Saturday, March 2, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮ ቴሌኮም የፀጥታ ችግር በገቢው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የወጪ ቁጠባ ስትራቴጂን ተግባራዊ በማደረጉ 5.4 ቢሊዮን ብር ማዳኑን ገለጸ

በ2014 የበጀት ዓመት አጠቃላይ ገቢውን 70 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ወጥኖ የነበረው ኢትዮ ቴሌኮም፣ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ያቀደውን ገቢ እንዳያገኝ ተፅዕኖ ማሳደሩን አስታወቀ፡፡

ኩባንያው ካሉት አጠቃላይ 7,622 የሞባይል ጣቢያዎች ውስጥ 3,473 ያህሉ የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭትን  ጨምሮ በሌሎች የፀጥታ መደፍረስ ባለባቸው አካባቢዎች በተፈጠረ ችግር በተጠናቀቀው ዓመት አገልግሎት ሳይሰጡ የቆዩ መሆናቸውን፣ 1,144 ጣቢያዎች ደግሞ ወደ ሥራ እንዳልገቡ አስታውቋል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ የተጠናቀቀውን በጀት ዓመት የኩባያንውን የሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ ኩባንያው በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 61.3 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ በማግኘት የዕቅዱን 87.6 በመቶ አሳክቷል፡፡

የተገኘውን ገቢ ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋና ምቹ ስለነበሩ አይደለም ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ በበጀት ዓመቱ ኢትዮ ቴሌኮምን በርካታ ተግዳሮቶች እንደፈተኑት አስረድተዋል፡፡

ኩባንያው የዕቅዱን ገቢ ሙሉ በሙሉ ያላሳካው በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍልና በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ሳቢያ፣ 45 በመቶ የሚሆኑት የኩባንያው የሞባይል ጣቢያዎች አገልግሎት እንዳይሰጡ አድርጓቸው በመቆየቱ ሳቢያ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ካሉት አጠቃላይ የሞባይል ጣቢያዎች 45 በመቶ የሚሆኑት አገልግሎት ሳይሰጡ ከ61 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱ፣ ጥንካሬውን አመላካች መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል፡፡

በበጀቱ አጋማሽ ኩባንያው ባቀረበው ሪፖርት ላይ ዕቅዱን ይከልሳል ወይ የሚል ጥያቄ መቅረቡ የሚታወስ ሲሆን፣ ኩባንያው ዕቅዱን ሳይከልስ የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የታጣውን ገቢ ለመተካት መጠነ ሰፊ ጥረቶች መደረጉ ተመላክቷል፡፡

ወ/ሪት ፍሬሕይወት እንዳስታወቁት አገልግሎት ሳይሰጡ የቆዩት የሞባይል ጣቢያዎች ከሥራ ውጪ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ ውድመትና ጉዳት የደረሰባቸው ነበሩ፡፡ የፀጥታ ችግሩ በተሻሻለባቸው አካባቢዎች ጥገና በማድረግ ጣቢያዎቹ ወደ ሥራ የተመለሱ መሆኑን፣ ነገር ግን 1,144 ጣቢያዎች አገልግሎት እንደማይሰጡ ተገልጿል፡፡

የኩባንያው ገቢ በ2013 ዓ.ም. ከነበረው አጠቃላይ ገቢ የ8.5 በመቶ ጭማሪ እንደተገኘበት፣ ገቢው በአስቸጋሪና በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ የተገኘና አበረታች መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ አገልግሎቶቹ ኩባንያው 146.6 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሲያገኝ፣ ገቢው የዕቅዱን 82.3 ከመቶ በመሸፈን ዓምና ከነበረው የ166.5 ሚሊዮን ዶላር ግን አንሶ መገኘቱ ተመላክቷል፡፡

ወ/ሪት ፍሬሕይወት እንደተናገሩት፣ ከውጭ ምንዛሪ ግኝት ጋር በተገናኘ በታቀደው ልክ እንዳይገኝ ካደረጉት ውስጥ በአብዛኛው ግጭት ባላባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ጣቢያዎች የውጭ ጥሪ ባለማስተናገዳቸው ነበር፡፡

ወልዲያ፣ ደሴና ኮምቦልቻ በመሳሰሉት አካባቢዎች ኢትዮ ቴሌኮም የውጭ ጥሪዎች ሳይቀበል መቆየቱ የተመላከተ ሲሆን፣ በእነዚህ ከፍተኛ የውጭ ጥሪ በሚያስተናግዱ አካባቢዎች ለረዥም ጊዜ ኔትወርክ መቋረጡ የዓለም አቀፍ ጥሪ ገቢ ማሳጣቱ በገቢ ግኝቱ ላይ ወዲያውኑ እንደሚንፀባረቅ ገልጸው፣ ገቢው ከዚህም በላይ ይቀንስ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

በተለይ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከተፈጠረው ግጭት ጋር በተያያዘ ያጋጠመውን የንብረት ውድመትና የገቢ ዕጦት የተጠየቁት ወ/ሪት ፍሬሕይወት በሰጡት ምላሽ፣ ኩባንያው በትግራይ ምን ያህል መሠረተ ልማት እንዳለው ቢያውቅም በዚህ ወቅት በምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ለማወቅ አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የደረሰን ጉዳት ተመን መግለጽ ጥንቃቄ የሚጠይቅ መሆኑን ያስታወቁት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ ከዚህ ጋር በተያያዘ ያለውን ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላትን ጨምሮ ወደፊት የሚገለጽ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከተጀመረ 14 ወራት ባስቆጠረው የቴሌ ብር የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት መጠቀም የጀመሩ ደንበኞች 21.8 ሚሊዮን የደረሱ መሆናቸውን፣ በገንዘብ ዝውውር አማራጩ 30.3 ቢሊዮን ብር መዘዋወሩ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም ከ37 አገሮች ጋር በመተሳሰር በቴሌ ብር ዓለም አቀፍ የሃዋላ አገልግሎት 974,300 ዶላር ዝውውር መከናወኑ ተነግሯል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በቴሌ ብር የአነስተኛ ብድርና ቁጠባ አገልግሎት ለመስጠት ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ማግኘቱን ያረጋገጠ ሲሆን፣ በፈቃዱ ከተቀመጡት ጉዳዮች ውስጥ ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቱን ለማቅረብ የሚያስፈልገው ገንዘብ በባንኮች በኩል የሚቀርብ ስለሆነ፣ አጋር ሆኖ ከሚሠራው ባንክ ጋር ከስምምነት ለመድረስ ከቅድመ ዝግጅት ሒደት ላይ መሆናቸውን ወ/ሪት ፍሬሕይወት ተናግረዋል፡፡

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የገቢ አማራጮችን ከማስፋት ባሻገር አላስፈላጊ ወጪዎችን ለማስወገድና ኩባንያውን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የወጪ ቁጠባ ስትራቴጂ ቀርፆ ተግባራዊ በማድረግ፣ 5.4 ቢሊዮን ብር  ወጪ መቀነሱን ኩባንያው አስታውቋል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም አጠቃላይ ደንበኞች 66.59 ሚሊዮን የደረሱ መሆናቸውን፣ ከዚህ ውስጥ 64.5 ሚሊዮን ያህሉ የሞባይል ደንበኞች፣ 25.5 ሚሊዮን የሞባይል ዳታ ተጠቃሚዎች፣ ከ506 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ደግሞ የመደበኛ ብሮድባንድ ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች