Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምበጥቁር ባህር ሰብል እንዲላክ ዩክሬንና ሩሲያ የገቡት ስምምነት

በጥቁር ባህር ሰብል እንዲላክ ዩክሬንና ሩሲያ የገቡት ስምምነት

ቀን:

‹‹ከዚህ በፊት ያልታየ›› ይሉታል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ፡፡ ዓለም በጣም በተቸገረችበት ሰዓት የታየ የተስፋ ብርሃን እንደሆነም ያክላሉ፡፡ በጥቁር ባህር ሰብል ለመላክ በዩክሬንና ሩሲያ መካከል የተፈረመውን ስምምነትም በወሳኝ ወቅት የተደረገ ይሉታል፡፡ ይህ ለዓለም ሕዝቦች በተለይም ለረሃብ ለተጋለጡት የምስራች ነውና፡፡

 የኢኮኖሚ ተንታኞች በሩሲያና በዩክሬን መካከል ጦርነት እንዳይጀመር የምግብ እጥረት መከሰትን እንደ ምሳሌ በማንሳት ማስጠንቀቅ የጀመሩት ከጦርነቱ አስቀድሞ ቢሆንም፣ ምዕራባውያኑ ጦርነቱ እንዳይጀመር ለማድረግ ካደረጉት ጥረት ይልቅ እንዲጀመር ያደረጉት ግፊት ያይል ነበር፡፡

የጦርነቱ መጀመር ግን እንደ ሌሎች በውክልና ጦርነት እንደፈራረሱ አገሮች ሩሲያን ሊያንኮታኩት አልቻለም፡፡ ይልቁንም በግብርና፣ በቱሪዝም ሆነ በማዕድን ሀብቷ የበለፀገችውን ዩክሬን ሲያንኮታኩትና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿን ለስደት ሲዳርግ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ከሁለት አሠርታት በፊት ታይቶ የማይታወቅ የዋጋ ግሽበት እንዲከሰት አድርጓል፡፡

ከአሜሪካ እስከ አውሮፓ፣ ከእስያ እስከ አፍሪካ መላው ዓለም በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ኢኮኖሚው ተነክቷል፡፡ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተንኮታኮተው የዓለም ኢኮኖሚ ማገገም እንደጀመረ የተቀሰቀሰው ጦርነትም ከነዳጅ እስከ ምግብ፣ ከአልባሳት እስከ ማዕድናት፣ ከግብርና እስከ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ያሉ ምርቶች ሁሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋጋቸው እንዲንር እንዲሁም እጥረት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡

ከሁሉም በላይ አሳሳቢ የሆነው ደግሞ፣ የምግብ መወደድና እጥረት እየተከሰተ መምጣት ነው፡፡ በተለይ ከዩክሬንና ሩሲያ ስንዴ፣ ገብስ፣ በቆሎ፣ የምግብ ዘይት እንዲሁም ነዳጅ ዘይትና ጋዝ የሚያስገቡ አገሮች በችግሩ የተመቱት ከጦርነቱ ዋዜማ ጀምሮ ነው፡፡

የዓለም የፀጥታና የምግብ አቅርቦት ላይ የተጋረጠው ችግር ሥጋት ውስጥ ከቶኛል ሲል የከረመው ተመድ፣ በተለይ ከድርቅ ጋር ተደማምሮ በአፍሪካና በሌሎች በኢኮኖሚ ባላደጉ አገሮች የገባው የምግብ ቀውስና ረሃብ ከጫፍ መድረሱንና 47 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ላይ ረሃብ እንደተጋረጠም አሳውቋል፡፡

ዓርብ ሐምሌ 15 ቀን 2014 ዓ.ም. በቱርክ ኢስታምቡል፣ በሩሲያና ዩክሬን መካከል የምግብ ሰብል ወደ ሌሎች አገሮች ለመላክ የተደረሰውን ስምምነትም ‹‹ዓለም በተቸገረ ጊዜ የተደረገ›› ሲል ይሁንታ ችሮታል፡፡

የቱርክ ፕሬዚዳንት ረጂብ ጣይብ ኤርዶዋንና የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ በተገኙበት፣ ሩሲያን በወከሉት የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሼጉ እና ዩክሬንን በወከሉት የዩክሬን መሠረተ ልማት ሚኒስትር አሌክሳንደር ኢብራኮቭ መካከል የተደረገው ስምምነት፣ ጥቁር ባህር ዳግም እህል እንዲመላለስበት ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡

‹‹ብላክ ሲ ግሬን ኢንሽየቲቭ›› ስምምነት በቱርክ ፕሬዚዳንት አመቻችነት የተደረገ ሲሆን፣ ስምምነቱ በዓለም በምግብ እጥረት በጣም የተጎዱ ሕዝቦችን ከረሃብ  ለማውጣት ያግዛል ተብሏል፡፡

በጥቁር ባህር ሰብል እንዲላክ ዩክሬንና ሩሲያ የገቡት ስምምነት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ስምምነቱ ስንዴ፣ የሱፍ ዘይት፣ ማዳበሪያና ሌሎች የምግብ ሰብሎችን በጥቁር ባህር በመላክ የዓለምን ገበያ ለማረጋጋት ያስችላል

‹‹ጥያቄው ለአንደኛው ወይም ለሌላኛው ወገን የቱ ጥሩ ነው የሚለው ሳይሆን፣ ስምምነቱ ለዓለም የተደረገ ነው›› ሲሉ የገለጹት ጉተሬስ፣ የስምምነቱ ትኩረት የዓለምን ሕዝብ መሠረት ማድረጉን አጽንኦት ሰጥተውታል፡፡

አምስት ወራትን ያስቆጠረው የዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት፣ በምግብና በነዳጅ ዋጋ ላይ ያደረሰው ግሽበት በሪከርድ የተመዘገበ እንደሆነ በገጹ ያሰፈረው ተመድ፣ የአቅርቦት ሰንሰለቱ በመስተጓጎሉ በርካታ እህል በዩክሬን መከማቸቱን አስታውሷል፡፡

‹‹ጦርነቱ ከተጀመረ ጀምሮ የዩክሬንን የምግብ ምርቶችና የሩሲያን ምግብና ማዳበሪያ ማግኘት ካልተቻለ፣ ለዓለም የምግብ ቀውስ መፍትሔ አይመጣም ስል ከርሜያለሁ፤›› ያሉት ጉተሬስ፣ ስምምነቱ የሩሲያን ምግብና ማዳበሪያ ለዓለም ገበያ ለማቅረብም በር ይከፍታል፣ የዓለም የምግብ ዋጋ ያረጋጋል፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ በረሃብ የተጠቁ ሰዎችን ይታደጋል ብለዋል፡፡

ስምምነቱ ምንድነው?

ሩሲያና ዩክሬንስ ወሳኝ የተባለውን ስምምነት ያደረጉት ከጦርነቱ ጀምሮ የተዘጋውን የጥቁር ባህር በር ለማስከፈትና እህል ለማመላለስ ነው፡፡

የጥቁር ባህር ዳግም ወደ አገልግሎት መግባት በስንዴ፣ በሱፍ ዘይት፣ በማዳበሪያና በሌሎች የምግብ ምርቶችና ግብዓቶች እጥረት ሳቢያ የተከሰተውን የምግብ እጥረት፣ የዋጋ ሽግበትና ረሃብ ለመቀልበስ ያስችላል፡፡

ዩክሬን ከጦርነቱ በፊት ትልክ የነበረውን የምግብ ምርት ከጦርነቱ በኋላ በአንድ ስድስተኛ የቀነሰች ሲሆን፣ በስምምነቱ መሠረት፣ በየወሩ ከጦርነት በፊት እንደነበረው አምስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የሰብል እህል እንድትልክ ያስችላታል፡፡

የዓለም የምግብ ፕሮግራም እንደሚለው፣ 47 ሚሊዮን ሕዝቦች ለከፋ ረሃብ ተጋልጠዋል፡፡ በሌላ በኩል የዩክሬን ጎተራዎች ሙሉ በመሆናቸው በቀጣይ የምርት ወቅት የሚሰበሰበውን እህል ማከማቻ የለም፡፡

ዩክሬን የምግብ ምርቶችን በጥቁር ባህር እንድትልክ ከተደረሰው ስምምነት በተጨማሪ ሩሲያና ተመድ የሩሲያን ማዳበሪያና ሌሎች ምርቶች ባልተገደበ  መልኩ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

እህል መቼ ወደ ሌሎች አገሮች መጓጓዝ ይችላል?

አልጀዚራ የሩሲያውን መከላከያ ሚኒስትር ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ሰብል በጥቁር ባህር የማጓጓዝ ሥራ በቀናት ውስጥ ይጀምራል፡፡ ስምምነቱ ለቀጣይ 120 ቀናት ወይም አራት ወራት የሚቆይ ሲሆን፣ ጦርነቱ የማያቆም ከሆነ ደግሞ የሚታደስ ይሆናል፡፡

ከስምምነቱ ውስጥ ሩሲያ መርከቦች እህል ጭነው በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ጥቃት እንዳትፈጽም፣ ቱርክ በተመድ በመታገዝ የሩሲያ ‹‹መሣሪያ በሕገወጥ መንገድ ይንቀሳቀሳል›› የሚል ሥጋት ለማስወገድም መርከቦችን ትፈትሻለች፡፡ የሩሲያ ማዳበሪያና እህሎች በጥቁር ባህር ወደ ሌሎች አገሮች እንዲላኩ ሁኔታዎች ይመቻቻሉ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...