Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ባንኮች ካላቸው ካፒታልና ሀብት አንፃር መጪውን ውድድር እንዴት ሊቋቋሙት ይችላሉ?

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚሸጋገርበት ዋዜማ ላይ እንደሚገኝ መገለጽ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በተለይም መንግሥት የውጭ አገሮች ባንኮች ወደ አገር ውስጥ እንደሚገቡ በተለያየ አጋጣሚዎች ካሳወቀበት ጊዜ አንስቶ ርዕሰ ጉዳዩ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ ቆይተዋል፣ እየተሰጡም ይገኛሉ፡፡

የውጭ የፋይናንስ ተቋማት መቼና እንዴት ባለ መንገድ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገቡ እስካሁን የተባለ ነገር ባይኖርም፣ አይቀሬ ለሆነው ጉዳይ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት የንግድ ባንኮች ራሳቸውን ተወዳዳሪ አድርጎ ለማቆየት የሚያስችላቸውን ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ ጊዜ እንዳላቸው ይታመናል፡፡

የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው መሥራታቸው የሚፈጥረው ዘርፈ ብዙ ጥቅም በፋይናንስ ዘርፉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ እየተገለጸ ይገኛል፣ ይህ አስተያየት እንደጠበቀ ሆኖ የዘርፉ ባለሙያዎች አንድ የሚስማሙበት ጉዳይ አለ። ይኸውም፣ የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ይግቡም፣ አይግቡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ባንኮች የሚሰጡትን አገልግሎት አሁን ከሚገኝበት ደረጃ ወደላቀ አሠራርና ዘመኑ ወደሚጠይቀው የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻገር ይገባቸዋል፡፡

ከሰሞኑም የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ትምህርት ቤት የፋይናንስ ትምህርት ክፍል ከአካውንቲንግ ሶሳይቲ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ‹‹የውጭ አገሮች ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ መቀላቀል (መግባት)›› በሚል ርዕሰ የግማሽ ቀን የውይይት መድረክ አዘጋጅተው ነበር፡፡ 

በውይይቱ የተሳተፉ የፋይናንስ ትምህርት ዘርፍ ባለሙያዎች እንዳስታወቁት፣ የአገር ውስጥ የባንክ ገበያ ለውጭ ባንኮች ክፍት እንዲደረግ በተቀመጠው የመንግስት አቅጣጫ መሠረት ኮሚቴ ተዋቅሮ ለዚያ የሚሆን ፖሊሲና የሕግ ማዕቀፍ የማርቀቅ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ የውይይት መድረኩም የባንክ ሴክተሩ ሊበራላዜሽን ለአገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ለኅብረተሰቡና ለሌሎች ተቋማት የሚያመጣው ጠቀሜታና የሚያስከትለውስ ተግዳሮት ምንድነው? በሚለው ዙሪያ ትኩረቱን አድርጓል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዳኪቶ ዓለሙ (ዶ/ር) በኮንፍረንሱ ላይ እንዳስታወቁት፣ የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ መግባታቸውን ብቻ ማሰብ ተገቢ አይደለም፡፡ የውጭ ባንኮች እንደተባለው ወደ አገር ውስጥ ባይገቡስ? የሚለውንም ማሰብ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ልብ ሊባል የሚገባው አንድ ጉዳይ ቢኖር፣ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ቢገቡም ባይገቡም የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ በተለይም ‹‹ባንኮቻችን›› ማደግ አለባቸው የሚለው ጉዳይ ልብ ሊባል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የፋይናንስ ዘርፍን ዝግ አድርጎ መቀመጥ እንደማይቻል የሚገልጹት ዳኪቶ (ዶ/ር)፣ የማይቀረውን ተገንዘቦ መዘጋጀት እንጂ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ ወይስ አይመጡም እያሉ መሥጋት አስፈላጊ አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡

እ.ኤ.አ. በ1994 የኢትዮጵያ መንግሥት ለግል ባንኮች ፍቃድ በሰጠበት ወቅት አብሮ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ ፈቅዶ ቢሆን ኖሮ፣ ምን አልባትም በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሌሎች አገሮች ሥጋት ይሆን ነበር ብሎ ማሰብ ይቻላል የሚል ሐሳብ ይሰጣሉ፡፡ ለዚህ በማስረጃነት የሚያነሱት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲቋቋም ያልነበሩ የጎረቤት አገሮች ባንኮች የሚገኙበት ቁመና ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙት ባንኮች ሥጋት መሆኑን ነው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል የፋይናንስና ኢንቨስትመንት ረዳት ፕሮፌሰር ሰዋለ አባተ (ዶ/ር) በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት፣ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ መቀላቀል በረከቱ ብዙ እንደሆነ እየተነገረ ቢሆንም የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ቢገቡ ምን ያተርፋሉ የሚለውም መጠየቅ አለበት ብለዋል። ‹‹እኛ በፈራናቸው ልክ እነሱስ ወደው ወደ እኛ ይመጣሉ ወይ?›› የሚለው ጉዳይ ከግንዛቤ ሊያዝ የሚገባው ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡

በኢትዮጵያ ያለው ገበያ በትክክል የውጭ ባንኮችን የሚስባቸው ነው ወይ? የሚለው ጉዳይ መታየት አለበት የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ‹‹አሁን እኛ ተፈላጊ ነን እያልን እያሰብን ቢሆንም ነገር ግን ተፈላጊ ልንሆን እንደማንችልም ማዋቅ አስፈላጊ ነው›› በማለት ሐሳባቸውን ያጋራሉ፡፡

የግሎባላይዜሽን ተፅዕኖ ተፈልጎም ይሁን ሳይፈለግ በአንድ አገር ላይ መከሰቱ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የካፒታል (ሪሶርስ) ፍላጎት ለማሟላት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት ባንኮች አለመቻላቸው አብሮ ይገለጻል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግለሰቦች በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ባንኮች ብድር ለማግኘት የሚሄዱበት ርቀት ረዥም መሆኑ በተለያየ መድረኮች ላይ የተሰበሰቡ የፋይናንስ ዘርፍ ባለሙያዎች የሚገልጹት ጉዳይ ነው፡፡

መንግሥት የውጭ ባንኮች ወደ አገር እንዲገቡ የመፈለጉ ጉዳይ በዋናነት ካፒታል ከማምጣት አንፃር ነው የሚል ሐሳብ ይሰነዘራል፡፡ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ቢገቡ ከሚሰጡት ፋይዳዎች አንዱ፣ አገር ውስጥ ያለውን የብድር አቅርቦት እንዲሰፋ ማድረግ መሆኑ ይጠበቃል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን እንደ ባለሙያዎች አስተያየት፣ የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ በመግባታቸው አገር በቀል ባንኮች ተወዳደሪ ይሆናሉ፣ ይኼም ለዘርፉ ዕድገት መሠረት ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡

በጥናት መመለስ ያለበት ጉዳይ ቢሆንም ወቅታዊ የቁጥር መረጃዎች ሲቃኙ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት ባንኮች ካላቸው አጠቃላይ ካፒታልና ሀብት አንፃር ሲወዳደሩ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት ባንኮች አጠቃላይ ድምር በአፍሪካ አንደኛ የሚባለውን ባንክ አያክልም የሚሉት ሰዋለ (ዶ/ር)፣ ይህም ብቻ ሳይሆን የባንኮቹ የሥራ ባህል፣ የሠራተኛው የሥራ ትጋትና የመፈጸም ችሎታ በጣም ደካማ የሚባል እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ እንዲሠሩ የተሰጣቸውን ጊዜ በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል ራሳቸውን በማሳደግ ተግባራት ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በግልፅና በእርግጠኝነት ለመናገር ባይቻልም ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት የውጭ ባንኮች ለተወሰነ ጊዜ ከአገር ውስጥ ባንኮች ጋር በሽርክና (ጆይንት ቬንቸር) ይሠራሉ ተብሎ ይጠበቃል የሚል ቅድመ ግምት እንዳላቸው የሚናገሩት የፋይናንስ ምሁራን፣ በዚህ መንገድ ሊሠራ የሚመጣው የውጭ ባንክ፣ አብሮ የሚሠራውን የአገር ቤት ባንክ ለመምረጥ የሚከተለው መሥፈርት እንደሚኖር ይገልጻሉ። ስለሆነም በውጭ ባንኮቹ ለመመረጥ ደግሞ ዓለም አቀፍ የባንከ ስታንዳርድን ጠብቆ መገኘት አስፈላጊ ከመሆኑ አንፃር፣ አሁን በሥራ ላይ ያሉት ባንኮች ከፍተኛ ውድድር እንደሚጠብቃቸው ያነሳሉ፡፡ 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲቀር ሌሎቹ ምርጥ አሥር የሚባሉት የግል ባንኮች ካፒታላቸው በጣም ትንሽ የሚባል መሆኑን የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ይኼ ደግሞ ለውጭ ኢንቨስተሮች የሚያሳየው ገበያው ላይ ሀብት (ሪሶርስ) እንደሌለ ነው፡፡

የውጭ ባንኮች ይዘው በሚመጡት ሀብት (ሪሶርስ) ብቻ ሳይሆን ከዚህ ከአገር ውስጥ እናገኘዋለን ብለው የሚጠበቁት ሀብት እንዳለ ማወቅ እንደሚገባም መክረዋል። ምክንያቱን ሲያስረዱም ፣ እነዚህ የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ከፍተኛ የመደራደር አቅም (ባርጌይኒንግ ፓወር) ይዘው ነው ብለዋል፡፡ 

ሰዋለ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፣ ትልቁና ዋናው ነገር ባንኮች አቅማቸውን በሁሉም ዘርፍ ማጎልበት ይገባቸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ዋናውና ትልቁ ጉዳይ ብሔራዊ ባንክ ላይ ሊሠሩ የሚገባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ 16 የሚደርሱ ባንኮች ተደምረው ያላቸው ካፒታል ሁለት ቢሊዮን መሆኑን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ያለ መረጃን አጣቅሶ ለመድረኩ ታዳሚያን የቀረበ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻውን አንድ ቢሊዮን ዶላር ሲሸፍን ሌሎች ቀሪ 16 ባንኮች አንድ ላይ ተደምረው ያላቸው ካፒታል 1.2 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በመሆኑም እነዚህ ባንኮች ያላቸውን ካፒታል  ከዚህ የበለጠ ማሳደግ እንደሚገባቸው አኃዛዊ መረጃው ያሳያል፡፡ 

ሰዋለ (ዶ/ር) በንግድ ሥራ ትምህርት ቤት በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ እንዳስታወቁት፣ የአፍሪካ ምርጥ አሥር ባንኮች ዝርዝር ሲወጣ አንድም የኢትዮጵያ ባንክ በዝርዝር ውስጥ የለም፡፡ ከምርጥ አሥር የባንኮች ዝርዝሩ ውስጥ አሥረኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አፍሪካዊ ባንክ 29.9 ቢሊዮን ዶላር የሀብት (አሴት) መጠን አለው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት ምርጥ አሥር ባንኮች አጠቃላይ ሀብታቸው ተደምሮ ያላቸው ሀብት በአፍሪካ ውስጥ ከሚገኘው አሥረኛ ደረጃ ላይ ካለው ባንክ ጋር እኩል ነው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት ባንኮች  ሀብታቸው (አሴት) ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የሆኑት ባንኮች ሰባት ናቸው፡፡ የተቀሩት ባንኮች ያላቸው ሀብት ከአንድ ቢሊዮን በታች ነው፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት ባንኮች በካፒታል ብቻ ሳይሆን በሀብት መጠናቸውም የቀጨጩ መሆናቸው በውይይት መድረኩ ላይ ተወስቷል።

በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ ከሚገኙት ባንኮች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመጀመሪያዎቹ አሥር ዝርዘር ውስጥ አናት ላይ ከመቀመጡ ውጭ በዝርዝር ውስጥ የሚገኝ የኢትዮጵያ ባንክ እንደሌለ ቁጥራዊ ማስረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ ደረጃ በካፒታል አሥረኛ ላይ የተቀመጠው ባንክ 2.9 ቢሊዮን ዶላር እንዳለው በማስረጃነት ያነሱት ሰዋለ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በሁለተኛ ደረጀ ላይ የተቀመጠው ባንክ ያለው ካፒታል 2.4 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ይህ ባንክ በምሥራቅ አፍሪካ ደረጃ እንኳን ባለው ካፒታል 13ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በማንሳትም የካፒታል መጠንን ማሳደግ ወሳኝ እንደሆነ አሳስበዋል። በተጨማሪም፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ ባንኮች የቁጠባ ሥራ (ዲፖዚት ሞቢላይዜሽን) ላይ እጅግ በጣም መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ተመላክቷል፡፡

በምሁራን አስተያየት፣ የኢትዮጵያ ባንኮች በቀጣይ ይገባሉ ተብለው ከሚጠበቁት የውጭ ባንኮች ጋር ለመወዳደር ትልቁና ዋነኛው ጉዳይ የካፒታልና የሀብት (አሴት) አቅማቸውን ማሳደግ ነው፡፡ ሰዋለ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች የካፒታል ጣሪያ እንደሚያስቀምጠው ሁሉ፣ እነዚሁ ባንኮች በየዓመቱ በትንሹ ሊያንቀሳቅሱ የሚገባውን የቁጠባ (ዲፖዚት) መጠን ላይ ሥራዎች ሊሠራ ይገባል ይላሉ፡፡

የባንክ ሥራ ትርፍ ማስገኘትና ያንንም ሪፖርት ማድረግ ብቻ አይደለም የሚሉት ምሁራን፣ ይልቁንም የዘርፉን የሰው ኃይል ማብቃት ላይ ማተኮር፣ ቴክኖሎጂ ላይ መሥራት ግዴታ መሆኑን አበክረው ያሳስባሉ፡፡ 

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንኪንግ ፖሊሲና የፋይናንሺያል አናሊሲስ (የባንክ ዘርፍ ፖሊሲና የፋናንስ ትንተና) ቡድን ኃላፊ የሆኑት አቶ ስንታየሁ ደሳለኝ፣ ተቋማቸውን በመወከል ሳይሆን በግል ወክለው በዘርፉ ያላቸውን ልምድ መሠረት አደርገው በሰጡት አስተያየት ከውጭ ባንኮች መግባት ጋር ተያይዞ የተደረጉት ጥናቶች የውጭ ባንኮች በገቡባቸው አገሮች የሚገኙ ማዕከላዊ ባንኮች አቅም መሻሻሉን ያስረዳሉ ብለዋል፡፡ ምክንያቱን ሲጠቅሱም፣ የውጭ ባንኮች መግባትን ተከትሎ ማዕከላዊ ባንኮች አቅማቸውን በማሻሻል ላይ እንደተጠመዱና እንደተሻሻሉ ጥናቶቹ ያስረዳሉ ብለዋል፡፡

እንደ ሰዋለ (ዶ/ር) አስተያየት፣ ብሔራዊ ባንክ በዘርፉ ላይ ያለውን ግዙፍ ስልጣን ተጠቅሞ በድንገት በመነሳት በግል ባንኮች ላይ የሚያሳልፈው መመርያና ውሳኔ ወደ አገር ውስጥ መግባት የሚፈልጉ የውጭ ባንኮችን ሊያሸሽ እንደሚችል በመጥቀስ ጥንቃቄ እንዲደረግ መክረዋል።

በፍርሀት ብቻ ብሔራዊ ባንክን እየታዘዙ ያሉ ድርጅቶች እንዳሉ የሚታወቅ ነው ያሉት ሰዋለ (ዶ/ር)፣ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ የሚጠበቁት የውጭ ባንኮች እንደ እነዚህ ዓይነት ችግሮች መኖራቸውን ቢያውቁ ወደ ኢትዮጵያ የመግባት ሐሳቡን ከመጀመሪያውኑ ላያስቡት ይችላሉ ባይ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች