የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት፣ በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2022 ብቻ ከ29 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አስታወቀ፡፡
የማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ ሐምሌ 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት፣ እ.ኤ.አ. በ2022 በቀጠለው ግጭት፣ በአየር ንብረት መለወጥና ድርቅ፣ በኢትዮጵያ አጠቃላይ ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት በመጨመሩ የአቅርቦት ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን አስታውቋል፡፡
ሪፖርቱ የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት እ.ኤ.አ. በ2020 ከነበረበት 8.4 ሚሊዮን በ2021 ወደ 23.5 ሚሊዮን ማደጉን፣ እንዲሁም እ.ኤ.አ. በ2022 ደግሞ ወደ 29 ሚሊዮን ማሻቀቡን አመላክቷል፡፡ ከዕርዳታ ጠባቂዎቹ መካከል ሩብ የሚሆኑት ሴቶችና ሕፃናት ናቸው ተብሏል፡፡
በትግራይ ክልል 91 በመቶ ወይም 5.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች አስቸኳይ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው፣ ከእነዚህ ውስጥ 2.1 ሚሊዮን የሚሆኑት የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች እንደሆኑ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
ከመጋቢት መጨረሻ እሰከ ሐምሌ 2014 ዓ.ም. አጋማሽ ድረስ 4,308 የዕርዳታ እህል የጫኑ ተሽከርካዎች፣ ከአንድ ሚሊዮን ሊትር በላይ ነዳጅ፣ እንዲሁም 52 የጭነት ተሽከርካዎች ማዳበሪያ ጭነው ወደ መቀሌ እንደተጓዙ ሪፖርቱ ያሳያል፡፡
በተመሳሳይ በአፋር ክልል በግጭት፣ በድርቅ፣ በገበያ ዕጦትና በምግብ ዋጋ መናር በተለይም በአባላ፣ በበርሃሌ፣ በዳሎል፣ በኢርቢቲ፣ በኮንነባ፣ በመጋሌ አካባቢዎች የሰብዓዊ ቀውሱ መባባሱንና በአሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በሪፖርቱ ተብራርቷል፡፡ በአፋር ክልል 20 ሺሕ ዜጎች ተፈናቅለው በካምፕ እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን አብዛኛዎቹ አጋቲና፣ ዱብቲና ጋይቦዳ በተባሉ አካባቢዎች ይገኛሉ ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል በአማራ ክልል ሐምሌ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰሜን ሸዋ ዞንና በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች በተከሰተ ግጭት፣ 1,600 ዜጎች እንደተፈናቀሉ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
በሶማሌ ክልል በተከሰተው ድርቅ 2.2 ሚሊዮን እንስሳት መሞታቸውን የገለጸው ሪፖርቱ፣ አሁን 22 ሚሊዮን እንስሳት አደጋ እንደተደቀነባቸው አስረድቷል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የዓለም ምግብ ድርጀትን ጠቅሶ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳው፣ በድርቅ ክስተት ብቻ 3.3 ሚሊዮን ዜጎች በኦሮሚያ ክልል፣ 3.3 ሚሊዮን ዜጎች በሶማሌ ክልል፣ 1.1 ሚሊዮን ዜጎች በደቡብ ክልል፣ እንዲሁም 2.8 ሚሊዮን ዜጎች በሌሎች አካባቢዎች ለረሃብ አደጋ ተጋልጠዋል፡፡