Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በግብርና ምርቶች ላይ የተንጠለጠለው የወጪ ንግድና የቀጣይ ዓመት ዕቅድ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተጠናቀቀው 2014 የበጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 4.12 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማግኝት በዘርፉ የመጀመርያ የሚባል ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበ ቢሆንም የአገሪቱ የወጪ ንግድ አሁንም በግብርና ምርቶች ላይ እንደተንጠለጠለ ነው።

ባለፉት ሦስት የበጀት ዓመታት የአገር በቀል ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት፣ የወጭ ንግድን በመጠን፣ በዓይነትና በጥራት ለማሳደግ የፖሊሲ፣ የስትራቴጂና የመዋቅራዊ ለውጥ ዕርምጃዎች መወሰዳቸው በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ለተገኘው ውጤት ዓይነተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት በሰጠው የኤክስፖርት አፈጻጸም መግለጫው አስታውቋል፡፡ 

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተመዘገበው ገቢ የዕቅዱን 90.3 በመቶ ሲሆን፣ ከባለፉት ዓመታት አፈጻጸም አንፃር በዓመቱ የነበረው እንቅስቃሴ በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመዘገበ ከፍተኛ የወጪ ንግድ ገቢ መሆኑን ተመላክቷል፡፡

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ ትስስርና ወጪ ንግድ ፕሮሞሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ እንዳስታወቁት፣ በ2014 ዓ.ም. በወጭ ንግድ የታየው አፈጻጸም ትርጉሙ ፈርጀ ብዙ ነው፡፡ 

‹‹በውሰጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች ውስጥ ሆነን ያስመዘገብነው ውጤት ነው›› ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታው፣ ለመጀመሪያ ጊዜ አገሪቱ ከወጪ ንግድ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘችው በ1998 ዓ.ም. መሆኑን በማስታወስ፣ ከዚያ በኋላ የውጭ ግኝቱ ብዙም ሳይጨመር በመቶ ሚሊዮን ብልጫዎች እየታዩበት ቆይቶ በ2012 ሁለት ቢሊዮን አምና ደግሞ ሦስት ቢሊዮን እንደደረሰ ተናግረዋል፡፡

እንደ ሚኒስቴር ዴኤታው ገለጻ፣ የወጭ ንግድ ማደጉ ከዶላር ገቢ ባሻገር የአገሮችን የውጭ ብድር የማግኘት ዕድል የሚያሰፋ ነው፡፡ ለጋሽ ወይም ዕርዳታ ሰጪ አገሮች ለሚያርጉት ድጋፍ በተለይም በወጭ ንግድ የሚደረገው የአገሮች ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው፡፡

የተገኘው ውጤት ከዘርፍ አንፃር ሲታይ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ያልታየበት ቢሆንም፣ በአፈጻጸሙ መሠረት የግብርና ምርቶች የወጪ ንግድ 72 ከመቶ የሚሆነውን ድርሻ መያዙንና የግብርና ዘርፎች በአማካይ የዕቅዳቸውን 106 በመቶ አፈጻጸም እንዳስመዘገቡ ተናግረዋል፡፡

ከግብርና ምርቶች ቡና ከፍተኛ አፈጻጸም የተገኘበት ሲሆን፣ አገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ውጭ ከላከችው የቡና ምርት 1.4 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች፡፡ ከዚያ ውጪ የአበባ ምርት ውጤቶች በመጠንና በገቢ ጭማሪ የታየባቸው መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

ከግብርና በመቀጠል ኢንዱስትሪ ለወጭ ንግድ አፈጻጸሙ 12 በመቶ የሚደርስ አስተዋፅኦ አደርጓል፡፡ የኢንዱስትሪ ምርቶች ደግሞ የዕቅዳቸውን አማካይ 84 በመቶ የሆነ አፈጻጸም አስመዝግበዋል፡፡ የማዕድን ዘርፍ የወጭ ንግድ አፈጻጸሙን 14 በመቶ ድርሻ መሸፈኑ የተመላከተ ሲሆን፣ ዘርፉ በአጠቃላይ ከያዘው ዕቀድ 53 በመቶ የሚሆነውን ብቻ መፈጸም ችሏል፡፡

ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የላከቻቸውን ምርቶች አፈጻጸም የተለያዩ ተቋማት የሚከታተሏቸው ሲሆን፣ ቡናን የቡናና ሻይ ባለሥልጣን፣ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬን የግብርና ሚኒስቴር፣ የጥራጥሬና ቅባት እህሎችን፣ ጫት፣ የቁም እንስሳት፣ ዕጣን ሙጫና ባህር ዛፍ፣ የብርዕ አገዳ እህሎችን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሲከታተል፣ በሌላ በኩል ማዕድን ሚኒስቴር የማዕድን ምርቶችን እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርቶችን ደግሞ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ይከታተሉታል፡፡ እነዚህ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በጋራ ብሔራዊ የአስተባባሪ ኮሚቴ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው የተተገበረ እንቅስቃሴ መሆኑን አቶ ካሳሁን አብራርተዋል፡፡

መዋቅራዊ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር አለመምጣቱ በበጀት ዓመቱ ታዩ ከተባሉት ተግዳሮቶች አንደኛው መሆኑ ተገልጿል፡፡ አሁንም አገሪቱ በግብርና ኤክስፖርት ላይ የተመሠረተ ሥራዎችን እየመራች መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የኮንትሮባንድ ንግድ አሁንም የኤክስፖርት ወይም የወጪ ንግዱን እየፈተነው ይገኛል ብሏል፡፡ ድርጊቱን ለመቆጣጠር የሚያስችል ግብረ ኃይል ተደራጅቶ በእያንዳንዱ ቦታዎች ከቁም እንስሳት፣ ከጫት አንፃር ቁጥጥር የማድረጉ ሥራ ዓምና የጀመረ፣ በዚህ ወቅትም ሰፋፊ ዕርምጃዎች እየተወሰደበት የሚገኝ ተግባር መሆኑን መሥሪያ ቤቱ አያይዞ ገልጿል፡፡

በተለይም የፌዴራል ፖሊስ፣ ጉምሩክ ኮሚሽንና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በጋራ በመሆን በእያንዳንዱ የወጪ ንግድ መውጫ ማዕከላት ተብለው በተለዩት በጋላፊ፣ በጅግጅጋ፣ በድሬዳዋ መውጫ፣ በሞያሌ በኩል ባሉት በሮች ሁሉ ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል ሲል የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያስረዳል፡፡ ያም ሆኖ ኮንትሮባንድ ቁጥጥር እየተደረገበትም የወጪ ንግዱን እየተፈታተኑት ከሚገኙት ዋነኛ እንቅፋቶች የሚጠቀስ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ዴኤታው ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የታችና የጎንዮሽ ግንኙነቶች በተሟላ ደረጃ አለመዳበር ሌላው የበጀት ዓመቱ ፈተና እንደነበር ተመላክቶ፣ ከላይ የተነሱትን ነቅሶ አውጥቶ በመቅረፍ የብሔራዊ ኤክስፖርት አስተባባሪ ኮሚቴው በ2015 የበጀት ዓመት ከወጭ ንግድ አገሪቱ 5.4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንድታገኝ ዕቅድ ወጥኖ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተነግሯል፡፡

አቶ ካሳሁን እንደሚናገሩት፣ በ2015 የበጀት ዓመት ለማግኘት የተወጠነው ዕቅድ የተንጠራራ ቢመስልም ኢትዮጵያ ካላት አቅም አንፃር፣ በአግባቡ ከተመራና የባለ ሚናና ባለድርሻ አካላት ቅንጅት በሚጠበቀው ልክ ከመጣ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ 

በ2014 የበጀት ዓመት በቡና፣ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ የወጭ ንግድ ምርቶች ከዕቅድ በላይ ገቢ እንደተገኘው ሁሉ በአንፃሩ የቅመማ ቅመም፣ የቁም እንስሳት፣ ወርቅና ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ዝቅተኛ ገቢ ያስገኙ የወጭ ምርቶች ነበሩ፡፡

የማዕድን ወጭ ንግድ በታሰበው ልክ አፈጻጸም እንዳይመዘገብበት ካደረጉት ጉዳዮች ውስጥ በማዕድን ማውጫ አካባቢዎች ያጋጠመው የፀጥታ ችግር ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ሚኒሰቴር መሥሪያ ቤቱ ያስረዳል፡፡ ይህንን ተግዳሮት በተያዘው አዲሱ የበጀት ዓመት ይቀረፋል የሚለው ጉዳይ ታሳቢ ማድረግ ይገባል ሲሉም አቶ ካሳሁን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከውጭ ንግድ በ2014 የበጀት ዓመት ያገኘችው የ4.1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ከፍ እንዲል ካደረጉት ጉዳዮች ውስጥ በዓለም አቀፍ ገበያ የዕቃዎች ዋጋ ማሻቀብ አንዱ ምክንያት መሆኑን በተለያዩ ባለሙያዎች እንደሚነሳ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ካሳሁን፣ አስተያየቱ በዘርፉ የተሠራውን ሥራ ለማደብዘዝ የቀረበ እንጂ አገሪቱ ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶች ከቀደሙት ዓመታት በመጠንም ብልጫ የታየባቸው መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

 የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የ2015 የበጀት ዓመት ዕቅድ የወጭ ንግድ ታሳቢ ሲደረግ ከታሰቡት ጉዳዮች ውስጥ ብዙ የማደግ አቅም ያላቸውን ዘርፎች መለየታቸውን ያነሳል፡፡ አቶ ካሳሁን እንዳስረዱት፣ ቡና በዚህ ወቅት ካስመዘገበው በላይ የተሻለ አፈጻጸም ሊመዘገብበት ይችላል፡፡ ከአበባ አኳያም የበለጠ ቢሠራ የተሻለ ገቢ እንደሚገኝ አመላካቾች ይገኛሉ፡፡ ጫት ከዚህ በላይ የአሠራር ሥርዓቱ ዘምኖና የኮንትሮባንድ ንግዱን በመቆጣጠር የተገኘውን ገቢ በዕጥፍ መጨመር የሚችልበት ዕድል እንዳለ ሚኒስቴር ዴኤታው ይናገራሉ፡፡

በሌላ በኩል አገሪቱ ከፍተኛ አለመረጋጋትና የተለያዩ ችግሮች ውስጥ ባለችበት በዚህ ወቅት የወጪ ንግድ ላይ ስኬት ማስመዝገብ መቻሏ የራሱ አንድምታ እንዳለውና በቀጣይም የዕድገቱን ዘላቂነት ለማስቀጠል የተለያዩ ተግባራት መከናወን እንዳለባቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያብራራሉ::

በወጪ ንግድ ዘርፉ የተመዘገበው ውጤት እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም ብዙ ክፍተቶች መኖራቸውን የሚናገሩት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች፣ አገሪቱ በወጪ ንግድ ልታሳካ ግብ የጣልችበትን ያህል ውጤት በዚህ ወቅት አስመዝግባለች ለማለት የሚያስደፍር አለመሆኑንም ያነሳሉ፡፡

የታሰበውን ያህል እንዳይሳካ ያደረጉ የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ቢችሉም፣ አገሪቱን ብዙ ዋጋ ያስከፈላት ጦርነት መካሄዱና የወጪ ንግድ ምንጭ የሆኑት አንዳንድ ምርቶች ጦርነቱ ከሚካሄድበት አካባቢ የሚገኝ መሆኑ በዘርፉ ለማሳካት የታቀደው ግብ እንዳይሳካ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ሪፖርተር በተለያየ ወቅት ያነጋገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

ሰላምና መረጋጋት የወጪ ንግድን ጨምሮ ለሁሉም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ስኬት ወሳኝ ነው የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች፣ በቀጣይ ጊዜያት በዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ አገሪቱ ወደ ሰላምና መረጋጋት እንድትመለስ ማድረግ ያስፈልጋል የሚል ሐሳብ ያቀርባሉ:: 

ከሰሞኑ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ይህንኑ የወጪ ንግድ ተግዳሮቶችና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ስለወጪ ንግድ ዕድልና ተግዳሮት በዋና አጀንዳነት ቀርቦ ሰፊ ውይይት መደረጉ ይታወሳል፡፡  

በኢትዮጵያ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ምርትን አለማሳደግ፣ የጥራት ችግርና የመሳሰሉት በፊትም የሚቀርቡ፣ አሁንም እንደ ችግር መነሳታቸው መንግሥትም ሆነ የግሉ ዘርፍ ይህንን ችግር እየፈቱ መሄድ ያለመቻላቸውን ያሳያል የሚል ሐሳብ በውይይቱ ቀርቦ ነበር፡፡ 

የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ አሁንም በአነስተኛ ገበሬዎች ተመርቶና ተሰብስቦ ለገበያ እንደመቅረቡ ይህንን አሠራር መቀየር ሳይቻል ከወጪ ንግድ ዕድገት መጠበቅ እንደማይቻል በባለሙያዎች የቀረበው ሙያዊ አስተያየት ያስረዳል፡፡

የወጪ ንግዱ ትልቅ ችግር ያለበትና በወጪና በገቢ ንግድ መካከል ያለውን የንግድ ሚዛን ጉድለት እያሰፋ እንዲሄድ ማድረጉንም የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ባደረገው የውይይት ወቅት መነሳቱ ይታወሳል፡፡

ለአብነትም የኢትዮጵያን የጫት የወጪ ምርት አፈጻጸም በተመለከተ አስተያየት የሚሰጡ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች፣ የጫት ወጪ ንግድ ለአገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ቢያስገኝም፣ ነገር ግን ለምርቱ ምንም ዓይነት ማበረታቻ ሳይደረግለት ከሌሎች ምርቶች የበለጠ የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስገኝ ያስረዳሉ፡፡ አንዳንድ አገሮች ግን ከዚህ የበለጠ የከፋ ምርት እየላኩ የውጭ ምንዛሪ ግኝታቸውን እያሳደጉ በመሆኑ በወጪ ንግድ ላይ አገሪቱ ያላትን ሀብት ሁሉ መጠቀም ይገባታል የሚል የሰላ ትችት ያቀርባሉ፡፡  

አሁንም የወጪ ንግዱ መጠነኛ ለውጥ ታይቶበታል ቢባልም፣ ዘለቄታው ላይ ግን የሚጠራጠሩ መሆኑን የሚናገሩት የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ለአብነት ዘንድሮ ቡና በጥሩ ሁኔታ እየተላከ ቢሆንም፣ ይህ ለውጥ የታየው ሌሎች አምራቾች ተወዳዳሪ አገሮች ችግር ስለገጠማቸው እንጂ፣ የቡና የወጪ ንግድ በዚህ ደረጃ አድጎ አይደለም የሚል ሐሳብም ይሰነዝራሉ፡፡

እንደ ማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች አስተያየት፣ የተገኘውን የወጪ ንግድ ለማስቀጠልና የወጪ ንግድ ገቢው ከዚህም በላይ እንዲሆን ዋናው ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ነው፡፡ ምርትን በብዛት ማምረት አንድ ነገር ሲሆን፣ በትንሽ ወጪ ብዙ ማምረት ሲጀመር ከዓለም ገበያ ጋር መወዳደር እንደሚቻል ይጠቁማሉ፡፡

በሌላ በኩልም የተዛቡ ኢንቨስትመንቶች ካሉ እነሱን ማስተካከልም ለቀጣይ የወጪ ንግድ ገቢው ዕድገት ሌላኛው ሥራ ተደርጎ መወሰድ እንዳለበት ይገለጻል፡፡ ለኤክስፖርተሮች የሚሰጠው የውጭ ምንዛሪም መታየት እንደሚገባው አስተያየት ሰጪ ባለሙያዎች የሚያነሱት ሐሳብ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች