የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን እንዳይፈርስ ሲከራከርበት የቆየውና ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረበት ከ1928 – 1933 ዓ.ም. ውስጥ የተሠራው ቅይጥ የጋራ መኖሪያ ቤት ‹‹ቪላ ራቲዬሪ›› ሕንፃ መፍረስ ጀመረ፡፡
የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረዳት ፕሮፌሰር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ይህ ነገር የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ሕንፃው ከተሠራ ጊዜ አንስቶ ለቅርስና ጥበቃ የተሰጠ ባለመሆኑ ነው፡፡
በ2012 ዓ.ም. ላይ ባለሥልጣኑ በፋሺስት ጣሊያን ወቅት የተሠራውን ቅይጥ የጋራ መኖሪያ ቤት ‹‹ቪላ ራቲዬሪ›› ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብና ያሉት ችግሮች እንዲፈቱ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ቢያስታውቅም፣ ምንም ዓይነት ለውጥ ማምጣት አለመቻሉን አብራርተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት እየፈረሰ ያለው ሕንፃ ትልቅ ቅርስ መሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ቀደም ብሎ ሕንፃው ሙሉ ለሙሉ ለባለሀብት የተሰጠበት ውል በመኖሩ ሕንፃው ሊፈርስ እንደቻለ አክለው ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ በቅርስነት ከተመዘገቡት መካከል 11 መሰረዛቸውን ገልጸው፣ ለአብነት ያህል በአዲስ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የኮርያ ቃኘው ሆቴል እንደሚገኝበት ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ላይ 132 ታሪካዊ ኪነ ሕንፃ ቅርስነት ያላቸው መመዝገባቸውን አስረድተዋል፡፡
በዚህ መሠረት ለምሳሌነት ያነሱት የዓድዋ ሆቴልን ሲሆን፣ ዓድዋ ስለተባለ ብቻ በቅርስነት መመዝገብ እንደማይችል ገልጸዋል፡፡ ባለሥልጣኑ ካወጣቸው አሥር መሥፈርቶች ውስጥ ሁለቱን ያሟላ በቅርስነት እንደሚመዘገብ ተናግረው፣ በአሁኑ ወቅት እንደ ትልቅ ችግር የሚታየው ከዚህ በፊት እንደ ቅርስ የሚታዩ ሀብቶች ለባለሀብቶች መሰጠታቸው እንደሆነ፣ ይህም ለከተማ አስተዳደሩም ሆነ ለቅርስና ጥበቃ ባለሥልጣን ችግር መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ቅርስን በተመለከተ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮን ቢመለከትም፣ ቢሮው ግን በአሁኑ ወቅት ምንም ዓይነት ሥራ እየሠራ አይደለም በማለት ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡
ከዚህ በፊት የከተማ አስተዳደሩ በቅርስነት የተመዘገቡ ስምንት ቅርሶችን ለባለሀብቶች መስጠቱንና ውል መዋዋላቸውን አክለዋል፡፡
አሁን በመፍረስ ላይ ያለው በቀድሞ ስሙ ‹‹ቪላ ራቲዬሪ›› ሕንፃ ሺ ሰለሞን ኃይሉ፣ ላይንባር፣ በርካታ መጽሐፍ መሸጫዎችና የተለያዩ ድርጅቶች ይገኙበት የነበረና ከታሪካዊ ሕንፃዎች መካከል አንዱ እንደነበር ይነገራል፡፡
ወራሪ ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በያዘበት ወቅት እንደተገነባ፣ በመዲናዋ እንደ ገበያ ሞልነት በማገልገል ከ80 ዓመታት በላይ ሲያገለግል መቆየቱ ይታወቃል፡፡