ከአንድ ወር በፊት የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ፈቃድ ከኢትዮጲያ ብሔራዊ ባንክ ማግኘቱን ያስታወቀው ካቻ ዲጂታል ፋይናንሺያል ሰርቪስ፣ በቅርቡ አገልግሎቱን ማቅረብ እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡
በ13 ባለአክሲዮኖች በ200 ሚሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል መቋቋሙ የተገለጸው ድርጅቱ፣ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ባለሙያዎችን ተጠቅሞ በተዘጋጀው የራሱ ቴክኖሎጂ ነባርና አዳዲስ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎቶችን እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ አብርሃም ጥላሁን እንደተናገሩት፣ ካቻ በፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ ያልተካተቱ እንዲሁም አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ማዕከል በማድረግ፣ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ለመስጠት በማሰብ ኢንዱስትሪውን ተቀላቅሏል፡፡
ከብሔራዊ ባንክ የተሰጠው ፍቃድ ድርጅቱ የሞባይል ሒሳብ መክፈት፣ በወኪሎችና ሌሎች አማራጮች በመጠቀም ገንዘብ ገቢና ወጪ ማድረግን፣ አነስተኛ ቁጠባ፣ የንብረት መያዣ የማይጠየቅባቸውን አነስተኛ ብድሮች፣ አነስተኛ የኢንሹራንስ አገልግሎቶች፣ የቀጥታ ክፍያዎች፣ ዓለም አቀፍ ሐዋላና ሌሎች አገልግሎቶችን ለማቅረብ የሚያስችለው መሆኑን አቶ አብርሃም ተናግረዋል፡፡
ካቻ ከብሔራዊ ባንክ ፍቃድ ማግኘቱን ተከትሎ ከዘርፉ ተዋንያን እንዲሁም ከአጋሮቹ ጋር የትውውቅ መርሐ ግብር በስካይ ላይት ሆቴል ሐምሌ 21 ቀን 2014 ዓ.ም አካሄዷል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፣ የግል ዘርፉ በኢትዮጵያ ውስጥ ከተለመዱት የንግድ አገልግሎት አቀራረቦች ባሻገር በዲጂታል አሠራሮች ታግዞ ሊቀርብ ይገባዋል ብለዋል። በተለይም በባንኮች ያላቸውን አንድ ቅርንጫፍ ለአሥር ሺዎች የመዳረስ ንፅፅር በዲጂታል መንገድ መቅረፍ እንደሚቻል ተመላክቷል፡፡
ካቻ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት የሥራ ፈቃድ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በማግኘት፣ ከግሉ ዘርፍ የመጀመሪያው የዲጂታል ፋይናንስ ኩባንያ ለመሆን መብቃቱ የተገለጸ ሲሆን፣ የማዕከላዊ ባንኩ፣ በወጣው የክፍያ ሰነድ አውጪዎችን ለማስተዳደር በወጣው ONPS/01/2020 መሠረት ፍቃድ ማግኘቱ ተነግሯል፡፡