Tuesday, September 27, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የሴራ ፖለቲካ መረብ ይበጣጠስ!

  ኢትዮጵያ አሁንም ከበርካታ ፈተናዎች ጋር እንደ ተፋጠጠች ነው ያለችው፡፡ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ምክንያት ግብፅ በጎረቤት አገሮች አማካይነት ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ፍጥነቷን ጨምራ እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡ ሰሞኑን ሶማሊያ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው አሸባሪው አልሸባብ ድንበር ጥሶ ለመግባት ያደረገው ሙከራ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብና በጋምቤላ ክልሎች ውስጥ የሚስተዋሉ የሰላም ዕጦቶች የመፍትሔ ያለህ እያሉ ነው፡፡ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ የጅምላ ግድያዎች፣ ማፈናቀሎችና ዘረፋዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ አሳሳቢነታቸው እንደ ቀጠለ ነው፡፡ በአገር ውስጥ የሚስተዋሉ ቅራኔዎችን አርግቦ ሰላም ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ከሚጠበቀው በታች ነው፡፡ አሁንም ግጭት ለመቀስቀስና የበለጠ ዕልቂትና ውድመት ለማስከተል የሚደረገው ፍጥጫ መርገብ አልቻለም፡፡ ገዥው ፓርቲ ብልፅግና በሚመራው መንግሥት ውስጥ ኃላፊነት ያላቸው ግለሰቦች ጭምር ሕግ ይከበር እያሉ ድምፃቸውን እያሰሙ ነው፡፡ ነገር ግን ሕግ ከማክበር ይልቅ የሕግ ጥሰት እየተበራከተ ነው፡፡ ለአገርና ለሕዝብ ከማሰብ ይልቅ ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነት እየተንሰራፋ ነው፡፡ ሌብነት የሚያስከብር ይመስል በሁሉም ሥፍራ ዝርፊያ ተጧጡፏል፡፡ የሴራ ፖለቲካውም ገደቡን እያለፈ ነው፡፡

  የኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ ከባድ የሚባል ጊዜ እያሳለፈ እንደሆነ መናገር ለቀባሪው ማርዳት ነው የሚሆነው፡፡ አገሩ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ተጠፍራና ለመሸከም ከባድ ከሆነ የኑሮ ውድነት ጋር እየታገለ መሆኑም ይታወቃል፡፡ ከራሱ ኑሮና ሕይወት በላይ ለአገሩ ቅድሚያ የሚሰጠው ይህ ኩሩና አስተዋይ ሕዝብ አንድም ቀን ኑሮ መረረኝ፣ የዳቦም ሆነ የሌሎች ሸቀጦች ዋጋ ይቀንስልኝ ብሎ አደባባይ ወጥቶ አያውቅም፡፡ በሌሎች አገሮች በተደጋጋሚ የሚስተዋሉ የገቢ ጭማሪና የኑሮ ውድነት ማቅለያ ሠልፎችንም ሲያደርግ አይታወቅም፡፡ አገሩ በበርካታ ችግሮች የተተበተበች መሆኑን በሚገባ ስለሚረዳ የበለጠ ችግር ለመፍጠር አይቃጣውም፡፡ ነገር ግን ይህንን በጎ አሳቢነቱንና አስተዋይነቱን የሚረዳለት መንግሥት ማግኘት ግን አልቻለም፡፡ በተለያዩ የመንግሥት የኃላፊነት እርከኖች ላይ የተቀመጡ ተሿሚዎች ከሕዝብ ይልቅ የሚያስቀድሙት ራሳቸውን በመሆኑ፣ አገሪቱ ማባሪያ የሌለው የዝርፊያ ማዕድ ሆናለች፡፡ ከዘረፋው በተጨማሪ በሰላም አብሮ የሚኖር ሕዝብን በማጋጨት ሥልጣንን ማደላደልና የጥቅም አድማስን ማስፋት የዘወትር ሥራቸው ሆኗል፡፡ ሕዝብ የሚሰማው አጥቶ እየተማፀነ ያለው ፈጣሪውን ነው፡፡ ከሴራ ምንም አይገኝም፡፡

  የነዳጅ ድጎማው ከመነሳቱ በፊትም ሆነ በኋላ በዋጋ ግሽበት እየተመታ ያለው ሕዝቡ ነው፡፡ መንግሥት ገበያው ውስጥ ገብቶ ዋጋ የመተመን ኃላፊነት ባይኖርበትም፣ መረን የተለቀቀውን የግብይት ሥርዓት ፈር ማስያዝ አቅቶት ሕዝብ የአልጠግብ ባዮች መጫወቻ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ሌላው ቀርቶ የንግዱ ማኅበረሰብ ወጥቶና ወርዶ ማግኘት የሚገባው ትርፍ ሥርዓት ሊበጅለት ሲገባ፣ ሸማቹ ሕዝብ በሰው ሠራሽ የዋጋ ግሽበት ሲመታ የሚከላከልለት የለም፡፡ በሌላው ዓለም የትርፍ ህዳግ የሚባል አሠራር አለ፡፡ ከአንድ ዕቃ ላይ መገኘት ያለበት ትርፍ በመቶኛ ተሰልቶ ነጋዴውም ሳይጎዳ፣ ሸማቹም ላልተገባ የዋጋ ግሽበት ሳይጋለጥ የግብይት ሥርዓቱ ጤናማ ሆኖ የሚዘልቅበት አሠራር ነው፡፡ ይሁንና በዚህ ዘመን የባለሥልጣናት ቤተሰቦች ሳይቀሩ ደላላና ነጋዴ እየሆኑ፣ እንዲህ ዓይነቱን ዘመናዊ አሠራር ተግባራዊ ማድረግ አልተቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት እንደ ዘይት፣ ሲሚንቶ፣ ሌሎች የግንባታ፣ የምግብና ምግብ ነክ ቁሳቁሶች ዋጋ አልቀመስ እያለ ነው፡፡ መንግሥት በአግባቡ ሥራውን ማከናወን ቢችል ኖሮ ግን ገበያውና የአቅርቦት ሰንሰለቱ አይታነቅም ነበር፡፡ ሴረኞች እጃችሁን ሰብስቡ፡፡

  የኢትዮጵያ ሕዝብ በየትም ሥፍራ ቢኖር፣ የትኛውንም እምነት ቢከተል፣ በተለያዩ ቋንቋዎች ቢገለገል፣ ባህሎቹና ልማዶቹ ቢለያዩም ለዘመናት የተገለገለባቸው ነባር ማኅበራዊ እሴቶቹ ለጨዋነት፣ ለትዕግሥትና ለፈሪኃ ፈጣሪ የሚሰጠው ግምት ተመሳሳይ ያደርጉታል፡፡ በዚህም ምክንያት ከአገሩ በፊት ምንም ነገር ስለማያስቀድም ሹሞች ሲያስቀይሙት እንኳ ይታገሳል፡፡ ይህንን የመሰለ አርቆ አሳቢና ጀግና ሕዝብ ይዘው አመራር መስጠት የማይችሉ ሹሞች ከምን ውስጥ ነው የበቀሉት ያሰኛል፡፡ ሕግና ሥርዓት አክብረው የተሰጣቸውን ኃላፊነት መወጣት ሲገባቸው፣ ለሥርዓተ አልበኝነት በር የሚከፍቱ ሕገወጥ ሹሞች እየተበራከቱ ነው፡፡ አገር ዙሪያዋን በተለያዩ አጣዳፊ ችግሮች ተወጥራ የግል ጥቅማቸውን ከማሳደድ ውጪ ምንም የማይታያቸው ቁጥራቸው እየበዛ ነው፡፡ በሕግና በሥርዓት መተዳደር የሚሻውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት በሚፃረሩ ፍላጎቶች ውስጥ ተወሽቀው፣ መሬት በጠራራ ፀሐይ የሚወሩና የሚያስወርሩ ሹማምንት እንደ እንጉዳይ መፍላታቸው ከማስገረም በላይ ያበሳጫል፡፡ በሕግ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለሕዝብ አገልግሎት ማዋል ሲገባቸው በሥልጣን የሚባልጉ፣ ፍትሕ የማስፈን ግዴታ እያለባቸው ፍትሕን የሚሸቅጡና ሕዝብ የሚያበሳጩ ሹሞችን መሸከም ያስደንቃል፡፡ ሴረኝነት ትርፉ ጥፋት ነው፡፡

  የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኮቪድ-19፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ በተከታታይ እየተመዘገበ ባለ የዋጋ ግሽበትና በማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ምክንያት ከባድ ችግር ውስጥ ነው ያለው፡፡ የተቆለለው የአገር ውስጥና የውጭ ዕዳም እንዲህ በዋዛ የሚገላገሉት አይደለም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሩሲያና በዩክሬን መካከል በሚካሄደው ጦርነት በነዳጅ፣ በምግብ ምርቶች፣ በኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃዎችና በሌሎች ምርቶች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ በማጋጠሙ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱም ከባድ ችግር ፈጣሪ ነው፡፡ የሕዝቡ ገቢ በሰባራ ሳንቲም ሳይጨምር የሸቀጦችና የአገልግሎቶች ዋጋ በየቀኑ እያሻቀበ ነው፡፡ በዚህ ላይ እነ ዓለም ባንክና የዓለም ገንዘብ ድርጅት ብድርና ድጋፍ ለማድረግ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠዋል፡፡ መንግሥት የብር አቅምን ከዶላር አኳያ እንዲያዳክም፣ የፋይናንስና የቴሌኮም ዘርፎችን ለውጭ ገበያ እንዲከፍት፣ የነዳጅ፣ የኤሌክትሪክና የሌሎች ድጎማዎችን እንዲያነሳ፣ በጀቱን እንዲቀንስና የታክስ መሠረቱን እንዲያሰፋ የሚሉ ቅድመ ሁኔታዎች ይገኛሉ፡፡ የምዕራባውያን የገንዘብ ድርጅቶች ቅድመ ሁኔታዎች ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ነው የሚል አንድምታ እንዳላቸው ቢነገርም፣ መንግሥትና ሹማምንቱ ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸው ጥርት ያለ ምልከታ መታወቅ አለበት፡፡ ሴራ ተገቶ ለአገር የሚበጀው ላይ ይተኮር፡፡

  በአጠቃላይ በአሁኒቷ ኢትዮጵያ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና ልሂቃን፣ የእምነት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ሕዝብና መንግሥት ጭምር በመሀላቸው የሚስተዋለው ሁኔታ ደስ አይልም፡፡ በእያንዳንዱ የዕለት ተዕለት ጉዳይ ሳይቀር ከመተማመን ይልቅ ጥርጣሬ፣ ከትብብር ይልቅ መገፋፋት፣ በግልጽ ከመነጋገር ይልቅ መተማማት፣ በማስረጃ ላይ ተመሥርቶ ውሳኔ ላይ ከመድረስ ይልቅ ባልተጣራ መረጃ መፈራረጅና የመሳሰሉት ከንቱ ነገሮች ጎልተው ይታያሉ፡፡ በማኅበራዊ የትስስር ገጾችና በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በሚስተዋሉ ሽኩቻዎች ከአገር አንድነት ይልቅ፣ አገርን ለመበተን የሚጎሻሸሙ ተቃርኖዎች ከመጠን በላይ በርክተው ይስተዋላሉ፡፡ በርካታ ችግሮች በተቆለሉባት ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቃቅን ልዩነቶችን አርግቦ ለጋራ ብሔራዊ ጉዳዮች አንድ ከመሆን ይልቅ፣ ምክንያት እየፈለጉ ጎራ ለይቶ ጥላቻና ክፋትን መዝራት የተለመደ ተግባር ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በዲፕሎማሲና በተለያዩ ጉዳዮች ተወጥራ መፍትሔ ከማቅረብ ይልቅ በሴራ የሚጠላለፉ ኃይሎች መፋለሚያ መሆኗ ያሳዝናል፡፡ አሁንም ጊዜው አልረፈደምና ለኢትዮጵያ ህልውና ሲባል የሴራ ፖለቲካ መረብ ይበጣጠስ!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ በተመድ ጉባዔ ‹‹የትግራይ መንግሥት›› በማለት ላደረጉት ንግግር ማስተካከያ እንዲደረግ ኢትዮጵያ ጠየቀች

  በስዊዘርላንድ ጄኔቭ እየተካሄደ በሚገኘው 51ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...

  በ15 ቢሊዮን ብር የተመዘገበ ካፒታል የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎቱን ያሻገረው ስንቄ ባንክ ሥራ ጀመረ

  ከማክሮ ፋይናንስ ተቋምነት ወደ ባንክ አገልግሎት ከተሸጋገሩ አምስት የማክሮ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ብልሹ አሠራሮች እንዲወገዱ ሕግና ሥርዓት ይከበር!

  በኢትዮጵያ ምድር ጦርነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ፊትን ወደ ልማት ለማዞር ያለው ፍላጎት አሁንም ፈተና እየገጠመው ነው፡፡ ኢትዮጵያ አዲሱ ዓመት ሲብት በሙሉ...

  የግብይት ሥርዓቱ የሕገወጦች መፈንጫ አይሁን!

  በጥቂቶች ስግብግብነት ብዙኃኑ ሕዝብ እንዳይጎዳ ተገቢ ሞራላዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ድጋፍ መስጠት ይገባል፡፡ ሰሞኑን መንግሥት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ሱር ታክስና ኤክሳይስ ታክስን ጨምሮ፣...

  የኢኮኖሚው ጉዞ ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይሆን!

  ጦርነት ውስጥ ያለች አገር ኢኮኖሚ ጤንነት እንደማይሰማው ለማንም ግልጽ ቢሆንም፣ ከጦርነቱ በተጨማሪ በየዕለቱ ገበያው ውስጥ የሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ ግን አስደንጋጭ እየሆነ ነው፡፡ የብር የመግዛት...