Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ዛሬ አዲስ አበባ ይገባል

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ዛሬ አዲስ አበባ ይገባል

ቀን:

ቡድኑ ደማቅ አቀባበል ይደረግለታል

በ18ኛው የኦሪገን ዓለም ሻምፒዮና የተካፈለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ምሽት አዲስ አበባ ይገባል፡፡ በዓለም ሻምፒዮና ደምቆ የከረመው ቡድኑ በቦሌ አየር ማረፊያ ሲደርስ ደማቅ አቀባበል እንደሚደረግለት ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ማክሰኞ ሐምሌ 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠው ሚኒስቴሩ፣ ቡድኑ ረቡዕ ምሽት ቦሌ አየር ማረፊያ ሲደርስ ደማቅ አቀባበል ከተደረገለት በኋላ፣ በነጋታው በተመረጡ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ በተለያዩ አገር መሪዎችና የከተማው ነዋሪ አቀባበል እንደሚደረግላቸው ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አትሌቶቹ በሻምፒዮናው ያሳዩትን ገድል የሚመጥን አቀባበል እንደሚደረግላቸው የገለጸው ሚኒስቴሩ፣ ሕዝቡም ልዑኩ ካረፈበት ሥፍራ ተነስቶ በጎዳናዎቹ ላይ ደማቅ አቀባበል እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል፡፡ ቡድኑ ሐሙስ ጠዋት በክፍት አውቶብስ ሆኖ በጎዳኖቹ ላይ የሚንሸራሸር ሲሆን፣ በመስቀል አደባባይ አቀባባል ይደረግለታል ተብሏል፡፡

በኦሪገን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ 4 ወርቅ፣ 4 የብር ሜዳልያና 2 ነሐስ በድምሩ አሥር ሜዳልያዎችን በመያዝ ከአሜሪካን ተከትሎ በአሥር ሜዳልያዎች ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ ችሏል፡፡

በዘንድሮ ዓለም ሻምፒዮና ደምቆ ያጠናቀቀው ቡድኑ ከፍተኛ አድናቆትን ያገኘ ሲሆን፣ በአትሌቲክስ አዲስ ታሪክ ማስፈር ችሏል፡፡ በዚህም ደብዝዞ የነበረውን የአትሌቲክሱን ውጤት ዳግም እንዲያንሰራራ ማድረግ የቻለ መሆኑም ተወስቷል፡፡ ቡድኑ ሻምፒዮናውን በበላይነት ከማጠናቀቁም በተጨማሪ አትሌቶቹ የርቀቶቹን ከብረወሰን ጭምር በማሻሻል ማጠናቀቃቸው ልዩ አድርጎታል፡፡ በተወሰኑ አገር አቀፍ ውድድሮች ላይ ውስን ልምድ ባላቸው አትሌቶች አሥር ሜዳልያዎችን ማሳካት የቻለው ቡድኑ፣ በቀጣይ በቡዳፔስት ለሚሰናዳው የዓለም ሻምፒዮና እንዲሁም በፓሪስ ለሚዘጋጀው የኦሊምፒክ ጨዋታ ከወዲሁ ተስፋ የሰነቁ አትሌቶችን ማሳየት ችሏል፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም እምብዛም በማትታወቅበት የ3,000 ሜትር መሰናከል ሁለት ሜዳልያዎችን ማግኘት መቻሏና በ800 ሜትር ሴቶች ለመጀመርያ ጊዜ በዓለም ሻምፒዮና ፍፃሜ ደርሳ በድሪቤ ወልተጂ ዲፕሎማ ማሳካቷ እንደትልቅ ስኬት ተነስቷል፡፡ ከዚያም ባሻገር ዓለም አቀፍ ውድድሮች በተቃረቡ ቁጥር ከአትሌቶች ምርጫ ጋር ተያይዞ ንትርክ የማያጠው መሰናዶ የተለመደ መሆኑና ከቀድሞ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ወልደ መስቀል ኮስትሬ (ዶ/ር) ሕልፈት በኋላ በብሔራዊ ቡድን ውስጥ የቡድን ሥራ መጥፋቱ በተደጋጋሚ የሚነሳ ችግር ነው፡፡

ከቶኪዮ ኦሊምፒክ መልስ በተካሄዱ የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ውድድሮች ማለትም በ18ኛው የቤልግሬድ የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና፣ የኬንያ የዓለም ከ20 በታች ሻምፒዮና፣ 22ኛው የሞሪሼየስ የአፍሪካ ሻምፒዮና፣ የታንዛንያ ከ18 እና 20 ዓመት በታች የምሥራቅ አፍሪካ ሻምፒዮናና በኦሪገኑ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በበላይነት በማጠናቀቅ በአትሌቲክሱ ስኬታማ ጊዜን ማሳለፍ ተችሏል፡፡

በዚህም ምክንያት በመላ ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በአንድ ድምፅ ደስታቸውን የገለጹበት አጋጣሚን የፈጠረበትና አገሪቷ ከገባችበት የፖሊቲካ ቀውስ ለአንድ አፍታም ቢሆን ዕረፍት ያገኘችበት አጋጣሚን የፈጠረ መሆኑ በበርካቶች ምስክርነት ያገኘበት ክስተት ሆኗል፡፡

ለዚህም በአሜሪካ ኦሪገንና ፖርትላንድ አካባቢ የሚገኙ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን በሥፍራው ለሚገኘው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ያሰናዱት ‹‹የእንኳን ደስ አላቹ›› መርሐ ግብር ማሳያ ነው፡፡

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት የፖለቲካ ሁኔታ በሕዝቡ መካከል መከፋፈልን የፈጠረ ቢሆንም፣ በአትሌቲክሱ የሕዝብን አንድነት ማምጣት እንደሚቻል ፍንጭ ያሳየ ነበር፡፡  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በበርካታ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ተሳትፎ ሲያደርግ፣  በሁለቱም ጾታ ውድድሮችን በበላይነት በማጠናቀቅ ይታወቃል፡፡ በአንፃሩ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የሴት አትሌቶች የበላይነት እያመዘነ መምጣቱ ሌላኛው አሳሳቢ ጉዳይ እንደሆነ እየተነሳ ይገኛል፡፡

የዘንድሮውን የዓለም ሻምፒዮና ጨምሮ ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ የወንድ አትሌቶች ሜዳልያዎችን የማሳካት ሁኔታ ከሴቶች ጋር ተመጣጣኝ አለመሆኑ ታይቷል፡፡ በዚህም የወንዶቹ ውጤት ከሴቶቹ ለምን እያሽቆለቆለ መጣ? የሚለው ጥናት እንደሚሻና የአትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቀጣይ የቤት ሥራ እንደሆነ የብዙኃኑ አስተያየት ነው፡፡

በመጨረሻም የዘንድሮ የዓለም ሻምፒዮና ውጤት አትሌቶችን እንዳያዘናጋና ከወዲሁ እ.ኤ.አ. በ2024 በፓሪስ ለሚሰናዳው ኦሊምፒክ ጨዋታ ከወዲህ መዘጋጀት እንደሚገባ ተጠቅሷዋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...