Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበእንስሳት መኖ ላይ የተጣለው ቀረጥና ታክስ ተነሳ

በእንስሳት መኖ ላይ የተጣለው ቀረጥና ታክስ ተነሳ

ቀን:

ገንዘብ ሚኒስቴር በእንስሳት መኖ ዋጋ መናር ምክንያት የሚከሰተውን የእንስሳት ተዋፅኦ ምርቶች ዋጋ መጨመር ለመግታት ሲባል፣ በመኖና ግብዓቶቹ ላይ የተጣለውን ቀረጥና ታክስ አነሳ፡፡

ሚኒስቴሩ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው ግብርና ሚኒስቴር ቀረጥና ታክስ መነሳቱ የእንስሳት ተዋፅኦ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጣ መግለጹን ተከትሎ ነው፡፡ በዚህም የገንዘብ ሚኒስቴር በየሦስት ወሩ በተባለው ልክ የእንስሳት ተዋፅኦ ዋጋ የመቀነሱን ጉዳይ ግብርና ሚኒስቴር እየተከታተለ ሪፖርት እንዲያደርግለት ጠይቋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና አሳ ግብአት አቅርቦትና ግብይት ዳይሬክተር አቶ ብርሃን ፈለቀ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ገንዘብ ሚኒስቴር ግንቦት ወር ላይ ይኼንን ውሳኔ ያሳለፈው ግብርና ሚኒስቴር በ2013 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ያደረገውን ጥናት ውጤት ካቀረበ በኋላ ነው፡፡

ጥናቱ የተደረገው ለመኖ ውድነት መንስዔው የግብአት መወደድ መሆኑንና ይህም የወተት፣ ሥጋና እንቁላል ዋጋ እንዲጨምር መነሻ ሆኗል በሚል ጥናቱ መደረጉን የተናገሩት አቶ ብርሃን፣ በጥናቱ ከ2008 እስከ 2013 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት የነበረው የመኖ ግብአት ዋጋ መዳሰሱን ገልጸዋል፡፡

ጥናቱ እንዳሳየው በአምስት ዓመታት ውስጥ ከስንዴ፣ አኩሪ አተር፣ በቆሎ፣ ኑግና ሌሎች እህሎች የሚገኙ የመኖ ግብአቶች ዋጋ በብዙ እጥፍ ማሳየታቸውና ይሄም የመጨረሻው ምርት ዋጋ ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ ከአኩሪ አተር ተረፈ ምርት የሚገኝ የመኖ ግብአትን በምሳሌለት ያነሱት ዳይሬክተሩ፣ በ2008 ዓ.ም. በኩንታል 450 ብር ሲሸጥ የነበረው የአኩሪ አተር ተረፈ ምርት በአምስት ዓመት ውስጥ ከስድስት እጥፍ በላይ ጨምሮ 2,975 ብር ደርሷል፡፡ ከኑግ የሚገኝ ግብአትም በተመሳሳይ ከ555 ብር ወደ 2,720 ጨምሯል፡፡

የገበያ ሰንሰለቱ ላይ ያሉ ደላላዎች መብዛትና የመኖ አቅርቦት በሚፈለገው ልክ አለመሆን ለመኖ ዋጋ መጨመር በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡

እነዚህ ችግሮች ባሉበት መኖና የመኖ ግብአት ላይ ቀረጥና ታክስ መኖሩ ጫናውን እንዳባሰው የሚናገሩት አቶ ብርሃን፣ በመኖ ላይ ያለው ታክስ በአጠቃላይ ተደምሮ 38 በመቶ እንደሚደርስ ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ የጥናት መሠረት የእንስሳት መኖ በሚፈለገው መጠንና ጥራት ለተጠቃሚው እንዲደርስ የመኖ ማቀነባበሪያ ግብአቶች ላይ የተጣለው ቀረጥና ታክስ ቢነሳ፣ ዋጋው እንደሚቀንስ፣ አቅርቦት እንደሚጨምርና ይህም የተዋጽኦዎችን ዋጋ ለመቀነስ እንደሚረዳ ሐሳብ የቀረበለት የገንዘብ ሚኒስቴር ታክስና ቀረጡን አንስቷል፡፡

በዚህም መሠረት ለመኖ ግብአት ሲባል ከውጭ የሚገቡት እንደ ቫይታሚን፣ አሚኖ አሲድና ሌሎች መደባለቂያዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ ይሁንና 95 በመቶ የሚሆነው የመኖ ግብአት የሚገኘው ከአገር ውስጥ በመሆኑ በተለይ የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) መነሳቱ ይበልጥ ለውጥ እንደሚያመጣ አቶ ብርሃን ተናግረዋል፡፡

በሚኒስቴሩ ውሳኔ መሠረት ማቀነባበሪያዎች ከአቅራቢዎች ግብአት ሲገዙም ሆነ መኖ ተጠቃሚዎች መኖውን ሲገዙ ቫት እንደማይከፍሉ አስረድተዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ይኼንን የውሳኔ ሐሳብ ሲያሳልፍ ውሳኔው በትክክል በጥናቱ የቀረበውንም ውጤት ስለማስገኘቱ ሪፖርት እንዲቀርብለት ጠይቋል፡፡ ግብርና ሚኒስቴር በየሦስት ወሩ የእንስሳት ምርት በመጠን መጨመሩን፣ የእንስሳት ምርት ዋጋ መቀነሱንና ምርትና ምርታማነት ማደጉን በሚመለከት ሪፖርት የማቅረብ ኃላፊነት አለበት፡፡

ሚኒስቴሩ ይኼንን ሪፖርት ለማቅረብ የክትትል ሥርዓት በመዘርጋት ሒደት ላይ መሆኑን አቶ ብርሃን ተናግረዋል፡፡

‹‹የዚህ ውሳኔ ውጤት ቀስ በቀስ የሚታይ ነው›› ያሉት አቶ ብርሃን፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የእንቁላል ዋጋ ከ12 ብር ወደ ስምንት ብር መቀነሱ የዚህ ውሳኔ ውጤት ‹‹ፍንጭ›› እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ከውሳኔው ሁለት ወር በኋላ በእርግጥ የዋጋ ቅናሽ ስለመታየቱ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ካሳሁን፣ እስካሁን ድረስ በመኖ ዋጋ ላይ ቅናሽ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡

በቅርብ ጊዜያት በእንቁላል ላይ የታየው ቅናሽም ቢሆን የግብርና ሚኒስቴር በአንዳንድ አካባቢዎች ያልታወቀ የዶሮ በሽታ መከሰቱን ተከትሎ ዶሮና እንቁላል ከቅርብም ሆነ ከሩቅ አካባቢዎች ወደ ገበያ እንዳይገቡ በማገዱ የመጣ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...