Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሲሚንቶ ለክልሎች በኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል  እንዲያከፋፈል ተደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፋብሪካዎች የዋጋ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ተጠይቋል

ከሰኔ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባር ላይ የዋለው የሲሚንቶ ግብይትና ሥርጭት መመርያ ቁጥር 908/2014ን ተከትሎ፣ የክልል የንግድ ቢሮዎች የሲሚንቶ ምርትን በትክክል ለተጠቃሚው ያደርሳሉ ባሏቸው ዩኒየኖችና የኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል እንዲያከፋፍሉ ተደረገ፡፡

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ወ/ሮ ቁምነገር እውነቱ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ከዚህ ቀደም ሲሚንቶ የሚከፋፈልባቸው ዲፖዎች ይቋቋማሉ ተብሎ ሲገለጽ የቆየው ጉዳይ፣ ለክልሎች የተቀመጠ ኃላፊነት መሆኑን አስረድተው፣ ይህም በየክልሉ የሚገኙት የንግድና ገበያ ልማት ቢሮዎች በትክክል ሲሚንቶን ለተጠቃሚው ያከፋፍላሉ ብለው ላመኑባቸው ዩኒየኖች ወይም የኅብረት ሥራ ማኅበራት በመስፈርቱ መሠረት እንዲደርስ የሚያደርጉበት አሠራር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚያ ውጭ ለሲሚንቶ ተብሎ የሚቋቋም የተለየ የሲሚንቶ ክምችት ዲፖ እንደማይኖር ወ/ሮ ቁምነገር አስታውቀዋል፡፡

ክልሎችም ሆነ የከተማ አስተዳደሮች ከላይ በተጠቀሰው አግባብ የሲሚንቶ ሥርጭት የሚያቀርቡበት አማራጭ በመመርያ ተደግፎ ቢቀርብም፣ ከሥርጭት፣ ትስስርና ከመሸጫ ዋጋ ጋር ተያይዞ ምርቱ ለተጠቃሚው እየደረሰ አለመሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከሰሞኑ አስታውቋል፡፡

ከመመርያ ውጪ እየተከናወነ የሚገኘውን ሕገወጥ የሲሚንቶ ግብይት ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ፣ የክልልና ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ተቋማት በአስቸኳይ ተገቢ ዕርምጃ እንዲወሰድ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በተጠናቀቀው ሳምንት መባቻ ማስታወቁ የሚታወስ ሲሆን፣ ለሲሚንቶ ሥርጭት የተመረጡ አካላት በአስቸኳይ ምርቱን ከፋብሪካ በመቀበል በተላለፈው ጊዜያዊ የመሸጫ ዋጋ እንዲያቀርቡ አሳስቧል፡፡

በሌላ በኩል የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ደኤታ በሆኑት አቶ ሃሰን መሃመድ ተፈርሞ ለክልልና የከተማ አስተዳደሮች፣ የንግድና ገበያ ልማት ቢሮዎች ሐምሌ 19 ቀን 2014 ዓ.ም. የተላከው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው፣ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን የመሸጫ ዋጋ ግንባታ ዘግይቶ በማሳወቅና ለየከተሞቹ የተሰላው መሸጫ ዋጋ የፋብሪካ መሸጫ ዋጋን ከፍ በማድረግ በመሆኑ፣ ማስተካከያ እንዲደረግ ከፋብሪካ ኃላፊዎችና የሲሚንቶ አምራቾች ማኅበር ጋር ውይይት በማድረግ የዋጋ ማሻሻያ እየተጠበቀ ይገኛል ተብሏል፡፡

አሥር ለሚደርሱ ፋብሪካዎች አባሪ ተደርጎ የተላከው ደብዳቤ ላይ እንደሰፈረው፣ በአንዳንድ ፋብሪካዎች የተደረገው ማሻሻያ በፋብሪካ በር መሸጫ ዋጋቸው ለውጥ ያመጣ ባለመሆኑ፣ ከመመርያ ቁጥር 908/2014 አፈጻጸም ጋር በተያያዘ የተሰላው ምክንያታዊ ያልሆነ የፋብሪካ በር መሸጫ ዋጋ ማሻሻያ እንዲያደርጉ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አቅጣጫ ሰጥቷል፡፡

የተለያዩ የሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባሳወቁት የምርት ማስረከቢያ ዋጋ ዝርዝር አባሪ ላይ እንደሚታየው፣ የተከለሰ የክልል ከተሞች የሲሚንቶ መሸጫ ዋጋ ከ598 ብር እስከ 1100 ብር እንደሚደርስ ያሳያል፡፡

የሲሚንቶ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በአዲስ አበባ ከተማ በኩንታል 1,350 ብር መድረሱን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ቤት ገንቢዎችና የሲሚንቶ ችርቻሮ ነጋዴዎች ያስታወቁ ሲሆን፣ አከፋፋዮች ጋር ሳይደርስ ከፋብሪካ በር ላይ ሲሚንቶ የሚሸጥበት ዋጋ ላይ ክለሳ መደረጉ፣ ምርቱን ከዚህ በላይ ያንረዋል የሚል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በሻገር በአዲስ አበባ ሲሚንቶን በኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት አቅራቢ ድርጅት (ኢግልድ) በኩል ለነዋሪው ለማዳረስ ሲባል በችርቻሮ ንግድ ላይ የተሰማሩት ነጋዴዎች በሱቆቻቸው ያለው ምርት ካለቀ በኋላ ዳግም ከአከፋፋዮች ተቀብለው ለገበያ እንዳያቀርቡ በክፍላተ ከተሞች በኩል እንደተገለጸላቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች