Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

አሠሪና ሠራተኛ የሚገናኙበት ዓውደ ርዕይ

በአዲስ አበባ ከተማ 23 ሚሊዮን ወጣቶች እንደሚኖሩ ከዓመት በፊት ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከዚህ ውስጥ መሥራት የሚችሉ ወይም ዕድሜያቸው ለሥራ የደረሱ 75 በመቶ (17 ሚሊዮን) ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በመዲናዋ የሚገኙ ወጣቶች ሲታዩ፣ በትምህርት ዝግጅታቸው ከአሥረኛ ክፍል በታች የሆኑትን ጨምሮ ሥራ አጥ የሆኑት 82 በመቶ ናቸው፡፡ በከተማ አስተዳደሩ በዓመት ውስጥ ከሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች መካከል፣ 75 በመቶው ለወጣቶች ነው፡፡ የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ መረጃ እንደሚያሳየው በ2013 ዓ.ም. ከተፈጠረው የሥራ ዕድል ውስጥ 76 በመቶው ለወጣቶች ነበር፡፡ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተመረቁትን በተመለከተ ደግሞ 65,000 ከዩኒቨርሲቲና ከቴክኒክና ሙያ ያጠናቀቁ ዜጎች የሥራ ዕድል አግኝተዋል፡፡ በ2014 ዓ.ም. በተለያዩ ዘርፎች ለተመረቁና ማንበብና መጻፍ ለሚችሉ ሥራ አጥ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር እየተሠራ መሆኑም በተለያዩ መድረኮች ይወሳል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ 18.2 በመቶ ሥራ አጥ ወጣቶች ይገኛሉ፡፡ ይህንን ወደ ዘጠኝ በመቶ ለማውረድ ከመንግሥት ሴክተሮች በተጨማሪ የሥራ ዕድል የሚያስገኙ የግል ተቋማት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ከመላ ኢቨንትና ከሌሎች የግል ሴክተሮች ጋር በመሆን የሥራና አሠሪዎችን የሚገናኝ ዓውደ ርዕይ አዘጋጅቷል፡፡ ይህንን አስመልክቶ የመላ ኢቨንትት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወ/ሮ እሌኒ ዳንኤል፣ ኢንተርፕራይዝና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የሥራ ስምሪት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ሰብሀዲን ሱልጣን፣ የሌዊ የሴቶችና ወጣቶች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ጢሞቲዎስ ሐዬስ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ይህንን የተከታተለችው ሔለን ተስፋዬ እንደሚከተለው አዘጋጅታዋለች፡፡

ጥያቄ፡- ሥራና አሠሪዎችን የሚያገናኙ ዓውደ ርዕዮችን በማዘጋጀት ብቻ የሥራ አጥ ቁጥርን መቀነስ ይቻላል?

መልስ፡- በዓውደ ርዕዩ ብቻ ችግሩ አይቀርፍም፡፡ ነገር ግን ችግሩን በተወሰነ መልኩ ያቃልላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሥራ አጥ ዙሪያ የሚሠሩ ሴክተሮች በጋራ ሲሠሩ ችግሮችን በቀላሉ መፍታት እንዲችሉ ዕድል ይከፍታል፡፡  ዓውደ ርዕዩ ትኩረቱን ያደረገው አነስተኛና መካከለኛ የትምህርት ደረጃና የሥራ ክህሎት ያላቸው ወጣቶችና ሴቶች ላይ ነው፡፡ ይህንን ዓውደ ርዕይ ሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ፣ መላ ኢቨንትና የሴቶችና ወጣቶች ኑሮ ማሻሻል ፕሮጀክት በጋራ ያዘጋጁት ነው፡፡ የመጀመሪያው በግዮን ሆቴል ተዘጋጅቷል፡፡ በዚህም ውጤታማ ሆነን አግኝተነዋል፡፡ 1,080 ለሚሆኑ ወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ሁለተኛው ዙር ደግሞ ከሐምሌ 21 እስከ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በኤግዚቢሽን ማዕከል ይደረጋል፡፡ በዋናነነት ትኩረት ያደረግነው ሴቶችና ወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ማገዝ ነው፡፡ የአገራችንን ሕዝብ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ወጣቶች ስለሆኑ፣ ለእነሱ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ ሥራ አጥነትን መቅረፍ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የተለያዩ ጥናቶችን በማዘጋጀት በሦስት ክፍለ ከተማ ወጣቶች የሕይወት ክህሎት ሥልጠና እንዲያገኙ አድርገናል፡፡ በዚህ ሥልጠና 2,000 ሴቶችና ወጣቶች የሕይወት ክህሎትና የሥራ ዝግጅትና መሰል ሥልጠናዎች አግኝተዋል፡፡

ጥያቄ፡- በዓውደ ርዕዩ ምን ያህል ድርጅቶች ይሳተፋሉ?

መልስ፡– በዓውደ ርዕዩ ከ50 በላይ የሚሆኑ ድርጅቶች ይሳተፋሉ፡፡ ማኑፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽን፣ የአገልግሎት ዘርፎችን በመለየት ዓውደ ርዕዩ ላይ እንዲሳተፉ ጋብዘናል፡፡ አነስተኛ የሥራ ክህሎት ያላቸውን የሚቀጥሩና ሕጋዊ ዕውቅና ያላቸው ኤጀንሲዎችን ይገኛሉ፡፡ ፅዳት፣ ጥበቃና አስተናጋጅ የሚያስቀጥሩ ድርጅቶችን በዓውደ ርዕዩ ይሳተፋሉ፡፡ በዋናነት ከቴክኒክና ሙያ የተመረቁ፣ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን፣ የትምህርት ደረጃቸው ዝቅተኛ መጻፍና ማንበብ የሚችሉ ወጣቶችም የሚሳተፉበት ነው፡፡ ለ15 ሺሕ ወጣቶች ግንዛቤ ለመስጠት ጥረት እናደርጋለን፡፡ ከእነዚህ ወጣቶች ውስጥ አሥር በመቶዎቹ የሥራ ዕድል ያገኛሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡ ከ3500 በላይ የሚሆኑት በዓውደ ርዕዩ ብቻ ሥራ ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 ጥያቄ፡- ለአምስት ዓመታት የሥራ ዕድል ለመፍጠር ስምምነት አድርጋችኋል፡፡ በአምስት ዓመታት ለምን ያህል ወጣቶች ሥራ ዕድል እናስገኛለን ብላችሁ አቅዳችኋል?

መልስ፡- ስምምነት ላይ የደረስነው በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለ200,000 ወጣቶች ሥራ ዕድል ያገኛሉ ብለን ነው፡፡ በአገራችን ላይ ትልቁ ችግር የሥራ ዕጦት ችግሩን ለመፍታት በጋራ እንሠራለን፡፡ በዓውደ ርዕዩ ልጆቻቸውን ይዘው ለሚመጡ ሥራ ፈላጊዎች የሕፃናት ማቆያ ተዘጋጅቷል፡፡ መግቢያም በነፃ ነው፡፡

ጥያቄ፡- በዓውደ ርዕዩ የሦስቱ ተቋማት አስተዋጽኦ ምንድነው?

መልስ፡- ሦስቱም ተቋሞች በመጀመሪያው ኤግዚቢሽን ተሳትፈዋል፡፡ የዘንድሮ ደግሞ ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶችና ወጣቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ የሕይወት ክህሎትና ለሥራ ዝግጁ ማድረግ ላይ የሴቶችና ወጣቶች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክትና መላ ኤቨንት ኦርጋኔይዜሽን ያግዛሉ፡፡ ከተማ አስተዳደሩ ደግሞ የኤግዚቢሽን ማዕከል ዋጋ ቅናሽ እንዲሆን አመቻችቷል፡፡ በዚህ የዓውደ ርዕይ ዝግጅት ላይ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በሥራና በተለያዩ ነገሮች እገዛ አድርገዋል፡፡ አሠሪና ሠራተኛን ሊያገኛኝ የሚችል ዘርፈ ብዙ ሁኔታዎችን አመቻችተዋል፡፡

ጥያቄ፡- በርካታ ሥራ አጥ ወጣቶች በመዲናዋ ይገኛሉ፡፡ ሥራ ለማግኘት የሚያስፈልገው መስፈርት ምንድነው?  

መልስ፡- አነስተኛ ገቢ ወይም ሥራ የሌላቸው ቅድሚያ የሚሰጣቸው ይሆናል፡፡ ፍላጎት ያላቸውና መሥራት የሚችሉ ወጣቶች ከሆኑ ሥራውን በቀላሉ ያገኛሉ፡፡

ጥያቄ፡- በዓውደ ርዕዩ የሚሳተፉ ድርጅቶች የሚከፍሉት ክፍያ አለ?

መልስ፡- ክፍያቸው ዝቅተኛ ነው፡፡ በዋናነት የተፈለገው ወጣቶች የሥራ ዕድሉን እንዲያገኙ ማስቻል ስለሆነ ክፍያው ብዙ አይደለም፡፡ የሦስተኛው ዓውደ ርዕይም ይቀጥላል፡፡ የሊዌ የሴቶችና ወጣቶች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ጋር በወጪ መጋራት ላይ ስምምነት ተደርጓል፡፡ 46 በመቶ ሊዌ ፕሮጀክት የተቀረውን ደግሞ በመላ ኤቨንት የሚሸፈን ይሆናል፡፡ 54 በመቶውን የሚሸፍነው በተወሰነ ደረጃ በሥራ የሚያግዙን ኤስኦኤስ ይሆናል፡፡ አጋርነታቸው የልጆች ማቆያን በማዘጋጀት ነው፡፡ የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ጋር በመመካከር ሕጋዊ ዕውቅና ያላቸው ኤጀንሲዎች ብቻ ይሳተፋሉ፡፡ ከፅዳትና ጥበቃ በተጨማሪ ሞግዚትና ዝቅተኛ ሥራዎች ላይ የሚሳተፉ የሕግ አግባብነት ያላቸው ድርጅቶች እንዲገቡና እንዲቀጠሩ ይፈለጋል፡፡ የዓምናው ተሞክሮ ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ በዓውደ ርዕዩ ስለሚገኙ፣ ለእነሱ የሚሆኑ ተቋሞች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ መካከለኛ የተባሉት ደግሞ በቴክኒክና ሙያ የተመረቁና በቅርቡ የተመረቁ ዜጎችም ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች