በፖለቲካ አለመረጋጋት በሚፈጠር ግጭት፣ ረሃብ፣ ድርቅ፣ ስደት፣ መፈናቀልና በመሰል ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች፣ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ለበርካታ ጊዜያት በመታመስ ይታወቃል፡፡ በመልካዓ ምድራዊ አቀማመጡ የተነሳ ባለው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚዊ ፋይዳ፣ የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚራሯጡና በጎሪጥ የሚተያዩ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤቶች፣ እንዲሁም ጠንካራ ወታራዊ አቅም የገነቡ አገሮች ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በአካባቢው ደፋ ቀና እያሉ ናቸው፡፡
የአፍሪካ፣ የእስያና አውሮፓ አኅጉሮች መገናኛ የሆነው የአፍሪካ ቀንድ ለኃያላኑ አገሮች የወታደራዊ ይዞታ እሽቅድምድም ዓይነተኛ ምክንያት ከመሆኑም በላይ፣ በትራንስፖርት ረገድ በቀጣናው በጣም ጠቃሚ ቦታ እንዳለው የሚነገርለት ቀይ ባህር ከስዊዝ ካናል ባለው ቅርበትና ትልቅ ጠቀሜታ አንፃር የዓለማችን የነዳጅና የሸቀጣ ሸቀጥ አቋራጭ ማጓጓዣ መሆኑም ሌላው ምክንያት ነው።
ኃያላኑ አገሮች በሚደርጉት ጥቅም የማስጠበቅ ትግል ውስጥ በቀጣናው በተለይም በኢትዮጵያ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት፣ የደቡብ ሱዳንና የሶማሊያ አለመረጋጋት፣ የአልሸባብ ተፅዕኖ፣ የኤርትራ የፖለቲካ አቋም፣ እንዲሁም የሱዳን ፖለቲካዊ ቀውስን እንደ ምክንያት በማቅረብ አገሮቹ የፖለቲካ ጎራ እየያዙ አካባቢውን ለማተራመስ ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል፡፡
ከተጀመረ ሁለት ዓመታት ሊሞላው የወራት ዕድሜ የቀሩት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ፣ በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል እርቅ አለማውረድ፣ እንዲሁም በሱዳንና በሶማሊያ ውስጥ የሚታየውን ፖለቲካዊና ወታደራዊ ቀውስ በሰላምና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት በሚል ዕሳቤ አሜሪካና ምዕራባውያን በአንድ በኩል፣ ቻይናና ሩሲያ በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ያንዣበበውን ፖለቲካዊና ወታደራዊ ቀውስ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት የየራሳቸውን የቀጣናው ልዩ ልዑክ እስከመሰየም ደርሰዋል።
ለአብነትም ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ የአሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የቻይና፣ እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኞቻቸውን ሾመው በኢትዮጵያና በአካባቢው ያለውን የፖለቲካ አለመረጋጋት ሰላማዊ መፍትሔ እንዲገኝ ጥረት እያካሄዱ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
የአሜሪካ መንግሥት በአንድ ዓመት ውሰጥ ለአፍሪካ ቀንድ ሦስት ልዩ መልዕክተኞችን በተከታታይ መለዋወጡ ይታወሳል፡፡ በ2013 ዓ.ም. ጄፍሪ ፌልትማን (አምባሳደር)፣ በመቀጠልም በጥር 2014 ዓ.ም. ዴቪድ ስታተርፊልድ (አምባሳደር) የተቀየሩ ሲሆን፣ በግንቦት 2014 ዓ.ም. ማይክ ሐመር (አምባሳደር) ስታተርፊልድን ተክተው እየሠሩ ነው፡፡
በሌላ በኩል ቻይና በየካቲት 2014 ዓ.ም. አንጋፋ የተባሉትን ዲፕሎማት ዙ ቢንግን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አድርጋ ከሾመች በኋላ፣ ከሰኔ 20 እስከ 21 2014 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ማዘጋጀቷ ይታወሳል፡፡
በዚህ ቀጥተኛና የእጅ አዙር ቅርምት በበዛበት የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና እምብዛም በፖለቲካ ሚናዋ በአፍሪካ የማትታወቀው ቻይና በልዩ መልዕክተኛነት ሾማ የላከቻቸው ዙ ቢንግ፣ በመጋቢት 2014 ዓ.ም. ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ቻይና የአፍሪካ ቀንድ አገሮችን የደኅንነት፣ የልማትና የአስተዳደር ችግሮችን ለመፍታትና አንድነትን ለማጎልበት አብራ እንደምትሠራ ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናግረው ነበር፡፡
በተጨማሪም፣ ‹‹ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የቀጣናው ወሳኝ አገር በመሆኗ፣ ሰላምን በማስፈን ረገድ ገንቢ ሚና መጫወት እንዳለባት አስምረውበታል፤›› ሲል የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም መግለጹ አይዘነጋም፡፡
በተመሳሳይ በየካቲት 2014 ዓ.ም. በዩክሬን ወታደራዊ ዘመቻ የከፈተችው ሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ፣ በአራት የአፍሪካ አገሮች ጉብኝት ጀምረዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ ፕሬስ አታቼ ማሪያ ቸርኑኪና ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ጉብኝት ከአፍሪካ ኅብረት ተወካዮችና ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በአገራዊና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ፡፡
የመጀመሪያ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን በግብፅ የጀመሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ማክሰኞ ሐምሌ 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ደርሰዋል፡፡ ከኢትዮጵያ በመቀጠልም በኡጋንዳ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተገልጿል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ላቭሮቭ ዋነኛ ጉብኝት በሚቀጥሉት ወራት ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው የአፍሪካ ሩሲያ የሰላም ኮንፈረንስ ቅድመ ዝግጅት ላይ ለመነጋጋር እንደሆነ ቢጠቀስም፣ በርካታ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ዓላማው ሌላ ነው፡፡ ዓለምን ለሁለት ከከፈለው የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ጋር በተያያዘ የአፍሪካ አገሮችን ድጋፍ ለማግኘት፣ እንዲሁም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከአንድ ሳምንት በፊት በመካከለኛው ምሥራቅ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ በዚሁ ቀጣና ሩሲያ ያላትን ተደማጭነት እንደገና ለመፈተሽና ከመሪዎች ጋር ለመምከር እንደሆነ ተንታኞቹ ያስረዳሉ፡፡
በሩሲያና በዩክሬን መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ሁለቱ አገሮች ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡት ነዳጅ፣ ጋዝና፣ ስንዴ፣ እንዲሁም ሌሎች ምርቶች ወደ ገበያ መቅረብ ካለመቻሉም በላይ የዓለምን የሸቀጦች ዋጋ ንረት አይነኬ አድርጎታል፡፡
ዩክሬንና ሩሲያ ከ40 በመቶ በላይ የሚሆነውን የአፍሪካን ስንዴ ፍላጎት እንደሚያሟሉ መረጃዎች የሚመላክቱ ሲሆን በተለይም ግብፅ፣ ናይጄሪያ፣ አልጄሪያ፣ ሞሮኮ፣ታንዛኒያ፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያና ሴኔጋል ዋናዎቹ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያን ከገጠሟት የውስጥ ችግሮች በተለይም በታላቁ ህዳሴ ግድብ የግብፅ ጫና፣ ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር ተያይዞ ከአሜሪካና ከምዕራባውያን አገሮች በኩል ተጠንስሰው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መድረክ የሚቀርቡና በኢትዮጵያ ላይ ሊደረጉ የታሰቡ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማዕቀብ ውጥኖችን በመቃወምና ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም የምትታወቀው ሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከኢትዮጵያና ከቀጣናው አገሮች ጋር በአካባቢው ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ላቭሮቭ ከዚህ ቀደም በነበሩ መድረኮች በህዳሴ ግድብ ግንባታ ሒደት ላይ የሚስተዋሉ አለመግባባቶች መፈታት ያለባቸው፣ በመነጋገርና በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ብቻ መሆኑን በመናገር ይታወቃሉ፡፡
በግብፅ ጉብኝታቸውን የጀመሩት ላቭሮቭ ከግብፅ አቻቸው ሳሚ ሹኩሪ፣ እንዲሁም በግብፅ ከዓረብ ሊግ አምባሳደሮች ጋር ውይይት ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ሚኒስትሩ ያገኟቸው ሁለቱም አካላት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ በተደጋጋሚ ተቃውሞ በማሰማት የሚታወቁና የታሰበው ንግግር በአፍሪካ ኅብረት በኩል መደረጉን የማይፈልጉ አካላት ናቸው፡፡
በሰኔ 2013 ዓ.ም. ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላቭሮቭ ጋር በሞስኮ ተገናኝተው በመከሩበት ወቅት፣ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚደረገውን ማንኛውም ጣልቃ ገብነት ሩሲያ እንደማትደግፍ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መግለጻቸውንና በሁለቱ አገሮች መካከል ያሉ የትብብር መስኮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ፣ እንዲሁም የተለያዩ የትብብር መስኮች ላይ አብረው ለመሥራት መስማማታቸውን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጾ ነበር፡፡
መዛግብት እንደሚሳዩት የቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት ተከትሎ በ1990ዎቹ የሶቪዬት ኅብረት መበታተንና በሩሲያ የነበረው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ፣ አገሪቱ በውጭ አገሮች የነበሩዋትን ጥቅሞችና እንደ የባህልና የኢኮኖሚ ማዕከሎችን የመሳሰሉ ተቋማትን መዝጋት አልያም ከሚጠበቀው በታቸ እንዲቀሳቀሱ ተገዳ ነበር።
በዚህም ሩሲያ በአፍሪካ ከሚገኙ 20 የባህል ማዕከላትዋ 13 ያህሉ እንዲዘጉ ማድረጓን፣ በዚህም በብዙ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የመንግሥታትና የርዕዮተ ዓለም ለውጥ እንዲመጣ፣ እንዲሁም የምዕራባውያን ተፅዕኖ እንዲጎላ ምክንያት ሆኗል።
በ1980ዎቹ መጀመሪያ በሶቪየት ኅብረት ወቅት በሞስኮ ከተማ በጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል የሁለተኛ ዲግሪያቸውን የተማሩትና አሁን በኢትዮጵያ በማስተማር ላይ የሚገኙት አቶ በላይነህ ወርቁ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በኢትዮጵያና በሩሲያ መካከል በደርግ ዘመን የነበረው ግንኙነት ከዕርዮተ ዓለም ቁርኝት የተነሳ ከፍተኛ ደረጃ የሚባል ግንኙነት ላይ ነበረ ይላሉ፡፡ ነገር ግን ኢሕአዴግ አገዛዝ ወቅት ከሩሲያ ይበልጥ ወደ ምዕራባውያን ያደላ ግንኙነት የነበረ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ከሩሲያ ማግኘት ትችል የነበረውን የወታደራዊ፣ የቴክኖሎጂ፣ የሰው ኃይል ግንባታና የግብርና ቴክኖሎጂ አቅም ማግኘት አለመቻሏን ተናግረዋል፡፡
በደርግ ዘመን በሶቭየት ኅብረት የተማሩና በወታደራዊና በግብርና ቴክኖሎጂ የሠለጠኑና የበቁ ባለሙያዎች በኢሕአዴግ ዘመንም ቢሆን ኢትዮጵያ እንዳልተጠቀመችባቸው የሚገልጹት አቶ በላይነህ፣ አሁንም ቢሆን ከምዕራባውያን አገሮች ባልተናነሰ ቴክኖሎጅ የሚቀሰምባት አገር በመሆኗ መንግሥት አካሄዱን ካስተካከለ ኢትየጵያ ከሩሲያ በርካታ አዳዲስ ፈጠራዎች መጠቀም እንደምትችል አክለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ሩሲያን ጨምሮ ኃያላኑ አገሮች በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ የሚያደርጉት ግብግብና ውድድር ሁሉም አገሮች የየራሳቸውን አገራዊ ጥቅም ለማስከበር የሚሮጡ በመሆናቸው፣ ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ብዛት አንፃር በቀጣናውና በኃያላኑ አገሮች ዘንድ የሚኖራትን የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ተደማጭነት ልታሳድግበት የምትችልባቸውን መንገድ መዘየድ እንዳለባትም አስረድተዋል፡፡
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝት ኃያላን አገሮች በአፍሪካ ቀንድ ውድድር ላይ መሆናቸውን አንዱ ማሳያ እንደሆነ የገለጹት ደግሞ፣ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ጉደታ ከበደ (ረዳት ፕሮፌሰር) ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ ከተጨማሪ በምሥራቅ አፍሪካ የመልክዓ ምድራዊ አቀማመጧና ካላት ተደማጭትና ትልቅ ቀጣናዊ ተዋናይነትና የአፍሪካ መግቢያ ተብላ የምትጠራ ከመሆኗ አኳያ በአሜሪካ፣ በቻይና፣ እንዲሁም በሩሲያ የሚታየው የውድድር መንፈስ ቀጣናውን የመቆጣጠርና የበላይ የመሆን አንድምታ ያለው መሆኑን የገለጹት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ኢትዮጵያ ምንም እንኳ በኢኮኖሚ ደሃ ተብላ የምትጠራ ቢሆንም ጂኦፖለቲካ አቀማመጧ ተመራጭ ያደርጋታል ብለዋል፡፡
የሚኒስትሩ ጉብኝት ሩሲያ በአፍሪካ ላይ ያላት ኢንቨስትመንት አናሳ በመሆኑና አንደ ቻይናና ምዕራባውያኑ በኢኮኖሚው የሚጠቀስና ግንኙነቱን ሊያጠናክር የሚችል መስክ እምበዛም ባለመኖሩ፣ ከዩክሬን ጋር በገባችበት ጦርነት በአሜሪካና በምዕራባውያን አማካይነት በተፈጠረው ጎራ የራሷ የሆነ ደጋፊ አገሮችን ከጎኗ ለማሠለፍ የታሰበ ስለመሆኑም አክለው ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ ከምሥራቅ አፍሪካ ተፈላጊ በመሆኗ ከየትኛውም ኃያል አገር ሊመጣ የሚችል ሥጋት፣ ጫናና መልካም አጋጣሚ ጥንቃቄ ተደርጎበት ከጭፍን ወገንተኝነት በፀዳና በዲፕሎማሲ ጥበብ ማስኬድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በፖለቲካል ሳይንስ አገሮች በግንኙነታቸው ወቅት ምክንያታዊ ናቸው ተብሎ እንደሚተረጎም የገለጹት ምሁሩ፣ ምንም ዓይነት የተለየ አገራዊ ፍላጎት ቢኖርም እንኳ ምንጊዜም ቢሆን እንደ አገር አዋጭ የሚባለውንና የሚያራምደውን መንገድ መምረጥ፣ የውስጥ ተጋላጭነትን መቀነስና ጥቅምና ፍላጎትን አጣጥሞ መሄድ ያስፈልጋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ዳምጠው ተሰማ በበኩላቸው፣ ቻይና በአፍሪካ ቀንድ የረዥም ጊዜ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ እንዳላትና በተለይም የኅብረቱን ዋና መቀመጫ ከገነባች ወዲህ የቻይና አፍሪካ ግንኙነት እየጨመረ በመምጣቱ፣ ይህም በአፍሪካ ቀንድ የኃያላን አገሮች እሽቅድምድም ማሳያ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በተመሳሳይ የአፍሪካ ሩሲያ ግንኙነት እምብዛም እንደ ሌሎቹ ኃያላን አገሮች የጎላ ባለመሆኑ፣ ከአሜሪካና ከሌሎች ምዕራባውያን አገሮች በአፍሪካ ላይ እየበረታ የመጣው ጫናና ጣልቃ ገብነት በሩሲያ ላይ ሊያመጣ የሚችለው ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደሚሆን ያስረዳሉ፡፡ ሩሲያ ወደ አፍሪካ ቀንድ በተለይም ወደ ኢትዮጵያ መምጣቷ ደግሞ ሌላኛው የዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፉክክር አንዱ መገለጫና ማሳያ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም ሩሲያ ወደ አፍሪካ ስትመጣ በምሥራቅ አውሮፓ እየሆነ ያለውን የፖለቲካ ግለት ለወዳጅ አገሮች ለማስረዳት፣ በአውሮፓውያኑ የሚነዛውን ወሬ ለመቀልበስ የሚያስችል ድጋፍ ማግኘትን ዓላማዋ አድርጋ እንደሆነም አቶ ዳምጠው ገልጸዋል፡፡
የሩሲያ አጋርነት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንኳ ከኢትዮጵያ ጥቅም ጋር አብሮ የሚሄድ እንደነበር የገለጹት መምህሩ፣ በደርግ ዘመንም ቢሆን የሩሲያ ድጋፍ ጦርነት አዋጭ ነው የሚል አቋም እንዳልነበረው አክለው ይገልጻሉ፡፡
እንደ ምዕራባውያንና አሜሪካ ሁሉ ሩሲያ ለአፍሪካ አገሮች የምታቀርበው ኢኮኖሚዊ ድጋፍ የሩሲያንና የአፍሪካን ግንኙነት በግልጽ ማሳየት አለመቻሉን የጠቆሙት መምህሩ፣ በዘመናዊ የወታደራዊና የግብርና ቴክኖሎጂ ረገድ ከሩሲያ መቅሰም የሚቻልበት ሁኔታ ከተገኘ የተለየ መላ መዘየድና ግንኙነትን የበለጠ ማሰደግ አዋጭ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ከባለሥልጣናቱ ጋር ምክክር ሲያደርጉ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የመነጋገሪያ ካርዳቸውን በሚገባ ማሳየት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡
በተለይም ሩሲያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስለኢትዮጵያ አጀንዳዎች በቀረቡ ቁጥር ከጎን ሆና ስትከራከር እንደነበረች ሁሉ፣ አሁንም የመንግሥት አካላት ሩሲያ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተደረገ ያለውን የፖለቲካ ሒደትና የድርድር ጅማሮ ግልጽ የሆነ መረጃ እንዲኖራቸው ማስገንዘብና ማስረዳት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በመሆኑም እንዲህ ዓይነት አጋር አገር ሲመጣ መታወቅ ያለበትን ሁሉም አገር ውስጥ ያሉ ችግሮች ሊፈቱ የታሰቡባቸውን መንገዶች በግልጽ በማስረዳት፣ በቀጣይም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተመልሰው ቢገናኙ እንኳ ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጎን መሆኗ እንድታሳይ አጋዥ መሆኑን አክለዋል፡፡
በሌላ በኩል ከሩሲያ ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶች ከፖለቲካ ትብብሩ ባለፈ ሩሲያ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆኗና ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት አውጥታ መጠቀም እንድትችል ሊያግዙት የሚችሉ ቴክኖሎጂዎች ስላሏት፣ ኢኮኖሚያዊ ትብብሮችን በመፈራረም ከምዕራባውያን በኩል የሚመጡ ማዕቀቦችን ሊቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ መገንባት ይቻላል ብለዋል፡፡