብዮት መለያዎች

እንስሳትን ለማርባትና ተጠቃሚ ለመሆን  አዳዲስ አሠራሮችንና ማስረፅና ለእንስሳቱ መኖ የሚሆኑ ምግቦችን ማዘጋጀትና መቀላቀል ነው፡፡

የነጩ አብዮት ዓላማዎች

የወተት አምራች ማኅበራት የጎርፍ ዘመቻን መሥርተዋል፡፡ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችና አስተዳደርን እስከ መጨረሻው በመጠቀም ወተት ያመረቱና አገልግሎትም የሰጡ ናቸው፡፡ ዓላማዎቹም የወተት ምርት አቅርቦትን መጨመር፣ በገጠር የአርሶ አደሩን ገቢ መጨመርና ለደንበኞች በተመጣጣኝ ዋጋ ወተት መሸጥ፡፡

የጎርፉ ዘመቻ ውጤቶች

ነጩ አብዮት በነጋዴዎች የሚስተዋለውን ብልሹ አሠራር በእጅጉ እንዲቀንስ አድርጓል፣ ድህነትን በመቀነስም ህንድ ከፍተኛ የወተት አምራች አገር ሆነች፣ የጎርፉ ዘመቻ በወተትና የወተት ምርቶች ላይ የተሰማሩ ገበሬዎችን ባፈሩት ምርት ላይ ተቆጣጣሪ እንዲሆኑና በራሳቸው ለማደግ በሚያደርጉት ጥረት ላይ ወሳኝ አድርጓቸዋል፡፡ ከ700 ከተሞች ያሉ ደንበኞችንና ወተት አምራቾችን ለማገናኘት ብሔራዊ የወተት ቋት ተመሥርቷል፡፡ አብዮቱ በወቅቶችና በቦታዎች ምክንያት የሚፈጠሩ የዋጋ መዋዠቆችን ቀንሷል፡፡ የገጠሩን የኑሮ ሁኔታ ያሻሻለና የገጠሩ ክፍለ ኢኮኖሚ እንዲያድግ አድርጓል፡፡

ነጩ አብዮት ያለፋቸው ሁኔታዎች

ምዕራፍ አንድ

የመጀመርያው ክፍል ለአሥር ዓመታት የቆየ ሲሆን፣ (1970 እስከ 1980) ይህ ክፍል በአውሮፓ ኅብረት በተገኘ ገንዘብ የተጀመረ ሲሆን ገበሬዎች ቅቤ፣ ክሬምና ጥሬ ወተት በመሸጥ አስቀጥለውታል፡፡ መርሐ ግብሩን በስኬት ለማጠናቀቅ በመጀመርያው ምዕራፍ የሚገኙ አንዳንድ ዓላማዎች በጉልህ መታየትና መከለስ ነበረባቸው፡፡ አንዱ በትልልቅ ከተሞች የነበረውን የገበያ አያያዝ በድጋሚ አጥንቶ ዓላማቸውን በስኬት እንዲወጡ ማሻሻል ነው፡፡

ምዕራፍ ሁለት

የቆየው ለአምስት ዓመት ነው (1981 እስከ 1985)፡፡ በዚህ ጊዜ ወተት ይሰበሰብባቸው የነበሩ ሼዶች ከ18 እስከ 136 አደጉ፡፡ የወተት መሸጫ ቦታዎች በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በከተማ ብቻ 290 ደረሱ፡፡ 4,250,000 ወተት አምራች ገበሬዎች በ43,000 የመንደር ኅብረት ተደራጁ፡፡ የወተት ዱቄት ምርት በ1980 ዓ.ም. 22,000 ቶን ሲሆን፣ በ1989 ወደ 140,000 ቶን ከፍ አለ፡፡ የወተት ሽያጭም በቀን ብዙ ሚሊዮን ሊትሮች ደረሰ፡፡ ይህ ሁሉ ውጤት ተገኘው በጎርፉ ዘመቻ ምክንያት ነው፡፡

ምዕራፍ  ሦስት

ይህ ምዕራፍ አሥር ዓመታትን ፈጅቷል (ከ1986 እስከ 1996) ይህ ምዕራፍ የወተትና  የወተት ምርት ውጤቶች ማኅበራትን እንዲሰፉና የመርሐ ግብሩ የመጨረሻ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ አስችሏል፡፡ የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶችን እንዲገዙና የገበያ ድርሻ በመጨመር የወተት መጠን እንዲጨምር ሆኗል፡፡ የነጩ አብዮት ማብቂያ አካባቢ 73,930 የወተትና የወተት ውጤቶችን የሚያመርቱ ማኅበራት የተመሠረቱ ሲሆን፣ በቢሊዮን ዶላር የሚያንቀሳቀሱ ሆነዋል፡፡ አብዮቱም ብዙ የህንድ መንደሮችን ከድህነት ወደ ብልፅግና ቀይሯል፡፡

ቢጫው አብዮት (Yellow Revolution) 

በቢጫው አብዮት ህንድ የቅባት እህሎችን ከውጪ ከማስገባት ራሷን ወደ መቻልና ወደ ውጪ መላክ የምትችል አገር ሆናለች፡፡ የቢጫው አብዮት የተበሰረው የቅባት እህሎች ምርቶችን በማሳደግ የአገር ውስጥ ፍላጎቶችን ለማርካት ነው፡፡

ቢጫው አብዮት ምንድነው?

በ1986/87 ባሉት ጊዜያት የምግብ ዘይት ምርትን በተለይም የሰናፍጭ፣ የሱፍ፣ የሰሊጥ እህሎችን ምርት ማሳደግ በተመለከተ የተጀመረ አብዮት ሲሆን፣ አገሪቱ በምግብ ዘይት ራሷን መቻል አለባት የሚል ቁርጥ ሐሳብ የሰነቀ ነው፡፡ ሳም ፒትሮዳ በህንድ የቢጫው አብዮት አባት ነው፡፡ ቢጫው አብዮት ዓላማ ያደረጋቸው ዘጠኝ የቅባት እህሎች ናቸው፡፡

የቢጫው አብየት ታሪካዊ ዳራ

የቢጫው አብየት እንዲሳካ ህንድ የዘይት ቴክኖሎጂ ተልዕኮን በ1986 ዓ.ም. አወጀች፡፡ አብዮቱ የሰናፍጭና የሰሊጥ ዘሮችን በማዳቀል በመዝራት በጉልህ የሚታይ የምርት ለውጥ ታየ፡፡ ይህም በዘይት ምርት ላይ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ነው፡፡ አብዮቱ በመጀመርያው ወቅት የፑንጃብ ግዛት የሱፍ አበባ ምርቶችን በብዛት በማምረት ጥሩ ውጤት አሳየ፡፡ በአገሪቱ የሚታየውን የማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ልዩነቶችንም እንዳይጎሉ አድርጓል፡፡ አብዮቱ ሲጀመር ዓመታዊ የቅባት እህሎች ምርት 12 ሚሊዮን ቶን የነበረ ሲሆን፣ በአሥር ዓመታት ጊዜ ውስጥ ምርቱ በእጥፍ አድጎ 24 ሚሊዮን ቶን ደርሷል፡፡ የተዳቀሉ ዘሮችን ከመጠቀም ጎን ለጎን የተለያዩ መንግሥት የተለያዩ አበረታች ዕርምጃዎችንም ይወስድ ነበር፡፡ ለምሳሌም 26 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ለቅባት እህል ማምረቻ የተሰጠ ሲሆን፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችም እንዲሁ ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡

የቢጫው አብዮት ባህሪያት

ቢጫው አብዮት እንዲሳካ ለገበሬዎች ማበረታቻ ይደረግ ነበር፡፡ ማበረታቻዎቹም ምርቱን በመስኖ እንዲያመርቱ ዕገዛዎችን በማድረግ፣ የማዳበሪያና የፀረ አረም አቅርቦትን በበቂ ደረጃ በማቅረብ፣ የትራንስፖርት አገልግሎትን በማመቻቸት፣ አስፈላጊ ዕገዛዎችን በአነስተኛ ዋጋ በማቅረብ፣ ምርቶች ሳይበላሹ የሚከማቹበትን መጋዘኞች በየቦታው በመገንባት በዚህ አብዮት የተለያዩ የሥራ አመራር ቦርዶች ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ለአብነት ያህልም የብሔራዊ የወተትና የወተት ውጤቶች ቦርድ የቅባት እህሎች ምርትን በማስተዋወቅ ከፍተኛ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ይህ ቦርድ በጉጅራት የለውዝ ዘይት ምርት እንዲያድግ ሠርቷል፡፡ ሌላኛው ቦርድ የብሔራዊ የቅባት እህሎችና የአትክልት ዘይት ልማት ቦርድ ሲሆን፣ የቅባት እህል ምርትን በአገሪቷ ባሉ ቦታዎች እንዲመረቱ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የቅባት እህል ምርት ትረስት አራት ዋና ዋና የሆኑ የዘይት እህሎችን ማለትም ሰናፍጭ፣ አኩሪ አተር፣ ሱፍና ለውዝ በሕዝቡ ዘንድ ትኩረት እንዲሰጣቸው የአሕዝቦት ሥራ ሠርቷል፡፡ 3,000 የሚደርሱ የቅባት እህል አምራች ማኅበራትንም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እንዲመሠረቱ አድርጓል፡፡

ምንም እንኳን ህንድ በዘይት ምርት ራሷን ብትችልም የዘይት ቅርቦት ፍላጎቷን ለማሟላት አልቻለችም፡፡ ይህን ፍላጎቷን ለማሟላት የዘይት እህሎችን ከሌሎች አገሮች ታስገባ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2007 አምስት ሚሊዮን ቶን ከማሌዥያ፣ ከአርጀንቲናና ከብራዚል አስገብታለች፡፡

የቢጫው አብዮት የወደፊት አቅጣጫ

በአሁኑ ጊዜ ለቅባት እህሎች የሚሆን የሚታረስ መሬት እየተጨመረ አይደለም፡፡ የምግብ ዘይት እጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩን የቅባት እህሎች ቴክኖሎጂ ተልዕኮ (Oilseeds Technology Mission-OTM) የጠቆመ ሲሆን፣ ለዘይት የሚሆኑ የፓልም ተክሎች ማሳደግ በጥቂቱ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ በእነዚህ ተክሎችና እህሎች ላይ ብዙ ተግዳሮቶች አሉባቸው፡፡ ዝርያዎቹ ለአረምና ለበሽታዎች የተጋለጡና በአብዛኛው ለሰው ልጅ በማይስማማ በአስቸጋሪ የአየር ንብረት አካባቢ የሚበቅሉ ናቸው፡፡ በቅርቡ ውጤቶችን ለማሳደግ ገበሬዎች ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ ዝርያዎችን በተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች እየተጠቀሙ ትርፋማ እየሆኑ ነው፡፡ የአብዮቱ ቀጣይ ሥራ የቅባት እህሎች ዋና እህሎችና የአገሪቱን የምግብ ዘይት ፍላጎትን ስለሸፈኑ፣ እንዲሁም በበረሃማ ቦታዎች ላይ ያለውን የእርሻ ሥራ ምርታማነት ለማሳደግና የገበሬዎቹን ገቢ ለመጨመር ተስማሚ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም አስፈላጊ ሆኗል፡፡ አገሪቱ በቅባት እህል አምራችነት ራሷን ከቻለች በግብርናውና በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ለውጥ የሚመጣና ከውጭ የገበያ ጥገኝነት ይቀንስላታል፡፡ 

ከግብርና አብዮት ውጪ ጥቁሩ አብዮት (Black Revolution)

ይህ አብዮት የፔትሮሊየም ምርትን ከፍ ለማድረግ መንግሥት የኢታኖል ምርትን በመጨመርና ከፔትሮሊየም ጋር በመቀላቀል ባዮዲዝል እንዲመረት አገራዊ ዕቅድ አወጣ፡፡ ኢታኖል ታዳሽ ኃይልና ከስኳር ተረፈ ምርት ከሞላሰስ የሚገኝ ነው፡፡ ኢታኖልን ከነዳጅ ጋር የማዋሀድ ተግባር በአሜሪካና በብራዚል ለ70 ዓመታት ሲተገበር የኖረ ነው፡፡ ኢታኖልን ለትራንስፖርት ከሚውል ነዳጅ ጋር መቀላቀል ለገበሬዎች የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡ በእጥረት የሚገኙ ኃይድሮ ካርቦኖችን (ማገዶዎችን) በመተካትና አካባቢን የሚበክሉትን በመቀነስ ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲመረት ያደርጋል፡፡

የተጋረጡበት ችግሮች

ኢታኖል ከስኳር ፋብሪካዎች የሚገኝ ምርት ሲሆን፣ ማምረቻዎቹ  የኢታኖል አቅራቢዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን የባዮኢታኖል ምርት ከነዳጅ ጋር ተቀላቅሎ ጥቅም ላይ ለማዋል በቂ አልነበረም፡፡ በዚህም መሠረት ከነዳጅ ጋር ለመቀላቀል ከታቀደው 50 በመቶ ብቻ ነው ጥቅም ላይ የዋለው፡፡ የባዮኢታኖል መግዣ ዋጋ አለመረጋጋትም አንደኛው ችግር ነው፡፡ ጥቁሩን አብዮት እንደተፈለገ እንዳይጓዝ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ሌላኛው የሸንኮራ አገዳ ምርት እጥረት ነው፡፡ የሸንኮራ አገዳን ለማምረት ሩብ የሚክለው መሬት ቢሰጥም  ይህን የሚያክል መሬት ሌሎች አዝርዕት እንዳይመረቱ በማድረጉ፣ በምግብ ሰብል ላይ ከፍተኛ የዋጋ መናርን አስከተለ፡፡ በህንድ ያለ የባዮፊውል ፖሊሲ ደግሞ የነዳጅ አቅርቦትን ለማሟላት የምግብ አቅርቦት ላይ የሚደረጉ ማንኛውንም ዓይነት ጫናዎችን አይታገስም፡፡ ቅድሚያ ለምግብ አቅርቦት ነው የሚሰጠው፡፡ ባዮኢታኖልን ለማምረት አማራጮች አለመኖርም ተግዳሮት ነው፡፡ የጃትሮፋ ዘር ለባዮኢታኖል ምርት የሚያገለግል ቢሆንም፣ ከገበያ ማግኘት እጅግ ከባድ ነበር፡፡ የኢታኖል ምርት ተቀጣጣይ ከመሆኑ አንፃር ምርቱን ከአደጋ ጠብቆ የሚያቆበትና ትራንስፖርት ወደ ሚፈለግበተት ቦታ ማመላለሻ ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም የደኅንነትና የሥጋት ዕርምጃዎችም በሁሉም የምርትና የአቅርቦት ሒደቶች ላይ አስገዳጅና ጥብቅ ናቸው፡፡

ጥቁሩ አብዮት ያስገኘው ፋይዳ

የካርቦንዳይ ኦክሳይድ ልቀትን ቀንሷል፣ ከቅሪተ አካል ከሚገኘው ነዳጅ (Fossil Fuels) አንፃር የኦዞን መሳሳትን የሚፈጥሩ በካይ ጋዞችና ኬሚካሎችን አይለቅም፣ ባዮፊውልን ለማምረት በየተዳፋት ቦታዎች የተተከሉ የጃትሮፋ ተክሎች የአፈር መሸርሸርን ተከላክለዋል፡፡

የተራቆቱ መሬቶችን በደን ለመሸፈን፣ የውኃና የአፈር ጥበቃ ሥራን፣ በንፋስ የሚወሰደውን አፈር ለመከላከልም እጅግ ጠቀሜታ ነበረው፡፡ የህንድ መንግሥት በዘጠኝ ክልሎች የኢታኖል ምርት ከነዳጅ ጋር የሚቀላቀልበት መጠንን አምስት በመቶ እንዲሆን አድርጓል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይም መንግሥትን የሚያማክር፣ የጥናትና ምርምር ሥራን በኃላፊነት የሚሠራ ብሔራዊ የባዮዲዝል ተልዕኮ መሥሪያ ቤትን ተቋቁሟል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ